ሚካኤል ማለት መኑ ከመ እግዚአብሔር ሚ ዕፁብ ነገር ማለት ነው፤ በዕብራይስጥ ‹‹እንደ እግዚአብሔር ያለ ማን ነው!›› ማለት እንደሆነ ቅዱሳት መጻሕፍት ይጠቅሳሉ፡፡
አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በመዝገበ ቃላት መጽሐፋቸው ላይ እንዳሰፈሩት ደግሞ የስሙን ፊደላት በመተንተን እንዲህ ተርጉመውታል፤ ሚ-መኑ፣ ካ-ከመ፣ ኤል-አምላክ፤ ‹‹መኑ ከመ አምላክ፤ እንደ አምላክ ማን ነው!›› (መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ)
በዚች ዕለት እስራኤልን በሙሴና በአሮን መሪነት ባሕር ከፍሎ ጠላት ገድሎ፣ መና አውርዶ፣ ደመና ጋርዶ በብዙ ሣህል ታድጎ ከምድረ ግብጽ ማውጣቱ ይነገራል፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ሕዝበ እስራኤልን ከግብጽ ባርነት ነፃ ሲያወጣቸው ይመራቸው የነበረ መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ነበር፡፡ ሹመቱ በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይም በመሆኑ ስለ እነርሱ ዲያብሎስን ይዋጋው፣ በጸሎትም ረድቷቸዋል፡፡
አምላካችን እግዚአብሔር ሳጥናኤልን በትዕቢቱ ምክንያት ከሥልጣኑ አውርዶ ወደ ምድር ሲጥለው ቅዱስ ሚካኤል በእርሱ ቦታ በዐሥሩ ከተማ በመቶውም ነገደ መላእክት ላይ ተሹሟል፡፡ የቅዱስ ሚካኤል ሹመት በነገደ መላእክት ላይ ብቻ አይደለም ፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር ሕዝብ በሆኑት ላይም ጭምር ነው፡፡
በኅዳር ወር በዐሥራ ሁለተኛው ቀን ቤተ ክርስቲያናችን የታላቁ መልአክ የቅዱስ ሚካኤልን በዓል በታላቅ ድምቀት ታከብረዋለች፡፡
መላእክት ሰዎች በዓለም ፈተና ውስጥ ሆነው ሰይጣን ሊያደክማቸው ሲፈልግ ኃይልን ብርታትን የሚሰጡ፣ ይህን ዓለም ንቀው በበርሃ ወድቀው ከሥጋ ምኞት ጋር የሚጋደሉትን፣ በከተማም እየኖሩ መንፈሳዊ ትሩፋት የሚያደርጉትን ደግሞ የሚያበረቱ ናቸው፡፡
የቅዱስ ሚካኤል አማላጅነት በሐዲስ ኪዳንም እንደነበር ይህ ነቢይ በትንቢቱ ‹‹በዚያም ዘመን ስለ ሕዝብህ ልጆች የሚቆመው ታላቁ ሚካኤል ይነሣል›› በማለት ተናግሮለታል፡፡ ስለዚህም ቅዱስ ሚካኤል እኛን ከሰይጣን አሽክላና ወጥመድ ይጠብቀንና በጸሎቱ በእግዚአብሔር ፊት ይቆምልን ዘንድ በእኛም ላይ ሹም ነው፡፡ ምክንያቱም እኛ የእግዚአብሔር ሕዝቦችና የርስቱ ወራሾች ነንና፡፡ (ዳን.፲፪፥፩)
በመጽሐፈ ስንክሳርም ተመዝግቦ እንደምናኘው ቅዱስ ሚካኤል በየወሩ በዐሥራ ሁለት ቀን ለመታሰቢያው በዓል ተሠርቶለታል፤ እርሱ ስለ እኛ የምድሩን ፍሬ ይባርክልን ዘንድ ዝናሙም በጊዜው እንዲወርድልን የወንዙንም ውኃ እንዲመላልን ነፋሱንም የምሕረት ነፋስ እንዲያደርግልን ሁሉንም የተስተካከለ እንዲያደርግልን ወደ እግዚአብሔር በጸሎት ይማልዳልና፡፡ (ስንክሳር ኅዳር ፲፪)
ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ‹ሚካኤል ሥዩም በዲበ ኃይላት፤ በኃይላት ላይ የተሾምክ ሚካኤል› ሲል ያመሰገነው ቅዱስ ሚካኤል በኃይላት መላእክት ላይ የተሾመ ሊቀ መላእክት እንደመሆኑ በዓለ ሢመቱ ኅዳር ፲፪ ቀን በመላው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በድምቀት ይከበራል፡፡ (መጽሐፈ አክሲማሮስ)
የሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል አማላጅነትና ተራዳኢነት አይለየን፤ አሜን፡፡
ምንጭ፤ መጽሐፈ አክሲማሮስ
ስንክሳር ዘወርኃ ኅዳር
መድብለ ታሪክ ቁጥር አንድ (በመ/ር ዐይነ ኩሉ ያየህ 2011 ዓ.ም)
የዩቱብ የቴሌግራምና የቲክቶክ ቻናሎቼ ቤተሰብ መሆን የምትሹ
ቴሌግራም
https://t.me/tsidq
ዩቱብ
https://www.youtube.com/@12Samual
ቲክቶክ
https://vm.tiktok.com/ZMhn1uTp4/
fb
https://www.facebook.com/share/p/GsxfVN3TKR8X8jwL/