በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት-ke gedilat andebet) @kegedilatandebet2716 Channel on Telegram

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት-ke gedilat andebet)

@kegedilatandebet2716


በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ ገድላት ውስጥ የተጻፉ የቅዱሳን አባቶቻችንና የቅዱሳት እናቶቻችን ገድላቸውና አስገራሚ ታሪካቸው ዓመቱን ሙሉ ምንም ሳይቋረጥ በየቀኑ ይነገርበታል!

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት-ke gedilat andebet) (Amharic)

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት-ke gedilat andebet) ተዋሕዶ ቤ/ክ ገድላት በኢትዮጵያ እናቶቻችንን የተጻፉ አባቶቻችንን እናቶቻችንን እና አስገራሚ ታሪካቸው ዓመቱን ሙሉ ምንም ሳይቋረጥ ስለበየቀኑ ቅዱሳን ተጨማሪ መረጃሽን እና የቅዱሳን አባቶቻችንን እና እናቶቻችንን የተጻፉ መረጃሽን በማስተካከላቸው እንዲያረጋግጥ ይከናዉንበታል። የቅዱሳን ኅሩያን ገድላቸው በየቀኑ ይነገረበታል። እናቱና አባታቸው ኅሩያን እና እናቶቻቸው ኅሩያን መቼ እንደምትረዳ ስብስቡ ማወቅ ብቻ ነው።

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት-ke gedilat andebet)

25 Jun, 18:47


The owner of this channel has been inactive for the last 11 months. If they remain inactive for the next 10 days, they may lose their account and admin rights in this channel. The contents of the channel will remain accessible for all users.

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት-ke gedilat andebet)

06 Jul, 04:48


Wedmachin endet neh?

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት-ke gedilat andebet)

05 Jul, 07:04


Hello! Please vote for me on the site. Please It is very important for me! Thank you in advance! https://cutt.ly/0wuLChZj 🔽🔽

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት-ke gedilat andebet)

05 Jul, 06:50


ክርስቲያን ገብተው በእጃቸው ሲያጨበጭቡ አስሯቸው የነበረው ልጃቸው ድምፅ ሰምቶ ሲመጣ አባታችንን ሲመለከት ደነገጠና አባቴ ሆይ! ማን አወጣህ?›› ማንስ እጅህንና እግርህን ፈታህ አላቸው። እርሳቸውም ለልጆቻቸው የሆነውን ሁሉ ነገሯቸው።

አቡነ ክፍለ ሥላሴ ደብረ መድኀኒት ብለው በሰየሟት ገዳማቸው ባምብቆ አካባቢ የከብት በሽታ (ጉልሓይ) ተከስቶ ነበር ነገር ግን ያንን በሽታ ያመጣውን ክፉ ሰይጣን ጻድቁ በጸሎታቸው ኀይል እያስጮኹ አባረው ጣሉት፤ ድምፁንም ሰምተው የአካባቢው ሰዎች ጠላታቸው እንደወደቀ ዐውቀው ከብቶቻቸውም ጤነኞች ስለሆኑላቸው የአቡነ ክፍለ ሥላሴን አምላክ አመሰገኑ።

ጻድቁ የተሰወረውን ሁሉ ያውቁ ነበር፤ አንድ ቀን ወደ ቤተ ክርስቲያን መሔድ የማያስችል ሕማም አጋጠማቸውና በእርሳቸው ፋንታ አንድ እግሩን የሚያመው ወዳጃቸውን ሔዶ ዕጣን እንዲያጥን ነገሩት። እርሱም ሔዶ ግድግዳውን ተጠግቶ በሰሜንና በደቡብ አጥኖ በምዕራንና በምሥራቅ ሳያጥን ተመልሶ ሊጠይቃቸው ሲመጣ አባታችንም ‹‹አንተ ወንድሜ ስለምን እንደዚህ ታደርጋለህ? ለምን እንደአባቶቻችን አድርገህ በምዕራብና በምሥራቅ አላጠንክም?›› አሉት ይህንንም ሲሰማ ያ ካህን ደንግጦ በሠራው ስሕተት ንስሓ ገባና እግዚአብሔርን አመሰገነ።

በመጨረሻም የአቡነ ክፍለ ሥላሴ ጊዜ ዕረፍታቸው ሲደርስ ለአንድ ወዳጃቸው ለሆነ ካህን “ወንድሜ ሆይ! እኔ ማክሰኞ ቀን በአባታችን በአብርሃም በዓል ዕለት እሞታለሁ›› በማለት የሚያርፉበትን ቀን ነገሩት። በተናገሩትም መሠረት ከምንኵስናቸው በፊት 20 ዓመት ከምንኩስናቸው በኋላ 8 ዓመት ኖረው በ28 ዓመታቸው ሰኔ 28 ቀን በዕለተ ማክሰኞ ዐረፉ። ጻድቁ ራሳቸው በተከሏትና በጸለዩባት በደብረ መድኀኒት ቅድስት ሥላሴ ባምብቆ ከተቀበሩ በኋላም ብዙ ተኣምራት አድርገዋል። ዝክራቸውን ያደረገ በጸሎታቸው የተማጸነ በዚህ ዓለም ከመከራ ሥጋ፣ በሚመጣውም ዓለም ከመከራ ነፍስ እንደሚድን ጌታችን በአምላካዊ ቅዱስ ቃሉ ቃልኪዳን ስለገባላቸው የባምብቆ ሕዝብና የዛውል ሕዝብ ሰኔ 28 ቀን በዓላቸውን በታላቅ ክብር ያከብራሉ።

የአቡነ ክፍለ ሥላሴ ዘዛውል ወዘባንብቆ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን በጸሎታቸው ይማረን!
(ምንጭ በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን መጽሐፍ)
✞ ✞ ✞

(የቅዱሳን ገድላቸውን ተኣምራታቸውን በየቀኑ በቴሌግራም ቻናል እና በዩቲዩብ በድምፅ ያዳምጡ።)

1. ቴሌግራም ቻናል፦
https://t.me/kegedilatandebet2716

2. ዩቲዩብ፦
https://www.youtube.com/channel/UC_BIHIqn1uygbjMZlwyoxPA/featured።

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት-ke gedilat andebet)

05 Jul, 06:50


አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አሜን
ሰኔ 28 ስመ እግዚአብሔር ከተጠራባቸው በፍርሀት ይታዘዙ የነበሩት ዳግመኛም ለነቢዩ ዕዝራ ታቦተ ጽዮን ባዘነች ሴት አምሳል እንደታየችው እንዲሁ ለአባታችንም አንዲት ያዘነች ሴት በራእይ መጥታ ዕጣን በማይታጠንበትና መሥዋዕተ ቍርባን በሌለበት ቦታ እንደ ሽኮኮ በጉድጓድ ውስጥ እንዳስቀመጧት የነገረቻቸው አቡነ ክፍለ ሥላሴ ዘዛውል ወዘባንብቆ ዕረፍታቸው ነው።

ኣቡነ ክፍለ ሥላሴ ከአባታቸው ከተክለ ማርያም ወልደ ዘኪዎስ እና ከእናታቸው ከርግበ ዳዊት ዛውል በሚባለው ቦታ ተወለዱ። በመጀመሪያ የወጣላቸው ስም ‹‹መሓርየ እግዚ» የሚባል ነው። አእምሮአቸው ንጹሕና ብሩሕ የሆኑት አቡነ ክፍለ ሥላሴ በልጅነታቸውም በጎችንና ፍየሎችን እያገዱ (እየጠበቁ) ወላጆቻቸውን ያገለግሉ ነበር።

አቡነ ክፍለ ሥላሴ በእናታቸው ማሕፀን ሳሉ የተመረጡ ስለነበሩ እግዚአብሔርን በመፍራት ይታወቁ ነበር፡ ስመ ሥላሴን በከንቱ አያነሡም ነበር። ስመ እግዚአብሔርም ከተጠራባቸው በፍርሃት ይታዘዛሉ። እረኞችም ከብቶቻቸውን እንዲመልሱላቸው የእግዚአብሔርን ስም ከጠሩባቸው ይታዘዟቸው ነበር። በዚኸም ነገር አቡነ ክፍለ ሥላሴ ታላቁን ጻድቅ አቡነ ዐቢየ እግዚእን መሰሉ። በትግራይና በጎንደር በእጅጉ የሚታወቀው ታላቁ ጻድቅ አቡነ ዐቢየ እግዚእ ገና ከልጅነቱ ጀምሮ የእግዚአብሔርን ስም ከጠሩበት ምንም ነገር ከማድረግ ወደኋላ አይልም ነበር። ከልጆችም ጋር ሲጫወቱ ልጆቹ ስለ እግዚአብሔር ብለህ ይህን አድርግልን " ሲሉት ያደርግላቸዋል። በእረኝነት ሳሉ ምሳውንም ሆነ እራቱን ለምስኪኖች ይሰጣል። ለእግዚአብሔር ስም እጅግ ቀናተኛ ስለነበረ ስሙን በመፍራት ስመ እግዚአብሔርን ጠርተው ‹‹ይህን ክፉ ነገር በራስህ ላይ. አድርግ›› ባሉት ጊዜ እንኳን በራሱ ላይ አንዳች ክፉ ነገር ወይም አደጋ ለማድረስ ወደኋላ አይልም ነበር። ይህንንም ሊፈትኑት ብለው አንድ ቀን ስለታም ጦር አምጥተው ስለ እግዚአብሔር ብለህ እስቲ ራስህን በዚህ ስለታም ጦር ትወጋ ዘንድ ና› ባሉት ጊዜ አብርሃም ልጁን ይስሐቅን ሊሠዋ በሕሊናው እንደወሰነ እርሱም በቁርጥ ሕሊና ሆኖ ራሱን በጦሩ ሊወጋ ሲል ዘለው ያዙት። በሌላም ጊዜ እንዲሁ ሊፈትኑት በጭነት ምክንያት ጀርባው የቆሰለ አህያ አምጥተው ዐቢየ እግዚእ ስለ እግዚአብሔር ብለህ የዚያችን አህያ ቁስሏን ላስ አሉት። እርሱም ያን ጊዜ ርኩስን ብስም ኃጢአት ይሆንብኛል፣ አይሆንም ካልኳቸው ደግሞ ስመ እግዚኣብሔርን ጠርተንበት እምቢ አለ ስለሚሉ የፈጣሪዬን ስም መዳፈር ይሆንብኛል ብሎ በልቡ አሰበና ያን ጊዜ ይስም ዘንድ ተመለሰ። ባልንጀሮቹም በቁርጥ ሕሊናው እንደወሰነ ባወቁ ጊዜ ሊያደርገውም ሲሔድ ተመልክተው ቶሎ ብለው ሮጠው ከኋላው ያዙት። እርሱም «እኔስ የፈጣሪዬን ስም እፈራለሁ ስሙን ተደፋፍሬ በምድር በሕይወት ከምኖር ሞት ይሻለኛል» አላቸው። አቡነ ክፍለ ሥላሴም እንዲሁ በፈሪሃ እግዚአብሔር ይታወቃሉ። ስመ ሥላሴን በከንቱ ፈጽመው ጠርተው አያውቁም፣ ስመ እግዚአብሔር ከተጠራባቸው ማንኛውንም ነገር ያደርጉ ነበር።

ከዚኸም በኋላ አቡነ ክፍለ ሥላሴ ወደ አቡነ ሳሙኤል ገዳም ደብረ ዓባይ ሔደው በሚያስደንቅ ትሕትና ለአባቶች እየታዘዙ መዝሙረ ዳዊትን ተማሩ፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን አጠኑ። ከዚያም የአባቶችን ቡራኬ በመቀበል ወደ ደብረ ቢዘን በመሔድ የአቡነ ፊሊጶስንና የአቡነ ዮሐንስን ልጆች በማገልገል የቅዱሳኑን አሠረ ፍኖታቸውን ተከትለው በተጋድሎ ኖሩ። ሌሊትና ቀን በእያንዳንዱ ሥርዓተ ጸሎት ላይ አንድ አንድ ሺህ እየሰገዱ ይጸልዩ ስለነበር የእንቅልፍና የዕረፍት ጊዜ አልነበራቸውም። በእንደዚህም ዓይነት ተጋድሎ ከቆዩ በኋላ ከአቡነ ፊሊጶስ 6ኛ አበ ምኔት ከሆኑት ከአባ ገብረ ማርያም እጅ ምንኩስናን ተቀበሉ። ከመነኰሱም በኋላ መነኰሳቱ እህል እንዲፈጩ ሲያዟቸው አባታችን ክፍለ ሥላሴ በመታዘዝ ወደ እህል መፍጫው ቤት ገቡ፣ ነገር ግን አባታችን እህል መፍጨት አይችሉም ነበር። እርሳቸውም ወደ እግዚአብሔር ቢጸልዩ ሁሉም ሊፈጭ ተዘጋጅቶ የነበረው እሀል በተኣምራት ተፈጭቶ ተገኘ። መነኰሳቱ ግን ይህን አላወቁም ነበር።

አቡነ ክፍለ ሥላሴ ከዚኽ በኋላ ወደ ሀገረ ደምብያ ሔደው ከጳጳሱ እጅ ሥልጣነ ክህነትን ተቀበሉ። ከዚያም ሲመለሱ መረብ ወንዝ ሲደርሱ አብሯቸው የነበረውን የሥጋ ወንድማቸውን ‹‹ኦ ወንድሜ እነሆ በሥጋ የወለደን አባታችን ዛሬ ዐረፈ» በማለት የአባታቸውን መሞት በመንፈስ ቅዱስ ዐውቀው ነገሩት ወደ ሀገራቸውም ክገቡ በኋላ የሀገራቸው የውል ሰዎች ያላወቁ መስሏቸው የአባታቸውን መሞት ለኣቡነ ክፍለ ሥላሴ ነገሯቸው። አባታችንም አባቲ እንደሞተ አስቀድሜ ዐውቄያለሁ፤ እግዚአብሔር ወደ ገነት እንዲያስገባው በጸሎት አግዙኝ እንጂ አታልቅሱ›› አሏቸው። ሰዎቹም የተሰጣቸውን ጸጋ አድንቀው እግዚአብሔርን አመሰገኑ።

ጻድቁ ወደ ደብረ ቢዘን ተመልሰው ሔደው በክህነት እያገለገሉ ሳለ ወደ አቡነ እንድርያስ ሰፍኣ ደብረ ጽጌ ገዳም ለመሔድ እሰቡ፤ ነገር ግን ትልቅ ዋርካ ያለበትን ባምብቆ የተባለውን ተራራ በራእይ ከተመለከቱ በኋላ ወደዚያ እንዲሔዱ እምላካዊ መልእክት መጣላቸው። እርሳቸውም የመንፈስ ቅዱስን ፈቃድ በደስታ ተቀብለው ወደ ባምብቆ በመሔድ ቤተ ክርስቲያን አንጸው የቅድስት ስላሴን ታቦት አስገብተው በታላቅ ተጋድሎ መኖር ጀመሩ፤ በርካታ ደቀ መዛሙርትንም አፈሩ።

አቡነ ክፍለ ሥላሴ በባምብቆ ሳሉ ታቦተ ጽዮን ለነቢዩ ዕዝራ ባዘነች ሴት አምሳል እንደታየችው እንዲሁ ለአባታችንም አንዲት ያዘነች ሴት በራእይ መጥታ ዕጣን በማይታጠንበትና መሥዋዕተ ቍርባን በሌለበት ቦታ እንደ ሽኮኮ በጉድጓድ ውስጥ እንዳስቀመጧት ነገረቻቸው። በዚያም በበረሓ ውስጥ ደብቀው ያስቀመጧት ዮልዮስ የተባለ አንድ አመጸኛ መኰንን ቤተ ክርስቲያንን ሊያቃጥል በፈለገ ጊዜ ነው። አቡነ ክፍለ ሥላሴም ወደተነገራቸው ቦታ በመሔድ ካህናቱን በጉድጓድ ውስጥ ስላስቀመጡት ታቦት ሲጠይቋቸው እነርሱ ግን የደበቅነው ታቦት የለንም› አሏቸው። አባታችንም “ወንድሞቼ ሆይ! እውነቱን ተናገሩ›› በማለት በራእይ የተመለከቱትን ነገር ነገሯቸው። ካህናቱም ፈርተው አዎን አባታችን ይቅር በሉን፣ ዮልዮስን ፈርተን ታቦቱን ዋሻ ውስጥ ደብቀነዋል›› ብለው ቦታውን አሳዩአቸውና አውጥተው ወደ ቤተ ክርስቲያን መለሱት።

ከዚኽም በኋላ አቡነ ክፍለ ሥላሴ በገዳማቸው በጽኑ ተጋድሎ ላይ ሳሉ የጌታችን ጾም በደረሰ ጊዜ ልጆቻቸውን ጠሩና ሰባት ክንድ የሚሆን ጉድጓድ ቆፍራችሁ እኔ እዚያ ውስጥ ከገባሁ በኋላ ጉድጓዱን ሸፍኑት፣ ከላይ የዕንጨት ሰሌዳ አድርጋችሁ በድንጋይና በጠጠር አድርጋችሁ በመቃብር ምልክት ዝጉት” በማለት ነገሯቸው። ዳግመኛም ሰዎች የት ናቸው? ብለው ቢጠይቋችሁ የት እንዳለ አናውቅም, በሏቸው፤ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ሲሆን ግን ከፍታችሁ አረጋግጡ አሏቸው። አብርሃም የተባለው ደቀ መዝሙራቸውም ወደ ጉድጓዱ አብሯቸው በመግባት የአቡነ ክፍለ ሥላሴን እጆቻቸውንና እግሮቻቸውን በሰንሰለት ካሠራቸው በኋላ ወጣ፣ ጻድቁም እንዳዘዙት ጉድጓዱን ዘጉትና ሰው እንዳያውቀው አንድ ትልቅ መደብ ሠሩለት። ነገር ግን በማግሥቱ “ወዳጄ ክፍለ ሥላሴ ሆይ! ለምን እንደዚህ አደረግህ? አንተ ከዚህ ጉድጓድ ውስጥ ገብተህ ማነው ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን የሚያቀርብ? ማንስ ዕጣን ያጥናል? ስለዚህ አሁን ና ከዚህ ተነሥተህ ውጣ የሚል ራእይ ተመለከቱ፡ ወዲያውም የተዘጋው ጉድጓድ በተኣምር ተከፈተ ታስሮ የነበረው እጅና እግራቸውም ሰንሰለቱ በተኣምር ተፈታ። እርሳቸውም ወደ ቤተ

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት-ke gedilat andebet)

05 Jul, 05:38


አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አሜን
ሰኔ 28-በዚህች ቀን ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ሠላሳ ሦስተኛ የሆነው ቅዱስ አባ ቴዎዶስዮስ የእስክንድርያ ከተማ ሊቀ ጳጳሳት አረፈ።
+ ዳግመኛም በዚኽች ዕለት የባስልዮስና የቢፋሞን፤ የባሊዲስና የኮቶሎሰ የአርዳሚስም መታሰቢያቸው ነው ረድኤት በረከታቸው ይደርብን፣ በጸሎታቸው ይማረን፡፡
+ ቅዱስ አባ ቴዎዶስዮስ ፡-በዚህም ቅዱስ በስሙ በግብጽ ምድር ውስጥ ምእመናን ቴዎዶስዮሳውያን ተብለው ተጠርተውበታል።ይህም የሆነው እንዲህ ነው ሊቀ ጵጵስና ከተሾመ በኋላ ክፉዎች ሰዎች በእርሱ ላይ ተነሥተው በንጉሥ ምክር ከመንበረ ሢመቱ አሳደዱት በእርሱ ፈንታም
አስቀድሞ በእስክንድርያ ከተማ ሊቀ ዲያቆናት የነበረ ስሙ አቃቅያኖስ የሚባለውን አንድ ሰው ሾሙ እርሱም ለአባ ቴዎዶስዮስ ሊቀ ጵጵስና እንዲገባው ከፈረሙት ቁጥር ውስጥ ነበረ።ይህም አባት ወደ ግርማኖስ አገር ሒዶ ሦስት ወሮች ኖረ በዚያም ወራት በግብጽ አገር ንቡረ እድ አባ ሳዊሮስ ነበረ እርሱም በአባቶቻችን ሐዋርያት እንዲሁም በአትናቴዎስና በዮሐንስ አፈወርቅ የደረሰባቸውን መከራ እያስታወሰ ያጽናናቸው ነበር።ከዚያም ተነሥቶ መሊግ ወደሚባል አገር ሔደ በዚያም ሁለት ዓመት ተቀመጠ።
የእስክንድርያ ከተማ ሰዎችም የጠባቂያቸው የቴዎዶስዮስን መመለስ ሽተው በእስክንድርያው መኰንን ላይ ተነሡበት መኰንኑም ወደ መንበረ ሢመቱ መለሰው አቃቅያኖስንም አባረሩት።ይህም ነገር በንጉሥ ዮስጣቲያኖስና አምላክን በምትወድ በንግሥት ታዖድራ ዘንድ ተሰማ ንግሥቲቱም አስቀድሞ የተሾመው በሹመት ወንበሩ ይቀመጥ ብላ
ጻፈች።ሃምሳ ስምንት ካህናትም ጉባኤ አደረጉ አስቀድሞ የተሾመ አባ ቴዎዶስዮስ ነው ሲሉም ጻፉ። ያን ጊዜም አቃቅያኖስ በሕዝብ ፊት ቁሞ ክፉዎች ሰዎች ስለ አስገደዱኝ ይህን ሥራ ለመሥራት ሕግን ተላልፌአለሁ አለ። ከዚህም በኋላ አቃቅዮስን ከውግዘቱ እንዲፈታው ነገር ግን ክህነትም ሆነ ሊቀ ዲቁና ለዘለዓለሙ እንዳይኖረው ሕዝቡ አባ ቴዎዶስዮስን ለመኑት። አቃቅያኖስም አዎ እንዲሁ ይሁን አለ ይህም አባት ከግዝቱ ፈታው።ሃይማኖቱን ያጠፋ ንጉሡ ግን በከፋች ሃይማኖቱ ሊቀ ጳጳሳት አባ ቴዎዶስዮስ ከእርሱ ጋራ የሚስማማ መስሎት በእስክንድርያ ወዳሉ መኳንንቶቹ እንዲህ ብሎ ጻፈ ሊቀ ጳጳሳት አባ ቴዎዶስዮስ በሃይማኖት ከእኛ ጋራ የሚስማማ ከሆነ ሹመት ይጨመርለታል። ለእስክንድርያ ከተማ ገዥ ይሆናል። ይህ ካልሆነ ግን ከሹመቱ ይሻር።ይህም አባት ይህን ነገር በሰማ ጊዜ እንዲህ አለ ሰይጣን በበረሀ ጌታችንን ብትሰግድልኝ የዓለም መንግሥታትንና ክብራቸውን ሁሉ እሰጥሃለሁ አለው። ያን
ጊዜም ይህ አባ ቴዎዶስዮስ ተነሥቶ ከእስክንድርያ ወጣ ወደ ላይኛው ግብጽም ሔደ በዚያም ሕዝቡን እያስተማራቸው በቀናች ሃይማኖትም እያጸናቸው ጥቂት ቀኖች ኖረ።ንጉሡም አባ ቴዎዶስዮስ ከእስክንድርያ ከተማ እንደ ወጣ በሰማ ጊዜ
እየሸነገለው ወደ እርሱ መልእክት ላከ እንዲህም አለው እኔ ከአንተ ጋራ ልነጋገር ከአንተም ልባረክ እንድትመክረኝም እሻለሁ።ከዚህም በኋላ ወደ ቍስጥንጥንያ ከተማ ሔደ የጳጳሳት አለቆችና ሕዝቡ ሁሉ ሠራዊቱም ተቀበሉት በከፍተኛ ወንበርም ላይ አስቀመጡት። እርስ በርሳቸውም ስለ ሃይማኖት ተከራከሩ ንጉሡም አብዝቶ ሲሸነግለውና ሲአባብለው ሰነበተ ቅዱስ አባት ቴዎዶስዮስም ከቅዱሳት መጻሕፍት በመጥቀስ ይረታው ነበረ።ከእርሱም ጋራ ባልተስማማ ጊዜ ከመንበረ ሢመቱ ወደ ላይኛው ግብጽ
አሳደደው። በእርሱም ፈንታ ጳውሎስ የሚባለውን ሰው ሾመው። ጳውሎስም ወደ እስክንድርያ ከተማ በመጣ ጊዜ ሕዝቡ አልተቀበሉትም ዓመት ሙሉም ኖረ በእጁም ማንም ቍርባንን አልተቀበለም።ንጉሡም ይህን በሰማ ጊዜ ለመና*ፍቁ ጳውሎስ እስከሚታዘዙ ድረስ አብያተ ክርስቲያናት እንዲዘጉ አዘዘ። ምእመናንም ከእስክንድርያ በመውጣት ወደ ቅዱስ ወንጌላዊ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን ወደ ቆዝሞስና ድምያኖስ ቤተ ክርስቲያን ይሔዱ ነበር ካህናቱም በዚያ እየቀደሱ ያቈርቧቸው ነበር የአገር ልጆችንም የክርስትና ጥምቀትን ያጠምቋቸው ነበር።ንጉሡም ይህን በሰማ ጊዜ አብያተ ክርስቲያናትን እንዲከፍቱላቸው አዘዘ አባ ቴዎዶስዮስም ሰምቶ ንጉሡ እንዳያስታቸው ፈራ ማጽናኛ ቃልን የተመላች መልእክትም ጽፎ በቀናች ሃይማኖት እያበረታታቸው ወደ ምእመናን ላካት እንዲህም አላቸው ለዚያ ከሀዲ ጳውሎስ እንዳትታዘዙ ተጠበቁ። ይህም አባት ሃያ ስምንት ዓመት በስደት ኖረ። መላው የሹመቱ ዘመን ሠላሳ ሁለት ነበር።ይኸውም በእስክንድርያ አራት ዓመት በስደትም ሃያ ስምንት ዓመት ነው።ይህም አባት ብዙ ድርሳናትን ደርሷል ምእመናንም በያዕቆብ ዘመን ያዕቆባውያን እንደ ተባሉ በስሙ ቴዎዶስዮሳውያን እየተባሉ ሲጠሩ ኖሩ። መልካም ጉዞውንም ፈጽሞ በሰላም አረፈ።ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣ በጸሎቱ ይማረን፡፡
(ምንጭ፡-ስንክሳር ዘወርኀ ሰኔ መዝገበ ቅዱሳን)
✞ ✞ ✞

(የቅዱሳን ገድላቸውን ተኣምራታቸውን በየቀኑ በቴሌግራም ቻናል እና በዩቲዩብ በድምፅ ያዳምጡ።)

1. ቴሌግራም ቻናል፦
https://t.me/kegedilatandebet2716

2. ዩቲዩብ፦
https://www.youtube.com/channel/UC_BIHIqn1uygbjMZlwyoxPA/featured።

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት-ke gedilat andebet)

03 Jul, 17:22


አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አሜን
ሰኔ 27-በሉቃስ ወንጌል ላይ ታሪኩ የተነገረው ድኃው አልዓዛር መታሰቢያው ነው፡፡
+ የሐዋርያው የቅዱስ ጳውሎስ የንስሓ አባት በመባል የሚታወቀው ሐዋርያው ቅዱስ ሐናንያ ዕረፍቱ ነው፡፡
+ ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ ዕረፍቱ ነው፡፡
+ የሰማዕቱ የቅዱስ ቶማስ የምስክርነቱን ፍጻሜ ሆነ፡፡ ከእርሱም ጋር ማኅበርተኞቹ የሆኑ 709 ሰዎች በሰማዕትነት ዐረፈ፡፡
ቅዱስ ቶማስ ሰማዕት፡- ሰንደላት ከሚባል ሀገር የተገኘ ታላቅ ጻድቅ ነው፡፡ በ11 ዓመቱ እረኝነት ላይ ሳለ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ተገልጦለት ወደ ከሃዲው መኰንን ዘንድ ሄዶ በክርስቶስ ስም ሰማዕት እንዲሆን ነገረው፡፡ ቅዱሱም ወደ እስክንድርያ ሄዶ በመኰንኑ ፊት ስለ ክርስቶስ አምላክነት መሰከረ፡፡ መኰንኑም ለአማልክቶቹ ቢሠዋና ቢሰግድ ጸሐፊው እንደሚያደርገው ቃል ገባለት፡፡ በዚህም ጊዜ ቅዱስ ቶማስ እረኝነት ይጠብቅባት የነበረችውን አለንጋ አውጥቶ መኰንኑን ገረፈው፡፡የመኰንኑም ሎሌዎች ይዘው እጅግ አሠቃዩት፡፡ ሥጋውንም በብረት መጋዝ ሠነጠቁት ነገር ግን መልአኩ መጥቶ ፈወሰው፡፡ በእሥር ቤት ሳለ የእሥር ቤቱ ጠባቂው ልጁ ስለታመመበት ቅዱስ ቶማስን ለመነው፡፡ ቅዱስ ቶማስም እረኝነት ይጠብቅባት የነበረችውን አለንጋ ሰጠውና ወስዶ በታመመ ልጁ ላይ እንዲያኖረው ነገረው፡፡ ሄዶም አለንጋውን በልጁ ላይ ቢያስቀምጠው ልጁ ወዲያው ዳነ፡፡ ምእመናንም ከቅዱስ ቶማስ ከሰውነቱ የሚፈሰውንም ደም እየወሰዱ ዕውራንን ያበሩበት ጀመር፡፡ ከሃዲያኑም በዚህ ተቆጥተው ቅዱሱን ለተራበ አንበሳ አሳልፈው ቢሰጡት አንበሳው ሰግዶለታል፡፡ ቀጥለውም አባለ ዘሩን ቆርጠው በአውድማ ላይ አበራዩት፡፡ ልዩ ልዩ ዓይነት በሆኑ ሥቃዮችም እጅግ ካሠቃዩት በኋላ ሰኔ 27 ቀን አንገቱን በሰይፍ ቆርጠው ሰማዕትነቱን በድል እንዲፈጽም አደረጉት፡፡ ከእርሱም ጋር 709 ሰማዕታት አብረው ተሰይፈው በመንግሥተ ሰማያት የድል አክሊልን ተቀዳጁ፡፡ የሰማዕቱ የአቡነ ቶማስ ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣ በጸሎቱ ይማረን፡፡
+ + + + +
አቡነ ያዕቆብ ዘሥሩግ፡- የዚኽም ቅዱስ ሰኔ 27 ልደቱ ፣ ዕረፍቱ ግን ሰኔ 7 ነው እየተባለም በሊቃውንት ይነገራል፡፡ የቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ ሀገሩ ሶርያ ሲሆን አባቱ ሊቀ ካህናት ነበር፡፡ በኤጲስ ቆጶስነት የተሾመባት ሀገር በጤግሮስና በኤፍራጥስ መካከል በምትገኝ ሥሩግ በምትባል ሀገር ስለሆነ ያዕቆብ ዘሥሩግ ተባለ፡፡ በሦስት ዓመቱ እናቱ ቤተ መቅደስ ስትወስደው መልአክ እጁን ይዞ በሊቀ ጳጳሱ እጅ እንዲቆርብ አድርጎታል፡፡ በዚህም ጊዜ ምሥጢራት ሁሉ ተገልጠውለታል፡፡ ገና በ7 ዓመቱ ስለ ሦስት ነገሮች በእጅጉ ያለቅስ ነበር፡፡ ይኸውም ‹‹ነፍሴ ከሥጋዬ ተለይታ ስትወጣ፣ ከጌታችን ጋር ስገናኝና መጨረሻውን ፍርድ ስሰማ እነዚህን ሦስት ነገሮች በእጅጉ እፈራለሁ›› እያለ ያለቅስ ነበር፡፡
አቡነ ያዕቆብ በ12 ዓመቱ ብሉይንና ሐዲስን አጠናቆ ተምሮ ጨርሷል፡፡ ጸጋውን ዐውቀው 5ቱ ታዋቂ ሊቃነ ጳጳሳት መጥተው እጅ ነስተውት አዲስ ድርሰት ድረስልን ቢሉት እርሱም በፍጹም ትሕትና ‹‹በእናንተ ፊት እንኳን አዲስ ድርሰት ልደርስ ቀርቶ የተደረሰውንም መናገር አልችልም›› አላቸው፡፡ ያንጊዜም ሕዝቡና ሊቃነ ጳጳሳቱ ‹‹እግዚአብሔር በዚህ ሕጻን ላይ አድሮ ገሠጸን›› እያሉ ንስሓ ገብተዋል፡፡
ቅዱስ ያዕቆብ በነበረበት ዘመን በሮማው መና*ፍቅ ልዮን አማካኝነት ቤተ ክርስቲያን ለመጀመሪያ ጊዜ ለሁለት የተከፈለችበት ጊዜ ነበርና እነ ዲዮስቆሮስ ‹‹የውሾች ጉባኤ›› ከተባለው ከኬልቄዶን ጉባኤ ተለይተው ሃይማኖትን ሲያጸኑ ልዮንንም ማውገዛቸውን ያዕቆብ ሲሰማ በዲዮስቆሮስ ጽናት በእጅጉ ተደስቶ ደብዳቤ ጽፎ አመስግኖታል፡፡ እነ ልዮንን ግን አውግዞ እረግሟቸዋል፡፡ ልዮንም ተከታይ ባገኝ ብሎ ‹‹እኔን ምሰል›› በማለት ለቅዱስ ያዕቆብ ደብዳቤ ጻፈለት፡፡ አቡነ ያዕቆብም ‹‹ሳጥናኤል ከመላእክት ጋር ምን አንድ አደረገው? አንተ ርኩስ ነህ፣ የዲዮስቆሮስን ጥርስ አስወልቀህ፣ ጢሙን አስነጭተህ፣ ሃይማኖትህን የቀየርህ ከሁለት ዓለም ስደተኛ ጋር አልተባበርም፣ ይልቅስ ንስሓ ግባ፣ ንስሓ ባትገባ ግን አንተ ዲያብሎስ ነህ ተከታዮችህም አጋንንት ናቸው›› በማለት መልሱን ጽፎለታል፡፡ ልዮንም እምቢ ብሎ በክህደቱ ቢጸናበት አውግዞና እረግሞ ለይቶታል፡፡
ንጽሕናውና ቅድስናው ‹‹እንደ መላእክት ነው›› የተባለለት ያዕቆብ ዘሥሩግ ጻድቅም ሐዋርያም ደራሲም ተከራካሪ መምህርም ነው፡፡ ሦስት ድርሰቶች ያሉት ሲሆን በስሙ የተጠራው ቅዳሴም አለው፡፡ ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣ በጸሎቱ ይማረን፡፡
+ + + + +
ድሀው አልዓዛር፡- ይኸኛው አልዓዛር በሉቃስ ወንጌል ላይ እንደተነገረው ባለጸጋው ነዌ ድሀው አልዓዛር በደጁ ወድቆ ትራፊውን ፍርፋሪ ይመኝ የነበረ ውሾች ቁስሉን እስኪልሱለት ድረስ በባጸጋው ዘንድ የተናቀና የወደቀ ነበር፡፡ ሁለቱም ሲሞቱ ግን ባለጸጋው ነዌ በሲኦል ሆኖ እየተሠቃየ ድሀው አልዓዛርን በአብርሃም እቅፍ አይቶታል፡፡ ቅዱስ አልዓዛር በዚህች ዕለት በዓመታዊ በዓሉ ታስቦ ይውላል፡፡ ሙሉ ታሪኩ በሉቃስ ወንጌል 16፡19-31 ላይ እንዲህ ተቀምጧል፡-
‹‹ቀይ ልብስና ቀጭን የተልባ እግር የለበሰ አንድ ባለ ጠጋ ሰው ነበረ፣ ዕለት ዕለትም እየተመቸው በደስታ ይኖር ነበር፡፡ አልዓዛርም የሚባል አንድ ድሀ በቍስል ተወርሶ በደጁ ተኝቶ ነበር፣ ከባለ ጠጋውም ማዕድ ከሚወድቀው ፍርፋሪ ሊጠግብ ይመኝ ነበር፣ ውሾች እንኳ መጥተው ቍስሎቹን ይልሱ ነበር፡፡ ድሀውም ሞተ፣ መላእክትም ወደ አብርሃም እቅፍ ወሰዱት፣ ባለ ጠጋው ደግሞ ሞተና ተቀበረ፡፡ በሲኦልም በሥቃይ ሳለ አሻቅቦ አብርሃምን በሩቅ አየ አልዓዛርንም በእቅፉ፡፡ እርሱም እየጮኸ ‹አብርሃም አባት ሆይ ማረኝ፣ በዚህ ነበልባል እሣቀያለሁና የጣቱን ጫፍ በውኃ ነክሮ መላሴን እንዲያበርድልኝ አልዓዛርን ስደድልኝ› አለ፡፡ አብርሃም ግን ‹ልጄ ሆይ አንተ በሕይወትህ ሳለህ መልካም እንደ ተቀበልህ አስብ አልዓዛርም እንዲሁ ክፉ፤ አሁን ግን እርሱ በዚህ ይጽናናል አንተም ትሠቃያለህ፡፡ ከዚህም ሁሉ ጋር ከዚህ ወደ እናንተ ሊያልፉ የሚፈልጉ እንዳይችሉ፣ ወዲያ ያሉ ደግሞ ወደ እኛ እንዳይሻገሩ በእኛና በእናንተ መካከል ታላቅ ገደል ተደርጎአል› አለ፡፡ እርሱም ‹እንኪያስ አባት ሆይ ወደ አባቴ ቤት እንድትሰደው እለምንሃለሁ፤ አምስት ወንድሞች አሉኝና፡፡ እነርሱ ደግሞ ወደዚህ ሥቃይ ስፍራ እንዳይመጡ ይመስክርላቸው› አለ፡፡ አብርሃም ግን ‹ሙሴና ነቢያት አሉአቸው፤ እነርሱን ይስሙ› አለው፡፡ እርሱም አይደለም፣ አብርሃም አባት ሆይ ነገር ግን ከሙታን አንዱ ቢሄድላቸው ንስሐ ይገባሉ› አለ፡፡ አብርሃምም ‹ሙሴንና ነቢያትንም የማይሰሙ ከሆነ ከሙታንም እንኳ አንድ ቢነሣ አያምኑም› አለው፡፡›› ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣ በጸሎቱ ይማረን፡፡
+ + + + +
ሐዋርያው ቅዱስ ሐናንያ፡- ቁጥሩ ከ72ቱ አርድእት ነው፡፡ ሕገ ኦሪትን ጠንቅቆ የሚያውቅ ምሑር ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌልን ማስተማር በጀመረ ሰዓት ነው ለተልዕኮ የጠራው፡፡ ሐናንያም በበጎ ፈቃድ ስለተከተለውና ስላገለገለው ከ72ቱ አርድእት ደምሮታል፡፡ ሐዋርያው ለሦስት ዓመታት ከጌታችን እግር ሥር ተቀምጦ ተምሯል፡፡ ቅዱስ ሐናንያ በበዓለ ዕርገት ተባርኮ በ50ኛው ቀንም ሀብተ መንፈስ ቅዱስን ተቀብሎ ለስብከተ ወንጌል ተሰማርቷል፡፡ ሐዋርያትም የሶርያ ደማስቆ ከተማ የመጀመሪያው ጳጳስ አድርገው ሾመውታል፡፡

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት-ke gedilat andebet)

03 Jul, 17:22


ጌታችን ባረገ በ8ኛው ዓመት ክርስቲያኖችን ያሠቃይ የነበረው ሳውል ወደ ደማስቆ የተጓዘው ክርስቲያኖችን ለማሳደድ ነበር፡፡ የቅዱስ ሐናንያንም የወንጌል ሰባኪነት ስለሚያውቅ እርሱንም ለማሠር ነበር ጉዞው፡፡ እግዚአብሔር ግን ሳውልን (ጳውሎስን) ምርጥ ዕቃው ይሆን ዘንድ መርጦታልና በመብረቅ አስደንግጦና ዐይኑን ጋርዶ የጥሪውን ደወል አሰማው፡፡ ‹‹ለምን ታሳድደኛለህ?›› በማለትም በጌታችን በስሙ ያመኑ ክርስቲያኖችን ማሳደድ ማለት ራሱን ክርስቶስን ማሳደድ መሆኑንም ነገረው፡፡
ከዚህም በኋላ ጌታችን ሳውልን ወደ ሐናንያ እንዲሄድ ነገረው፡፡ እንዲሁም ጌታችን ለሐናንያም ተገልጦለት ጳውሎስ ወደ እርሱ እንደሚመጣና ምርጥ ዕቃውም አድርጎ እንዳዘጋቸው ነገረው፡፡ ነገር ግን የሳውልን አሳዳጅነት ጠንቅቆ ያውቅ ስለነበር ሐናንያ ራሱ ጌታችን ጳውሎስ ስለመመለሱ የነገረውን ለማመን ከብዶት ነበር፡፡ ምክንያቱም በመጽሐፍም እንደተጻፈው ‹‹ሳውል ግን የጌታን ደቀ መዛሙርት እንዲገድላቸው ገና እየዛተ ወደ ሊቀ ካህናት ሄደ›› (የሐዋ ሥራ 9፡1) የሚለውን ሳውል እንዴት ተግባራዊ ያደርገው እንደነበር ሐናንያ በተግባርም ጭምር አይቶት ነበረና ነው፡፡
ከዚህም በኋላ ሳውል (ጳውሎስ) በመሪ እየተመራ ወደ ቅዱስ ሐናንያ ሄደ፡፡ ቅዱስ ሐናንያም ሳውልን ካገኘው በኃላ አስተምሮ ከሕመሙም ፈወሰው፣ አጠመቀውም፡፡ ለዚህም ነው ሐናንያ የቅዱስ ዻውሎስ የንስሃ አባቱ መባሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ታሪኩን እንዲህ አስቀምጦታል፡- ‹‹ሳውልም ሳያይም ሦስት ቀን ኖረ፤ አልበላምም አልጠጣምም፡፡ በደማስቆም ሐናንያ የሚሉት አንድ ደቀ መዝሙር ነበረ፣ ጌታም በራእይ ‹ሐናንያ ሆይ!› አለው፡፡ እርሱም ‹ጌታ ሆይ እነሆኝ› አለ፡፡ ጌታም ‹ተነሥተህ ቅን ወደ ሚባለው መንገድ ሂድ፣ በይሁዳ ቤትም ሳውል የሚሉትን አንድ የጠርሴስ ሰው ፈልግ፡፡ እነሆ እርሱ ይጸልያልና፤ ሐናንያ የሚሉትም ሰው ገብቶ ደግሞ እንዲያይ እጁን ሲጭንበት አይቶአል› አለው፡፡ ሐናንያም መልሶ ‹ጌታ ሆይ! በኢየሩሳሌም በቅዱሳንህ ላይ ስንት ክፉ እንዳደረገ ስለዚህ ሰው ከብዙዎች ሰምቼአለሁ፤ በዚህም ስምህን የሚጠሩትን ሁሉ ለማሰር ከካህናት አለቆች ሥልጣን አለው› አለ፡፡ ጌታም ‹ይህ በአሕዛብም በነገሥታትም በእስራኤልም ልጆች ፊት ስሜን ይሸከም ዘንድ ለእኔ የተመረጠ ዕቃ ነውና ሂድ፤ ስለ ስሜ ስንት መከራ ሊቀበል እንዲያስፈልገው እኔ አመለክተዋለሁና› አለው፡፡ ሐናንያም ሄዶ ወደ ቤቱ ገባ፣ እጁንም ጭኖበት ‹ወንድሜ ሳውል ሆይ! ጌታ እርሱም በመጣህበት መንገድ የታየህ ኢየሱስ ነው፣ ደግሞ ታይ ዘንድና መንፈስ ቅዱስ ይሞላብህ ዘንድ ላከኝ› አለ፡፡ ወዲያውም እንደ ቅርፊት ያለ ከዓይኑ ወደቀ፣ ያን ጊዜም ደግሞ አየ፤ ተነሥቶም ተጠመቀ፤ መብልም በልቶ በረታ፡፡ በደማስቆም ካሉት ደቀ መዛሙርት ጋር ጥቂት ቀን ኖረ፡፡ ወዲያውም ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ በምኵራቦቹ ሰበከ፤ የሰሙትም ሁሉ ተገረሙ፡፡›› ሐዋ 9፡9-21፡፡
ከዚህም በኋላ ሐዋርያው ቅዱስ ሐናንያ ለብዙ ዓመታት በተለያዩ ሀገራት እየተዘዋወረ ወንጌልን ሰብኳል፡፡ ብዙዎችንም ከአምልኮ ጣዖት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር መልሷቸዋል፡፡ በዚህም ብዙ አሠቃቂ መከራዎችን ተቀብሏል፡፡ በአገልግሎቱ የቀኑ ጣዖታትን አምላኪ የሆኑ ክፉዎች ይዘው ብዙ ካሠቃዩት በኋላ በዚህች ዕለት ሰኔ 27 ቀን በድንጋይ ወግረው ስለገደሉት ሰማዕትነቱን በክብር ፈጽሞ የክብር አክሊልን ተቀዳጅቷል፡፡ የዚኽ ክቡር ሐዋርያ ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣ በጸሎቱ ይማረን፡፡
ከገድላት አንደበት
✞ ✞ ✞

(የቅዱሳን ገድላቸውን ተኣምራታቸውን በየቀኑ በቴሌግራም ቻናል እና በዩቲዩብ በድምፅ ያዳምጡ።)

1. ቴሌግራም ቻናል፦
https://t.me/kegedilatandebet2716

2. ዩቲዩብ፦
https://www.youtube.com/channel/UC_BIHIqn1uygbjMZlwyoxPA/featured።

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት-ke gedilat andebet)

03 Jul, 17:22


አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አሜን
ሰኔ 26-የነቢያት አለቃ የቅዱስ ሙሴ ደቀ መዝሙር የሆነ የነዌ ልጅ ነቢዩ ቅዱስ ኢያሱ ዐረፈ፡፡ ኢያሱ ማለት የስሙ ትርጉም ‹‹እግዚአብሔር አዳኝ ነው›› ማለት ነው፡፡ ኢያሱ የሊቀ ነቢያት ሙሴ ደቀ መዝሙር ነው፡፡ ዘጸ 24፡13፣ ዘኁ 11፡28፡፡እርሱም ከታናሽነቱ ጀምሮ ለሙሴ አንገቱን ዝቅ አድርጎ የሚታዘዝ ፍጹም ትሑት ሰው ስለነበር በዚህም በሙሴ ላይ ያደረ መንፈስ ቅዱስ በኢያሱም ላይ አድሮበታል ፡፡ኢያሱ ‹‹አውሴ›› ተብሎ ይጠራ ነበር፡፡ ዘኁ 13፡8፡፡
የከነዓንን አገር እንዲያዩ ከቃዴስ ከተላኩት 12 ሰላዮች ውስጥ አንዱ ነበረ፡፡ከእነዚህም ዐሥሩ ክፉ ወሬ ሲያመጡ ኢያሱና ካሌብ ግን በእምነት ‹‹ምድሪቱን እንወርሳታለን›› ብለዋል፡፡ ዘኁ 13፡14፡፡ ሊቀ ነቢያት ሙሴ ከሞተ በኋላ
የእስራኤል መሪ እንዲሆን ተመርጧል፡፡ ዘኁ 27፡15-32፣ ዘዳ 3፡28፡፡ በዚህም ምክንያት ሊቃውንት ‹‹መስፍኑ›› እያሉ ይጠሩታል፡፡ ኢያሱ ሕዝቡን ሁሉ በመልካም ሁኔታ ይመራ ነበር፡፡ የዮርዳኖስን ወንዝ ከፍሎ ሕዝቡን አሻግሯል፡፡ካህናቱ የታቦቱን ሕግ ተሸክመው በዮርዳኖስ ወንዝ መካከል ቆመው የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ እስኪሻገሩ ድረስ የወንዙ ውኃ እንደ ግድግዳ ቆሞ ነበር፡፡ ኢያ 3፡6-17፡፡ ከዚህም በኋላ በግንብ የተከበበች ኢያሪኮን 7 ቀን ዞራት፡፡ ኢያሪኮ ግንብ የፈራረሰው በኢያሱ መሪነት ነው፡፡ ኢያ 6፡1-121፡፡ ኢያሱ አሞራውያንን በገባዖን ሲዋጋ ፀሐይን በጸሎቱ እንድትቆም አድርጓል፡፡ ኢያ 10፡11-14፡፡‹‹እግዚአብሔርም በእስራኤል ልጆች እጅ አሞራውያንን አሳልፎ በሰጠ ቀን ኢያሱ እግዚአብሔርን ተናገረ፤ በእስራኤልም ፊት እንዲህ አለ፡- ‹በገባዖን ላይ ፀሐይ ትቁም፣ በኤሎንም ሸለቆ ጨረቃ፡፡› ሕዝቡም ጠላቶቻቸውን እስኪበቀሉ ድረስ ፀሐይ ቆመ፣ ጨረቃም ዘገየ፡፡ ይህስ በያሻር መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?ፀሐይም በሰማይ መካከል ዘገየ፣ አንድ ቀንም ሙሉ ያህል ለመግባት አልቸኰለም፡፡›› እንዲል መጽሐፉ፡፡ በብሉይ ኪዳን የነበረው ነቢይ ቅዱስ ኢያሱ ጠላቶቹን ድል እስኪያደርግና ምድረ ርስትን ለሕዝቡ እስኪያከፋፍል ድረስ ፀሐይን እንዳቆማት ሁሉ የሐዲስ ኪዳኖቹ የክርስቶስ ማደሪያዎች የሆኑት ቅዱሳን እነ አቡነ ዜና ማርቆስ፣ ዘርዐ ቡሩክ፣ ሳሙኤል ዘደብረ ወገግ፣ አቡነ አሮን፣ አቡነ ገሪማና ሌሎችም እንዲሁ ፀሐይን በጸሎታቸው ገዝተው አቁመዋታል፡፡ቅዱስ ኢያሱ ነቢይና መስፍን ሆኖ ሕዝበ እስራኤልን ለ40 ዓመታት ካገለገለ
በኋላ በ110 ዓመቱ ዐርፎ በኤፍሬም ሀገር በተምናሴራ ተቀብሯል፡፡ ኢያ 24፡1-30፡፡ እሥራኤልም ለ30 ቀናት ያህል አልቅሰውለታል፡፡ቅዱስ ኢያሱ ለእስራኤል ነገዶች ድርሻ ድርሻቸውን ካከፋፈለ በኋላ ሕዝቡ እግዚአብሔርን እንዳይተውት ያደረገላቸውን ሁሉ አስታወሳቸው፡፡ ሲፈጽምም
‹‹የምታመልኩትን ዛሬ ምረጡ፣እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን››አላቸው፡፡ ሕዝቡም ‹‹እግዚአብሔርን እናመልካለን›› ባሉት ጊዜ የቃል ኪዳን ምልክት ሐውልት አቆመ፡፡ ይህችም የቃል ኪዳን ምልክት ሐውልት ያቆመባት ቦታ ከቆላ የመጣው አቀበቱን፣ ከደጋ የመጣው ደግሞ መስኩን ጨርሶ የሚያርፍባት ናት፡፡ ከዚያች ላይ ሦስት ረድፍ ያላት ታላቅ ድንጋይ ተክለው ኢያሱና ሕዝቡ እግዚአብሔርን ለማምለካቸው ተማምለውባታል፡፡ ከቆላ የመጣው አቀበቱን፣ ከደጋ የመጣው ደግሞ መስኩን ጨርሶ ከዚያች ቦታ ላይ ሲያርፍ የማያውቀው የሚያውቀውን ‹ወንድሜ ይህቺ ድንጋይ ምንድናት?› ይለዋል፡፡የሚያውቃትም ‹ይህቺማ ኢያሱና ሕዝቡ እግዚአብሔርን ለማምለካቸው የተማማሉባት ስለሆነች አምልኮታቸውን ስትመሰክር ትኖራለች› ይለዋል፡፡
ይህችም ለጊዜው ብትደረግም ለኋላው ግን ምሳሌ ነበረች፡፡ ሐውልቷ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ ናት፡፡ ያቺ ያማረች እንደሆነች ሁሉ እመቤታችንንም ባማረ ባማረ ይመስላታልና (መኅ 4፡7) ሦስት ገጽ የሦስቱ ድንግልናዋ ማለትም የሥጋ፣ የነፍስና የኅሊና ምሳሌዎች ናቸው፡፡አንድም ያቺ ከላይ አንድ ከሥር ግን ሦስት እንደሆነች ሁሉ አንድነት ሦስትነትም ተለይቶ የታወቀው ጌታችን ከእመቤታችን ከተወለደ ወዲህ ነው፡፡ ዳግመኛ በዚያች ሐውልት አምልኮ እንደጸናባት በእመቤታችንም ‹‹ወረደ፣ ተወለደ…›› ተብሎ አምልኮ ጸንቶባታል፡፡ ቅዱሳን ሊቃውንት አባቶቻችን እመቤታችንን ለዚህ ነው‹‹የኢያሱ የምስክሩ ሐውልት አንቺ ነሽ›› ብለው በክብር ያመሰገኗት፡፡ ቅዳሴ ማርያም ቁ.34፡፡
+ + + + +
ዳግመኛም በዚህች ዕለት የመላእክት አለቃ የቅዱስ ገብርኤል መታሰቢያ በዓሉ ነው፡፡ ኔቅሎን በሚባል አገር በፍዩም ገዳም ቤተ ክርስቲያኑ የከበረችበት ዕለትም ነው፡፡ በዚኽችም ቤተ ክርስቲያን በውስጧ ከጣራዋ ዕንጨት ብዙ አስደናቂ ተአምራት ይገለጡ ነበር፡፡ ጥጋብ በሚሆንበት ዓመት ውኃ ይንጠፈጠፋል፤ ረኃብ ከሆነ ግን ላብ እንኳን አይታይም ነበር፡፡ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል በውስጧ ብዙ ተአምራትን አደረገ፡፡ ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣ በጸሎቱ ይማረን
ከገድላት አንደበት
✞ ✞ ✞

(የቅዱሳን ገድላቸውን ተኣምራታቸውን በየቀኑ በቴሌግራም ቻናል እና በዩቲዩብ በድምፅ ያዳምጡ።)

1. ቴሌግራም ቻናል፦
https://t.me/kegedilatandebet2716

2. ዩቲዩብ፦
https://www.youtube.com/channel/UC_BIHIqn1uygbjMZlwyoxPA/featured።

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት-ke gedilat andebet)

03 Jul, 17:22


አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አሜን
ሰኔ 25-የሐዋርያው ሰማዕት የቅዱስ ይሁዳ ዕረፍት ነው፡- ‹‹ይሁዳ›› ማለት ‹‹እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ›› ማለት ነው፡፡ ዘፍ 29፡35፡፡ አንድም ደግሞ‹‹ታማኝ›› ማለት ነው፡፡በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በይሁዳ ስም የተጠሩ 7 ሰዎች አሉ፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ይሁዳ፡- ይኸኛው በዛሬው ዕለት ሰኔ 25 ቀን ዕረፍቱ የሆነው ሐዋርያው ቅዱስ ይሁዳ ነው፡፡የጠራቢው ዮሴፍ ልጅ ሲሆን በልጅነቱ እናቱ ሞታበት የሙት ልጅ ሆኖ ሳለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተንከባክባ ያሳደገችው ዕድለኛ ሰው ነው፡፡ ነገሩም እንዲህ ነው፡-እመቤታችን በቤተ መቅደስ እየኖረች ሳለች 12 ዓመት በሆናት ጊዜ ሊቀ ካህናቱ ዘካርያስ ካህናቱን ሰብስቦ ‹‹የዚህችን ንጽሕት ልጅ ነገር ምን እናድርግ?›› ቢላቸው ካህናቱም በጋራ ‹‹ስለእርሷ ወደ ቤተ መቅደስ ገብተህ እግዚአብሔር የሚነግርህን በጸሎት ጠይቅ›› አሉትና እርሱም የክህነት ልብሱን ለብሶ ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ ገብቶ በጸሎት ሲጠይቅ እግዚአብሔር መልአኩን ልኮለት ሚስቶች የሌሏቸውን የዳዊት ወገን የሆኑ ወንዶችን ሰብስቦ በበትራቸው ላይ ስማቸውን ጽፎ ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ እንዲያገባው ነገረው፡፡ ሊቀ ካህናቱ ዘካርያስም በአዋጅ አስነግሮ 1985 ብሮችን ሰብስቦ ሲጸልይባቸው ቢያደር በአረጋዊ ዮሴፍ በትር ላይ ምልክት ታየ፡፡ በትሩንም ሲሰጠው ነጭ ርግብ መጥታ በዮሴፍ ላይ አረፈች፡፡ እርሱም ድንግልን እንዲወስዳት ሲነገረው አለቀሰ፡፡ ‹‹ይቅር በሉኝ እኔ ሽማግሌ ነኝና ልጆችም አሉኝ፤ ዕድሜዬም 83 ዓመት ነውና››እያለ አለቀሰ፡፡ ዘካርያስም ‹‹ይህ ሥራ ከእኛ ዘንድ አይደለም፣ እግዚአብሔር አዞናል እንጂ፡፡ እነሆ እርሷን ትጠብቃት ዘንድ ሰጥቶሃልና የእግዚአብሔርን ትእዛዝ እምቢ አትበል፤ ትእዛዙን አንቀበልም ያሉትን ፈጣሪህ እግዚአብሔር እንዴት እንዳደረጋቸው አስብ…›› እያለ አጽናናው፡፡ አረጋዊ ዮሴፍም እየፈራ ድንግል ማርያምን ወደቤቱ ወሰዳት፡፡እመቤታንም ወደ ዮሴፍ ቤት በገባች ጊዜ ልጆቹ እናታቸው በልጅነታቸው
ሞታባቸዋልችና የሙት ልጆች ሆነው አገኘቻቸው፡፡ ዮሴፍ አስቀድሞ ማርያም የምትባል ሚስት አግብቶ ነበር፡፡ ከእርሷም 3 ሴቶችና 4 ወንዶች ልጆች ነበሩት፡፡እነርሱም ስምዖን፣ ያዕቆብ፣ ይሁዳና ዮሳ ናቸው፡፡ ማቴዎስና ማርቆስም ይህንን በወንጌላቸው ጽፈውታል፡፡ ይህም ይሁዳ የተባለው በዛሬው ዕለት ያረፈው ሐዋርያው ነው፡፡ በኋላም ከጌታችን ጋር አብረው በማደጋቸው ምክንያት ‹‹የጌታ ወንድሞች›› ተብሎ ከተጠሩት ውስጥ አንዱ ይኸው ሐዋርያው ይሁዳ ነው፡፡ ማቴ13፡55፡፡ሐዋርያው ይሁዳ ቁጥሩ ከ72ቱ አርድእት ነው፡፡ ከጌታችን እግር ሥር ተቀምጦ 3 ዓመት ተምሮ መንፈስ ቅዱስን ተቀብሎ ወንጌልን በብዙ ሀገሮች ዞሮ በመስተማር አሕዛብን አሳምኖ አጥምቋል፡፡ወደ አንዲት ደሴትም ገብቶ
ወንጌልን በመስበክ በዚያ ያሉ ነዋሪዎቿን አሳምኖ አጥምቆዋቸዋል፡፡ ቤተ ክርስያንም ሠርቶላቸው አገልጋዮችን ሾመላቸው፡፡ ከዚህም በኋላ ወደተለያዩ ሀገሮች እየተዘዋወረ ብዙዎችን ከገቢረ ኃጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ መልሷቸዋል፡፡ ወደ ሮሀ ሀገር ሄዶ የሮሀውን ንጉሥ አውጋንዮስን ከደዌው ሁሉ ፈውሶታል፡፡ንጉሡንም ከነቤተሰቡ የክርስትናን ጥምቀት አጥምቆታል፡፡ ከዚህም በኋላ ሐራፒ ወደሚባል ሀገር ሄዶ የተለያዩ ተአምራትን በማድረግ ወንጌልን በመስበክ ነዋሪዎቿን አሳምኖ አጥምቆ ቤተ ክርስቲያን ሠራላቸው፡፡ አገረ ገዥውም ጣዖት አምላኪ ነበረና ሐዋርያው ይሁዳን ይዞ በጽኑ አሠቃየው፡፡ ስለታም ችንካሮች ያሉት ጫማ አሠርቶ በሐዋርያው እግሮች ውስጥ አድርጎ አሥሮ እየጎተተ አሠቃየው፡፡ይህም አልበቃው ብሎ ሰቅሎ በፍላፃ ነደፈው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ይሁዳም ከብዙ ሥቃዩ የተነሣ ሰማዕትነቱን ፈጽሞ ነፍሱ ከሥጋው ስትለይ ጌታችን ቅድስት ነፍሱን ተቀበላት፡፡ሐዋርያው ከማረፉ በፊት አስቀድሞ ለምእመናን አንዲት መልእክትን ጽፎ ልኳል፡፡እርሱ የጻፋት ይህችውም መልእክት ታላቅ ምሥጢርን የተመላች ናት፡፡መልእክቷም አንድ ምዕራፍ ብቻ ያላትን ስትሆን በጣም ብዙ ምሥጢርን የያዘች ናት፡፡ ብዙዎቻችን የምናውቃትን “ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለተሰጠች ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ” /ይሁዳ 1:3/ የምትለዋን የይሁዳን መልእክት የጻፋት ይኸው ሐዋርያ ነው፡፡ ሌሎቹም ሐዋርያት በሙሉ ይህን ዓይነት መልእክት ጽፈውልናል፡፡ አሁን በዘመናችን ያለውን የእምነት ችግር እነርሱ አስቀድመው በእምነት መነጽር አይተውት ስለነበር ነው የአደራ መልእክታቸውን ያስተላለፉልን፡፡የሐዋርያው የቅዱስ ይሁዳ ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣ በጸሎቱ ይማረን።
+++
ዳግመኛም በዚች ዕለት ለአባቶች ሊቃነ ጳጰሳት አርባ አራተኛ የሆነ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ አባ ጴጥሮስ ዕረፍቱ ነው ። ይህም አባት ከመሾሙ በፊት የማርቆስ መንበር ያለ ሊቀ ጳጳሳት ለብዙ ዘመናት ኖረ የእስላሞች ንጉሥና መኳንንቶቹ አልፈቀዱላቸውም ነበርና ።

ከዚህም በኋላ ሃይማኖቱ የቀና ደግ መኰንን በእስክንድርያ ከተማ ላይ ተሾመ ያንጊዜም የአገር ሽማግሌዎች ወደ ርሱ ተሰብስበው ሊቀ ጳጳሳት እንደ ሌላቸው ኀዘናቸውን ነገሩት ። እርሱም ደብረ ማሕው ወደሚባለው ወደ ደብረ ዝጋግ ወጥተው እንዲጸልዩ ለራሳቸውም ሊቀ ጳጳሳት እንዲሾሙ አዘዛቸው ። በዚህም ነገር ደስ ብሏቸው ቀሲስ አባ ጴጥሮስን ወስደው ሊቀ ጵጵስና ሾሙት በእርሱም ደስ አላቸው ።
በዚያም ወራት የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳት አባ ሳዊሮስ ሞተ የአንጾኪያ አገርም ያለ ሊቀ ጳጳሳት ትኖር ነበር የአንጾኪያ ምእመናንም ለእስክንድርያ ከተማ አባ ጴጥሮስ እንደ ተሾመ በስሙ ጊዜ እነርሱም የተማረ ደግ ሰው ለአንጾኪያ ሾሙ ስሙም ታውፋንዮስ ይባል ነበር ። እርሱም ከአባ ጴጥሮስ ጋራ ተስማማ እነርሱም ስለ ቀናች ሃይማኖት በመልእክቶቻቸው ይገናኙ ነበር ።

ከእነርሱም እያንዳንዱ በባልንጀራው ምክር በጸሎትና በቅዳሴ ጊዜ ይሰብክ ነበር ወደ አገራቸውም መግባት አልተቻላቸውም ነበርና አባ ጴጥሮስም በግብጽ ደቡብ በአንባንያ ገዳምና በዝጋግ ገዳም ይኖር ነበር አባ ታውፋንዮስም ከአንጾኪያ ከተማ ውጭ በአፍቆንያስ ገዳም ይኖር ነበር ።

በዚያም ወራት ከእስክንድርያ ከተማ ውጭ ሰባት መቶ ገዳማትና ሃይማኖታቸው የቀና ምእመናንም ያሉባቸው ሠላሳ ሁለት መንደሮች ነበሩ በግብጽ አውራጃ ሁሉና በላይኛው ግብጽ በአስቄጥስ ገዳማት የሚኖሩ መነኰሳት እንዲሁም ኖባና ኢትዮጵያ በዚህ በአባ ጴጥሮስ ስልጣን ሥር ነበሩ ። እኒህ ሁሉ ሃይማኖታቸው የቀና ነበር ።
በትእዛዙም ጸንተው ይኖሩ ነበር ። እርሱም በቀናች ሃይማኖት ይጸኑ ዘንድ ወደእርሳቸው መልእክቶችን መጻፍ አያቋርጥም ነበር ። የእስክንድርያን ገዳማት ሁሉና መንደሮችንም እየዞረ ያስተምራቸውና ይመክራቸው ያጽናናቸውም ነበር ።

ከእርሱ በኋላ ሊቀ ጳጳሳት የሆነ ቅዱስና ዐዋቂ የሆነ ደቀ መዝሙር ነበረው እርሱም በሊቀ ጵጵስናው ሥራ ሁሉ ይራዳው ነበረ ። ይህም አባት ጴጥሮስ አንዳንድ ጊዜ ወደ እስክንድርያ ከተማ ይገባ ነበር የሰዎቿንም ሥራቸውን ተመልክቶ ያስተምራቸውና በሃይማኖት ያጸናቸው ነበር ።

በዐሥራ ሁለቱ ዓመት የሹመቱ ዘመን እንደ ሐዋርያት መንጋዎቹን እየጠበቀ እንዲህ በሹመቱ ኑሮ በሰላም አረፈ ።
ከገድላት አንደበት
✞ ✞ ✞

(የቅዱሳን ገድላቸውን ተኣምራታቸውን በየቀኑ በቴሌግራም ቻናል እና በዩቲዩብ በድምፅ ያዳምጡ።)

1. ቴሌግራም ቻናል፦
https://t.me/kegedilatandebet2716

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት-ke gedilat andebet)

03 Jul, 17:22


2. ዩቲዩብ፦
https://www.youtube.com/channel/UC_BIHIqn1uygbjMZlwyoxPA/featured።

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት-ke gedilat andebet)

01 Jul, 00:51


አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አሜን
ሰኔ 24-ታላቁ አባት አባ አቡነ ሙሴ ጸሊም በሰማዕትነት ዐረፉ፡፡ አቡነ ሙሴ ጸሊም ኢትዮጵያዊ ሲሆኑ ተጋድሎአቸውን የፈጸሙት ግን በግብፅ ነው፡፡
መጀመሪያ ላይ እንደ አብርሃም በየዋህ ልቡና ሆነው ስነ ፍጥረትን በመመራመር እግዚአብሔር አምላካቸውን ያገኙ ታላቅ አባት ናቸው፡፡ ወላጆቻቸው ፀሐይ ያመልኩ ስለነበር ከልጅነታቸው ጀምሮ ኃጢአት በሠሩ ቁጥር ‹‹ተው አምላካችን ፀሐይ ይጣላሃል›› ይሏቸው ነበር፡፡ እሳቸው ግን ባደጉ ጊዜ ቀማኛ ዘራፊ ሆኑ፡፡እየዘረፉ ብዙ ይመገቡ ስለነበር ከትልቅነታቸውና ኃይለኛነታቸው የተነሳ ‹‹በገ ፈጅ›› እየተባሉም ይጠሩ ነበር፡፡ብዙ ወርቅ ከባለ ሀብቶች ሰብስባ ለነዳያንና ለቤተክርስቲያን ልትሰጥ ትሄድ የነበረችን አንዲት ክርስቲስቲያን ሴት ልጅ ሙሴና ግብረ አበሮቻቸው ለወርቁ ሲሉ እርሷንም ማርከው ወሰዷት፡፡ ማታ ላይ ስለ ውበቷ ሲያወሩ እርሷ ግን‹‹ስምህ ማን ነው?›› ስትላቸው ‹‹ሙሴ ነኝ›› ቢሏት ‹‹ይሄ ስምኮ እጅግ የተባረከ ስም ነው….›› ብላ ስለ ሊቀ ነቢያት ሙሴና ስለ ክርስቶስ አስረዳቻቸው፡፡ ከዚህ በኋላ በወላጆቻቸው ስለ ፀሐይ አምላክነት ሲነገራቸው ያደጉትን ነገር መመርመር ጀመሩ፡፡ ‹‹ፀሐይ አምላክ ከሆነ እስከዛሬ ድረስ ሽፍታና ዘራፊ ሆኜ ሰው ስገድልና ይህን ሁሉ ኃጢአት ስሠራ እንዴት ፀሐይ ሳታቃጥለኝ ቀረች? ደግሞም ፀሐይ ጠዋት ወጥታ ማታ ትጠልቃለች ይህችስ እንዴት አስገኚ ልትሆን ትችላለች ለራሷ አስገኚ አላት እንጂ…›› በማለት ፀሐይን፣ ጨረቃን ፣እሳትን፣ ነፋስን በየተራ አምላክ መሆናቸውን አለመሆናቸውን በሚገባ ከፈተኑና ከመረመሩ በኋላ ‹‹የፀሐይ የጨረቃ የሁሉ አስገኚ አምላክ ተናገረኝ›› ብለው ሲጸልዩ ከሰማይ ድምፅ መጥቶላቸው ወደ ገዳም ሄደው ከአባቶች ትምህርተ ሃይማኖትን እንዲማሩ ተነገራቸውና ወደ አስቄጥስ ገዳም ሄደው መምህር ኤስድሮስ ሁሉንም ነገር አስተምረው ለማዕረገ ምንኩስና አበቋቸው፡፡መጀመሪያ ወደ ገዳሙ ሲሄዱም ይዘርፉበትና ይጠቀሙበት የነበረውን ስለታም መሣርያ እንደያዙ ስለነበር ያዩአቸው መነኮሳት ሁሉ ‹‹ሊገድለን መጣ›› ነበር ያሉት፡፡ ከዚህም በኋላ ለመነኮሳቱ ሁሉ የሚላላኩ ሆኑ፡፡ ትንሹም ትልቁም‹‹ሙሴ ይህን አድርግልኝ›› ይሉታል እርሱም ሁሉንም እሺ ይላል፡፡ ራሱን በትሕትና ዝቅ በማድረግ በተጋድሎ እየኖረ ተአምራትን ማድረግ ጀመረ፡፡ በጸሎቱ ዝናብ ያዘንብ ነበር፤ ለቅድስና ደረጃ ከበቁም በኋላ 40 ዓመት ሙሉ ከሰው ሳይገናኙ ብቻቸውን ዘግተው ከኖሩ በኋላ ለ500 መነኮሳት አበምኔት ሆነው ተሾሙ፡፡ ቀን ወንጌል ሲያስተምሩ ይውሉና ሌሊት እየተነሱ ከበረሃ ሄደው ለሁሉም መነኮሳት ውኃ ይቀዱላቸው ነበር፡፡አገልግሎታቸው የታይታ እንዳይሆንባቸው አረጋውያን መነኮሳት መተኛታቸውን ካረጋገጡ በኋላ የግብፅ በረሃን አቋርጠው ከሩቅ ሥፍራ ሄደው ውኃ እየቀዱ መነኮሳቱ ሳያዩአቸው በየደጃፋቸው ላይ ያስቀምጡላቸው ነበር፡፡ብዙ መነኮሳትም ወደ አቡነ ሙሴ እየመጡ የሕይወትን ትምህርት ይማሩ ነበር፡፡በአንድ ወቅት አንድ ወንድም አባ ሙሴን ‹‹አንድን አገልጋይ ባጠፋው ጥፋት የተነሣ ጌታው መታው፡፡ አገልጋዩ ምን ማለት አለበት?›› ብሎ ጠየቃቸው፡፡ አባ ሙሴም ‹‹አገልጋዩ ብፁዕ ከሆነ፣ አጥፍቻለሁና ይቅር በለኝ ማለት አለበት›› አሉት፡፡ ‹‹ሌላ አይጠበቅበትምን?›› ሲል ያ ወንድም ጠየቃቸው፡፡ ‹‹አይጠበቅበትም፣ ለጊዜው ለጥፋቱ ኃላፊነቱን ወስዶ አጥፍቻለሁ ካለ ጌታው ይቅር ይለዋል፡፡ የዚህ ሁሉ ዓለማው በባልንጀራ ላይ ላለመፍረድ ነው፡፡በእውነቱ ጌታችን የግብፅን በኩራት ሁሉ ሲመታ ሰው ያልሞተበት አንድም ቤት አልነበረም›› ብለው መለሱለት፡፡ ያም ወንድም ‹‹ምን ማለት ነው?›› አላቸው፡፡እሳቸውም ‹‹ሁላችንም የየራሳችንን ጥፋቶች ካየን የባልንጀራችንን ለማየት ዕድል አንሰጥም፡፡ በራሱ ቤት ሰው የሞተበት በጐረቤቱ ልቅሶ ለማልቀስ አይሄድም፡፡ለባልንጀራ መሞት ማለት ለራስ ጥፋት ትኩረት በመስጠት፣ የሌላውን ጥፋት ከቁም ነገር አለመቁጠር ነው፡፡ ማንንም አትጉዳ፣ በማንም ላይ ክፉ አታስብ፣ክፉ የሚሠራውን ሰው አትናቀው፣ በባልንጀራው ላይ ክፉ በሚሠራ ሰው ላይ አትተማመን፣ በባልንጀራው ላይ ክፉ ከሚሠራ ሰው ጋር አትደሰት፣ ለባልንጀራ መዋቲ መሆን ማለት ይህ ነው፡፡ በማንም ላይ አትማረር፣ ነገር ግን ሁሉንም እግዚአብሔር ያውቃል በል፡፡ ከሚያማ ሰው ጋር አትተባበር፣ በሐሜቱም አትደሰት፣ ወንድሙን የሚያማውን ሰውም አትጸየፈው፡፡ አትፍረድ ማለት ትርጉሙ ይህ ነው፡፡ በማንም ላይ የጥላቻ ሀሳብ አይኑርህ፣ ጥላቻ ልብህን እንዲያሸንፈውም አትፍቀድለት፡፡ ባልንጀራውን የሚጠላውን አትጥላው፣ ሰላም ማግኘት ማለት ይህ ነው…›› ብለው መከሩት፡፡በዕድሜአቸው መጨረሻ አካባቢ ቡራኬ ለመቀበል ከመነኮሳት ደቀ መዛሙርቶቻቸው ጋር ወደ አባ መቃርስ ሄዱ፡፡ አባ መቃርስም ‹‹ልጆቼ ከናንተ መካከል በሰማዕትነት የሚሞት›› አለ ብለው ትንቢት ሲናገሩ ሙሴ ጸሊምም‹‹አባቴ ያ ሰው እኔ ነኝ፣ ‹ሰይፍ የሚያነሱ በሰይፍ ይጠፋሉ› የሚል ቃል አለ፡፡ይህን ጊዜ በጉጉት ስጠባበቀው ነበር›› አላቸው፡፡ እንደተባለውም የበርበር ሰዎች ገዳሙን ዘርፈው መነኮሳቱን ሊገድሉ ሲመጡ ደቀመዛሙርቶቻቸው ‹‹ሸሽተን እናምልጥ›› ሲሏቸው አቡነ ሙሴ ግን ‹‹በጎልማሳነቴ ጊዜ ደም አፍስሼያለሁና አሁን የእኔም ደም ሊፈስ ይገባል›› በማለት ራሳቸውን ለመሰየፍ አዘጋጅተው ጠበቋቸውና በርበሮች ሰኔ 24 ቀን አንገታቸውን በሰይፍ ቆርጠዋቸዋል፡፡ፈርተውና ሸሽተው የነበሩት ደቀመዛሙርቶቻቸውም ተመልሰው አብረዋቸው ተሰይፈዋል ፡፡የአባታችን የሙሴ ጸሊም ቅዱስ ሥጋቸው በገዳመ አስቄጥስ በክብር ይገኛል፡፡ግብፆች አቡነ ሙሴ ጸሊምን በእጅጉ ያከብሯቸዋል፡፡ በስማቸው ጽላት ቀርጸው ቤተክርስቲያን ሠርተው ሥዕላቸውን አሠርተው ገድላቸውን ጽፈው በስንክሳራቸው መዝግበው የዕረፍታቸውን መታሰቢያ በደማቅ ሁኔታ ነው የሚያከብሩት፡፡ የአቡነ ሙሴ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን፣ በጸሎታቸው ይማረን፡፡
ከገድላት አንደበት
✞ ✞ ✞

(የቅዱሳን ገድላቸውን ተኣምራታቸውን በየቀኑ በቴሌግራም ቻናል እና በዩቲዩብ በድምፅ ያዳምጡ።)

1. ቴሌግራም ቻናል፦
https://t.me/kegedilatandebet2716

2. ዩቲዩብ፦
https://www.youtube.com/channel/UC_BIHIqn1uygbjMZlwyoxPA/featured።

6,682

subscribers

1,269

photos

4

videos