የጉራጌዎች የሸንጎ ቡና አጠጣጥ ሥነ-ሥርዓት
የገፓት/የውኴር ቃዋ(የሸንጎ ቡና)
በሲሳይ ዓለሙ
[email protected]ጉራጌዎች መሸት ሲል ተጠራርተው የሚጠጡት ቡና "የገፓት ቃዋ" እያሉ ይጠሩታል፡፡ እናቶች ተራቸውን ጠብቀው ቡና ያፈላሉ፡፡ በገፓት/የውኴር #ቃዋ ድርድር የላቸውም፡፡ ከበድ ያለ ችግር እንኳ ቢያጋጥማቸው ተራቸውን ውልፍት አያደርጉትም፡፡
ባለተረኛዋ እማወራ ልክ ከምሽቱ 12፡30 ሲሆን ቃዋ የማፍላት ዝግጅቷን ትጀምራለች፡፡ ቀኑ ለምሽት ሥፍራውን ሲለቅ፣ ርቆ የሄደም ሲመለስ፣ #ደቦ ሥራ ላይ የነበሩት አባወራዎች ወደየቤታቸው ሲገቡ፣ ገበያ የሄዱት እማወራዎችም ግብይታቸውን አጠናቅቀው ከተመለሱ በኋላ፣ ከብቶችም ወደማደሪያቸው፣ በጎችና ፍየሎችም ወደ ጋጣቸው ከገቡ በኋላ ነው ቃዋ የሚጠጣው፡፡
ጉራጌዎች በማህበራዊ ኑሮዋቸው እጅግ ጠንካሮች ናቸው፡፡ የተጣላም ካለ እርቅ የሚያወርድበት፣ ያጣም ለአባላቶቹ ችግሩን ተናግሮ #መፍትሄ የሚያገኝበት ሰዓት ነው፡፡
አራስ፣ ለቅሶ፣ ሰርግ፣ ታማሚ ወይም በእድሜ የጃጀ ሰው በአካባቢያቸው ካለ ለእነዚህ ጉዳዮች ቅድሚያ ሰጥተው ጉዳዩ በተከሰተበት ቤት ሰብሰብ በማለት #ሸንጎ ያስመሻሉ፡፡ ሃዘንተኛም ሃዘኑን እስኪወጣለት ድረስ ያስተዛዝናሉ፡፡ የገፓት ቃዋቸውንም በእነዚያ ቤቶች ያደርጋሉ፡፡ ሰባት ቤት ጉራጌዎች አንዲት እናት ወልዳ ሁለት ወር እስኪሞላት ድረስ "#ጭን" እያሉ ይጠሩዋታል፡፡ አራስ ማለታቸውን ነው፡፡ ከአመጋገብ ጀምሮ ለአራስ የተለየ ትኩረት በመስጠት እንክብካቤ ይደረግላታል፡፡
የገፓት ቃዋ ጠጪ አባላቶች በተረኛዋ #ቡና አፍዪ እማወራ ቤት ይሰባሰባሉ፡፡ በእድሜ የገፉ አባቶች ከወተት ሰባት እጅ የነፃው ጋቢያቸውን ትከሻቸው ላይ አጣፍተው ከካቧት፣ ዮስጥየ ፣ጂፐ እና ከዳነራ በተዘጋጀው ምንጣፍ ላይ ያርፋሉ አሊያም ጋደም ይላሉ፡፡ ካቧትና ዮስጥየ ከእንሰት ኮባ የሚዘጋጁ ሲሆኑ #ጂፐ ደግሞ ከቃጫና አንጨት ከሚባል እፀዋት ይዘጋጃል፡፡ ዳነራ ከቆዳ የሚዘጋጅ ሲሆን ቆዳው እጅግ የተከበሩ ባለሙያዎች ፍቀው አለስልሰው የሚያዘጋጁ ነው በተለምዶ "ነፉረ" በመባል ይታወቃሉ፡፡
ጉራጌዎች ሦስት አይነት ቤቶች ይሠራሉ፡፡ የመጀመርያው #ጎየ በጣም ትልቅ ቤትነው፡፡ በነገራችን ላይ ጉራጌዎች በተለይም የቤቱ አባወራና እማወራ ከከብቶቻቸው ጋር በአንድ ጎጆ ጥላ ሥር በጎየ (በሰፊ) ቤት ነው የሚያድሩት፡፡ በዚሁ ጎየ ቤት ውስጥ ከብቶች የሚታሰሩበት ቦታ "ጋድር" ተብሎ ይጠራል፡፡
ከጋድር ፊት ለፊት የሚገኘው ሰዎች ቡና የሚጠጡበት እና የሚያርፉበት ሥፍራ ቃቀት እያሉ ይጠሩታል፡፡ #እንግዳ ተቀብለው የሚያስተናግዱበት፣ ድግስ የሚያሰናዱበትና ልጆች የሚያጠኑበትና የሚዝናኑበት እጅግ ያማረና የተዋበ ቤት እልፍኝ(ኽራር) ይባላል፡፡ ሦስተኛውና አነስ ያለው ቤት ዘገር ብለው ይጠሩታል፡፡ ዘገር ለኩሽና፣ ለከብቶች መኖ ማከማቻና ለመሳሰሉ አገልግሎቶች እንደ መጋዘን ይጠቀሙበታል፡፡
#ዘርማዎች (ወጣቶች) በገፓት ቃዋ ላይ ይገኛሉ፡፡ ምድጃውን (ጎርደት) ዙርያ ክብ ሠርተው ቦርጭማ ላይ ቁጭ በማለት ምድጃው መሀል ላይ የሚንቀለቀለው እሳት እየሞቃቸው ያሻቸውን ያወጋሉ፡፡ ጎርደቱ ላይ መሰቀልኛ ተጋድሞ የሚነደው ፍልጥ የሚለቀው ሙቀት ግድግዳና ምሰሶ ላይ ከተለኮሰ የኩራዝ ብርሃን ጋር ሲዳመር የቤቱን የውስጥ ገጽታ ባንዴ ወደ አንዳች ማራኪ እይታ ይቀየራል፡፡
ከብቶቹ ቀን ሲግጡት የዋሉት ሳር አይናቸውን ጨፍነው በመንጋጋቸው ግራና ቀኝ ሲያመነዥኩት አፋቸው ቅኝት (Rhythm) ያለው ድምፅ ያወጣል፡፡ የጉረሮዋቸው ትቦ የላመው ወደ ሆድ ሲያቀብል ሽርክቱ ደግሞ ወደ መንጋጋ ሲያደርስ ሲታይ #ፊልም የመመልከት ያህል ከመምሰል በተጨማሪ ተፈጥሮን አለማድነቅ አይቻልም፡፡
የተጣደው ቡና ቱፍ ብሎ እስኪሰክን ድረስ እማወራዋ ላሟን አልባ ትኩስ ወተት ከሸክላ በተሠራ "እንጃባ" ለሽማግሌዎቹ ትሠጣቸዋለች፡፡ #ሽማግሌዎቹ ማጀትሽ አይጣ፣ ከዓመት ዓመት ወተት አያሳጣሽ ብለው ይመርቋታል፡፡ ላሚቷም "ትትረፍ" ተብላ ትመረቃለች(ክፉ አይንካሽ ውለሽ ግቢ ማለታቸው ነው)፡፡
ለዘርማዎች ዮሸር ኤብ (እርጎ) ይሰጣቸዋል፡፡ ለልጃ ገረዶች (#ዘየዎች) ትኩስ ለጋ ቂቤ አናታቸው ይቀባሉ፡፡ ዘርማዎች ከዮሸር ኤብ በተጨማሪ ቄሳ (አይቤ) ይበላሉ፣ አጓት ይጠጣሉ፡፡
ሲኒ ይጎዘጎዛል፡፡ ቤት ያፈራውን የቡና ቁርስ ይቀርባል፡፡ በትልቅ #ጀበና የተፈላው ቡና መቀዳት ይጀምራል፡፡ ቀን በሥራ ላይ ታች እያለ ሲዳክር የዋለ ጉልበት አደብ ገዝቶ የተቀመጠበት ሰዓት ነው፡፡ እናቶች ጠበቅ አድርገው ወገባቸውን ካሰሩበት መቀነት (አዝጋርት) ተላቀው እረፍት የሚያደርጉበት ጊዜ ነው፡፡ ቡና በኡፋ ቂቤ ወይም ቡና ብቻ እንደየ ፍላጎቱ ተቀድቶ ይዳረሳል፡፡
አንዱ አባወራ #አረቄ ገዝቶ መርቁኝ ይላል፡፡ ቡናቸውን ፉት እያሉ የተለመደው ጨዋታቸውን ያደሩታል፡፡ የሰፈሩ ውሎ በጨዋታ ይገመገማል።
እናቶች በዕለቱ ስለነበረ #ገበያ ውሎ ያወራሉ፡፡ አረቄው ከቀረበ በኋላ በሥራና በተለያዩ ምክንያቶች ከአጠገባቸው ርቀው ለሚገኙ ቤተሰቦቻቸው የሄዱበት ቦታ እንዲቀናቸው ከክፉ እንዲሰውራቸውና ሃሳባቸውንም እንዲሞላላቸው አጥብቀው ይመርቃሉ፡፡
ጉራጌዎች ባህላዊ የሆነ የአረቄ አወጣጥ ዘዴ አላቸው፡፡ በተለያየ መንገድ ለተለያዩ ጥቅሞችና ለመድሀኒትነት የሚያገለግል አረቄ ያዘጋጃሉ፡፡ ከብቅልና ከጌሾ በተጫማሪ ከተለያዩ #እፀዋቶችና ሥራስሮች መጥነው የሚያዘጋጁት አረቄ ለደም ግፊት፣ ለሆድ ቁርጠት፣ ለኮሊስትሮል እና ለአላስፈላጊ ውፍረት ፍቱን መድሀኒት ነው ብለው ያስባሉ፡፡
ቀስ በቀስ #ሸንጎው እየተገባደደ ይሄዳል፡፡ የቡና ጠጪ አባላቶቹ አልፎ አልፎ እራትም አንድ ላይ ይመገባሉ፡፡ የበሰለ ጎመን በደቃቁ ተከትፎ ከአይቤ ጋር በቂቤ ያጣፈጡት ዝማሞጃት ከቆጮ ጋር ሲበላ እንደ ማር ከመጣፈጡ በላይ ለሰውነት አንዳች እርካታ ይሰጣል፡፡ እንደ ወቅቱ ሁኔታ የጎመን #ክትፎ አዘጋጅተው፣ በግ አርደውና ጠላ ጠምቀው ተሰባስበው የሚያከብሩት በዓላቶችም አሉ፡፡ከምሽቱ 4፡00 ሲሆን የገባት ቃዋ ተጠናቅቆ ወደየ ቤቶቻቸው ያመራሉ፡፡
Zebidar Tube/ ዘቢዳር ቲዩብ