ዘንድሮ እያነቡ እስክስታ ነው
ያሬድ ዘ-ካዛንቺስ
ሰፈሬ ካዛንቺስ ተራዋ ደርሶ ልትፈርስብኝ ነው። ለአዲስ አበቤ ሰፈሩ መታወቂያው ነች። ታሪኩ ነች። የልጅነት ትዝታው ነች። በሃያ ሺህ ሄክታር ግቢ ውስጥ ፈረስ ሲጋልብ ያደገ የክፍለሐገር ሰው ላይረዳን ይችላል።
"ያንተ ቤት ሲንኳኳ ይሰማል እኔ ቤት" የሚለው ዘፈን የተዘፈነው ለኛ ሰፈር ይመስለኛል። ከጎረቤቶቻችን ጋር ግድግዳ ብቻ ሳይሆን ጣራም እንጋራለን። ኑሮ ካሉት የቀበሌ ቤትም ይሞቃል። የኖርነው እንደምስጥ አፈር ቤት ነው። ቤታችን ተመሳሳይ ኑሯችን ተመሳሳይ። እኛ የካዛንቺስ ልጆች ከተለያየ እናት ብንወለድም አንድ አይነት ነን። ኑሯችን የተመታ ቢሆንም ለብዙ ሰፈር የሚተርፍ ፍቅር ግን አለን።
ካዛንቺስ ልትፈርስብን ቀጠሮ ተይዞላታል። ለዘመናት የኖሩበት ሰፈር ሲፈርስ የሆነ የሚሸክክ ነገር አለው። በተለይ እንደኔ typical habesha ከሆንክ አሮጌ ልብስህን መጣል ራሱ ይደብርሀል። ቤትህማ ከነ እርጅናው ፥ ከነ አይጦቹ ፥ ከነ ተደራራቢ አልጋው ፥ ከነ የህዝብ ሽንትቤቱ ሳይቀር ታሪክህ ይመስልሃል። ቅርስህ የፈረሰ ያህል ይሰማሃል። ቅር ቅር ይልሃል። ግን ደግሞ deep dawn ደስ ብሎኛል። አዎ ደስ ብሎኛል።
አዳነች አቤቤ ሌላ ሰፈር አስራ አራት ሆነው ከሚኖሩበት ያዘመመች የቀበሌ ቤት ውስጥ አውጥታ ፅድት ያለ አፓርትመንት ውስጥ የከተተቻቸውን እናቶች አይተን ይሄን እድል ለኛና ለደካማ ወላጆቻችን የተመኘን ብዙ ነበርን። ዛሬ ከዚህ ለዘመናት አፍኖ ከያዘን ጉሮኖ የምንተነፍስበት ቀን ሲቃረብ እያነቡ እስክስታን ነው የጨፈርነው። ከኖርንበት ቀዬ በመሄዳችን ብንከፋም ወደተሻለ ቦታ በመሄዳችን ግን ደስተኞች ነን። እኛ የችግርና የድህነት ሱስ የለብንም። የተሻለ ነገር እንወዳለን። ከኛ ከባለቤቶቹ ከካዛንቺስ ልጆች በላይ ስለኛ የሚያውቅ የለም። ከጳጳሱ በላይ ካቶሊክ መሆን ላሳር ነው ።
ሁሉን ነገር ማጥላላት ደስ አይልም። እኛ ወጣቶች ነን የትም እንኖራለን። ደሀና ደካማ ወላጆቻችን በተገቢው መንገድ ወደተሻለ ቤት ይዘዋወሩ እንጂ ፓላስ ላይ ሲኖር እንደነበረ ባለሃብት አንጨማለቅም። እናቶቻችን በጭስ አይናቸው ታሟል። ታናናሾቻቸው ፈታ ብለው የሚያጠኑበት በቂ ቦታ የላቸውም። እንደውም እኛ የኖርነውን ኑሮ ታናናሾቻችን ባለመድገማቸው ደስተኞች ነን።
እኛ በየአመቱ የምንጎበኝ ቅርስ አይደለንም። የተሻለ ነገር ያምረናል። ንፁህ አካባቢ ይናፍቀናል። ወደተሻለ ቦታ እንዘዋወር እንጂ ከንቲባዋ ልታፈርስ ስትመጣ አካፋና ዶማ ይዘን ቀድመን አፍርሰን እንጠብቃታለን። እኛ የማንም ፖለቲካ መሸቀጫ አይደለንም። ምቹ ሐገር ተቀምጦ በኛ በካዛንቺስ ልጆች ስም የሚነግድ ተራ ፖለቲከኛ እኛን እንደማይወክል ይታወቅልን።
Ethiopia Prevail Team