አርስቶትል
በህልውናችን ውስጥ ያለምክንያት የሚፈጠር ነገር የለም፡፡ ከእያንዳንዱ ፍጥረት በስተጀርባ አላማ አለ፡፡ ህይወትም ሆነ ሞት የተፈጠሩት በምክንያት ነው፡፡ ተፈጥሮ ማንኛውንም ነገር በከንቱ አትፈጥርም
ሰዎችም እንዲሁ የራሳቸው ተፈጥሯዊ አላማ፣ ግብና አቅጣጫ አላቸው፡፡ የአላማቸውና የተልእኳቸው ስኬት ውበት፣ እርካታና ደስታን ይፈጥራል፡፡ አምላክ ሰውን የፈጠረው በምክንያት፣ በአላማ ነው፡፡ ሰው የተፈጠረለትን አላማ መረዳት ሲሳነው ደስታና እርካታ ይርቀዋል፡፡ በአንጻሩ የተፈጠረበትን ምክንያት ተገንዝቦ ተልእኮውን ማሳካት ሲችል የአእምሮ ሰላምና የመንፈስ እርካታን ያገኛል፡፡
በብዙሀኑ ዘንድ ( Self - Realizationism) በመባል ፣ የሚጠራው የአርስቶትል የስነ ምግባር ፍልስፍና መልካም ህይወት ወይም ደስተኝነት ባህሪን፣ ሰብእናንና እምቅ ሀይልን ሙሉ ለሙሉ ጥቅም ላይ ከማዋል ይመነጫል የሚለውን እሳቤ መሰረት ያደረገ ነው፡፡
አንድ ህጻን እንደተወለደ ሰው አይባልም ሰው የመሆን እምቅ ሀይል ያለው ግን ሰው ለመባል ያልደረሰ ፍጡር ነው፡፡ እውነተኛ ሰው ለመሆን እምቅ ሀይሉ እውን ሆኖ መታየት አለበት፡፡
አንድ ሰው ከቤትሆቨን ያልተናነሰ ዜማዊ ተሰጥኦ ተችሮት ተሰጥኦውን ማወቅ ከተሳነው ወይም እያወቀ መጠቀም ካቃተው ከቶውኑ አርቲስት ሊሰኝ አይችልም፡፡ ታላቅ አርቲስት ለመሆን የሚያበቃ እምቅ ሀይል ቢኖረውም ሀይሉንና ተሰጥኦውን ጥቅም ላይ እስካላዋለው ድረስ የአርቲስትነት ተሰጥኦ ስላለው ብቻ አርቲስት አይባልም፡፡
እንደ አርስቶትል እሳቤ የሰው ልጅ ተቀዳሚ አላማ ተፈጥሮውና ተሰጥኦው እስከፈቀደለት አጥናፍ ተለጥጦ እምቅ ሀይሉን እውን ማድረግና ምሉእነትን መጎናጸፍ ነው፡፡ ይህን ማድረግ የቻለ ሰው ተልእኮውን ከመወጣት ስሜት የሚመነጭ የተሟላ እርካታና ደስታ ያገኛል፡፡
አንድ የአበባ ዘር ሊያብብ፣ ሊፈካና ሊያፈራ የሚችለው የእድገት ኡደቱን አጠናቆ ውበቱንና ሙሉነቱን አሟልቶ ሲገኝ ብቻ ነው፡፡ ሰው በርካታ ውስብስብ ባህሪያትን ይዞ ቢፈጠርም ተልእኮውን መወጣት ከቻለ ስኬታማ የሆነ ውብ፣ ደስተኛና ምሉእ ፍጡር ይሆናል፡፡
@tofamotivationallife