ሕማማት ዲ/ን ሔኖክ ኃይሌ @henok_haile1 Channel on Telegram

ሕማማት ዲ/ን ሔኖክ ኃይሌ

@henok_haile1


ሕማማት ዲ/ን ሔኖክ ኃይሌ (Amharic)

ሕማማት ዲ/ን ሔኖክ ኃይሌ በእንግሊዝ በብዙ መንገዶች ላይ ገና በመተንፈስ ስስት ገዛ ኃይሌ መደብና መመልከት እንዲሆን የሚያደርጉ እና ፈቃደኛዎች መዋጋት እንዲሆን በጣም ስለ ኃይሌ ከማወቅ ትገኛለህ። ሕማማት ዲ/ን ሔኖክ ኃይሌ ለርዕስ ምናልባትም ሌላ ይደግፉባቸዋል። እሱ የኃይሌ መረጃዎችን አላያይ ማንኛውም ነገር ላይ ከለዛዋ እንደሚላይ እና ምንኩለኛውን ማህበረሰብ እንደሚሰጥ ተጨማሪ ነው። ይህን የሚከተለውን ልናቀርበን እንደሚችል በማናቀርብ አስቀድሞ ለአንዳች ሰንበቴ በጣም እንዳሰጥህ ተመዝግበናል።

ሕማማት ዲ/ን ሔኖክ ኃይሌ

19 Nov, 19:38


"በሰው ላይ የምንመለከተው የእግዚአብሔር መልክ ነው። የእኛ ሰዓሊ ሲስለን እርሱን እንድንመስል አድርጎ ነው፡፡ የእርሱን ውበት በእኛ ውስጥ ይሰራዋል፡፡

በቀለም ፋንታ በተለያየ መንፈሳዊ በጎነት ያሳምረናል፤ የእግዚአብሔር ምስልና መልክም ከምንም ነገር ጋር ስለማይነጻጸር ሰውም ይህ እውነተኛ መልኩ በመሆኑ ከሌሎች ምድራዊ ነገሮች ጋር አይቀላቀልም፣... ተፈጥሯችንን ያስዋበ እግዚአብሔር ከተጠቀመበት ብሩሽ አንዱ #ፍቅር ነው።

#ቅዱስ_ጎርጎርዮስ_ዘኑሲስ

ሕማማት ዲ/ን ሔኖክ ኃይሌ

18 Nov, 19:05


በጉብዝናችን ወራት ፈጣሪያችንን እንድናስብ የሚረዳን አንደበታችን ከክፉ ከልክለን ሽንገላንም ከእኛ አርቀን ሰዎችን የሚያጽናና የሚያረጋጋ መልካም ነገርንም ብቻ ስንናገር ነው፡፡  እግዚአብሔርን የማሰብ አንዱ መገለጫ መልካም ነገር መናገር ነው፡፡  መጽሐፍ ‹‹እግዚአብሔር መልካም ነው›› ብሎ እንደተናገረ ስለ እግዚአብሔር ቸርነት፣ ታላቅነትና መጋቢነት የሚናገር መልካም ነገር ተናገረ፡፡ (ናሆ. ፩፥፯)
እግዚአብሔር ስለሚወደውና ስለሚፈቅደው ነገር ብቻ መናገር እግዚአብሔርን ማሰብ ነው፡፡  ዛሬ ላይ ብዙዎቻችን እግዚአብሔርን ማሰብ ስላቆምን ከአንደበታችን የሚወጣው ቃል ሁሉ ስድብ፣  ትችት፣  ነቀፋ፣ ሐሜት፣ ሽንገላ፣ ተረብና የመሳሰሉት ሆነዋል፡፡  ነቢዩ ዳዊት ‹‹ጉሮሮአቸው የተከፈተ መቃብር ነው፤ በምላሳቸው ሸነገሉ፤ ከከንፈራቸው በታች የእባብ መርዝ አለ፤  አፋቸው መርገምንና መራራን ተሞልቶዋል  …. እግዚአብሔርን መፍራት በዓይናቸው የለም›› ብሎ እንደተናገረው የእኛም ነገር እንዲሁ ሆኗል፡፡ (መዝ. ፲፫፥፬-፮)
እግዚአብሔርን የሚያስብ ወጣት የሚናገረውን ያውቃል፡፡ አንደበቱም የተገራና በመልካም ነገር የተቀመመ ነው፡፡ ሰውን የሚያስደነግጥ፣ የከፋውን የሚያባብስ፣  በወገኖች መካከል ልዩነትን የሚያሰፋና ጠብ የሚጭር ነገር ከአንደበቱ አይወጣም፡፡ እየጮኸ፣ ጎረቤት እያወከ፣ ሰዎችን እያሳቀቀ፣ የሰዎችን ክብር እየነካ፣ በሌላው የአካል መጉደል እያሾፈ አይናገርም፡፡ ‹‹በአፍ ይጠፉ በለፈለፉ›› እንደሚባለውም በአንደበቱ ምክንያት የማይገባውን እየተናገረ በራሱና በማኅበረሰቡም ሆነ በሀገሩ ላይ ጥፋትና መጠፋፋትን አያመጣም፡፡ የምንናገረውን ለማወቅ ፈጣሪያችን ልዑል እግዚአብሔርን እናስብ፡፡  እግዚአብሔርን ማሰብ ስላቆምን ስለተውነውም ሰዎች በድለውንም ይሁን ሳይበድሉን የስድብ ናዳ እናወርድባቸዋለን፡፡  በአንድ ሰው ስሕተት አባቱ፣ እናቱ፣ ወንድሞቹ በመጣበት ነገድ፣ የተወለደበት መንደር ሳይቀረን በስድብ እናጥረገርጋቸዋለን፡፡  እግዚአብሔርን ማሰብ ስላቆምን የምንናገረው እያንዳንዱ ነገር ሰዎች ላይ ምን ዓይነት አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር በሀገርም ላይ ምን ዓይነት ጥፋት ይዞ እንደሚመጣ ማስተዋል ተስኖናል፡፡  ጥቂት የማንባል ወጣቶች እግዚአብሔርን ማሰብ እንደሞት ስለምንቆጥረው የሞት ምክንያት የሆኑ አያሌ ነገሮች ከአጠገባችን ቆመዋል፡፡  ሽማግሎዎችን እንሳደባለን፤ አካል በጎደላቸው እንሳለቃለን፤ ችሎታ የጎደለውን እናሸማቅቃለን፤  ከደረስንበት ያልደረሰውን እናቃልላለን፡፡

እግዚአብሔርን  ማሰብ- ከመከራ ሁሉ መዳኛ መንገድ ነው፡፡

ጠቢቡ ሰሎሞን ‹‹በጉብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ›› ብሎ የተናገረበትን ምክንያት ሲገልጥ የመጀመሪያ ምክንያት አድርጎ ያቀረበው ‹‹የጭንቀት ቀን ሳይመጣ›› የሚል ነው፡፡ በወጣትነት በልዩ ልዩ ምክንያቶች የሚገጥሙንን የጭንቀት ፈተናዎች የምንወጣው በተለያዩ አደንዛዥ ዕፅ ሱሶች ውስጥ በመደበቅ፣ አልኮል መጠጦችን በማብዛት፣ መፍትሔ ብለን የምንወስዳቸው ሌሎች ችግር አምጪ አማራጮች ውስጥ በመግባትና ሌሎች መሰል ድርጊቶችን በመከወን መሆን የለበትም፡፡ የጭንቀት መድኃኒቱ እግዚአብሔርን ማሰብና እንደ ፈቃዱም መመላለስ ነው፡፡ የወጣትነት ዕድሜ ካለፈ በኋላም ለሚገጥመን የሽምግልና ጭንቀት መድኃኒቱ የወጣትነት ዕድሜን አካሄድ ማስተካከል እንደሆነ የሥነ ልቡና ባለሙያዎችም ሳይቀሩ ይመክራሉ፡፡ ነቢዩ ዳዊት ‹‹ጎልማሳ መንገዱን በምን ያነጻል? ቃልህን በመጠበቅ ነው›› ብሎ እንዳስተማረውም በኋለኛው ዘመን የሚኖረንን መዳረሻ የሠመረና ትርጉም ያለው የሚያደርገው በወጣትነት ዘመናችን ከእግዚአብሔር ጋር እንዲኖረን የምናደርገው መልካም አኗኗር ነው፡፡ በወጣትነት ያልዘሩትን በሽምግልና አያጭዱትም፡፡ በጉብዝና ያላረሙትን በዕርግና አያስተካክሉትም፡፡ (መዝ. ፻፲፰፥፱)
ጠቢቡ ሰሎሞን በጉብዝና ወራት ፈጣሪን የማሰብ ምክንያት አድርጎ ያቀረበው ሌላኛው ምክንያት ‹‹ደስ አያሰኙኝም የምትላቸው ዓመታት ሳይደርሱ፤ ፀሐይና ብርሃን ጨረቃና ከዋክብትም ሳይጨልሙ፥ ደመናትም ከዝናብ በኋላ ሳይመለሱ፤……….አፈርም ወደነበረበት ምድር ሳይመለስ÷ ነፍስም ወደሰጠው ወደ እግዚአብሔር ሳይመለስ ፈጣሪህን አስብ›› የሚል ነው፡፡ በፀሐይ በጨረቃና በከዋክብት የተመሰለ ማግኘት፣ ማሸነፍ፣ ነግዶ ማትረፍ፣ ሮጦ ማምለጥ፣ ወድቆ መነሣት የሚቻልበት የወጣትነት ጊዜ በእርጅና በድካም በደዌና ከፍ ሲልም በሞት ይደመደማል፡፡ በብርሃን ጀምረን በብርሃን፤ በድል ጀምረን በድል እንድንፈጽም ታናሽ የሆነ ጅማሬያችን እጅግ የበዛ እንዲሆን በጉብዝናችን ወራት ፈጣሪያችን ልዑል እግዚአብሔርን በመንገዳችንና በተግባራችን ሁሉ እናስብ፤ ከእርሱ ጋር እንኑር፤ ስለ እርሱም እንናገር!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ሕማማት ዲ/ን ሔኖክ ኃይሌ

18 Nov, 19:05


‹‹በጒብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ›› (መክብብ ፲፪፥፩)
መምህር ቢትወደድ ወርቁ

በቅዱሳት መጻሕፍት ወጣትነት ጉብዝና አንዳንዴም ጉልምስና እየተባለ ይጠራል፡፡  የወጣትነት ዕድሜ ብያኔ እንደ የማኅበረሰቡና እንደ የሀገሩ ቢለያይም ሰው ሠርቶ ማግኘት፣ ወድቆ መነሣት፣  የሚችልበት ዕድሜው የጉብዝናው ዕድሜ ነው፡፡ ወጣትነት  /ጉብዝና/  ከመነሻው አያሌ ባሕርያዊ አካላዊና ሥነ ልቡናዊ ለውጦች የሚከሠቱበት የዕድሜ ክልል ነው፡፡
በመሆኑም የሚመለከታቸውን አካላት የቤተ ክርስቲያን መምህራን፣  ወላጆች፣  የቀለም ትምህርት ቤት መምህራን፣  እንዲሁም ወጣቶችን ማዕከል አድርገው የተቋቋሙ የመንግሥት ተቋማት ወጣቶችን ከሥሩ በተገቢው መልኩ ካላስተማሩ የሚከሠተው ሰብአዊና ሀገራዊ ቀውስ ከፍተኛ ይሆናል፡፡  የሀገር ህልውናዋ የሚወሰነው ወጣቶች ላይ በሚሠራው ሥራ ነውና፡፡  የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችም ፍሬያቸው በዋናነት የሚመዘነው ምን ያህል ወጣቶችን በአገልግሎት ምርታማና ውጤታማ እንደሚሆኑና በነፍሳቸውም ለእግዚአብሔር የሚገዙ እንዲሆኑ አድርገዋል? በሚለው ሚዛን ነው፡፡  ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  ሲገልጽ ቅዱስ ጴጥሮስን በግልገል የተመሰሉ ሕፃናትንና በበጎች የተመሰሉ አረጋውያንን አሠማራ ሲለው በጠቦት የተመሰሉ ወጣቶችን ግን ጠብቅ ብሎታል፡፡  (ዮሐ. ፳፩፥፲፮)
ወጣቶች መንገዳቸው ከአምላካቸው  ከልዑል እግዚአብሔር ጋር የተስማማ ይሆን ዘንድ በማስተዋል ሊጓዙ ይገባቸዋል፡፡ በማስተዋል መጓዛችን ከሚገለጥባቸው መንገዶች መካከል አንዱና ዋነኛው ደግሞ ፈጣሪያችን ልዑል እግዚአብሔርን በኑሯችን ሁሉ ማሰብ ነው፡፡

እግዚአብሔርን ማሰብ – ከእግዚአብሔር ጋር መኖር

ጠቢቡ ሰለሞን ‹‹በጉብዝናህ ወራት ፈጣህን አስብ›› ብሎ የተናገረው ቃል በወጣትነት ወራት ከአምላካችን ከእግዚአብሔር ጋር እንድንኖር የሚያሳስብ ነው፡፡ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለድኅነተ ዓለም በመስቀል ላይ በተሰቀለ ጊዜ በቀኙ የተሰቀለው ወንበዴ ‹‹ጌታ ሆይ፥ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ›› ብሎ እንደተማጸነው እናስተውል፡፡  ለዚህ የወንበዴው ጸሎት ጌታችን ‹‹እውነት እልሃለው፥ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትኖራለህ›› በማለት ‹‹አስበኝ›› ለሚለው ጸሎት ‹‹ከእኔ ጋር ትኖራለህ›› በማለት ከመለሰለት መልስ እግዚአብሔርን ማሰብ ማለት ከእግዚአብሔር ጋር መኖር ማለት መሆኑን እንረዳለን፡፡  (ሉቃ. ፳፫፥፵፪)
ከእግዚአብሔር ጋር እንኖር ዘንድ የታዘዝን ክርስቲያን ወጣቶች ዛሬ ከማን ጋር እየኖርን ነው? ሐሳባችን፣  ንግግራችንና ተግባራችን የሚገልጸው ከእግዚአብሔር ጋር መኖራችንን ነው? እግዚአብሔርን የሚያስብ ወጣት አኗኗሩ እንደ ቅዱስ ዮሴፍ እግዚአብሔርን በመፍራትና በኑሮው ውጣ ውረድ ሁሉ እግዚአብሔርን አለመዘንጋት ነው፡፡  እግዚአብሔርን መፍራት የጥበብ ሁሉ መጀመሪያ የመልካምነትም ሁሉ መሠረት ነው፡፡ እግዚአብሔርን የሚፈራ ወጣት ዘወትር በማንኛውም ቦታና ሁኔታ አምላኩ ከእርሱ ጋር እንዳለ ስለሚያስብ ሰው አየኝ አላየኝ ብሎ ብቻ ሳይሆን እንደ ዮሴፍ እግዚአብሔርን በማሰብ ከኃጢአት ይሸሻል፡፡  ወጣቱ ቅዱስ ዮሴፍ እግዚአብሔርን በማሰብ ፈጣሪውን ከእርሱ ጋር እንዲሆን አድርጎታልና ትጉህና ውጤታማ ሠራተኛ ሆነ፡፡  ዋዛ ፈዛዛ ሳቅ ስላቅ ከበዛበት፣  ፌዝና ተረብ ከነገሠበት ነገር ራሱን በማራቅ ከዋዛ ፈዛዛ ይልቅ በሥራ መትጋትና ኃላፊነትን በአግባቡ መወጣት ለታላቅነት እንደሚያበቃ በመረዳት ትኩረቱን ሥራው ላይ ያደርግ ነበር፡፡  በዚህም በደረሰበት ሥፍራ ሁሉ እግዚአብሔር ከፍ ከፍ ያደርገው ነበር፡፡  ፍጻሜው የሚያምር ስኬት ላይ ለመድረስ መሠረቱ እግዚአብሔርን መፍራት እንደሆነ የተነገረው ለዚህ ነው፡፡  ዮሴፍ በተደላደለው መንገዱ ከጲጥፋራ ሚስት እግዚአብሔርንም እንዲያሳዝን ለመገፋፋት በዝሙት እንደተፈተነ ሊቀ ነቢያት ሙሴ በዘፍጥረት መጽሐፍ ጽፎልናል፡፡ (ዘፍ. ፴፱፥፰-፱)
እግዚአብሔርን በጉብዝናው በማሰብ ከእግዚአብሔር ጋር ይኖር ስለነበረ ዮሴፍ እንቢ ለኃጢአት አለ፤ ‹‹እነሆ ጌታዬ (አለቃዬ)  በቤቱ ያለውን ምንም ምን የሚያውቀው የለም፡፡  ያለውንም ሁሉ ለእኔ አስረክቦኛል፤  ለዚህ ቤት ከእኔ የሚበልጥ ሰው የለም፤  ሚስቱ ስለሆንሽ ከአንቺም በቀር ያልሰጠኝ ነገር የለም፤  እንዴት ይህን ትልቅ ክፉ ነገር አደርጋለሁ? በእግዚአብሔር ፊት እንዴት ኃጢአትን እሠራለሁ?›› እንዲል፤ (ዘፍ. ፴፱፥፰-፱)
ዛሬ የሰውን ሚስት የሚያባልጉ በሐሰትና በሚያሳስት ንግግር ወደ ዝሙት የሚወስዱ ይህንንም እኩይ ግብራቸውን እንደ ጀብድና ጀግንነት የሚቆጥሩ ወጣቶች መብዛታቸውን ስንመለከት የቅዱስ ዮሴፍ ታላቅነትና እግዚአብሔርን መፍራት እንደሚጎድላቸው እንረዳለን፡፡ ዮሴፍ ሕግ ባልተሰጠበትና ሰዎች በሕገ ልቡና በሚመሩበት በዚያ ዘመን የዝሙትን አስከፊነት መጽሐፍ ሳይጠቀስለት በትውፊት ከአባቶቹ ተምሮ ከዝሙት ሸሸ፡፡  ለራሱም፣ ለአለቃውም፣ ለፈጣሪውም የታመነ መሆኑን በተግባር አስመሠከረ፡፡ የዛሬ ወጣቶች ለምንሠራበት ተቋም፣ ለአለቃችን፣  ለጓደኛችን ታማኞች ነን? የአደራ ጥብቅነት ከሰማይ ርቀት ጋር ተነጻጽሮ በሚነገርበት ማኅበረሰብ መካከል አድገን ታማኞች መሆን አለመቻላችን ምክንያቱ ምን ይሆን? ዮሴፍ ዓለም በኃጢአት ስትፈትነው በወጥመዷ ላለመያዝ እግዚአብሔርን አስቧልና በሐሰት ወንጅለውና ወደ ወህኒ እንዲጣል አድርገው ለመከራ በዳረጉት ጊዜ እግዚአብሔርም እርሱን አሰበው፡፡  በወጣትነት ዘመን እግዚአብሔርን ማሰብ የጉልምስናና የሽምግልና ብሎም ከሞት በኋላ ለሚኖረውም ሕይወት ዋስትና በመሆኑ ጠቢቡ ሰሎሞን ‹‹አፈርም ወደ ነበረበት ምድር ሳይመለስ፥ ነፍስም ወደ ሰጠው ወደ እግዚአብሔር ሳይመለስ ፈጣሪህን አስብ›› ብሎ አስተማረ፡፡ (መክ.፲፪፥፩)
በዓለም ላይ ያሉ ማናቸውንም ነገሮች ያለማቋረጥ ማሰብ አንዱ የሥነ ልቡና ሕመም መነሻ መሆኑን ባለሙያዎቹ ይናገራሉ፡፡  ስለ ባለጠግነት ብቻ የሚያስብ ሰው ሐሳቡ ሳይሳካለት ቀርቶ በድኅነት ቢኖር ወይም ደግሞ ማግኘቱ ተሳክቶለት ዳግም ቢቸገር በሁለቱም ይጎዳል፡፡ የጤናን ነገር ሁሌ በማሰብ የሚኖር ሰው ሕመም በጎበኘው ጊዜ ይፍገመገማል፡፡  ደስታን ብቻ የሚያስብ ሰው ኃዘን በገጠመው ጊዜ ቆሞ መራመድ ያዳግተዋል፡፡ ማግኘትን ብቻ የሚያስብም ማጣትን አይቋቋምም፡፡ እግዚአብሔርን ያለማቋረጥ ሲሔዱም ሲቀመጡም፣ሲበሉም ሲጠጡም፣ ሲሠሩም ሲያርፉም ማሰብ ግን ሕይወትም፣ ጤናም፣ የደስታም ምንጭ ነው፡፡

እግዚአብሔርን ማሰብ – መልካም ነገርን መናገር

ማሰብ ከመናገር ጋር የአንድ ሳንቲም ገጽታ ነው፤ ሰው የሚናገረው ያሰበውን ነውና፡፡  ማሰብና መናገር ያላቸውን አንድነት ልበ አምላክ ነቢዩ ዳዊት ከተናገረው ኃይለ ቃል መረዳት ይቻላል፡፡  ‹‹አቤቱ በድንኳንህ ውስጥ ማን ያድራል? በተቀደሰውም ተራራህ ማን ይኖራል? በቅንነት የሚሄድ ጽድቅንም የሚያደርግ፣ በልቡም እውነትን የሚናገር›› በማለት የተናገረውን ቃል እናስተውል፡፡ ሰው በልቡናው ያስባል እንጂ አይናገርም፤ ሆኖም ግን በአንደበት የሚነገረው በልቡና የታሰበ ነውና በልቡም እውነትን የሚናገር ብሎ ተናገረ፡፡ (መዝ. ፲፬፥፩-፪)

ሕማማት ዲ/ን ሔኖክ ኃይሌ

14 Nov, 06:18


በምንመራው ኦርቶዶክሳዊ እውነተኛ ኑሮ ሕይወትን በተወሳሰበ እና ለዓለም በሚመች መልኩ ማድረግ ጣጣው ብዙ ነው፡፡ እኛ እንድንኖር የተፈቀደልን ሕይወት ጸሎት ያጀበው ሕይወት፣ የፍቅር ሕይወት፣ ለጎረቤቶቻችን ለወንድሞቻችንና እኅቶቻችን መልካም ነገርን የማድረግ ሕይወት ከምንም በላይ ለነፍሳችን ድኅነት የሚጠቅመንን ሥራ የመሥራት ሕይወት ነው፡፡ ንቁ ሆነን፣ አለባሰሳችን እንደ ሃይማታችን ሥርዓት ሆኖ፣ ለጸሎት የነቃን፣ የታጠቅን መሆን ይኖርብናል፡፡ እግዚአብሔር አምላክን በቃልም ቢሆን በተግባርም ቢሆን በኀልዮም ቢሆን የሠራነውን ኃጢአት ይቅር ይለን ዘንድ መትጋት ይጠበቅብናል፡፡ እግዚአብሔር ዘወትር በሥራው ከእኛ ጋር ይሆን ዘንድ ይህ የአንድ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ተከታይ የዘወትር ጸሎት ነው፡፡ መሻቱም፣ ፈቃዱም ፣ ውዱም ሁሉም ተጠቅሎ ያለው በዚያ ውስጥ ነው፡፡ መነሻውም መድረሻውም የጸሎት እና የምስጋና ሕይወት ነው፡፡

በዚህ መንገድ የሚኖር ኦርቶዶክሳዊ ወጣት፡- ሕይወቱ ለአንድ የተስተካከለ እና ጤናማ ሕብረተሰብ መኖር ምሰሶ ነው፡፡ የማኅበረሰብ ፍትኅ፣ ደስታ እና ሰላም የሚጠበቀውም በእንዲህ ዓይነት መንገድ አልፈው ማኅበረሰቡን በሚያገለግሉ ወጣቶች እንጂ አፈ ጮሌዎች ፣ ስግብግቦች እና ነገር አዋቂዎች አይደለም፡፡ እንዲህ ዓይነት እዩኝ እዩኝ የሚሉ ከንቱ ሰዎች ማኅበረሰብን መርተው ወደሚፈልገው ዕድገት አያሻግሩም፡፡

ሀብት አስፈላጊ ቢሆንም ኦርቶዶክስ ክርስቲያን የሚኖረው ሀብት ለማግበስበስ፣ ሌሎችን ለመቀማት ወይም ለማስቀናት አይደለም፡፡ ሀብትን ከፈለግነው በአባቶቻችን በእናቶቻችን መንገድ በርግጥ በእውነት እና በቅንነት ብንመላለስ የሚመጣ እንጂ የሚርቅ ነገር አይደለም፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ በመጀመሪያ ጽድቁን እና መንግሥቱን ሹ፤ ሥጋን ለሥጋ ነገር ማለማመድ ለአሁኑ ጊዜ ይጠቅማል፤ ሥጋን ለመንፈሳዊ ነገር ማለማመድ ለአሁኑ ጊዜ ለሚመጣውም ጊዜ ይጠቅማል ይላል፡፡

የሚገጥመን ተግዳሮት

በመንፈሳዊ ልምምድ ሳለን የሚገጥመን ተግዳሮት ቀላል አይደለም፡፡ ጠላታችን ዙሪያችንን ይዞራል፡፡ ወጥመዱን ይዘረጋል፡፡ የአጋንንትን ትምህርት በሚያስተምሩ ሰዎች ልባችንን ለመክፈል እንዲሠሩ ያደርጋል፡፡ ነገሮች ለእነርሱ አልጋ በአልጋ ሲሆኑ ለጊዜው ሁሉም ነገረ የተሳካላቸው አስመስሎ፤ የሌለ ነገር እንዳለ አድርጎ ማሣየት የአጋንንት ተግባር ነው፡፡ ከእውነተኛው ሃይማኖታችን ለማስወጣት የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም፡፡ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታይ በመሆናችን ሃይማኖታችንን የድኅነት ምንጭ፣ ስብከታችንንም ከንቱ አድርጎ ሊስል ይዳዳዋል፡፡ በእምነት የቀደሙንን ቅዱሳን፤ አሠረ ፍኖት ትተውልን የሄዱ ዋኖቻችንን ድካም ከንቱ ድካም አድርጎ ለመሳል የማይሄድበት ርቀት የለም፡፡ ረብህ የሌላቸውም ምናምንቴ ሰዎች በገበያ እና በፕሮሞሽን ወደፊት አውጥቶ ሰዎች እንዲከተሏቸው ያደርጋል፡፡ የዲያብሎስ ወጥመዱ ብዙ ነው፡፡

የቅዱስ ጳውሎስ ምክር “በቃልና በኑሮ በፍቅርም በእምነትም በንጽሕናም ለሚያምኑት ምሳሌ ሁን እንጂ ማንም ታናሽነትህን አይናቀው፤ እስክመጣ ድረስ ለማንበብና ለመምከር ለማስተማርም ተጠንቀቅ፡፤( ፩ኛ ጢሞ. ፬፥፲፪) የሚል ነው፡፡ ፍቅራችን፣ ራስን መግዛታችን በቃልም በኑሮም ከተገለጠ የወጣትነት ሕይወታችን እጅግ ጣፋጭ፣ ተወዳጅ እና ፍሬ የሚያፈራ ይሆናል፡፡ በእንዲህ ዓይነት የተቀደሰ ሕይወት ስንመላለስ ፈተና ቢገጥመን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እኛ ሲል የተቀበላቸው በርከት ያሉ መከራዎችን እናስብ፡፡ እርሱን በመልበሳችን ምክንያት ወደ እኛ የመጡ መከራዎች መሆናቸውን በማሰብ ዕለት ዕለት በፈተና እንጸና ዘንድ ሳናቋርጥ እንጸልይ፡፡ ጸሎታችንም መንፈሳዊ ድፍረትን፣ ጥበብን ፣ ማስተዋልን፣ ሰላምን፣ ትዕግሥትን፣ ፍቅርን፣ ትሕትናን በጎ ጤንነትን፣ ሀብትን፣ ረጅም የአገልግሎት ዕድሜን ይሰጠን ዘንድ ነው፡፡ ይቆየን፡፡

ሕማማት ዲ/ን ሔኖክ ኃይሌ

14 Nov, 06:18


ከኦርቶዶክሳዊ ወጣት ምን እንጠብቅ?
ዲ/ን ታደለ ፈንታው(ዶ/ር)

ክፍል አንድ

ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖታችን የደም ዋጋ ተከፍሎበት፤ ተፈትኖ፣ ነጥሮ፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ ተሸጋግሮ በቅብብሎሽ የመጣ እውነተኛ ሃይማኖት ነው፡፡ የዓለማውያን ፍልስፍና፣ ተረት ተረት፣ ድርሰትም፣ የታዋቂ ሰዎች ድንገተኛ ፈጠራም አይደለም፡፡

ቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ ደም ላይ ተመሥርታለች እና ተጠብቃ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንድትሸጋገርም ወጣቶች የከፈሉት ዋጋ ደማቅ በሆነ በደም ቀለም በቤተ ክርስቲያናችን ቅዱሳት መጻሕፍት የተመዘገበ ነወ፡፡ እንደ ምሳሌም ሊቀ ዲያቆናት ቅዱስ እስጢፋኖስን ማንሣት እንችላለን፡፡ ራሱን ለእግዚአብሔር አሳልፎ በመስጠቱ አይሁድ በድንጋይ ሲወግሩት ሰማያት ተከፍተው የእግዚአብሔርን ዙፋን እስከ ማየት አድርሶታል፤ ምሥጢርም ተገልጦለታልና አቤቱ ይህን ኃጢአት አትቁጠርባቸው” እስከ ማለት አደረሰው፡፡ የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም ወጣቶች አርአያ ሊያደርጉት ይገባል፡፡ (ሐዋ. ፯፥፶፬-፷)

ከአባቶቻችን፣ ከእናቶቻችን የተቀበልነውን ይህንን የደም ዋጋ የተከፈለበትን እውነተኛ ሃይማኖት እንደ ወጣት በምንኖርበት ዘመን የመጠበቅ፣ የመከላከል፣ የብዙዎች መዳንን የሚሹ፣ በእውነተኛው መንገድ ለመጓዝ የፈቀዱ ሰዎችን እንዲያውቁት፣ እንዲገነዘቡት፣ በሥጋቸውም በነፍሳቸውም እንዲጠቀሙበት ማድረግ የአንድ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ተከታይ ወጣት የሃይማኖት ግዴታ ነው፡፡ እምነታችንም የሚገለጠው ዕለት ዕለት በማኅበረሰቡ መካከል ስንመላለስ በምናሳየው የማይለዋወጥ ባህርይጥሩ ሥነ ምግባር አማካኝነት ነው፡፡ የእኛ ጽናት፣ አቋም፣ ጥንካሬ፣ መንፈሳዊ ሕይወት የሃይማኖታችንን እውነተኛነት ይገልጣል፡፡ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታይ የክርስቶስ መልክ የሚታይበት ሰው ነው፡፡ በክርስቶስም የእግዚአብሔር መልክ በእርሱ ላይ ታትሟልና፡፡

በምንኖርበት ሉላዊ ምድር በዓለም ላይ እንደሚኖር ሰው ተግዳሮቶች አሉብን፡፡ እኒህ ተግዳሮቶች ታስበው ታቅደው እንደሚሠሩ ሁሉ ሰው በመሆናችን፣ ሉላዊውን ዓለም በመጋራታችን ጭምር የሚመጡ እንጂ ክርስቲያን በመሆናችን ምክንያት ብቻ ተለይተው የሚመጡ አይደሉም፡፡ ክርስትናን ለመቃወም ታስበውም ሆነ ሳይታሰቡ የሚወጡ አፋኝ ሕጎች፤ የሉላዊነት ተጽእኖ፣ ኤችአይቪ ኤድስና ሌሎች ተላላፊ በሽታዎች፤ ድህነት፣ የደኅንነት ስጋት፣ ዘረኝነት፣ ያልተስተካከለ እና ሕይወትን የማያሻሽል መሠረቱን አገር በቀል እውቀትን ያላደረገ የተኮረጀ ትምህርት እና የመሳሰሉት ተግዳሮቶች ለአብነት ይጠቀሳሉ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በገላትያ መልእክቱ ሲያስተምር እንዲህ ብሏል፡- “እናንተ ለአርነት ተጠርታችኋልና ፤ ብቻ አርነታችሁ ለሥጋ ምክንያትን አይስጥ፤ ነገር ግን በፍቅር እርስ በርሳችሁ እንደ ባሪያዎች ሁኑ፤ ሕግ ሁሉ በአንድ ቃል ይፈጸማልና እርሱም ባልንጀራህን እንደራስህ አድርገህ ውደድ የሚል ነው፡፡ ነገር ግን እርስ በርሳችሁ ብትነካከሱና ብትበላሉ እርስ በርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ፡፡” እንዲል(ገላ 5፡13)

ፍቅር የእምነታችን እና ጽናታችን መሠረት

እንደ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማኝ ተከታይ የእምነታችን ታላቅነት የሚገለጠው ለሌሎች በሚኖረን ፍቅር እና አክብሮት ላይ ነው፡፡ ሕግ ሁሉ በሁለት ምሰሶዎች ላይ የቆመ ነው፡፡ እነርሱም ፍቅረ እግዚአብሔር እና ፍቅረ ቢጽ(የወንድም ፍቅር) ናቸው፡፡ ሰው የሚመለከተውን ወንድሙን፣ የሚመለከታትን እኅቱን የማይወድ ከሆነ የማይመለከተውንና ያላየውን እግዚአብሔርን መውደድ እንደምን ይቻለዋል? ስለዚህ ፍቅራችን በሰው እና በእግዚአብሔር መካከል የቆመች እውነተኛ የሃይማኖታችን መገለጫ ምልክት ናት፡፡ እኛም እውነተኛ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደመሆናችን፤ በቅዱሳት መጻሕፍትም መሠረትነት ላይ ልንጓዝ ግድ ይለናል፡፡

የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መገለጫው ፍቅር ደስታ፣ ሰላም፣ ቸርነት በጎነት የዋህት፣ ራስን መግዛት(ገላ. ፭፥፳፪) እንጂ ዝሙት ርኩሰት ፣ መዳራት፣፣ ጣዖትን ማምለክ ምዋርት፣ ጥል፣ ክርክር፣ ቅንዓት፣ ቁጣ አድመኛነት፣ መለያየት፣ መናፍቅነት፣ ምቀኝነት መግደል ስካር ዘፋኝነት (ገላ. ፭፥፳) አይደለምና በቀደሙ በአባቶቻችን የፍቅር መንገድ እንጓዝ፡፡

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “መልካሙን ሥራችሁን ተመልክተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን ያመሰግኑ ዘንድ ብርሃናችሁ በሰው ሁሉ እንዲሁ ይብራ” እንዳለ(ማቴ ፭፥፲፫) ከውኃና ከመንፈስ ዳግም ስንወለድ ሀብተ ጸጋ ሀብተ ልጅነት ሆነው የተሰጡን መንፈሳውያን ሀብቶቻችን ይገለጡ ዘንድ ብርሃናችን በዓለሙ ሁሉ ይብራ፡፡ እነዚህም አስቀድመን የገለጥናቸው ናቸው፡፡ ፍቅር የእግዚአብሔር ገንዘብ ነው፡፡ ፍቅር እግዚአብሔርን የምናውቅበት ፍኖት ነው፡፡

ፍቅር እግዚአብሔር የፈጠረውን ፍጥረት፣ ሰው፣ እንስሳ ሳንል የምንወድበት መሳሪያ ነው፡፡ ፍቅር ተፈጥሮአችንን የምናድስበት ነው፡፡ ፍቅር ጉድለታችንን የምንሞላበት መዝገብ ነው፡፡ ፍቅር የተጣመመን ሰብእና የምናርቅበት መዶሻ ነው፡፡ ፍቅርን ተከትለው የሚመጡ ሌሎች ሀብታት አሉ እንጂ ፍቅር ብቻውን የሚመጣ አይደለም፡፡ ፍቅር፡– ሰላምን፣ ደስታን ያስከትላል፡፡ ርኅራኄ እና ለጋስነት ያጅቡታል፡፡ ፍቅር ማደሪያውን ትሕትናን እና ራስን መግዛትን ያደርጋል፡፡

እንደ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት አማኝ የሚጠበቅብን ብዙ ነገር አለ፡- አስቀድመን በገለጽናቸው መንፈሳዊ ሀብታት መኖር እና ማደግ ዕድገታችንም ዕለት በዕለት ያለ ድካም፣ ያለ ፍርሃት፣ የሚጨምር ሊሆን ይገባዋል፡፡ እነዚህን ሀብታት ሳንታክት ገንዘብ ልናደርጋቸው የሚገቡ ጠቃሚ ሀብታት ናቸው፡፡ በእነዚህ ሀብታት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንደተናገረ ክርስቶስን እንለብሰዋለን፡፡ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደሶችም ተብለን በእውነት ልንጠራ የተገባን እንሆናለን፡፡

ሌሎች ሊኖሩን የሚገቡ ዕሤተ ምግባራት

እንደ ክርስቲያን በሕዝብ እና በአሕዛብ መካከል የምንመላስ የክርስቶስን እውነት የምንመሰክር ደምቀን የምንታይ አጥቢያ ኮከቦች ነን፡፡ አጥቢያ ኮከብ ደምቆ፣ ፈክቶ እና አብርቶ ስለሚኖር ለሁሉ እንደሚታይ እውነተኛ ክርስቲያንም በሰው ሁሉ ፊት የተገለጠ ነው፡፡ የበለጠ ደምቀን እንድንታይ የሚያደርጉን ኦርቶዶክሳዊ ዕሤተ ምግባራት አሉ፡ እነርሱም፡- አርምሞ፣ ሥርዓት፣ ሰላማዊ ኑሮ፣ ዕውቀት፣ ማስተዋል፤ በሕዝብ ተገብቶ ራስን አሳልፎ መስጠት፣ ከግለኝነት መጽዳት፣ በሰዎች ጉዳይ ጣልቃ አለመግባት፣ እና እኒህን የመሳሰሉ ናቸው፡፡ ልንታገሳቸው የማይገቡንም ነገሮች አሉ፡፡ እነርሱም፡- ሞራል ማጣት፣ የነፍስን ቅድስና ገንዘብ አለማድረግ፤ ጣዖትን ማምለክ፣ ጥንቆላ እና ተያያዥ ተግባራትን መውደድ፣ ምቀኝነትን አለመጥላት፣ ጠብንና አምባጓሮን መውደድ፣ ከቁጣ ነጻ አለመሆን፣ በተሰጠን ነገር አለመርካት፣ ራሳችንን ከሌሎች ጋር ማነጻጸር እና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ አስቀድመን የዘረዘርናቸውን ነገሮች የምንጠላቸው በሥጋችን ሥቃይን የሚጨምሩብን በነፍሳችንም የሚያስጎዱን እንጂ የሚጠቅሙን ባለመሆናቸው ነው፡፡

በእውነት መንገድ የሚኖር ኦርቶዶክሳዊ ወጣት፡-

ሕማማት ዲ/ን ሔኖክ ኃይሌ

12 Nov, 16:49


መልስ
የሰንበት ቂጣ ሃይማኖታዊና
ትውፊታዊ አንድምታ ምንድን ነው???
በቤተ ክርስቲያን የሚፈጸሙና የሚከናወኑ መንፈሳዊ ተግባራት ሃይማኖታዊ ሥርዓታዊና ትውፊታዊ መነሻ ያላቸው ሰዎችን ወደ ድኅነት የሚያደርሱና የሚያሸጋግሩ ናቸው።

ወደ ጥያቄ ስመጣ የሰንበት ቂጣ ሃይማኖታዊና ትውፊታዊ አንድምታው እንዴት ነው ስንል! በብሉይ ኪዳን ጀምሮ ቤተ እግዚአብሔር (ምኩራብ) ይመጡ የነበሩ ኦሪታውያን (እስራኤል) ያከናውኑት የነበረ ሃይማኖታዊ ትርጉም ያለው ተግባር ነው።
በኋላም በሐዲስ ኪዳን ዘመን
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሚያስተምርበት ጊዜ ሲማር የዋለው ሕዝብ ትምህርቱን ሰምቶ ወደ ቤቱ ለመሄድ ከመሰናበቱ በፊት ደቀ መዛሙርቱ ቀርበው ያለንበት ቦታ ምድረ በዳ ነውና ሰዓቱም አልፏልና በጊዜ ወደ ከተማ ሂደው ምግባቸውን ገዝተው ይመገቡ ባሉት ጊዜ ጌታ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው። “አኮ መፍትው ርኁባኒሆሙ ይሑሩ አላ ሀብዎሙ አንትሙ ዘይበልዑ፦ (በመሸም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው፦ ቦታው ምድረ በዳ ነው አሁንም ሰዓቱ አልፎአል፤ ወደ መንደሮች ሄደው ለራሳቸው ምግብ እንዲገዙ ሕዝቡን አሰናብት፡ አሉት። ኢየሱስም፦ እናንተ የሚበሉትን ስጡአቸው እንጂ ሊሄዱ አያስፈልግም፡ አላቸው። (ማቴ.፲፬፡፲፭) ይላል።

ያንን መነሻና ምክንያት በማድረግ ዛሬም ሥጋውን ደሙን የተቀበሉ ምእመናን ከቅዳሴ በኋላ በቤተ ክርስቲያን እንዲመገቡት የሚዘጋጅ መክፈልት ነው።

የሰንበት ቂጣ የአዘገጃጀት ሥርዓት?
የሚያዘጋጁትና ማዘጋጀት ያለባቸው በእድሜ ገፋ ያሉ መነኮሳይያት እናቶች ሙቀት ልምላሜ የተለያቸው፤ ደም ያደረቁ፤ ጭምቶች የሆኑ ለሌላው አርአያና ምሳሌ መሆን የሚችሉ ነውር ነቀፋ የሌለባቸው መነኮሳይያት ናቸው።

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለሚወደውና በመንፈስ ለሚልደው ለደቀ መዝሙሩ ለጢሞቴዎስ ምን ዓይነት ዲያቆናይትን መሾም እንዳለበት ጽፎ በላከለት መልእክቱ ላይ እንዲህ ብሎታል፦ “ባልቴት በመዝገብ ብትጻፍ ዕድሜዋ ከስድሳ ዓመት እንዳያንስ፥ የአንድም ባል ሚስት የነበረች እንድትሆን ያስፈልጋል።
ልጆችን በማሳደግ እንግዶችንም በመቀበል፥ የቅዱሳንንም እግሮች በማጠብ፥ የተጨነቁትንም በመርዳት በጎንም ሥራ ሁሉ በመከተል፥ ይህን መልካም ሥራ በማድረግ የተመሰከረላት ልትሆን ይገባል”። (፩ጢሞ.፭፡፱) ብሎ የሚመርጥበትን መስፈርት አስቀምጦለታል፤ በዚህ መንገድ እንደነዚህ ያሉ እናቶች እንዲያዘጋጁ ይደረጋል።
ነገር ግን በዚህ የዕድሜ ደረጃና መዓርግ የደረሱ ቢታጡና ቢጠፉ ግን ክብረ ንጽሕናቸውን የጠበቁ፣ በድንግልናቸው የታወቁ፣ ጥሩ ስነ ምግባር ያላቸው ደናግል ሴቶች ሊመረጡና የሰንበት ቂጣውን ሊጋግሩ ይችላሉ።
ከመ/ር ፍሬስብሐት ካሳ

ሕማማት ዲ/ን ሔኖክ ኃይሌ

10 Nov, 19:19


የምስራች

እነሆ በTikTok በYoutube እናበተለያዩ ሶሻል ሚዲያዎች የምናውቀው ወንድማችን ልጃችን መምህራችን ዲያቆን ዘላለም ታየ በቴሌግራም መጥቷል ትምህርቶችን እንዲሁም እርሱ የሚጽፋቸውን ጦማሮች እንከታል ለህይወት ስንቅ ናቸውና::

Link👉https://t.me/dn_zelalem_taye

ሕማማት ዲ/ን ሔኖክ ኃይሌ

10 Nov, 18:15


ጭንቀት ~ምን ያህል ከአምላክ መንፈስ እንደራቅን የሚጠቁም ስሜት ነው::

ሰላም ~ ምን ያህል ወደ አምላክ መንፈስ እንደቀረብን የሚናገር ስሜት ነው::

ከፈጠረን አምላክ አስበልጠን ሌላ ነገር ስንፈልግ በውስጣችን ጭንቀት ይፈጠራል::በልባችን ፍርሃት እና ውጥረት ያድራል::

ከሁሉም ነገር አብልጠን የአምላክን መንፈስ ስንፈልግ ሰላም በውስጣችን ይወለዳል::ልባችን በፍቅር እና በደስታ ይሞላል::

ዓለም እና ነገሮቿን ሁሌም ከእኛ ጋር ማድረግ አንችልም::ሰው ..ገንዘብ …ስልጣን ….ዝና እና ወ.ዘ.ተ ምንም ጊዚያዊ ደስታን ቢሰጡም ቶሎቶሎ የመቀያየር ጠባይ አላቸው::ያዝናቸው ስንል ይሄዳሉ::

የማይሄደው እና ምንጊዜም በልባችን የሚኖረው እኛንም እስከመጨረሻ የሚወደን ቅዱሱ የእግዚአብሄር መንፈስ ብቻ ነው::

ገንዘብ ብናገኝ ብናጣ ~ሰው ቢፈልገን ባይፈልገን ~
ጤና ቢኖረን ባይኖረን በቅፅበት በሚለዋወጠው አለም ሁሌም የማይቀያየር አምላካችን ብቻ ነው::

ይህንን አምላክ ከዓለም ያስቀደሙ አለምን ያሸንፋሉ::ለከንቱ ምኞት ውድ ነፍሳቸውን አይሰጡም::በጊዜያዊ ደስታ ዘለዓለማዊውን አምላክ አይለውጡም::
በሚለዋወጠው ዓለም የማይለዋወጥ ግንኙነት ከአምላክ ጋር አድርገዋል::ከጊዚያዊው አብልጠው ዘለዓለማዊውን መርጠዋል::

እርሱ የእውነት መታመን የሚቻልበት ወዳጃቸው ነው::ጥበብ ~ፍቅር ~ሀይል ~ስልጣን ~በረከት ~ሀብት እና ሁሉም ነገር አለው::

ወደዚህ መልካም አምላክ ስንቀርብ እርሱም ወደ እኛ ይቀርባል::ሰላሙንም በልባችን ያኖራል::ጭንቀት እና ፍርሃታችን ይወገዳል::

ሕማማት ዲ/ን ሔኖክ ኃይሌ

08 Nov, 05:01


አህያና ግርዛት

አሁን ሐዲስ ኪዳን ነው:: መገረዝ ግዴታ አይደለም:: ዋናው ጥምቀት ነው:: ባንገረዝ ምንም አይጎድልብንም::  በዚህ ጉዳይ በመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን ውዝግብ ተነሣ:: አሕዛብ ሳይገረዙ ኖረዋልና ጸረ ግዝረት ሆኑ:: አይሁድ ደግሞ እንዴት ግዝረት እንተዋለን አሉ::

ወደ ክርስትና የተጠሩት እነዚህ ሁለት ወገኖች ሁለቱም ከራሳቸው አመጣጥ አንጻር እውነት አላቸው:: አሕዛብ የማያውቁትን ነገር መቀበል ሊገደዱ አይችሉም:: ክርስትናም አላስገደዳቸውም:: አይሁድ ደግሞ የኖሩበትን መተው አይችሉም:: ክርስትናም ግዝረትን ባይጠይቅም አልከለከለም::

በመጨረሻ በብዙ ምክር የሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን አሕዛብንም ያላገለለ እስራኤልንም ያላቃለለ ውሳኔ ወሰነች:: ውሳኔውን በጥሩ ቃል በመልእክቱ ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ሲል ገልጾታል::

"ማንም ተገርዞ ሳለ ተጠርቶ እንደ ሆነ፥ ወደ አለመገረዝ አይመለስ፤ ማንም ሳይገረዝ ተጠርቶ እንደ ሆነ አይገረዝ። ... እያንዳንዱ በተጠራበት መጠራት እንደዚሁ ይኑር" 1 ቆሮንቶስ 7:18፣ 20

በዚህ መሠረት ኦሪትን ተቀብለው ተገርዘው ወደ ክርስትና የተጠሩት እስራኤል በመገረዛቸው ይቀጥሉ እንጂ ወደ አለመገረዝ አይመለሱ ተባለላቸው:: ሳይገረዙ የተጠሩት አሕዛብ ግን መገረዝ የእነርሱ ልማድ አልነበረምና አይገረዙ ተባለ:: ይህ ለእስራኤል የተወሰነ ውሳኔም እንደ ኢትዮጵያ ኦሪትን ተቀብላ ለኖረችና ተገርዛ ሳለ የተጠራች (ሐውልቶችዋ ሳይቀር የተገረዘ ወንድን የሚያሳዩባት) ሀገርም ላይ ይጸናል::

ይህ ውሳኔ ለሁሉም እንደ ግዝረት ያሉ ሕግጋት ይሠራል::

"ማንም ተገርዞ ሳለ ተጠርቶ እንደ ሆነ፥ ወደ አለመገረዝ አይመለስ፤ ማንም ሳይገረዝ ተጠርቶ እንደ ሆነ አይገረዝ"

"ማንም አህያ እየበላ ተጠርቶ እንደ ሆነ አህያ ወዳለመብላት አይመለስ ፤ ማንም አህያ ሳይበላ ተጠርቶ እንደሆነም አህያ አይብላ"
(የአህያን ስም በአሳማ በአይጥ በውሻ ወዘተ እየቀየሩ ዐረፍተ ነገር ይሥሩ:: ሃሳቡ ያው ነው) ግዝረትም የማይበሉ ምግቦችም ከ613 የአይሁድ ሕግጋት (The 613 Mitzvot) ውስጥ ናቸው::

እስራኤል በግዝረት ቀጥሉ ሲባሉ ደስ አላቸው አሕዛብም አትገረዙ ሲባል ደስ አላቸው:: ለእስራኤል ሔደህ የአሕዛብን ዜና ብትነግራቸው ምንም እንኩዋን ግዝረት ግድ ባይሆንም ቅር ይላቸዋል:: የአህያ መበላት ዜናም የሚያስደስተው አህያን እንዴት ልንተው እንችላለን ብለው ለተጨነቁ አሕዛብ ብቻ እንጂ ለእኛ ሆድ የሚበጠብጥ ዜና ነው::

ከዚያ ውጪ እንደ ክርስቲያን ብሉ ብለን ልንሰብከው የሚገባን የሕይወት እንጀራ ሥጋ ወደሙ ብቻ ነው::

እያንዳንዱ በተጠራበት መጠራት ይኑር!

ዲ/ን ሄኖክ ኃይሌ
2017 ዓ.ም.
አዲስ አበባ  ቄራ (የበሬ)

"ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፥ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ" ኤፌሶን 4:29

ሕማማት ዲ/ን ሔኖክ ኃይሌ

07 Nov, 16:59


👆👆👆 ጠቃሚ ምክር!

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ "ለደካሞች ትጉላቸው " ብሎ በተናገረው መሠረት ምንጊዜም የሰዎችን ሞራልና መንፈስ ለመጠበቅ እንሞክር። [1ኛ ተሰ 5*14]  አንድን ሰው ሲቆጡት፤ ሲወቅሱትና ፤ትህትናን ሲነፍጉት ብትመለከቱት እርሱን ከጎናችሁ አድርጋችሁ የሚገባውን በእርሱ ስም ተናገሩለት። በእርግጥም ይህ ሰው ይህንን ታላቅ ሥራችሁን በእድሜው ዘመን ሙሉ አይረሳውም። ይህ ማለት ደግሞ በፍቅርና በቸርነት በተሞሉ ታታላላቅ ልቦናዎች መንፈሳቸው ለደከመ ሰዎች የተደረገ ታላቅ ሥራ ነው። በኃጢአት የተተበተበ አንድ ሰው ብታገኙ ከዚህ ነፃ አውጡት እንጂ አትገስጹት።

  በአንድ ወቅት አንድ ወጣት ልጅ የገባበት ውኃ ሊያሰጥመው ሲል ራሱን ለማዳን በመፍጨርጨር ላይ ሳለ በዚያ የሚያልፍ አንድ ሰው "ልጄ ሆይ ዋና ሳትችል እንዴት እዚህ ባሕር ውስጥ ልትገባ ቻልክ! ?" እያለ ሲቆጣው ልጁ "በእርግጥ ተሳስቻለሁ ወደዚህ ባሕር የገባሁበትን ምክንያት እንድነግርህ ግን በመጀመሪያ ከሞት አድነኝ " ብሎ መልሶለታል። እናንተም ልክ እንደዚህ ሰውዬ መሆን የለባችሁም። ማንንም ሰው ሲወድቅ ብትመለከቱት አትገስጹት ይልቁንም። ተስፋ ስጡት። " እኔ ብዙ ጠቃሚ ምክሮች መክሬሃለሁ አንተ ግን አልተጠቀምክባቸውም ስለዚህ ከባድ መከራ ቢደርስብህ አይቆጨኝም " ብለን አንናገር።

   የሐዋርያው ቃል በንቃት አድምጡ። "...... ለደካሞች ትጉላቸው ሰውን ሁሉ ታገሱ" [1ኛ ተሰ 5*14] ። ሥሩን የሰደደ ኃጢአትን ነቅሎ ለመጣል ጊዜና ትዕግስት ስለሚጠይቅ እግዚአብሔር እንደነዚህ ያሉትን ደካሞች በጸጋው እስኪጎበኛቸው ነጻ እስኪያወጣቸው ድረስ ትዕግስት አድርጉላቸው። አንተም ተፈጥሮህ ከእነርሱ ጋር ተመሳሳይ ስለሆነ ከዚህ የሚከተለውን የሐዋርያውን ቃል ዘወትር ከፊትህ አስቀድም። " ከእነርሱ ጋር እንደ ታሰረ ሆናችሁ እስሮችን አስቡ የተጨነቁትን ደግሞ ራሳችሁ ደግሞ በሥጋ እንዳለ ሆናችሁ አስቡ ።[ዕብ 12*3] ።
  #የእግዚአብሔርን_ሕዝብ_ተስፋ_ለማስቆረጥ_የተጉትን_ሰዎች_እግዚአብሔር_ወደ_ተስፋይቱ_ምድር_እንዲገቡ_አልፈቀደላቸውም።
እግዚአብሔር ሕዝቡን ".....በኃይል ከእኛ ይበረታሉና በዚህ ሕዝብ ላይ መውጣት አንችልም...... ያየናቸው ሰዎች ሁሉ ረጃጅም ሰዎች ናቸው. .... እኛም በዓይናችን ግምት እንደ አንበጣዎች ነበርን " በማለት ሊያዳክሙት የነበሩትን ሰዎች ገድቧቸዋል ። [ዘኁ13*31-33]።
  እናንተ ግን አንድ ሰው ኃጢአተኛ ወይም ደካማ ቢሆንም እንኳ በሕይወቱ ውስጥ መልካም ጎኑን በመፈለግ አውጥታችሁ እነዚያ ባሕርያቱን አሞግሱለት። ኢየሱስ ክርስቶስ ለሳምራዊቷ ሴት ያደረገው እንደዚህ ነው። " ባል የለኝም በማለትሽ መልካም ተናገርሽ. ..."በዚህ እውነት ተናገርሽ "[ዮሐ 4*17እና 18] ።ይህ ውዳሴ ሴቲቱ ኃጢአቷን እንድትናዘዝ ስላደረጋት ለንስሓ ትበቃ ዘንድ ጌታ አሸንፏታል። አንዱ ሰው ሌላው ሸክሙን በሚያቀሉለት በቅዱሳት መጻሕፍት ታሪኮች ሲበረታታ ሌላው ደግሞ ስለ እግዚአብሔር ጸጋና ሥራ ሲነገረው ይበረታታል። ከዚህ ሌላ ስህተቶቹን ሁሉ በመርሳት የሚበረታታ ሰው ይኖራል። ለተፈጸመ ስህተት ሁሉ ቁጣን ማቅረብ ግን ወደ ተስፋ መቁረጥ ያደርሳል።
  አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ እንዳስተማሩት! !

ሕማማት ዲ/ን ሔኖክ ኃይሌ

07 Nov, 15:21


የክርስትና ሃይማኖት፦

፩.ከባለቤቱ ለቅዱሳን የተገለጠ
፪.የተቀበልነው
፫.የምንጠብቀው
፬.የምናቀብለው ነው።
በዚህ መንገድ ከሐዋርያት እስከ ዛሬ ደርሰናል። ነገር ግን በክፉ ሥርዓት እና በስንፍናችን ምክንያት ጠባቂም ተቀባይም እያጣ ነው።
በዕቅበተ እምነት ሁኖ በሥጋ መሞት ተፈጥሯዊ ርሥት ነው።በሃይማኖት ደክሞ በነፍስ መሞት ግን ዘለዓለማዊ ደይን ነው።
ቤተ ክርስቲያን ከብዙዎቻችን ጀምሮ ተናጋሪ እንጂ ሠሪ እያጣች ነው።
በተለይም ፍርሀት እና ማስመሰል በጢሟ ሊደፏት ተቃርበዋል።

ሕማማት ዲ/ን ሔኖክ ኃይሌ

06 Nov, 01:10


እራቁቴን አይደለሁም
የለበስኩት ልጅሽን ነው
ሐዘን ደስታ ቢፈራረቅ
የማርያም ልጅ
የማርያም ነው።

ሕማማት ዲ/ን ሔኖክ ኃይሌ

04 Nov, 04:07


      እርዱኝ እረዳችኋለሁ     
አንድ ትልቅ አረጋዊ በረጅም የሽምግልና ዘመናቸው ጆሯቸው ሳይደነግዝ ሁሉን ይሰማሉ፣ዓይናቸው ሳይፈዝ ሁሉን ያያሉ።አንድ ሰው ይጠይቃቸዋል እንዲህ ብሎ፦"አባ እግዚአብሔር ረድቶዎት ነው እንጂ በእርስዎ እድሜ ውስጥ ያሉት እኮ ዓይናቸው ዓያይም ጆሯቸው አይሰማም?" ይላቸዋል።
እሳቸውም፦"ምን እግዚአብሔር ብቻ ይረዳኛል እኔም እግዚአብሔርን ረድቸው ነው እንጂ ወራት እየለየሁ ቅቤ እቀባለሁ፣በፀሐይ አላነብም፣ጨረር አላይም እና እኔስ እየረዳሁት አይደለምን? እግዚአብሔር የሚረዳን ስንረዳው ነው"ይሉታል።
ታዲያ በሀገራችን ብሂልም "እርዱኝ እረዳችኋለሁ ብሏል" እየተባለ ይነገራል።
ይሄንን ሀሳብ ወድጀዋለሁ እግዚአብሔር የነጻነት አምላክ ነው ወደን ፈቅደን የምናደርገውን መልካም ነገር ሁሉ ይባርክልናል።የድርሻችንን ሳንወጣ ግን እርዳን ማለት ትልቅ ስንፍና ነው።
እግዚአብሔር አስገድዶ ምንም ነገር አድርጉ አይለንም። የሚጠቅመንን የሚያጸድቀንን እንድናደርግ ግን ይወዳል።
ቁጭ ብለን እግዚአብሔር ይርዳን ብንል ግን ስንፍናን በሰማይ ሰሌዳ ላይ እንደመጻፍ ነው።
"የተነቃነቀ ጥርስ ቢስቁበት አያደምቅ ቢበሉበት አያደምቅምና"ጠንክረን እንሥራ።
በሆነ ባልሆነው ነገር፦ብእል እንደበላው አቡጄዴ፣ዋግ እንደ መታው ስንዴ መሟሸሽ የወንድ ልጅ ተግባር አይደለም።

ሕማማት ዲ/ን ሔኖክ ኃይሌ

03 Nov, 08:00


የምስራች

እነሆ በTikTok በYoutube እናበተለያዩ ሶሻል ሚዲያዎች የምናውቀው ወንድማችን ልጃችን መምህራችን ዲያቆን ዘላለም ታየ በቴሌግራም መጥቷል ትምህርቶችን እንዲሁም እርሱ የሚጽፋቸውን ጦማሮች እንከታል ለህይወት ስንቅ ናቸውና::

Link👉https://t.me/dn_zelalem_taye

ሕማማት ዲ/ን ሔኖክ ኃይሌ

01 Nov, 17:55


"በጎ ነገር አግኝተህ እንደ ሆነ እግዚአብሔርን አመስግን፤ ያም በጎ ነገር ከአንተ ጋር ጸንቶ ይኖራል፡፡ በጎ ያልሆነ ነገር ደርሶብህ እንደሆነም እግዚአብሔርን አመስግን፤ ያም በጎ ያልሆነ ነገር ወደ በጎ ነገር ይቀየራል፡፡"

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ

6,455

subscribers

146

photos

10

videos