ያቺ በአባታችን አዳምና በእናታችን ሔዋን በደል ተዘግታ የነበረችውን የገነትን ደጅ ማን ከፈታት? ሱራፊ በእሳት ሰይፍ እየጠበቃት ተዘግታ የኖረችዋ የተድላ ደስታ ስፍራዋን ገነትን ማን ከፈታት? ሲል ሊቁ አባ ጽጌ ድንግል ይጠይቃል። እውነትም ግን በአምላክ ላይ በማመጽ በመፈንቅለ አምላክ ሙከራ ምክንያት የተዘጋችውን የገነትን ደጅ ማን ከፈታት? ሊቁ ጠይቆ ብቻ አያቆምም መልሱን አስቀድሞ ከላይ እንዲህ ሲል መልሶልናል፦ ከአንቺ ጽድቅ ውጪ የገነትን ደጅ የከፈታት ማን ነው። የገነት ደጅ የተከፈተው በእመቤታችን ጽድቅ መሆኑን አስረግጦ ይነግረናል።
ይህ ገነትን ያስከፈተ የቀድሞውን በደል የካሰ ጽድቅ እንዴት ያለ ነው? መልሱም ይኸውም ጽድቋ የማኀጸኗ ፍሬ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ስለምን ጽድቋ ብሎ ጠራው ከተባለም ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍሷም ነፍስን ነስቶ ከርሷ የነሰውንም ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍሶ በደሙ ማኀተምነት የገነት ደጅ ተከፍቷልና ጽድቅሽ ብሎ ጠራው። አንድም በንጽሕና በቅድስና ሆና ቢያገኛት በጽድቋ ምክንያት ከእርሷ ለመወለድ መርጧልና የአምላክ ከእርሷ መወለድ ከእግዚአብሔር ሁሉን ቻይነት ቀጥሎ የእርሷ በጽድቅ(በንጽሕና በቅድስና) መገኘት አስፈላጊ ነውና ጽድቅሽ ሲል ጠርቶታል። ይህ መዐዛ ቅድስናዋ መዐዛ ንጽሕናዋ የፍጥረታትን ንጉስ የገነትን ጌታ ወደምድር ሳበው። ከበደለው ከሰው ልጅ ጋርም አስታራቀው። የገነትን ፈጣሪ ወደዚህ ምድር ከሳበው ከሰው ጋር ካስታረቀው ከዚህ ከጽድቅሽ በቀር የገነትን ደጅ የከፈታት ማን ነው ሲል ነው ሊቁ።በዚህ ጽድቅሽም አዳም ወደ ቀድሞ ስፍራው ወደ አበባዋ ምድር ወደ ተድላዋ ስፍራ ገነት ተመለሰ እናታችን ሔዋንም አጥታው የነበረውን ገነት አግኝታለችና ከገነት ጣዕም የተነሳ በደስታ ዘለለች።
ድንግል ሆይ እኛም ዛሬ በኃጢአታችን ምክንያት ዘወትር የምንዘጋትን የገነት ደጅ የሚከፍትልን ከአንቺ ጽድቅ በቀር ማን ነው? ስለዚህ ቸል አትበይን አትተይንም የገነትንም ደጅ ምሪን መንገዱን ዘንግተናዋልና ፍለጋዋንም ጠቁሚን በዓለም ማዕበል በመባዘን መንገዷን ስተናልና። የገነትን ደጅ ዘግቶ የምትገለባበጥ ሰይፍ ሆኖ እንዳንገባ የሚከለክለን ኃጢአታችንንም ከእኛ አርቂልን ወደ ቀደመ ሥፍራችን እንገባ ዘንድ እንደ እናታችን ሔዋንም ከደስታ ብዛት ለመዝለል ያበቃን ዘንድ የገነትን ደጅ በጽድቅሽ ክፈቺልን የገነትን መዐዛዋን አሽትተን እንታደስ ዘንድ የገነትን ጣዕም አቅምሽን የገነትን ደጅ የሚያስከፍት ምንም ጽድቅ በእኛ ዘንድ የለምና።
ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና የገነትን ደጅ ነገር እንመርምር የሊቁ ምሥጢር በዚህ ብቻ የሚያበቃ አልመሰለኝምና ግሩም የሆነውን ይህንን ምስጢር እንረዳ ዘንድ አምላካችንን እንለምነው የተሰወረውን የሚያውቅ ምስጢርን የሚገልጥ እርሱ ነውና እንማጸነው። ይህች የገነት ደጅ ሯሷ ድንግል ማርያም ናት። በር ከውጭ ያለው ወደ ውስጥ እንዲገባ ምክንያት እንዲሆን ከገነት ውጭ የነበርን እኛ በእርሷ ምክንያት ወደ ገነት ገብተናልና ወደገነት የገባንባት የገነት ደጃችን እርሷው ናት። ጽድቅሽ ያለውም መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ነው። ሊቁ"እንበለ ጽድቅኪ መኑ ለአንቀጸ ገነት ዘአርኀዋ" ማለቱ ፍጹም የሆነ የድንግልናዋን ነገር ማንሳቱ ነው። አስቀድሞ ሕዝቅኤል በትንቢቱ ከወደ ምስራቅ ያያት ከኃያላን ጌታ በቀር ማንም ያልገባባት በምስራቅ የተተከለችዋ ደጅ ገነቲቱ እመቤታችን ናት።
ድንግለ ሆይ የገነትን መዐዛ እንናፍቃለንና የገነት መዐዛ የተባለ መዐዛሽን አሻችን በኃጢያት የከረፉውን ሰውነታችንን በመዐዛሽ ይታደስልን ዘንድ። በምልጃሽ ቁልፍነትም የገነትን ደጅ ክፈቺልን።
በጌጋየ አዳም ወሔዋን ሱራፊ ዘዐፀዋ
እንበለ በጽድቅኪ መኑ ለአንቀጸ ገነት ዘአርሃዋ
ተፈስሒ ድንግል መያጢተ አዳም እምጼዋ
በተዓምርኪ ውስተ ምድረ ነኪር አቲዋ
ከመ ጣዕዋ አንፈርዓፀት ሔዋ
ዲ/ን በረከት ንጉሴ