#ክፍል #ስድስት
(ፉአድ ሙና)
.
በህይወት ዉስጥ ምንም አይነት መደነቃቀፍ ባይኖር ኖሮ የሰዉ ልጅ አምላክ መሆኑን የሚጠረጥር ይመስለኛል። አንድም ቀን እንደዚህ ይጨንቀኛል ብዬ ገምቼ አላዉቅም። እናቴ ሁሉንም ቀዳዳዎቼን ሸፍና አንደላቃኝ ነበር። ዛሬ ግን እናቴ መተማመኛ እንደማትሆነኝ ሊያሳየኝ ሲፈልግ ንቁዋ እናቴን ድንዝዝ አድርጎ ከአልጋ አጋደማት። አሁን ከእናቴ ዉጪ ዞር ብዬ አይቼዉ የማላዉቀዉን ጌታ እየተማፀንኩት ነዉ። ችግር ሲጨመድደን ትናንት ዞር ብለን ያላየነዉን አምላክ ከመማፀን በቀር ምን አማራጭ አለ? ምንም!
.
ማክሰኞ ጠዋቱን እማዬን ከተኛችበት የሆስፒታል አልጋ ላይ እንደተጋደመች ክፍሉ ዉስጥ ካለዉ የኦክስጅን ሳጥን ጎን ተቀምጬ አያታለሁ። እማዬ ፊቷ ሙሉ ለሙሉ ወደ ቢጫነት ተቀይሯል። ፈጣሪ ግን ምነዉ አለ? ያለአባት በመከራ ያሳደገችኝን እናቴን ለምን ያሰቃይብኛል? ለነገሩ ጉልበተኛ ነኝ አይደል የሚለዉ እንዳሻዉ! ብቻ ዝም ብዬ እናቴን አያታለሁ። ያላደላት ሚስኪን ፍጡር!
አብነት እንቅልፍ በዘጋዉ ጎርናና ድምፅ "ስማ ቁርስ አያመጡልንም እንዴ?" አለ። ማታ አብረን ያደርነዉ እኔናአብነት ነበርን።
ቀና ብዬ የተቀመጠበትን ነጭ ባለስፖንጅ ወንበር የእጅ መደገፊያ እያየሁ "አንተ አስታዉሰኸዉ እነሱ የሚረሱት ይመስልሀል?" አልኩት። አብነት ሳቁን ለቀቀዉና "ኧረ ባክህ? ፈጣሪህን ይህን ያህል ብታምነዉ ወርቅ ከሰማይ ያዘንብልህ ነበር።" አለኝ።
ዉስጤ ላይ ብሶቴ እየተቀጣጠለ "ባክህ እሱ መከራ ያዝንብ ተወዉ!" አልኩ።
እኔና አብነት እየተጨዋወትን ብዙም ሳንቆይ አምሪያ የክፍሉን በር ከፍታ ገባች። በእጇ ሰማያዊ ዘንቢል አንጠልጥላለች። አብነትን ዞር ብዬ አየሁትና ሳቅኩ።
አምሪያ በሩን ዘግታ ወደኛ እየዞረች "ምን ያስቅሀል? ለነገሩ ሲጀማምር እንደዚህ እኮ ነዉ።" አለች።
አብነት ወዲያዉ ዘንቢሉን ተቀብሎ ምግቡን ማቀራረብ ጀመረ። እንደሆዱ የሚያፈቅረዉ ነገር ያለ አይመስለኝም።
አምሪያ ከእማዬ አጠገብ ያለዉ ወንበር ላይ እየተቀመጠች "ሀቢቤ አሁንም ምግብ መዉሰድ አልጀመሩም?" አለችኝ። "አዎ ባክሽ ግልኮስ ነዉ የያዛት! ምንም አላማረኝም።" አልኳት። እማዬ በሲቃ በታጀበ ድምፅ "ተዉ ሀቢቤ እንደሱ አይባልም። ፈጣሪ አለ።" አለችኝ። እማዬ መናገር ተራራ ከመግፋት እየከበዳት መጥቷል። እንደዉም ዛሬ ትንሽ አነጋገሯም ተስተካክሏል። አይ እማዬ ፈጣሪ አለ ነዉ ያለችዉ? ፈጣሪማ ለማሰቃየት ሲሆን መች ይጠፋል!? አብነት ምግቡን አቀራርቦ ሲጨርስ አምሪያን "ባለአጥሯ ነይ እንብላ!" አላት። ሳቅኩኝና ወደ አብነት ተጠጋሁ። አምሪን በአንገቴ ነይ ስላት ወንበሯን ይዛ ከኛ ጋር ተቀመጠች። አብነት ገና እጁን ወደ ምግቡ ሲሰነዝር አምሪያ "ወይኔ ስጋ ነዉ እንደዛኛዉ ልጅ ነህ አይደብርህም አይደል?" አለች። እንደዛኛዉ ልጅ ያለችዉ ሚኪያስን ነዉ። አብነት የጠቀለለዉን እየጎረሰ "በፈጣሪ ስም ነዉ የታረደዉ አይደል እንዴ? በእግዚአብሔር ይሁን በአላህ እነሱ ይስማሙበት። የኔ ሀላፊነት መብላት ነዉ።" አለ። እኛ አንድም ቀን የሙስሊም የክርስቲያን ስጋ ብለን ለይተን በልተን አናዉቅም። ያገኘነዉን ማተራመስ ነዉ።
አምሪያ የአብነት ንግግር ስቅጥጥ እያላት "አይ እምነት እንኳ እንዲህ ድንበር የሚታለፍበት ጉዳይ አይደለም። ማንነትህን በደንብ የምትረዳዉ ስታከብረዉ ነዉ።" አለች።
አየር ስለያዙብኝ እየበሸቅኩ "ይቅርታ እንብላበት!" አልኩ።
"እሺ እጃችሁን አትታጠቡም? ከመድሀኒት ጋር አድራችሁ?" አለች።
"አምሪ ኧረ ምንም አንሆንም ይኸዉ ሀያ አመት ሊሞላኝ ነዉ አንድም ቀን ታጥቤ አላዉቅም። ምን ሆንኩ?" አልኳት።
ካልታጠባችሁ አልበላም ብላ ስታሸማቀን ተነስተን ታጠብንና መብላት ጀመርን።
አብነት የአምሪያን ፊት የሚያክል ጉርሻ ጠቅልሎ ላጉርስሽ ሲላት ከአይኗ እንባ እስከሚፈስ ድረስ ሳቀች። በመሀል እማዬ እያየችን ፈገግ ስትል አየኋት። ወደሷ ስዞር "ሀቢቤ ለሴት ልጅ የሚሆን ጉርሻ በመጠኑ አጉርሳት!" አለችኝ።
እማዬ ብላኝ እንቢ ብዬ አላዉቅም። አጎረስኳት። አምሪ መጉረስ አልፈለገችም ነበር ግን እማዬን ላለማስከፋት ብላ ጎርሳልኝ ፈገግ አለች።
.
አምሪያ ከሄደች በኋላ የክፍል ተማሪዎች እየተንጋጉ ሆስፒታሉን ወረሩት። የኢምባሲ በር ጋር ተቃዉሞ የወጡ እንጂ በሽተኛ ሊጠይቁ የመጡ አይመስሉም። እየመሯቸዉ የመጡት ሚኪያስናከሪሜ ናቸዉ። አምስት አምስት እየሆኑ እየገቡ እናቴን አይተዋት ወጡ። እኔም እናቴም በጣም ደስ ብሎናል። ሆስፒታሉ ዉስጥ ግርግር ላለመፍጠር ብለን ግቢዉ ዉስጥ ወርደን ማዉራት ጀመርን። ሀብታሙ እንባ እየተናነቀዉ "ሀቢቤ አብሽር እሺ ለፈተና እንዳታስብ እኔ አለሁልህ።" አለኝ። ሀብታሙ እና እኔ እኮ በወጉ እንኳ ክፍል ወስጥ አዉርተን አናዉቅም። ብቻ ሀበሻ በችግር ሰዓት መልዓክ ካልሆንኩ የሚል ሚስኪን ፍጡር ይመስለኛል። ፈገግ ብዬ አየሁት። ሴቶቹ በየተራ ምግብ ካላመላለስን አሉ። እኔ ግን ምንም የምግብ ችግር ስለሌለ እንዳይለፉ ነገርኳቸዉ። ብቻ ብቅ እያሉ እንደሚጠይቁ ነግረዉን ነገ ለፈተና እንዳላረፍድ አስጠንቅቀዉኝ ሄዱ። ሰብስበዉ የሰጡኝን ብር ደስ እንዲላቸዉ ብዬ ተቀብያቸዋለሁ።
.
ማታዉን ወ/ሮ ለይላ መጥተዉ እማዬን በደንብ ፈታ አደረጓት። ሀጂ ቀጣዩን ሶስት ቀን ፈተና መሆኔን ስለተረዱ ለሊት ስድስት ሰዓት ድረስ እየተኙ የቀረዉን ለሊት አምሪያን ሆስፒታል አድርሰዉ እኛን ወደቤት መልሰዉን ከአምሪያ ጋር እማዬን ሲጠብቁ ለማደር አሰቡና አማከሩን። ምንም ቢከብደንም አማራጭ ስላልነበረን ተቀበልነዉ። ፈተናዉ ተጀመረ። የረቡዕ እለትን ሙሉ ፈተና የሰራልኝ ሀብታሙ ነበር። ትምህርት ብቻ ሳይሆን ማስኮረጅም አንደኛ ነዉ። ሀሙስ ጠዋት ወደ ፈተና ልገባ ስል ሁለት ሀይማኖተኛ ሀይማኖተኛ የሚሰራራቸዉ የግቢያችን ልጆች አገኙኝና "ሀቢብ አሁንስ የትም ብትዘል የማታመልጠዉ አምላክ መኖሩ ገባህ?" አሉኝ። ሸምድደዉት የመጡ እስከሚመስለኝ ድረስ ሁለቱም ደጋገሙልኝ። ዉስጤ በጣም ቆስሏል። ሌላ ጊዜ ቢሆን አንስቼ አፈርጣቸዉ ነበር። አሁን ግን ቅስሜ ስብር ስላለ ትቻቸዉ ሄድኩ። ምን ራሳቸዉን የፈጣሪ መልአክተኛ ያስመስላሉ? የሆኑ አመዳሞች።
.
እማዬ ከሆስፒታል መዉጣት የነበረባት እነሚኪ በነገሩኝ መሰረት ከሆነ ማክሰኞ ወይም ረቡዕ ነበር። ግን ምግብ ስለማትወስድ ትንሽ ትቆይ ብለዉ እስከአሁን አልወጣችም። ፌቪዬ በቀን ከአስሬ በላይ የምትደዉልበት ጊዜ ሁሉ አለ። እማዬን ለማሳየት ምቹ ጊዜ አላገኘሁላትም እንጂ አስጎበኛት ነበር። ወይ እንደክፍል ልጆች ሰብሰብ ብለዉ ቢመጡ ያመች ነበር። ለነገሩ ነግሬያት ቅዳሜ ትምህርት ቀርተዉ ከጓደኞቿ ጋር እንደሚመጡ ነግራኛለች። የግል ስለምትማር ቅዳሜም ቀኑን ሙሉ ትምህርት አላቸዉ።
ቀኑ እየቆጠረ ሄዶ አርብ ደረሰና ፈተና ጨረስን። እኔ እኮ ባልማርም ግድ የለኝም። የምማረዉ እማዬን ደስ እንዲላት ብዬ ነዉ።
.
አርብ ከፈተና መልስ አራታችንም ተሰብስበን ወደ ሆስፒታል ሄድን። ልክ ስንደርስ እናቴ የተኛችበት አልጋ አጠገብ ዶክተሯ እና አምሪያ አብረዉ ቆመዋል። ነርሷ በተቃራኒ አቅጣጫ በኩል ቆማ ዶክተሯ የምትነግራትን ትመዘግባለች። እንደገባን ዶ/ር ቀመሪያ ፈገግ እያለች "ሄይ ሀቢብ" አለች። እየሳቅኩ "እሺ ዶ/ር አለሽ ግን?" አልኳት።