አምባ ዲጂታል፤ ዐርብ ግንቦት 23፣ 2016 - የሚኒስትሮች ምክር ቤት ከሕጋዊ እና ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማዕቀፍ ውጪ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የፖለቲካ ቡድኖች መልሰው እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ለመመዝገብ የሚያስችላቸውን ድንጋጌ የያዘ የአዋጅ ማሻሻያ ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መርቷል፡፡
ምክር ቤቱ የአዋጅ ማሻሻያውን ተቀብሎ ወደ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመራው ዛሬ አርብ ግንቦት 23፣2016 ባደረገው ስብሰባ እንደሆነ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አስታውቋል። ጽሕፈት ቤቱ ያወጣው መረጃ እንደሚያስረዳው ምክር ቤቱ በዛሬው ዕለት በአራት ረቂቅ አዋጆች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በዛሬው ስብሰባ ውሳኔ እንደተላለፈበት በቀዳሚነት የጠቀሰው የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ አዋጅ ማሻሻያ የቀረበበት በ2012 የወጣው የምርጫ ሕግ፤ እውቅና የተነፈጉ የፖለቲካ ፓርቲዎችን መልሶ ከመመዝገብ ጋር በተያያዘ ክፍተት ያለበት እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡
“ከሕጋዊ እና ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማዕቀፍ ውጪ የቆዩ የፖለቲካ ቡድኖች በሰላማዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ ፍላጎት በሚያሳዩበት ጊዜ እነዚህን አካላት ሕጋዊ የፖለቲካ ፓርቲ አድርጎ ለመመዝገብ የሚያስችል ሥርዓት በነባሩ አዋጅ ላይ አልተካተተም” ሲል በሥራ ላይ ያለው አዋጅ ላይ የታየውን ክፍተት ይገልጻል።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ የመራው ማሻሻያ ላይ የፖለቲካ ቡድኖች “በሰላማዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ እና ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት ፍላጎት በሚያሳዩበት ጊዜ” መልሰው ለመመዝገብ የሚችሉበትን ሥርዓት የሚዘረጋ እንደሆነም ተጠቅሷል።
ዛሬው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ ውሳኔ ላይ የተጠቀሰው የፖለቲካ ቡድኖች መልሶ የመመዝገብ ጉዳይ ከሕወሓት ዳግም ሕጋዊ እውቅና የማግኘት ጉዳይ ጋር በተያያዘ ውዝግብ ፈጥሮ ነበረ ጉዳይ መሆኑ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት መቀስቀስን ተከትሎ የአመጻ ተግባር ላይ ተሰማርቷል በሚል የህወሓትን ሕጋዊ ሰውነት የሰረዘው ጥር 2013 ነበር።