እንቅልፍ ሲበዛ የስንፍና ምልክት መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው:: "ድሀ እንዳትሆን እንቅልፍን አትውደድ፤ ዓይንህን ክፈት፥ እንጀራም ትጠግባለህ” ፤ “የእንቅልፍም ብዛት የተቦጫጨቀ ጨርቅ ያስለብሳል" የሚሉት ጥቅሶች ለዚህ ምስክር ናቸው:: (ምሳሌ 20:13 ፣ 23:21)
ሆኖም በእንቅልፋቸው የተጠቀሙ ብዙ ሰዎችም አሉ:: አንቀላፍቶ ሚስቱን ያገኘው አዳም እንዴት ይረሳል? ከኤሳው ጋር ሲታገል የኖረው ያዕቆብ ሲባረክ ያደረውስ በእንቅልፉ አልነበር? ያዕቆብማ ምነው ባልነቃ ያሰኛል:: ሰማይ ድረስ መሰላል ወጥቶ መላእክት ሲወጡና ሲወርዱ ያየው በእንቅልፉ ምክንያት ነበር:: በባቢሎን ምርኮ ዘመን የነበረው አቤሜሌክ ደግሞ የእንቅልፋሞች ንጉሥ ቢባል አያንስበትም:: የኢየሩሳሌምን ጥፋት አታሳየኝ ብሎ ሲጸልይ የነበረው ይህ ሰው በፈጣሪ ፈቃድ ለስድሳ ስድስት ዓመታት ያህል ተኝቶ ነበር:: ከእንቅልፉ ሲነሣም እንቅልፍ ሳይጠግብ እየተበሳጨ ነበር:: ማንቀላፋቱ ግን ብዙ ጉድ ከማየት አዳነው:: (ተረፈ ኤርምያስን ይመልከቱ)
ዛሬ ግን በቤተ ክርስቲያን ታሪክ የአቤሜሌክን የእንቅልፍ ክብረ ወሰን የሰበሩ ሰባቱ እንቅልፋሞች (The Seven Sleepers) የተሰኙ ቅዱሳንን እንተዋወቅ:: ወቅቱ የሮም ነገሥታት አላውያን የነበሩበት ክርስቲያኖች በግፍ እየተገደሉ የነበረበት ዘመነ ሰማዕታት ነው:: ክርስቲያን መሆን ወንጀል በነበረበት በዚያ ወቅት ክርስቲያኖች ከአንበሳ ጋር እየታገሉ በመስቀል እየተሰቀሉ በሰይፍ እየተቀሉ እየሞቱ የነበረበት ዘመን ነው::
በንጉሥ ዳክዮስ ዘመነ መንግሥት (249-251) ታዲያ በንጉሣዊ ምክር ቤቱ ውስጥ አባል የነበሩ ሰባት ወጣት ልዑላን ድንገት ክርስትናን ተቀብለው "ለጣዖት መሥዋዕት አንሠዋም" ብለው አሻፈረኝ አሉ፡፡ ወጣቶቹ ይህን በማድረጋቸው የሚከተለውን ጽኑ ቅጣት ያውቁ ነበረና ፈርተውም በቅርብ ወዳለ አንድ ተራራ ሸሽተው በዋሻ ውስጥ ተደበቁ።
@diyakonhenokhaile
በዚያ ዋሻ ውስጥ ተደብቀው እያሉ ታዲያ ሰባቱንም እንቅልፍ ይጥላቸዋል፡፡ ንጉሥ ዳክዮስ አሳድዶአቸው ሲመጣ ተኝተው እንዳሉ ያያል:: አውሬው ንጉሥ ሁኔታውን ሲያውቅ እዚያው ዋሻ ውስጥ ይሙቱ ብሎ የዋሻውን መግቢያ በር በግንብ አስደፍኖት ሔደ፡፡
ይህ ሁሉ ሲሆን ወጣቶቹ እንቅልፍ ላይ ናቸው::
ከመቶ ሃምሳ እስከ ሁለት መቶ ዓመታት ገደማ ከሆነ በኋላ እነዚህ ወጣቶች ከእንቅልፋቸው ይነቁና የረሃብ ስሜት ይሰማቸዋል፡፡ ከእነርሱ አንዱን ወደ ከተማ ሔዶ ምግብ እንዲገዛላቸው ይልኩታል፡፡
ዋሻው የተዘጋበት በር ከዘመን ብዛት ፈርሶ ነበርና የተላከው ወጣት ከዋሻው በቀላሉ ወጥቶ ወደ ከተማ አቀና፡፡ ወደ ከተማ ገብቶ ለሰባቱም የሚበቃቸውን ምግብ አገኘና ሂሳብ ሊከፍል ከኮሮጆው ሳንቲም አወጣ፡፡ ያወጣው ገንዘብ ግን ከሁለት መቶ ዓመታት በፊት መገበያያ የነበረውን 'የጣዖት አምላኪዎቹን' ነገሥታት የወርቅ ሳንቲም ነበር። ሰባቱ ያንቀላፉ ቅዱሳን ከእንቅልፍ የነቁበት ያ ዘመን ዘመነ ሰማዕታት አልፎ የኤፌሶን ከተማ ሙሉ በሙሉ ክርስቲያናዊት ከተማ በሆነችበት ደግ ዘመን ነበር፡፡
@diyakonhenokhaile
የሰባቱ ወጣቶች ዝና ወዲያው በወቅቱ የነበሩት ክርስቲያን ነገሥታትና ሊቃነ ጳጳሳት ዘንድ ደረሰ፡፡ ወጣቱ ወደ ዋሻው ከተመለሰ በኋላ ግን ሰባቱም ቅዱሳን ድጋሚ እንቅልፍ ጣላቸው፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ ሲተኙ ግን እስከወዲያኛው በክብር አሸለቡ፡፡ ለእነዚህ ሰባት ሰማዕታት በሥፍራው ትልቅ ቤተ መቅደስ ተሠርቶላቸዋል፡፡
"እኔ ተኛሁ አንቀላፋሁም፤ እግዚአብሔርም ደግፎኛልና ነቃሁ" መዝ.3:5
“የኤፌሶን ወንዝ” ገፅ 64 የግርጌ ማስታወሻ ላይ የተወሰደ
ሙሉ ገቢው ለግሸን ደብረ ከርቤ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን እድሳት የሚውለው የኤፌሶን ወንዝ መጽሐፍ የመጀመሪያ እትም እያለቀ ነው:: እርስዎ እጅ ገብቶ ይሆን?
አርጋኖን መጻሕፍት መደብር Areganon Book Store
#share
▫️@diyakonhenokhaile
https://t.me/diyakonhenokhaile