ነጃሺ ቲቪ የካቲት 8/2017
ጅቡቲን ለብዙ ዓመታት በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ያገለገሉት መሐመድ ዓሊ ዩሱፍ ቀጣዩ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ኾነው ተመረጡ። ‘
አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኘው የአፍሪካ ኅብረት ዋና ጽሕፈት ቤት እየተካሔደ ባለው 38ኛው የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ ላይ፣ መሪዎቹ በሚስጥር በሰጡት ድምጽ የጅቡቲው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ ኮሚሽኑን በሊቀመንበርነት እንዲመሩ ተመርጠዋል።
ኮሚሽኑን እንዲመሩ በሊቀመንበርነት የተመረጡት የጅቡቲው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ በአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ በተካሔደውና ብርቱ ፉክክር በታየበት፣ እንዲኹም እስከ ሰባተኛ ዙር ድረስ በዘለቀ ምርጫ ሁለት ሦስተኛ ድምጽ አግኝተው ነው።
ከሳምንት በፊት 60ኛ ዓመት የልደት በዓላቸውን ያከበሩት ዩሱፍ፣ በምርጫው አሸናፊ የኾኑት የኬንያውን የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋ እና የማዳጋስካር የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሪቻርድ ራንድሪያማንድራቶን በማሸነፍ ነው።
ዩሱፍ በመጀመሪያዎቹ ሁለት ዙሮች በ18 እና በ19 ድምፅ አግኝተው ከራኢላ ጋራ በተቀራረበ ሁኔታ ሁለተኛ ዙር ላይ ነበሩ። ከሦስተኛው ዙር ጀምሮ በተካሔዱት የድምጽ አሰጣቶች ግን ዩሱፍ በመሪነት ቀጥለዋል። በመጨረሻም ለአሸናፊት የሚያበቃው 33 ድምጽ በማግኘት የመሪነቱ ቦታ ተረክበዋል።
አዲሱ የኅብረቱ ተመራጭ ኮሚሽነት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር፣ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ የጅቡቲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኾነው አገልግለዋል። በአፍሪካ አህጉር ረዥም ጊዜ ያገለገሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርም ናቸው።
ከኅብረቱ ከታገዱት ስድስት ሀገራት በስተቀር 55ቱም የአባል ሀገራት በ38ኛው የኅብረቱ መሪዎች ጉባኤ ላይ እየተሳተፉ ነው።