ደስተኛው እስረኛ
~
ኢብኑ ተይሚያ ለቆሙለት አላማ ሲሉ ብዙ ተንገላተዋል፣ ተደብድበዋል፣ በተደጋጋሚ ታስረዋል። ሆኖም ግን ፈተናዎች ጭራሽ አላጠፏቸውም። በተደጋጋሚ ወህኒ ቢወረወሩም ከምንም አይቆጥሩትም ነበር። እንዲያውም ካይሮ ሳሉ ደማስቆ ወይም አሌክሳንድሪያ ውስጥ በገደብ ከመኖርና ከመታሰር ሲያስመርጧቸው መታሰርን መርጠዋል። መታሰራቸው ጠላቶቻቸው ከሚያስቡት በተቃራኒ ፍፁም ደስታን ነበር ያጎናፀፋቸው። ወደ እስር ቤቱ ግቢ በዘለቁ ጊዜ ይህቺን የቁርኣን አንቀፅ አነበቡ፦
فَضُرِبَ بَيۡنَهُم بِسُورٖ لَّهُۥ بَابُۢ بَاطِنُهُۥ فِيهِ ٱلرَّحۡمَةُ وَظَٰهِرُهُۥ مِن قِبَلِهِ ٱلۡعَذَابُ
“በውስጡ ችሮታ ያለበት፤ በውጪው በኩል ስቃይ ያለበት የሆነ (አጥር) በመካከላቸው ተደረገ።” [ሐዲድ፡ 13]
“ቅጣት የሚመስለው ለናንተ እንጂ ለኔ የእፎይታ አፀድ ነው” የሚል የሚደንቅ መልእክት እያስተላለፉ ነው።
እንዲያውም ጠላቶቻቸውን ለመታሰራቸው ሰበብ በመሆናቸው ባለትልቅ ውለታ እንደሆኑ ይገልጿቸው ነበር። ከወህኒ ቤት ሆነው እንዲህ ይሉ ነበር፦ “የዚህን እስር ቤት ሙሉ ወርቅ ብታደል እኔን በማሳሰር ለዋሉልኝ ውለታ ልከፍላቸው አልችልም።” ሱብሓነላህ!
እነሱ በማሰር ቅስማቸውን ሊሰብሩ ያልማሉ። እሳቸው ግን፡ “ጠላቶቼ ምን ያደርጉኛል?! እኔኮ ጀነቴ፣ የአትክልት ስፍራዬ ልቤ ውስጥ ነው ያለችው። የትም ብጓዝ ከኔው ጋር ነች፤ አትለየኝም። መታሰሬ ኸልዋ ነው። ብገደል ሸሃዳ ነው። ከሃገር መባረሬ (የአላህን ተአምራት የምመለከትበት) ጉብኝት ነው” ይሉ ነበር። ድንቅ ንግግር ከድንቅ ፍጡር!
እስር ላይ በነበሩ ጊዜ ሱጁድ ላይ ሆነው “አላሁመ አዒኒ ዐላ ዚክሪከ ወሹክሪከ ወሑስኒ ዒባደቲክ። ይሉ ነበር። ደስታ! እርካታ! እንዲያውም ራሳቸውን እንደ እስረኛም አይቆጥሩም ነበር። በተደጋጋሚ አብረዋቸው የታሰሩት ተማሪያቸው ኢብኑል ቀይም በአንድ ወቅት፡ “ 'እስረኛ ማለት ልቡ ከጌታው የታሰረ ነው። ምርኮኛ ማለት ደግሞ ስሜቱ የማረከው ነው' አሉኝ” ይላሉ። ኢብኑል ቀይም አሁንም ስለ ሸይኻቸው እንዲህ ሲሉ ይቀጥላሉ፦
“ኑሮው የተጣበበና ከምቾት የራቀ ከመሆኑ ጋር፤ እንዲሁም ከነበረበት እስር፣ ዛቻና ማጨናነቅ ጋር እንደሱ ደስተኛ ህይወት የሚኖር፣ ፈታ ያለና ልቡ የፀና እንዳላየሁ አላህ ያውቃል። ይህ ሁሉ ከመሆኑ ጋር በህይወቱ ደስተኛ፣ ዘና ያለ እና ልቡ የፀና፣ ነፍሱ የረጋ ነው። የድሎት ፀዳል ከፊቱ ያንፀባርቃል። እንዲያውም ስጋት ሲበረታብን፣ ክፉ ጥርጣሬ ሲያጠቃን፣ ምድር ሲጠበን ቀጥታ ወደሱ ነበር የምንሄደው። ከዚያም ስናየውና ንግግሩን ስንሰማ ያ ሁሉ ይወገድልናል። ልባችን ይሰፋል። ብርታታችንም፣ የቂናችንም፣ መረጋጋታችንም ይጨምራል። አላህ ከሱ ጋር ሳይገናኙ በፊት ለልዩ ባሮቹ ጀነቱን ስላሳያቸው፣ በስራ አለም በሮቿን ስለከፈተላቸው ጥራት ይገባው። እሷን በመፈለግና ወደሷ በመሽቀዳደም የደከሙትን ያክል ከድሎቷ፣ ከለዛዋ አቀመሳቸው።”
እናት ወልዳለች የተይሚያ ልጅ! ድንቅ የአላህ ተአምር! “ዱንያ ውስጥ ጀነት አለች። እሷን ያልገባት የኣኺራዋን ጀነት አይገባትም” ይሉ ነበር። [አልዋቢሉ ሶይብ፡ 48] አላህ ከላይኛው ፊርደውስ ያቀማጥላቸው።
https://t.me/Halal_Zewje