አርቲፊሻል ስኳር ሲባል እንደ ስኳር ጣፋጭነት ያላቸው የምግብና መጠጥ ማጣፈጫነት ጥቅም ላይ የሚዉሉ የስኳር ምትክ ናቸው። የካሎሪ መጠናቸው ዜሮ አሊያም እዚህ ግባ የማይባል እጅግ በጣም ዝቅተኛ ስለሆነ ለስኳር ታካሚዎች ስኳርን የሚተኩ ምርቶች ሆነው ያገለግላሉ።
የተለመዱ የአርቲፊሻል ስኳር አይነቶች የሚከተሉትን ያካትታሉ፤ አስፓርቴም፣ አድቫንቴም፣ ኒዮቴም፣ ሳካሪን፣ ሱክራሎዝ፣ ዛይሊቶል፣ ኢሪትሪቶል፣ ሶርቢቶል ወዘተ ናቸው። ጣፋጭነታቸው ከስኳር እኩል ወይም የበለጠ ሊሆን ይችላል።
አርቲፊሻል ስኳር ያለተጨማሪ ካሎሪ ጣዕምን ስለሚያጣፍጡ የስኳር ፍጆታን በመቀነስ ውፍረት እና ተያያዥ በሽታዎችን ለመከላከል ይረዳሉ ተብለው ቢታሰቡም በተቃራኒው የጤና እክል አደጋን ሊጨምሩ እንደሚችሉ አዳዲስ ጥናቶች ይጠቁማሉ።
በዚህ ዙሪያ ያለውን ግርታ ለማጥራት የዓለም ጤና ድርጅት እኤአ በ2019 አጥኚ ኮሚቴ አዋቅሮ ሰፊ ምርምር እንዲሰራ አድርጓል። በዋናነት ትኩረት የተሰጣቸው የጤና መለኪያዎች መካከል ክብደት፣ የሰውነት ስብ መጠን፣ የስኳር ህመም፣ የደም ግፊት፣ የኮሌስትሮል መጠን፣ የልብና ደም ስር ህመሞች፣ የኩላሊት ህመም፣ ካንሰር፣ የምግብ ፍላጎትና ረሃብ ስሜት ወዘተ ናቸው። ይህ የጥናት አማካሪ ቡድን የአርቲፊሻል ስኳር አጠቃቀም በጤና ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት ያጠኑ 370 ወሳኝ ምርምሮችን ገምግሞ የሚከተለውን ውጤት ይፋ አድርጓል።
1️⃣ ለክብደት መቀነስ ይረዳሉ የሚለው ወሬ የተረጋገጠ እንዳልሆነ ነው በጥናቶች የታየው። በተለምዶ እንደሚታሰበው እነዚህን አርቲፊሻል ስኳር ጣፋጮችን መጠቀም ክብደትን ለመቀነስ ላይረዳ ይችላል። እንዲያዉም የምግብ ፍላጎታችንን ሊጨምሩ ስለሚችሉ ተጨማሪ ምግብ በመመገብ ክብደታችን ሊጨምር ይችላል።
2️⃣ የልብ ህመም እና የደም ቧንቧ ችግሮች ያመጣሉ። በቅርቡ የወጡ ጥናቶች እንዳሳዩት ከፍተኛ መጠን ያለው አርቲፊሻል ስኳር መጠቀም ለልብ ህመም ብሎም የሞት ስጋት ተዛማጅነት አላቸው።
3️⃣ የሆድ ህመም ሊያመጡ ይችላሉ። በአንዳንድ ሰዎች ላይ እንደ ጋዝ ወይም ተቅማጥ ያሉ የጨጓራና አንጀት ህመም ሊያስከትሉ ይችላሉ። በተጨማሪም ለምግብ መፈጨት፣ በሽታ መከላከልና አጠቃላይ ጤና ጠቃሚ የሆኑ የአንጀት ባክቴሪያዎችን በመጉዳት ስራቸውን ያስተጓጉላሉ። የጠቃሚ የአንጀት ባክቴሪያዎችን ቁጥር እንዲመናመን በማድረግ በሽታ አምጭ ጎጂ ባክቴሪያዎች እንዲነግሱ ያደርጋሉ የሚሉ በርካታ ማረጋገጫዎች በታዋቂ የህክምና መጽሄቶች ላይ እየታተሙ ነው።
✍️ በእነዚህና ሌሎችም ምክንያቶች በመመርኮዝ የአለም ጤና ድርጅት ምግብና መጠጥ ማጣፈጫ አርቲፊሻል ስኳሮችን መጠቀም አይመክርም። ከዚህ ባሻገር አርቲፊሻል ስኳሮች ለክብደት ህክምና እንደማይረዱ ብሎም የልብ ህመምን ጨምሮ ሌሎች በርካታ የረጅም ጊዜ የጤና ችግሮችን ሊያስከትሉ እንደሚችሉ አፅንዖት ሰጥቷል።
የዚህን ጽሁፍ ሙሉ መረጃ በዶ/ር መላኩ ታዬ ብሎግ https://melakutaye.com/artificial-sweeteners-and-their-health-risk/ ማንበብና ለሌሎችም ማጋራት ይችላሉ።
ቴሌግራም https://t.me/hakimmelaku
ቲክቶክ https://www.tiktok.com/@hakimmelaku
WhatsApp/Telegram consults at +251921720381
Dr. Melaku Taye (Endocrinologist, Lipidologist, Health advocate practicing at Tikur Anbessa Specialized Hospital, Addis Ababa University)
Get social with Hakim on Youtube: http://www.youtube.com/@Hakim207
@HakimEthio