አንተ ማለት ትክክለኛው ማንነትህ ነህ። ዛሬ ታይቶ የሚጠፋ ማንነት የለህም፤ በየጊዜው የሚቀያየርና ለሰዎች እይታ ብቻ የሚኖር ስብዕና የለህም። የምታደርገውን ሁሉ ሰዎች አይተው እንዲያደንቁህ አትፈልግ፤ በሰው ፊት ተወዳጅና ጥሩ ስም ያለው ለመምሰል ከአቅምህ በላይ አትኑር። ሁላችንም ደረጃ አለን፤ እያንዳንዳችን የሚወክለን የገቢ ምንጭ፣ ማንነትና ስብዕና አለን። ለእራሳችን ከመገዛታችን፣ እራሳችንን ከማስደሰታችን፣ በእራሳችን ከመኖራችን በፊት ግን ለታይታና እይታ ውስጥ ለመግባት የምናወጣው ወጪ፣ የምናባክነው ጊዜና ንብረት ሁሉ ዋጋችንን የሚያወርድ እንጂ የሚያሳድግ አይደለም። ሳይኖርህ እንዳለህ ስለታሰብክ፣ ከደረጃህ በላይ ስለተለካህ፣ በማይወክልህ ማንነት ስለታወቅክ ጊዜያዊና የውሸት ኩራት (pride) ሊሰማህ ይችላል፣ ነገር ግን በስተመጨረሻ እራስህን ስታታልል እንደነበር ትገነዘባለህ። መኖራችን ለሰዎች፣ ለስም፣ ለይውንታ፣ ለመወደድና ለክብር አይደለም። መኖራችን ከእራሳችን በላይ ሰዎችን በትክክለኛው መንገድ ለመርዳትና ለማገዝ ነው።
አዎ! ጀግናዬ..! ልክህን አስቀድም! እንደ አቅምህ፣ በደረጃህ ተንቀሳቀስ። ሃብታም መስለህ መታየትህ ያለህንም ከማሳጣቱ ውጪ ምንም የሚያተርፍልህ ነገር የለም፤ የቤትህን ክፍተት ሳትሞላ በሔድክበት ሁሉ ካላጋበዝኩ ማለትህ ክፍተትህን አይሞላም፤ ባልሆንከው ሰውነት ለመታወቅ መጣርህ ትክክለኛውን አንተነትህን አይቀይርም። እውነት እውነት ነው፤ ምንም ብትደብቀው፣ ብታስመስልበት፣ በውሸት ብትሸፍነው በጊዜው መታወቁና መገለፁ አይቀርም። ያንቺ ባልሆነው ጌጥ ብታጌጪ አንድም ድጋሜ በእራሱ ጌጥ ለመታየት ትቸገሪያለሽ፣ ሌላም ያለጌጥ ያለውን ማንነት ለማሳወቅ አጣብቂኝ ውስጥ ትገቢያለሽ። ማንም የሚችለውን ያውቃል፤ ወጪውን ገቢውን ጠንቅቆ ይረዳል፤ መጠኑ ለእራሱ ግልፅ ነው።
አዎ! ለጊዜያዊ ከንቱ አድናቆትና ውዳሴ ብለህ እወነተኛ ማንነትህን (identity) አትጣ፤ ከምትችለው በላይ ለመኖር አትሞክር፤ አቅምህን ተረዳው፤ ችሎታህን በሚገባ እወቅ። ማስመሰል ከከፋው ውድቀት በቀር የሚያመጣው ነገር የለም። ሙሉና የተረጋጋ ህይወት የሚገኘው ሰዎች ፊት መስሎ ለመታየት በሚደረገው ጥረት ሳይሆን፣ የእራስን መልክና ገፅ፣ አቅምና ደረጃ በመቀበል በእርሱ ልክ በሚገባ በመኖር ነው። ከሌለህ የለህም፤ እንዳለህ ለማስመሰል የምታስመስልበት ምክንያት የለም። ድህነትህን አይቶ የሚርቅህ ካለ ቢመጣም አንተን ብሎ ሳይሆን ንብረትህን ብሎ እንደሆነ ተረዳ። በየጊዜው እራስህን ከማሻሻል በላይ ለታይታ በመኖርና በማስመሰል እራስህን አታድክም። መኩራት ካለብህ ባለህና እጅህ ላይ ባለው ነገር ኩራ፤ መደሰት ካለብህ ከውጭ በሚመጣ አድናቆትና ውዳሴ ሳይሆን ከገዛ ማንነትህ ከውስጥህ በሚመነጨው ጥልቅ ስሜት ተደሰት።
ውብ ምሽት ይሁንልን! 🌘🌒
(Epha A.)
ምክረ-አዕምሮ ለተሻለ ነገ!
#SHARE እንዳይረሳ ቤተሰቦች! 🙏😍
በYouTube አማራጭ ይቀላቀሉን!
🔺🔻 SUBSCRIBE NOW
https://www.youtube.com/channel/UCIZv4h3iDx2C7CGbv9WIkVg?sub_confirmation=1
ምክረ-አዕምሮ/ @mikre_aimro 😊 💪