ዶክተር ኢትዮጵያ | Doctor Ethiopia @ethiodoc Channel on Telegram

ዶክተር ኢትዮጵያ | Doctor Ethiopia

@ethiodoc


✓ስለ ጤናዎ መረጃን እናካፍላለን፣
✓ጤናዎን የተመለከቱ ጥያቄዎችን በዶክተር የታገዘ ምላሽ እንሠጣለን እናማክራለን።
✓ያለወትን የጤና ነክ መረጃና ምክር @Yonase2323 ላይ ያካፍሉን፣ መልሰን ለአንባቢያን እናደርሳለን::

ዶክተር ኢትዮጵያ | Doctor Ethiopia (Amharic)

የሶስት ወጣቶች የሚዘገይ ምልክት ለእርስዎ ሀገር አገልግሎት ነው። የዶክተር ኢትዮጵያ በዚህ ቦታ ይገኛል። የቡላው ኤብሮች ለሚጸልይ የሴቶች ጤና ቅምሻ ጊዜ ለሚገኝ ሀፍረቷን ደስታ በመጠቆም የሚያግዝ ወገኖችን ይዞ እና ስነልቦናውን በድረ-ገፅ መመልከት ይችላል። በእርስዎ ሀገር ተጠቃሚያቸውን በመጠቆም ለዶክተር ኢትዮጵያ በፍጥነት እንዲያስፈልግ ይህን መልኩን አገልግሎት ለማስከበረም የሰራተኞችን ዲሞክራሲን በግንኙነቷ ወስን አንዱ አስተማሪ ችሎታን ሊያደርግ ይገባል።

ዶክተር ኢትዮጵያ | Doctor Ethiopia

22 Nov, 04:03


እስትሮክ ወጣትን ያጠቃልን?

ከስድስት ግዜ በላይ * ስትሮክ * ያጋጠመውን ታካሚ ማከም የሚቻለው የተዛባ እሳቤውን በቅድሚያ ማከም ሲቻል ብቻ ነው።

<ምን እያልከኝ ነው ? አንድ.. ፍሬ.. ልጅ.. እኮ ነው ዶክር... > ብለው ንግግራቸውን መጨረስ ያቃታቸው እናት ለዛሬ ላካፍላችሁ ስለምፈልገው ጉዳይ መነሻ አድርጌ እንዲህ አቀርብላችሗሉሁ።

በዙዎች እስትሮክን የአዛዉንቶች ብቻ አድርገው ይወስዱታል። እስትሮክ በሁሉም የአድሜ ክልል ሊፈጠር የሚችል ህመም ነው። የችግሩ መጠን ፤መንስኤ ባጠቃላይ ተጋላጭነትና የመከሰት እድሉ በፆታና በእድሜ የተለያየ መጠንና ይዘት ያለው ቢሆንም ፥ ጨቅላ ፣ እምቦቀቅላ ፣ ወጣት፥ ጎልማሳ፤ ታዋቂ የማይታወቅ፤ ወንድ ሴት ሳይል እያጠቃ ያለ የአለማችን ሁለተኛው ግዙፍ አስከፊ የሰው ልጅ ጤና ነጣቂናቋሚ ችግር አድራሽ በሽታ ነው፦ Stroke.

ልብ ይበሉ! ይኽ የመጠን መለያየት እንዳለ ሆኖ እስትሮክ ገና ከእናት ማህፀን ጀምሮ የሚከሰት ወሰን የሌለው የጤና እክል ነው።

ሁሉንም ሊያጠቃ ይችላል ፤ በመሆኑም ሁሉም የችግሩን ጥልቀትና ወሰን-የለሽነት ተረድቶ አስፈላጊውን የመከላከል መፍትሔ ይውሰድ እንላለን።

ዛሬ በዋናነት በወጣትነት ዘመን እስትሮክን ሊያስከትሉ የሚችሉትን እናያለን። ፤ዋና ዋና መንስኤዎች፦

1) የልብ ህመም ተጠቂ የሆኑ ከሆነ። ሁሉም የልብ ህመም ተጠቂ የዚህ ችገር ተጠቂ ላይሆን ይችላል። የሚጠቃ አለ የማይጠቃ አለ። ይኸን ለማወቅ የልብ ህመም ካለባቸው ችግራቸው ከስትሮክ ጋር የሚኖረውን ትስስር ማወቅ ይገባቸዋል። ሐኪሞን ያማክሩ! ያለዎትን የተጋላጭነት ደረጃ ማወቅ ለቅድመ እስትሮክ መከላከል በጣም አስፈላጊ ነው። እስትሮክን ቆደሞ መከላከል ይቻላል።

እስትሮክ ሊከሰት የሚችለው በልብ ከረጢት ውስጥ የረጋ ደም ወደ አንጎል ከሚሔድ ደም ጋር አብሮ በመጋዝ የአንጎል የደም ስሮችን በድንገት በመዝጋት ነው። ይኸም መነሻውን ከልብ ያደረገ የረጋ ደም እስትሮክ አምጪ ተብሎ በህክምና ይጠራል። መንስኤውን ማወቅ ትልቁ የእስትሮክ የህክምና መሰረት ነው። ለዚህም ሲባል ጠለቅ ያለ ምርመራ ይደረጋል።

በኛ ሀገር ከዚህ ችግር ጋር ከፍተኛ ቁርኝት ያላቸው የህፃናት/የወጣትነት የልብ ህመሞች ሁለት ናቸው። በላንቃናቶንሲል ኢንፌክሺን ስር መስደድ ምክነያት የሚከሰት የልብ ጤና እክል (Rheumatic heart disease)፤ ሲወለዱ አብሮ ከሚወለድ የልብ ክፍተት ችግር ናቸው።

በተለይ የመጀመሪያው ኢንፌክሺንን በተገቢ ሁኔታ ካለመከላከልና ካለማከም/ማሳከም ጋር የሚመጣ አብሮ የሚከተለን ትልቅ የማህበረሰብ የሗላ ዘመን ዘመን ተሻጋሪ ችጎራችን ነው። ችግሩን ከታች ከእንጭጩ ማጥፋት ነገን ማሳመር ፤ ከልብ የጤና እክል ብሎም ወጣትነትን ከሚያቀዘቅዝ "እስትሮክ" መከላከል ነውና ሳንሰለች የላንቃና ቶንሲል ኢንፌክሺንን እንግታ። ያስታውሱ እንጥል በመቁረት ችግሩን መከላከል ፈፅሞ አይቻልም። ይልቁንም ሰዎች ለትንታሌሎች ተጓዳኝ ችግሮች ተጋላጭ እንዲሆኑ ያደርጋል።

መጀመሪያ የልብዎን ጤንነት ያስመርምሩ ፤ ከዚያ ያለብዎትን የልብ ችግር የተጋላጭነት ደረጃ ይወቁ ፤ ቀጥሎ በደረጃዎ መሰረት የሚያስፈልገውን ቅድመ መከላከያ መድሐኒት በአግባቡ ይውሰዱ።

2) የደም መርጋት ችግር ያጋጠማቸው ሰዎች። የደም መርጋቱ በዋናነት በራስ ቅል ውስጥ በሚገኙ የደም መላሾችና ደም ወሳጆች ቧንቧ ፤ አንዳንዴም ከራስ ቅል ዉጪ በሚገኙ የውስጠኞቹ የደም መላሾች ቧንቧ ውስጥ ተሰርተው ወደ አንጎል በመጓዝ ሊሆን ይችላል። በለተይ ወጣት ሴቶች ለዚህ ችግር በልዩ ሁኔታ ተጋላጭነታቸው ሰፋ ያለ'ነው። ለወሊድ መቆጣጠሪያነት ከሚወሰድ ክኒን ጋር አለያም በእርግዝናናከድሆረ ወሊድ ጋር ተያይዞ በሚከሰት ተፈጥሯዊ የሆንሞን መዘበራረቅ እንደ ተጨማሪ ከጋሌጭ ተብለው ይወሰዳሉ። #በራስ ቅል ውስጥ የደም መርጋት እንዴት ይከሰታል? ለሚለው በሌላ ትምህርት ማስጨበጫ ይጠብቁ።

3) በልብ ውስጥ የሚፈጠር ኢንፌክሺን ለየት ያለ እስትሮክ ሊያስከትል ይችላል። ለልብ ውስጥ ኢንፌክሺን ተጋላጭ የሆኑ የልብ ታማሚዎች አሉ። አንዳንዴ ጤነኛ ልብ ያላቸውም ሰዎች ለዚህ ችግር ሊዳረጉ ይችላሉ። በተለይ በራሳቸው ደም ስር መድሐኒት የመውሰድ መጥፎ ልማድ ያላቸው ለዚህ ችግር ተጋላጭ ናቸው።

4) የመድማት አዝማሚያ በአንድ ሰው ውስጥ ሲኖር ደም በቀላሉ ወደ አንጎል በመፍሰስ እስትሮክን ያመጣል። አንድ ሰው ለመድማት ተጋላጭ ሊሆን የሚችለው በሚከተሉት ሁኔታዎች ሊሆን ይችላል፦

ሀ) ለደም ማቅጠጫ የሚወሰድ መድሐኒት ከመጠን አልፎ ሲገኝ (warfarin,.. ይኸን ለማስቀረት የራሱ ክትትል ስላለው በደንብ መከታተል)

ለ) ተፈጥሯዊ የደም ማርጋትና ማቅጠን በለተያየ ሁኔታ አለመጣጣም ሲኖር (Coagulopathies)፤

ሐ) የደም ካንሰር ተጠቂ ሰዎች /የ አንጎል እጢ መድማት ሲያስከትል ፤

5) ሀገ ወጥ የማነቃቂ መድሐኒቶችን የሚወስዱ ጎለሰቦች (ለምሳሌ.cocaine ..) .cocain በራሱ ለእስትሮክ መከሰት ብቸኛ መይስኤ ሊሆን ይችላል። ከcocain ደስታን ለማግኘት መሞከር ከመብረቅ ብረሐን አገኛለሁ ብሎ እንደማመን አጥፊ ሐሳብ ነው። ለሴኮንድ ከማይቆይ መብረቅ መብራት ለማግኘት ሲቅበዘበዙ በመብረቅ እሳት ወደ አፈርነት መቀየር አለና ስለ ጥቅሙ አለማሰብ ይበልጥ ጥቅም የሚያስገኝ ብልህነት ነውና ብልህ እንሁን፤

6) የአንጎል የደም ስሮች ስር የሰደደ መቋጣትና የደም ስሮች ማበጥ ለእስትሮክ እንደ መንስኤ የመሆን አጋጣሚዎች በአንዳንድ ሰዎች ላይ ይታያል።

......እና ሌሎች ያልተጠቀሱ መንስኤዎችም አሉ።

መነሻውን ልብ ላይ ያደረገ እስትሮክ ለየት ያለ ባህሪ አለው። የመጀመሪያው በቀኝ አንጎል ክፍል ተከስቶ በቀጣይ በግራ የመከተስ ሰፊ እድል ስላለው ችግሩ ሰፋ ያለ። ግራና ቀኝ የሰውነት ክፍል በእስትሮክ የአንጎል ደዌ ሰንሰለት ሲታሰር የሚፈጥረው ጫና ከባድ ነው።

በዚህ አጋጣሚ ስድስት ግዜ እስትሮክ ያጋጠማት ታካሚ አግኝቼ ስለ መድሐኒት አወሳሰድ ልምዷ የነገረቺኝ ዛሬም የህክምናን ጥቅም ያለመረዳት/ግዴለሽ መሆንን ነው ልገነዘብ የቻልኩት። ብዙ የሒወት ዘመን ልምድ ያላቸው የኛ መምሕራኖች ከዚህ በላይ ብዙ ለማመን የሚከብዱም የሒወት ገጠምሺኝ ይኖራቸዋል።

#መፍትሔ:-
ከላይ የተጠቀሱትን የመንስኤ ሰንሰለቶችን ለይቶ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ተገቢ ነው። አብዛኞቹ በወጣትነት እድሜ ክልል አጋላጭ ተብለው የተጠቀሱት ግማሾቹ ሙሉ በሙሉ ማስወገድ የምንችላቸው ናቸው፤ሌሎቹ ቢያንስ ከሐኪም ጋር በቅርበት ተሁኖ ቅድመ መከላከል እርምጃ ያላቸው ናቸው።

እይከላከል ፤ እንመርመር፣ እንታከም ፤የጤና ምክር ተግባራዊ እናድርግ።

ትልቁ ነጥብ ነገን የሚሻ ትውልድ እንዲኖረን በማድረግ ወጣቱን መንገድ ላይ የሚያስቀሩትን የሒወት መሰናክሎችን መቅረፍ። ለዚህ ደግሞ ቤተሰብ፣ ማህበረሰቡ ፤ የሐይማኖት ሰዎች ፣ መንግስት ከጤና ባለሙያው ጋር እጅና ጓንት ሆኖ መስራት ይጠበቃል።

አዎ...! እማማ እስትሮክ በየትኛውም የእድሜ ክልል ሊመጣ የሚችል በድንገተኛ የአእምሮ ደም ዝውውር መቋረጥ ምክነያት የሚመጣ ችግር ነው ብዬ ... ቀለል ያለች ማብራሪያ ሰጥቼ አፋጣኝ ህክምና መስጠት ነበረብኝና ወደ ታካሚዬ ተጓዝኩኝ።

Dr. Mesfin Behailu, Neurology Resident, Neurology depratment Tikur anbessa


https://t.me/ethiodoc

ዶክተር ኢትዮጵያ | Doctor Ethiopia

21 Nov, 06:12


ሥር የሰደደ (የማያቋርጥ ) ስርቅታ | Chronic/persistent Hiccups

ሥር የሰደደ ስርቅታ ምንድ ነው !?

ስርቅታ የሚከሰተው ዲልሺ (ዲያፍራም) ያለፍላጎቱ (involuntarily) ሲኮማትር ወይም ሲሰበሰብ ነው። ዲልሺ (ዲያፍራም) ለመተንፈስ የሚረዳ ጡንቻ ነው። በደረትዎ እና በሆድዎ መካከል ይገኛል። ያለፈቃዱ መኮማተር ከተጠናቀቀ በኋላ ሃብለ ድምጽ በፍጥነት ይዘጋሉ። ከስርቅታ ጋር የሚፈጠረውን ድምጽ የሚያመጣው የሐብለ ድምፅ በፍጥነት መዘጋት ነው።

ስርቅታ አብዛኛውን ጊዜ ለጥቂት ደቂቃዎች ወይም ሰዓታት የሚቆይ ሲሆን ብዙ እማያሳስብና ሕክምናም ላያስፈልገው ይችላል። ነገር ግን፣ የእርስዎ ስርቅታ ቶሎ እማይቆምና ከሁለት ቀናት በላይ የሚቆይ ከሆነ፣ እንደ ሥር የሰደደ ወይም የማያቋርጥ ስርቅታ ይቆጠራሉ።

በአንዳንድ ሰዎች ላይ ሥር የሰደደ ስርቅታ ለዓመታት ሊቆይ ይችላል። እናም አብዛኛውን ጊዜ ሕክምና ሊያስፈልገውና ለሌላ አሳሳቢ የጤና ችግር ምልክት ሊሆን ይችላል። እንዲሁም ስርቅታ እራሱን ችሎ የጤና ችግሮችን ሊያስከትል ይችላል። ለምሳሌ፣ እንቅልፍ ማጣትና ድካም መሰማት፣ የምግብ ፍላጎትዎን ወይም የመብላት ፍላጎትን መቀነስና ለክብደት መቀነስም ምክንያት ሊሆን ይችላል።
ስር የሰደደ ስርቅታ ብዙውን ጊዜ ከሴቶች የበለጠ ወንዶች ላይ የመከሰት እድሉ ከፍ ያለ ነው።

ሥር የሰደደ ስርቅታ የመያዝ ዕድላቸው ከፍተኛ የሆነባቸው ሰዎች የሚከተሉትን ያካትታል፡-
- በቅርቡ አጠቃላይ ሰመመን የወሰዱ
- ጭንቀት ወይም ሌሎች የአእምሮ ጤና ችግር ያለባቸው
- በሆድ አካባቢ ቀዶ ጥገና ያደረጉ
- የአንጀት፣ የሆድ ወይም ድልሺ በሽታ ያለባቸው
- እርጉዝ ሴቶች
- ካንሰር ታካሚ
- ከመጠን በላይ አልኮል የሚጠጡ

ሥር የሰደደ ስርቅታ መንስኤዎች

ስርቅታን እንደሚያስከትሉ የሚታመኑ ብዙ ነገሮች አሉ። ነገር ግን ሥር የሰደደ ስርቅታ በሽታ መንስኤ ሁልጊዜ በቶሎ ላይታወቅ ይችላል። መንስኤውን ለማወቅም ረዘም ያለ ጊዜና ምርመራ ሊያስፈልገው ይችላል።

የሚከተሉት ለስርቅታ መንስኤ ሊሆኑ ከሚችሉት ምክንያቶች ጥቂቶቹ ናቸው።
-የቅርብ ጊዜ ቀዶ ጥገና እና አጠቃላይ ሰመመን
-የአንጀት በሽታዎች፣ የጨጓራ ኩስለት፣ ኢንፌክሽን፣ እጢ
-የኩላሊት ወይም የጉበት በሽታዎች
-የልብ ደም ስር መዘጋት ውይም ቁስለት
-ዕጢዎች (ብዙውን ጊዜ ከጨጓራ የሚነሱ፣ ከአንጎልና ከሳንባ)
-የአንጎል ጉዳቶች እንደ እስትሮክ፣ ማጅራት ገትር፣ እጢዎች
-እሚጥል በሽታ ጋር ታያያዥ የሆነ የነርቭ ጉዳት
-የሳንባ ምች፣ የጉበት እና ጉበት አካባቢ ኢንፌክሽን
-አተነፋፈስን የሚቆጣጠሩ ነርቮች ጉዳት ወይም መብገን
-መድሃኒቶች እንደ ደክሳ ሜታሶን (dexamethasone) ፣ ድያዜፓም(diazepam) ፣ የካንሰር ህክምና መድሃኒቶች (chemotherapy)

ተዛማጅ ሁኔታዎች

ከረጅም ጊዜ ስርቅታ ጋር የተያያዙ ሁኔታዎች ራስን በራስ ገዝ የነርቭ ሥርዓትን (Autonomuos nervous system) የሚጎዳ ማንኛውንም የሕክምና፣ የጤና ጉዳይ ወይም ችግር ያጠቃልላል።

ስርቅታን እንደት እናክማለን

ከ48 ሰአታት (ከሁለት ቀን ) በታች የሚቆይ ለአጭር ጊዜ የሚቆይ ስርቅታ ህክምናው በማስታገስ ላይ ያተኮረ ነው። በአብዛኛው በአጭር ጊዜ የሚቆም ሲሆን እስጊ በሆነ ተያያዥ ችግር የተከሰቱ አይደሉም። ስለዚህም ስለ መንስኤዎቻቸው ብዙ መጨነቅና ምርመራ ማድረግ አያስፈልጋቸውም። በቤትም ውስጥ ሆነ በህክምና ተቋም ስርቅታን ለማስታገስ ውይም ለማቆም የሚከተሉትን ልናድርግ እንችላለን።

● ከ 5 እስከ 10 ሰከንድ (ወይም የቻሉትን ያህል) እስትንፋስ መያዝ
● ለአምስት ሰከንድ ያህል እስትንፋስ በመያዝ የሆድ ግፊት ወይም ፕሬዠር መጨመር (የቫልሳልቫ ማኑዌርን) ማከናወን።
● በጣም ቀዝቃዛ ውሃ መምጠጥ ወይም በአፍ ውስጥ ማንበቅበቅ።
●ምላስን በእጅ ወደፊት መሳብ።
●አንድ የሻይ ማንኪያ ደረቅ ስኳር መዋጥ።
● በእርጋታ አይንን ጨፍኖ በዐይን ኳሶች ( eye ball) ላይ መጫን።
● በሚቀመጡበት ጊዜ ጉልበቶችን ወደ ደረት መጎተት ወይም ደረትን ለመጫን ወደ ፊት ዘንበል ማድረግ፣ ከተቻለ ከ 30 ሰከንድ እስከ አንድ ደቂቃ ድረስ በዛው ቦታውን መያዝ
● ከፍተኛ የመሳብ ጥረት የሚጠይቅ መዝጊያ ወይም ቫልቭ ባለው ጠንካራ ቱቦ ውስጥ ውሃ መጠጣት ወይም መምጠጥ

ሥር የሰደደ ስቅታን ማከም

ሥር የሰደደ ወይም የማያቋርጥ የስርቅታ ሕክምና ብዙውን ጊዜ አንድ ብርጭቆ ውሃ ከመጠጣት ወይም ከለይ ከተዘረዘሩት የማስታገሻ ህክምናዎች የበለጠ ነገር ይፈልጋል። ሥር የሰደደ ስርቅታ የጤና ችግሮችን ስለሚያስከትል እና ትልቅ የጤና ስጋት ምልክት ሊሆን ስለሚችል፣ አብዛኛዎቹ ህክምናዎች የሕክምና ባለሙያ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። ብዙውን ጊዜ ችግሩን እራስዎ ማከም ወይም ችግሩን በቤት ውስጥ መፍታት አይችሉም።

ሕክምናው እንደ ዋና መንስኤው ይወሰናል እናም የሚከተሉትን ሊያጠቃልል ይችላል:-
1 - ስርቅታ የሚያመጣውን የጤና ሁኔታ ወይም መንስኤ መለየትና ማከም
-ስርቅታን በአጭር ጊዜ መቆጣጠርና ደጋግሞ እንዳይከሰት ያደርጋል
2- በሐኪም የታዘዙ መድኃኒቶችን መውሰድ:-
3- ቀዶ ጥገና ማድረግ (ድልሺ ጋር ተያያዥ የሆኑ)
-የቫገስ ነርቭን በኤሌክትሪክ ሾክ ማነቃቃት
-የፍሬኒክ ነርቭን ለይቶ የሚያደነዝዝ መድሃኒት መስጠት (ለአጭር ጊዜ ወይም በቋሚነት ክፊል ድልሺ እንዳይንቀሳቀስ ማድረግ)
4- አኩፓንቸር (Acupuncture)

ማሳሰቢያ:-

አንድ ጊዜ ወይም አልፎ አልፎ የሚከሰት ስርቅታ (Hiccups) በጣም የተለመደ እና በፍጥነት የሚቆም ነው። ሥር የሰደደ ስርቅታ በጣም ያልተለመደና አልፎ አልፎ የሚከሰት ሲሆን ለማከም በጣም አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። በተደጋጋሚ የሚከሰትና ከሁለት ቀናት በላይ የሚቆይ ስርቅታ ካለብዎ የከባድ የጤና መታወክ ምልክቶች ሊሆኑ ስለሚችሉ የሕክምና ባለሙያ ማማከር እና ህክምና ማድረግ አስፈላጊ ነው። ሥር የሰደደ ስርቅታ ካልታከመ ጤናዎንና የአኗኗር ሁኔታዎን ሊጎዳ ይችላል።

ዶ/ር ሙሃመድ ዩሱፍ (MD, Internist)


https://t.me/ethiodoc

ዶክተር ኢትዮጵያ | Doctor Ethiopia

19 Nov, 05:06


አንድ እጅግ አሳዛኝ ገጠመኜን ላካፍላችሁ

ቁጥራቸው ብዙ የሆኑ ግለሰቦች እየሮጡ እንዲሁም እየጮሁ ትንሽ ልጅ አቅፈው ወደ ስራ ገበታ ይመጣሉ። ምንድ ነው ብለን ህፃኑን ከለበሰው ልብስ ስናወጣው በህይወት እና በሞት መሃል ሆኖ ያጣጥራል እራሱንም ስቷል።

ወድያው እኛም የድንገተኛ እርዳታ እስትንፋስ (CPR) መስጠት ጀመርን ይሁን እና የህፃኑ እስትንፋስ እና የልብ ምት እንደቆመ ተራዳን። እኛም ክስተቱን ለማወቅ ስንሞክር አንድ አብራ የመጣች የልጁ ተንከባካቢ ውሃ የያዘ ባልዲ ውስጥ ሰጥሞ ነው አለችኝ።

ምግብ ማብሰያ ገብቼ ስወጣ የህፃኑ ጭንቅላት ከባልዲው ውሃ ውስጥ ነው አለችኝ። ማመን አልቻልኩም በድንጋጤ መጮህ ጀመርኩኝ አለችኝ።

ጎረቤት ተሰበሰበ ህፃኑን ይዘን እየሮጥን መጣን አለችኝ። እኔም እንባዬ መጣ። እዛው እንዳለው የህቴን ልጅ ሞት ትዝ አለኝ። ቀጥላም ባልዲ ወስጥ ያለው ውሃ ጥልቀት ስላልነበረው ይሰጥማል ብዬ ፈፃሞ አላሰብኩም አለችኝ። እኔም እንደው ትንሽ ጀባ ልበላችሁ።

መስጠም በእንግሊዘኛ drowning ምንድነው?

መስጠም ውሃ ወደ ሳንባችን እንዲገባ እና የመተንፈስ ችግር እንዲከሰት ያደርጋል። ውሃ ወደ ሳንባ ሲገባ የኦክስጅንና የካርቦን ዳይ ኦክሳይድ ልውውጥን ያስተጓጉላል። በዚህም ምክንያት መስጠም የገጠመው ልጅ የመስጠም ምልክቶች ያሳያል። መተንፈስ መቸገር፣ ቶሎ ቶሎ መተንፈስ ፣የፊት የከንፈር መጥቆር። የልብ ምት መጨመር እና የምት መዛባት። ውሃ ከአፍ ውስጥ መውጣት እንዲሁም የሆድ መነፋት ያስከትላል።

እንደዚ አደጋ ሲያጋጥሞት ብቻዎትን ከሆኑ እርዳታን ይጥሩ። ተጎጂውን ከውሃ ውስጥ ያውጡት። ከውሃ ውስጥ ካወጡት በኃላ ተጎጅው የሚተነፍስ ከሆነ በማገገሚያ አቀማመጥ ያስተኙት። የአንገት አጥንቶች ተሰብረው ሊሆን ስለሚችል እንዳይነቃነቅ ጥንቃቄ ያድርጉ። ብርድ ልብስ ወይም ጃኬት ይደርቡለት።

ተጎጅው የማይተነፍስ ከሆነ ወደ ድንገተኛ መርጃ ስልክ ይደውሉ። እንዲሁም ተጨማሪ እርዳታን ጮኸው ይጣሩ። ተጎጅውን በጀርባው ያስተኙት አፍ ወስጥ መተንፈስ ሚከለክል ነገር ካለ በጥንቃቄ ይመልከቱ። ባህድ ነገር ካገኙ በጣትዎ እስከደረሰበት ያስወግዱ። እስትንፋስ (CPR) መስጠት ይጀምሩ።

በደቡብ አፍሪካ በየዓመቱ 600 ህጻናት ሰጥመው እንደሚሞቱ ይገመታል። ሜይ 15 ዓለም አቀፍ የውሃ ደህንነት ቀን ነው እናም በዚህ አመት ለመስጠም ተጋላጭ ለሆኑት - ከአምስት አመት በታች ለሆኑ ህጻናት ትኩረት መስጠት እንፈልጋለን። ታዳጊዎች በውሃ ላይ ከፍተኛ አደጋ የሚያጋጥሟቸው ቦታዎች እና በቤታቸው አቅራቢያ ናቸው።

ወላጆች እና ተንከባካቢዎች - እባክዎን በቤትዎ ውስጥ ወይም በአቅራቢያዎ ያለ ማንኛውም የተከማቸ ውሃ ለልጆች ደህንነቱ የተጠበቀ መሆኑን ያረጋግጡ። ባልዲዎች፣ ታንከሮች እና ገንዳዎች በአስተማማኝ ሁኔታ የተዘጉ ወይም ለህጻናት የማይደርሱ መሆን አለባቸው።

የአለም ጤና ድርጅት ህጻናትን ከመስጠም የሚከላከሉ አራት እርምጃዎችን ይጠቁማል፡- የውሃ አቅርቦትን የሚቆጣጠሩ እንቅፋቶችን መትከል; ለቅድመ ትምህርት ቤት ህጻናት ከውሃ ርቀው አስተማማኝ ቦታዎችን መስጠት ፣ ብቃት ባለው የልጅ እንክብካቤ ፣ እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ህጻናት የውሃ ደህንነት እና የመዋኛ ክህሎትን ያስተምሩ እና በአስተማማኝ ማዳን እና ማነቃቂያ ውስጥ ያሉ ተመልካቾችን ማሰልጠን።

ልጆች በጥቂት ሴንቲሜትር ውሃ ውስጥ ሊሰምጡ ይችላሉ። እባክዎን ቤትዎ ከውሃ የተጠበቀ መሆኑን ያረጋግጡ። አብዛኛው የጨቅላ ህፃናት ሞት በመታጠቢያ ገንዳዎች እና በትላልቅ ባልዲዎች ውስጥ ይከሰታል።

ህጻናት በውሃ ውስጥ እና በአካባቢው ሲሆኑ እንዲሁም በልጆች እና ጎልማሶች መካከል የህይወት ጃኬቶችን በሚጠቀሙበት ጊዜ ቅርብ ፣ የማያቋርጥ ፣ በትኩረት እና ችሎታ ያለው የአዋቂዎች ቁጥጥር።

ክትትል የማይደረግበት መዳረሻን ለመከላከል፡ ባለ አራት ጎን ገንዳ አጥር ቢያንስ 4 ጫማ ቁመት ያለው በራሱ የሚዘጋ እና የሚዘጋ በሮች ገንዳውን ከቤት እና ከጓሮው ሙሉ በሙሉ የሚለይ።

በቤት ውስጥ፣ የሕፃናት መታጠቢያ ወንበሮች ወደላይ ሊጠጉ እንደሚችሉ ይወቁ፣ እና ልጆች ከነሱ ሾልከው ወጥተው በመታጠቢያ ገንዳ ውስጥ በጥቂት ኢንች ውሃ ውስጥ ሊሰምጡ ይችላሉ። ጨቅላ ሕፃናት በመታጠቢያ ገንዳ ውስጥ ብቻቸውን መተው የለባቸውም፣ ለአንድ ደቂቃም ቢሆን።

ወላጆች እና ተንከባካቢዎች ቁጥጥር ካልተደረገበት ወደ መዋኛ ገንዳ ፣ ክፍት ውሃ ወይም መታጠቢያ ገንዳ እንዳይገቡ መከላከል አለባቸው።

በመጸዳጃ ቤት ውስጥ መስጠምን ለመከላከል ትናንሽ ልጆች በመታጠቢያ ቤት ውስጥ ብቻቸውን መተው የለባቸውም እና የመጸዳጃ ቤት መቆለፊያዎች ጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ።

ከተጠቀሙ በኋላ ወዲያውኑ ውሃ ከኮንቴይነሮች ለምሳሌ ከፓል እና ባልዲዎች መወገድ አለበት።

ዶ/ር መሐመድ በሽር የህፃናት ስፔሻሊስት ሐኪም አንብበው ሲጨርሱ በቀናነት ለወዳጅ ዘመድዎ ያጋሩ



https://t.me/ethiodoc

ዶክተር ኢትዮጵያ | Doctor Ethiopia

18 Nov, 06:27


የማህበራዊ ሚዲያ መስኮት ሱስ

ለድባቴ ፣ ራስ ለማጥፋት እሳቤ ፣ ለመካንነት... ወዘተ በኪሳችን የምንይዘው ስልክ መንስኤ እየሆነ ነው ።

አለም ረቀቅ ብላለች። ሰው መረጃን በቀላሉ እንዲያገኝ ፤ እንዲለዋወጥ ፤ የቦታ ርቀት ሳይገድበው እርስ በራሱ እንዲገናኝ ያደረጉት የፈጠራ ውጤቶች ናቸው ። የመገናኛና የመረጃ መሳሪያዎች የሚሰጡት ጥቅም ቁጥር ስፍር ባይኖረውም የራሳቸው የሆነ አሉታዊ ጫና አላቸው ። መመጠን መልካም ነው ።

የማህበራዊ ሚዲያ መሳሪያ-መስኮት አጠቃቀም ርዝማኔ ገደብ ሳይኖረው ሲቀር ለከፍተኛ የጤና ቀውስ ሊያጋልጥ እንደሚችል ጥናቶች ያሳያሉ ። ጠቅለል ተደርጎ Screen addiction /የማህበራዊ ሚዲያ -መስኮት ሱስ / ተብሎ ተሰይሟል ።

ይኸ ሱስ ልክ እንደ ኮኬይንና አልኮል ሱስ አንጎልን ምጥጥ አድርጎ ለከፋ የአእምሮና አካላዊ ህመሞች የሚዳርግ የዚህ ዘመን አዲስ የሱስ አይነት ነው ። Digital Drug ብለው ይጠርሩታል ማህበራዊ ሚዲያ መስኮትን !

ለአእምሮ ጤና መታወክ፣ ለህፃናት አንጎል እድገት መገታት፣ ለመካንነትና ሌሎች አካላዊ ህመሞች እየዳረገ ስላለው የማህበራዊ ሚዲያ መገናኛ ቁስ- መስኮት ሱስ'ን በወፍ በረር ላካፍላችሁ ፦

ድባቴ በአለማችን ላይ ብዙዎችን እየፈተነ ያለ የአእምሮ ጤና መታወክ ህመም ነው ። ብዙዎች ህመማቸውን በጓዳ ደብቀው ለህመማቸው ሌላ ህመም እየሰጡ ያሉ አሉ ። ለዚህ ደ'ሞ ትልቁን ሚና የሚጫወተው ለአእምሮ ጤና የሚሰጠው ትኩረትና ጥንቃቄ ነው ። አእምሮ እንደሚታመም ፤ የታመም አእምሮ መታከም እንደሚችል የሚያቁ ቢኖሩም ያልተረዱት ያይላሉ ።

በቀን በስልካችን መስኮት ላይ የምናሳልፈው ግዜ ሲረዝም ለልዩ ልዩ የአእምሮ ህመሞች እንጋለጣለ ። በአንድም ሆነ በሌላ መስተጋብር ከስልካችን መስኮት ጋር ያለን የሁለት-እዮሽ ግንኙነት በቀን ከሁለት ሰዓት በላይ ሲሆን ለድባቴ ፣ ራስን ለማጥፋት እሳቤ ፣ ከልክ ላለፈ ፍራቻ፣ በራስ አለመተማመን ፣ አሉታዊ ለሆነ ቅናት፣... ወዘተ ችግሮች እንድንጋለጥ ያደርጋል ። ሲደብረን ዘና ለማለት የከፈትነው ማህበራዊ ሚዲያ ወደ ድባቴ ይዞን ይገባል ።

ወጣቶች በአእምሮ ህመም መጠቃታቸው ሳይታወቅ ሒወታቸውን የሚነጠቁበት አጋጣሚ እየሰማን ነው ። እያየን ነው ። መሳቅ የአንድን ሰው አእምሮ ጤና አለመታወክ አያረጋግጥም ። ብዙዎች እየሳቁ ይቺን አለም ሳይወዱ ተገደው ተሰናብተዋል ። የአእምሮ ጤና መታወክ ብዙ ምክነያቶችና ውስብስብ ጉዳዮች ቢኖሩትም ቴክኖሎጂ በራሱ ለከፉ የአእምሮ ህመሞች እየዳረገ ነው ። የስልክ ፣ የታብሌት፣ የቲቪ... አጠቃቀማችን አሁን አሁን አሳሳቢ ደረጃ ደርሶ ውጤቱ መታየት ጀምሯል ። ከነዚህ ቁሳቁሶች ጋር ረዘም ላለ ሰዓት ስንቆይ በቀጥታ ለድባቴ አሳልፈው ይሰጣሉ።

ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ የታዳጊ ህፃናት አንጎል ጤና ነው ። ህፃናት በስልክ፣ በታብሌት ፣ በቲቪ-መስኮት ላይ አዘውትረው ሲቆዩ አዳጊ በሆነው አንጎል ላይ ከፍተኛ የሆነ አካላዊና መዋቅራዊ ለውጥ እንዲካሔድ ምክነያት እየሆነ ነው ። አንጎል እድገቱ ይገታል ፥ እድገቱን ያልጨረሰ አንጎል አለያም መዋቅሩ የተዘበራረቀ አእምሮ ውጤቱ የከፋ ነው ። ልጆችን ለስነ ባህሪ ፣ ለትት አቀባበል ፣ ለትኩረት ማነስ ፣... ለብቸኝነት ወዘተ ችግሮች ሰለባ እየደረጋቸው ነው ። ሁሉም ወደ ልጆቹ ይመልከትና ትዝብቱን ይውሰድ ። ከዚህ ባለፈ ምናልባትም ቀስ በቀስ ሰው ሊያስብለን የሚችለውን አንጎል ሊያሳጣና ስነ ምግባር የሌለው አለያም አረመኔ ትውልድ እንዲፈጠር ሊያደርግ ይችላል ። ገና አዲስ ክስተት ስለሆነ ተጠንቶ አላለቀም ፤ ነገ አስደንጋጭ የጥናት ውጤት መስማታችን አይቀርምና ካሁኑ እንጠንቀቅ ።

አንድ አመት ከስድስት ወር በታች ለሆነ ህፃን ለምንም አይነት የመገናኛ ቁሳቁስ መስኮት ማጋለጥ እንደማይገባ ምሁራን ይመክራለሉ ። በቀን ከ1-2 ሰዓት በላይ የትኛውም ልጅም ሆነ አዋቂ መጋለጥ የለበትም ። የህፃናትን አንጎል መጠበቅ የወላጅ ብቻ ሐላፊነት ሳይሆን የሁሉም ሐላፊነት ነው ።

ወንዶችን ለመካንነት መዳረጉ ሌላው የስልክ መዘዝ ነው ። በተለይ በፊተኛው የሱሪ ኪስ መያዛቸው ከስልኩ የሚወጣው Electromagnetic radiation and thermal heat የወንድ ዘር ፍሬ አመራረትን በማስተጓጎል የወንድ ዘር ፍሬ እንዲቀንስና የተመረተውም የመቀሳቀስ አቅሙን እንዲያጣ በማድረግ መካን ያደርጋል ። በቅርቡ በአለም አቀፍ ደረጃ የወንድ ዘር ፍሬ ቁጥር በከፍተኛ መጠን መቀነሱ ይታወቃል ። ብዙ ምክነያቶች ቢኖሩም የስልክ አስተዋፅዖም የሚዘነጋ አይደለም ። በፊት ኪስ አይያዙ ወይም ቦርሳ ይዘው በውስጡ አኑረው በጀርባዎ ይሸከሙ !

ሰው ስልኩን ከፍቶ ያንንም ያንንም ሲያይ በሰውነት ውስጥ የሚመረቱ ቅመሞች(Hormones) ተፈጥሯዊ ዑደታቸውን ትተው በዘፈቀደ መመረት ይጀምራሉ ። መብዛት የሌለባቸው ቅመሞች ይበዛሉ ፤መኖር ያለባቸው ቅመሞች ይጠፋሉ በዚህም ሰውን ለዘርፈ ብዙ አካላዊና ስነ አእምሯዊ ህመም ይዳረጋል ። ሰው የሚደሰተው በነዚህ ቅመሞች ነው፤ የሚከፋውም እንደዛው ። በነዚህ የሰውነት ውስጥ ቅመሞች በሚፈጠር መዘበራረቅ ሳቢያ ብዙ ህመሞች ይከሰታሉ ። አንድ ሰው በቀን ከ362 ግዜ በላይ ከስልኩ ጋር ይፋጠጣል ። በተለይ ሌሊት ጉዳቱ የከፋ ነው ።

እንቅልፍን በማዛባት ቀዳሚ መሳሪያ ነው ስልክን መነካካት ። መልእክት ለብዙ ግዜ መላላክ አለያም የላኩት መልእክት መልስ እስኪያገኝ ደጋግመው የስልኮን መልእክት መቀበያ ሳጥን ሲያዩ በውስጦ ጭቀትና መረበሽ ይፈጥራል ። ቀስ እያለ በራስዎ የመተማመን አቅሞን እያሟጠጠ ወደ ከፋ ስነ ልቦናዊ ቀውስ ይወስዶታል ። በሌላ መልኩ ሰው ስልኩን እያሸራተተ ሲቆይ ለውፍረት ይጋለጣል ። ውፍረትን ተከትለው የሚመጡ እንደ ልብ ህመም ፣ እስትሮክ፣ ደም ግፊት መጨመር ... ቀስ እያሉ ይከተላሉ ።

ሁሉም ሰው የስልክ አጠቃቀሙ ላይ ለራሱም ለልጆቹም እቀባ መጣል አለበት ። በተለይ ቲክቶክ ከልጅ እስከ ደቂቅ እያደቀቀው ይመሰላል ። ዛሬ በስሜት እና በምን አለብኝነት የምናደርጋቸው ያልተገቡ ድርጊቶች ነገ አእምሯችንን እየጎነተሉ ወደ ቀውስ ሊወስዱ ስለሚችሉ በልክ መጠቀም የራስን ነገ ማሳመር ነው ።

ዛሬ እያጨበጨበ ማኖ ያስነካሽ ነገ <ፈጣሪ ይማርሽ> ሳይሆን የሚልሽ <አብዝታው ነበር > እንደሚል እያሰብሽ ነገሺን በዛሬ አታስታምሚ !!

ሚስት በቲክቶክ ሱስ ፣ ባል በመጠጥና ጫት ሱስ ሲለከፉ ትዳር የመፍረስ አደጋ ይገጥመዋል፤ የትውልድ ቅብብሎሽን ሊያመክን የሚችል መጥፎ ልምምድ ነው ይሆናል ። ሱስን እንከላከል!

ዶ/ር መስፍን በኃይሉ: ጥቁር አንበሳ



https://t.me/ethiodoc

ዶክተር ኢትዮጵያ | Doctor Ethiopia

17 Nov, 12:15


"ስለ ቶንሲል የምናውቀው አና የምንሳሳተው ምንድን ነው?" - ዶ/ር ንጉሴ ጫኔ ፤ የህጻናት ስፔሻሊስት ሀኪም

- ቶንሲል ምንድን ነው?

ቶንሲል ለብዙዎቻችን እንደሚመስለን በሽታ አይደለም።
ቶንሲል ማለት ትንንሽ አበጥ ያሉ የተፈጥሮ የበሽታ መከላከያ አካላት ስብስብ ነው። ይህም በክብ ቀለበት ከምላስ ጀርባ የላንቃን የጎን ግድግዳ እና የላንቃን ክዳንና የአፍንጫን የውስጠኛ ክፍሎች ያስተሳስራል።

- ቶንሲል ጥቅሙ ምንድን ነው?
በአፍም በአፍንጫም የሚገቡ ተዋህስያንን መዋጋት ነው። የሰውነትን በር ከጠላት መከላከያ ነው።

- ቶንሲል እና እንጥል አንድ ናቸው?
ሁለቱም በላንቃ አካባቢ ይገኛሉ። ግንኙነታቸው ግን ጉርብትና እንጅ በአገልግሎት አይገናኙም።

- Uvula/እንጥል
እንጥል ማለት ከላንቃ ላይ የተንጠለጠለ ማለት ነው። ከቶንሲል ጋር ምንም ግንኙነት የለውም።

- የቶንሲል ህመም/tonsialiophayngitis?
ይህ የቶንሲል እና የላንቃ አካባቢ በተዋህስያን መወረር ነው።

- የህመም ምልክቶች
ትኩሳት ፣ ለመዋጥ መቸገር ፡ ራስ ምታት ፣ የአፍ መሽተት ፣ የአንገት ንፍፊት እብጠት ፣ ማንኮራፋት ፣ ሳል

የቶንሲል ህመም መተላለፊያ መንገዶች
1. በትንፋሽ ጠብታ
2. በንክኪ

- የባክቴሪያ ቶንሲል በብዛት የሚያጠቃው ማንን ነው?

የባክቴሪያ ቶንሲል ከሁለት አመት በላይ የሆኑ ህጻናትን የሚያጠቃ ሲሆን አብዛኛዎቹ ከ5-15 እድሜ ያሉት ይጠቃሉ። የቫይረስ ሲሆን ለጋ ህጻናትም ይጠቃሉ።

የቶንሲል ህመም ተያያዥ ችግሮች
1 ፡ መግል መቋጠር tonsiar, peritosilar or retropharyngeal abscess
2. የሳንባ ምች / የማጅራት ገትር
3. የልብ ህመም rheumatic heart disease ይህን ለመከላከል ቶንሲል እንዳመመን ወደ ጤና ተቋም መሄድ።
4. የኩላሊት ህመም PS glomerulonephritis
5. የቶንሲል መፋፋት adenotonsilar hyperthrophy

- የቶንሲል ህመም ህክምና
መጀመሪያ የባክቴሪያ ወይስ የቫይረስ ነው የሚለውን መለየት ያስፈልጋል።

መለያ መንገዶች
1. የቫይረስ ከሆነ የጉንፋን ምልክት አብሮ ይኖራል ግን አንዳንድ ጊዜ እንደ ቫይረስ ጀምሮ ወደ ባክቴሪያ ሊቀየር ስለሚችል ጥንቃቄ ይፈልጋል።
2. መግል የያዘ ከሆነ የባክቴሪያ ምልክት ነው ግን ይህን በደንብ እርግጠኛ መሆን ይፈልጋል።
3. ድድ፣ ከንፈር ወይም ምላስ የቆሰሉ ከሆነ የቫይረስ ምልክት ነው።
4. የነጭ የደም ሴል እና ተያያዥ ምርመራ

መድሃኒት
1. የህመም ማስታገሻ
2. እንደ ቶንሲሉ ህመም መነሻ የተለያዩ ጸረ ባክቴሪያ አለበለዚያም ፀረ ቫይረስ መድሃኒት
3. በቂ ፈሳሽ መውሰድ ረፍት ማድረግ።
4. ማር እና የውሃ ኢንፋሎት መታጠን
5. የብርቱካን ወይም ሎሚ ጭማቂ።

ለተጨማሪ መረጃዎች ቴሌግራማችንን


https://t.me/ethiodoc

ዶክተር ኢትዮጵያ | Doctor Ethiopia

16 Nov, 16:44


🧰 ያልተለመደ የማህፀን ደም መፍሰስ (AUB)

🩸የማሕፀን ውስጠኛው ክፍል ሁለት ንብርብሮች አሉት. ቀጭን ውስጠኛው ሽፋን አንዶመትርየም (endometrium) ይባላል. ወፍራም ውጫዊ ጡንቻ ግድግዳ ማዮመትርየም (myometrium) ነው.

🩸የወር አበባ እንቁላል ከተለቀቀ ከ10 እስከ 14 ቀናት ውስጥ ይከሰታል.

♦️ይህም ሆርሞኖችን ወይም የወሊድ መከላከያ በማይጠቀሙ ሴቶች እንቁላል ከእንቁልጢ (ovary) መለቀቁን ያመለክታል.

🩸በመደበኛ ሁኔታ እንቁላል ከእንቁልጢ የሚለቁ ሴቶች ላይ ; የኢስትሮጂን እና ፕሮጀስትሮን (estrogen and progesterone) ሆርሞን በብዛት ስለሚመረት በየወሩ ዉስጠኛውን የማህፀን ሽፋን (endometrium) እንዲወፈር ያደርገዋል ይህም ለእርግዝና ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል.

♦️ፅንስ ካልተፀነሰ, በወር አበባ ጊዜ የዉስጠኛው የማህፀን ሽፋን በወር አበባ መልክ ይፈሳል.

🩸በማረጥ ወይም የወር አበባ ማየት ባቆመች ሴት (postmenopausal) የእንቁላል ሆርሞን ምርት በአብዛኛው ይቆማል እና ሽፋኑ ማደግ እና መፍሰስ ያቆማል.

🩸በተለመደው ሁኔታ ከማህፀን በእያንዳንዱ የወር አበባ ጊዜ ከ 5 የሾርባ (80ml) ያነሰ የተወሰነ መጠን ያለው ደም ይፈሳል. መደበኛ ያልሆነ መጠን፣ የቆይታ ጊዜ ወይም የጊዜ ሰሌዳ ያልተለመደ የማህፀን ደም መፍሰስ እንደሆነ ይቆጠራል.

👌መደበኛ ያልሆነ መጠን:-ከ5 ሾርባ ማንኪያ በላይ ወይም በሷ ግምት ብዙ ነው ብላ ካሰበች
👌መደበኛ ያል የቆይታ ጊዜ:-ከ8 ቀን በላይ የቆየ
👌መደበኛ ያልሆነ የጊዜ ሰሌዳ:-ቢያንስ 24ቀን ሳይሞላ ወይም ከ38ቀን በላይ አሳልፎ የሚመጣ ከሆነ

ያልተለመደ የማህፀን ደም መፍሰስ መንስኤዎች

🩸ያልተለመደ የማህፀን ደም መፍሰስ የሚያስከትሉ አብዛኛዎቹ ሁኔታዎች በማንኛውም እድሜ ሊከሰቱ ይችላሉ, ነገር ግን አንዳንዶቹ በሴት ህይወት ውስጥ በተወሰነ የእድሜ ክልል የመከሰት እድላቸው ከፍተኛ ነው. ለምሳሌ:

🩸በወጣት ልጃገረዶች (young girls) ላይ ያልተለመደ የማህፀን ደም መፍሰስ — ከወር አበባ በፊት ደም መፍሰስ ሁልጊዜ ያልተለመደ (abnormal) እና ሕክምና የሚያስፈልገው ነው.
♦️በአደጋ
♦️በባዕድ አካል (እንደ መጫወቻዎች፣ ሳንቲሞች ሕፃናት ወይም የአእምሮ ህመም ያለባቸው ሰዎች ብልታቸው ዉስጥ ሊያስገቡ ይችላሉ )፣
♦️የብልት አካባቢ መቆሳሰል (አለርጂ ወይም ኢንፌክሽን ምክንያት)
♦️የሽንት ቱቦ ችግሮች
♦️በጾታዊ ጥቃት ምክንያት ሊከሰት ይችላል.

🩸በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ሴቶች (Adolescents)— ብዙ ልጃገረዶች ከመጀመሪያው የወር አበባ በኋላ ባሉት የመጀመሪያዎቹ ወራት ውስጥ መደበኛ ያልሆነ የደም መፍሰስ ችግር አለባቸው, ይህም እንቁላል ገና በመደበኛ መልኩ አለመልቀቁ እና የሆርሞን ዑደት አለመስተካከል ያመለክታል. እንዲህ ዓይነቱ መደበኛ ያልሆነ የደም መፍሰስ ብዙውን ጊዜ የሚለቀቀው የሴት ልጅ የሆርሞን ዑደት እና እንቁላል መደበኛ በሚሆንበት ጊዜ የሚስተካከል ነው .

♦️በዚህ ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሴቶች ያልተለመደ የደም መፍሰስ ተጨማሪ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ. ከእነዚህም መካከል: እርግዝና, ኢንፌክሽን እና የደም አለመርጋት ችግር ወይም ሌሎች የሕክምና ችግሮች

🎈ቅድመ ማረጥ ሴቶች (premenopausal women)— የተለያዩ ሁኔታዎች በጉርምስና እና በማረጥ መካከል በሴቶች ላይ ያልተለመደ የደም መፍሰስ ሊያስከትሉ ይችላሉ.

ለምሳሌ :-
♦️ እንቁላል ከእንቁሊጢ (ovary) በሚለቀቅበት ጊዜ በሆርሞን መጠን ላይ ድንገተኛ ለውጦች ሲኖር አነስተኛ መጠን ያለው ደም መፍሰስ ሊያስከትሉ ይችላሉ.

♦️የሆርሞን የወሊድ መቆጣጠሪያ ዘዴዎችን በሚጠቀሙ ቅድመ ማረጥ ሴቶች ላይ ጊዜዉን ያልተጠበቀ የደም መፍሰስ ሊከሰት ይችላል.

♦️ የማህፀን እጢ (uterine fibroid), የማህፀን አድኖሚዮሲስ (adenomyosis) ወይም አንዶመትሪያል ፖሊፕ (endometrial polyps) ናቸው.

♦️በቅድመ ማረጥ ሴቶች ላይ ያልተለመደ የማህፀን ደም መፍሰስ ሌሎች መንስኤዎች የሚከተሉትን ያካትታሉ:
❤️እርግዝና

❤️የማህፀን ጫፍ ወይም የማህፀን ሽፋን (endometrial) ካንሰር ወይም ቅድመ ካንሰር.

❤️የማህፀን ጫፍ ወይም የማህፀን ሽፋን (endometrial ኢንፌክሽን ወይም

❤️የደም መርጋት ችግር
❤️የዉስጥ ደዌ በሽታዎች: ለምሳሌ የእንቅርት በሽታ ፣ የጉበት በሽታ ወይም ሥር የሰደደ የኩላሊት በሽታ

❤️የሆርሞን የወሊድ መቆጣጠሪያ:- የሆርሞን የወሊድ መቆጣጠሪያ (ለምሳሌ, ክኒኖች ) የሚጠቀሙ ሴቶች በወር አበባ መካከል ያልተለመ የደም መፍሰስ (breakthrough bleeding) ሊያጋጥማቸው ይችላል. ይህ በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ወራት ውስጥ የሚከሰት ሲሆን, በማህፀን ውስጥ ባለው ሽፋን ላይ በሚደረጉ ለውጦች ምክንያት ሊሆን ይችላል. ከጥቂት ወራት በላይ የሚቆይ ከሆነ ተጨማሪ ምርመራ ሊያስፈልግ ይችላል እና/ወይም የተለየ የወሊድ መከላከያ ክኒን ሊመከር ይችላል.

🎈በማረጥ ሽግግር ውስጥ ያሉ ሴቶች (menopousal transition): የወር አበባ ከማለቁ በፊት አንዲት ሴት ማረጥ ሽግግር (menopousal transition) ውስጥ ታልፋለች . በማረጥ ሽግግር ወቅት, እንቁላል መደበኛ ባልሆነ ሁኔታ መለቀቅ(irregular ovulation) ይጀምራል.

♦️በማረጥ ሽግግር ውስጥ ያሉ ሴቶች የእንቁላል ከረጢት( ovaries) ኢስትሮጅንን መሥራታቸውን ሲቀጥሉ, ፕሮጄስትሮን ማምረታቸዉን ግን ይቀንሳል. እነዚህ የሆርሞን ለውጦች የማህፀን ሽፋን (endometrium) እንዲያድግ እና ከመጠን በላይ እንዲወፍር ሊያደርግ ይችላል, ይህም ፖሊፕ ወይም endometrial hyperplasia (ወፍራም የማህፀን ሽፋን ወደ ካንሰር ሊሸጋገር ይችላል) እንዲዳብር እና ያልተለመደ የደም መፍሰስ ሊያስከትል ይችላል.

♦️የማረጥ ሽግግር ሴቶች ያልተለመደ የማህፀን ደም መፍሰስ የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ የሆነበት ጊዜ ነው.

♦️በማረጥ ሽግግር ውስጥ ያሉ ሴቶች ካንሰርን፣ ኢንፌክሽንን እና የተለያዩ የዉስጥ ደዌ በሽታዎችን ጨምሮ ያልተለመደ የደም መፍሰስ ለሚያስከትሉ ሌሎች ሁኔታዎች ተጋላጭ ናቸው.

♦️የማያቋርጥ መደበኛ ያልሆነ የወር አበባ ዑደት ወይም ከፍተኛ የደም መፍሰስ ችግር ባለባቸው ሴቶች ላይ ተጨማሪ ምርመራ ያስፈልጋል.

🎈ያረጡ ሴቶች ( postmenopousal) — በርካታ ሁኔታዎች በማረጥ ወቅት ያልተለመደ የደም መፍሰስ ሊያስከትሉ ይችላሉ. በማረጥ ወቅት ያልተለመደ የደም መፍሰስ መንስኤዎች የሚከተሉትን ያካትታሉ:

❤️የሆርሞን መዳኒቶች

❤️የማህፀን ሽፋን መጠን መቀነስ(endometrial atrophy), በዝቅተኛ የሆርሞን መጠን ምክንያት.

❤️የማህፀን ሽፋን (endometrium) ቅድመ ካንሰር ወይም ካንሰር ለውጦች (hyperplasia/endometrial cancer)

❤️ፖሊፕ ወይም ፋይብሮይድ.
❤️የማሕፀን ኢንፌክሽን
❤️የደም ማቅጠኛ መዳኒቶችን መጠቀም.

ያልተለመደ የማህፀን ደም መፍሰስ የምርመራ ሂደት እና ሕክምናው ይቀጥላል...

ዶ/ር አሚር ኑሪ (የማህፀን እና ፅንስ እስፔሻሊስት)
ሃላባ ቁሊቶ ጀነራል ሆስፒታል 📞 0938291797



https://t.me/ethiodoc

ዶክተር ኢትዮጵያ | Doctor Ethiopia

15 Nov, 18:27


የምጥ ህመም ማስታገሽያ

ብዙ አይነት የምጥ ህመም ማስታገሽያዎች አሉ ሆኖም ግን በአይነቱ ለየት ያለና ዉጤታማ የሆነዉ የኢፒዱራል የምጥ ህመም ማስታገሽያ (epidural labour analgesia) ምንድን ነዉ?

የኢፒዱራል የምጥ ህመም ማስታገሽያ በጀርባ አጥንቶች መካከል በኢፒዱራል ክፍተት ዉስጥ በሚቀበር ረቂቅ በሆነ ትቦ አድርጎ የሚሰጥ የማስታገሽያ አይነት ነዉ።

በምጥ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ለተለያዩ ከአንገት በታች ለሆኑ ህመሞች እንደ ማስታገሽያነት ያገለግላል ። በተጨማሪም ታካሚው ሳይተኛ እንደ ከፊል አንስቴዢያነት ያገለግላል።

🔵 ጥቅሞች

- በምጥ ጊዜ ና ከምጥ በኋላ ያሉ ህመሞችን ያስታግሳል

- በእንግዴ-ልጅ ወደ ፅንሱ የሚደርሰዉን የደም ዝዉዉር ያሻሽላል።

- ከወሊድ በኋላ የሚመጡ ድብርተኝነት ይቀንሳል።

- በምጥ ህመም ምክንያት የሚመጡ የሱዉነት ጫናዎችን ይቀንሳል። ለምሳሌ በልብ፣ በጨጓራ፣በሳንባ ላይ የሚመጡትን ጫናዎች ይቀንሳል።

🟣በምን አይነት ታካሚዎች ላይ እንጠቀም?

- ለሁሉም ምጥ ላይ ላሉ እናቶች?
- በቀላሉ ደም የመፍሰስ ችግር የሌለባቸው
- የጀርባ ወይም የመቀመጫ ቁስል የሌላቸዉ
- የአዕምሮ እጢ ወይም ከፍተኛ የሆነ የአዕምሮ ዉስጥ ግፊት የሌላቸዉ መሆን አለባቸዉ።

- ሆኖም ግን በሀገሪቱዋ ዉስጥ ባለው እጥረት ምክንያት በመንግስት ሆስፒታሎች በተወሰኑ የልብ ወይም ሌላ ተጓዳኝ በሽታ ላላቸዉ እናቶች ይሰጣል።

⚫️የጎንዮሽ ጉዳቶች?

- ጥቂትና በቀላሉ የሚታከሙ የጎንዮሽ ጉዳቶች አሉት። እነሱም
- የደም ግፊት የማዉረድ
- የማሳከክ
- የራስ ምታት- ጋደም በማለትና ፈሳሽ በመዉሰድ ማስታገስ ይቻላል።
- የጀርባ ህመም- እረፍት በመዉሰድ ና ከባሰም በአፍ በሚወሰዱ ማስታገሻዎች ይጠፋል።

⚪️የሚያስፈልጉ ዝግጅቶች

- የሀኪም ምርመራ
- አንዳንዴም የደም ምረመራ ሊያስፈልግ ይችላል።
- ከሀኪሙ ጋር ከተወያዩ በኋላ የስምምነት ፍርሚያ ያስፈልጋል።
- ምግብም ሆነ ፈሳሽ አይከለክልም።

🟤 ኢፒዱራል የማስገባቱ ሂደት እንዴት ይመስላል?

- መጀመሪያ ታካሚዉ/ነፍሰጡር በጎን ማስተኛት ወይም አጎንብሰው አንዲቀመጡ ማድረግ።

- የደም ግፊት መለኪያ ና የፅንሱን መቆጣጠርያ መሳሪያዎች ማድረግ።

- በመቀጠልም ጀርባቸውን በአልኮል ወይም ተመሳሳይ በሆነ አንቲሴፕቲክ ማጠብ።

- የሚቀባ ወይም አነስና አጠር ባለች መርፌ የሚሰጥ ማደንዘዣ በጀርባ መስጠት። በሂደቱ ላይ ያለን ህመም ይቀንሳሉ።

- ቀጥሎም ወደ አፒዱራል ክፍተት የሚገባዉን መርፌ ማሳለፍ።

- በመርፌ ዉስጥ የሚያልፈዉን ረቂቅ ትቦ ማስገባት ና መርፌውን ማዉጣት።

- በመጨረሻም በፕላስተር ቦታ አስይዞ ማጣበቅ።

- አንስቴዝዬሎጂስቱም ያዘጋጀዉን የአንስቴዝያ መድሀኒት በመመጠን በትቦዉ አድርጎ ይሰጣል። ከጎንም በመሆን የደም ግፊትና የፅንሱን ሁኔታ ይከታተላል።

- ባስፈለገ ልክ በየስዓቱ ወይም ከዚያ በታች በሆነ ጊዜ መድሀኒቱን ይሰጣል።

- ፅንሱ ከተወለደ ከተወሰነ ስዓት ወይም አንድ ቀን በኋላም ትቦዉን ማዉጣት ይቻላል።

ዶ/ር ይስሐቅ አብርሃም ፥ በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የአንስቴዝዬሎጂ ስፔሻሊስት




https://t.me/ethiodoc

ዶክተር ኢትዮጵያ | Doctor Ethiopia

15 Nov, 07:10


ነፍሰጡሮች ላይ የሚበረታው እና ለሞት ሊዳርግ የሚችለው የጥርስ ኢንፌክሽን

ከእርግዝና ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ ውስብስብ የሆኑ የሰውነት ውስጥ ለውጦች/physiological changes/ለተለያዩ የአፍ ውስጥ ችግሮች ሊያጋልጡ ቢችሉም;ብዙ ሴቶች ግን በእርግዝናቸው ወቅት ለአፍ ውስጥ ጤና እንክብካቤ ያን ያህል ትኩረት ሲሰጡ አይታይም።

እናም ይህ በቂ ያልሆነ/የተገደበ/የአፍ ውስጥ ጤና ታድያ ከእርግዝናው አጠቃላይ የሰውነት ውስጥ ለውጦች ጋር ተዳምሮ ለተለያዩ ከጥርስ እና አካባቢው ካሉ አካላት ለሚነሱ ኢንፌክሽኖች (ህመሞች) በቀላሉ ከማጋለጥ አልፈው እጅግ የከፋ የጤና መታወክን ባስሲል ደግሞ የነፍሰጡሯን እና ፅንሱን ህይወት አደጋ ላይ እሰከመጣል ወይም እስከማሳጣት ሊያደርስ የሚችል ኢንፌክሽንን ሊያስከትል ይችላል።

ከእርግዝና ጋር ተያይዘው የሚከሰቱት ጤናማ እና ጊዜያዊ የሆኑ ለውጦች በአብዛኛው ከሆርሞን ጋር የተያያዙ እና እንዲሁም አካላዊ ለውጦች ሲሆኑ ;እነኚህም ለውጦች በተለያዩ የሰውነታችን ክፉሎች ወይም ስርአቶች ላይ የተለያዩ ተፅኖዎችን ሊያሳድሩ ይችላሉ። ነገር ግን አብዛኛዎቹ ተፅኖዎች ጊዜያዊ እና ሰውነታችን በራሱ ተፈጥሮአዊ መንገድ ሊቆጣጠራቸው ሚችላቸው ወይም ለክፉ የማይሰጡ እና ከወሊድ ቡሀላ ሚስተካከሉ ሲሆኑ : አንዳንዶቹ ግን በጊዜ ታውቀዉ ልንቆጣጠራቸው ካልተቻለ ወደ ከፍተኛ የጤና ችግሮች ሊሻገሩ ይችላሉ።

በእርግዝና ላይ ያለች ሴት በተለያዩ ምክንያቶች ለተለያዩ ኢንፌክሽኖች የተጋለጠች ስትሆን : ከእነዚህም ውስጥ ደግሞ የአፋ ውስጥ ወይም የጥርስ ኢንፌክሽን አንዱ ነወ።

ለጥርስ /የአፍ ውስጥ ኢንፌክሽን አጋላጭ የሆኑ ዋነኞቹ ከእርግዝና ጋር ተያይዘው የሚመጡ ለውጦች:

1.የአፍ ውስጥ ስጋ አካላት; ድድን ጨምሮ በቀላሉ መቆጣት:ማበጥ:መቅላት:በቀላሉ መቆራረጥ/መበጣጠስ

2.የሰውነት በሽታ የመከላከል ሀይል ለውጥ;የበሽታ መከላከል አቅም ፍጥነቱ መቀነስ/መዘግየት..

3.የእርግዝ ወቅት የስኳር ህመም እና የምራቅ መቀነስ

4.ከእርግዝና ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ ሌሎች አካላዊ ለውጦች እና ተጓዳኝ ህመሞች

እነኚህ ከላይ የተዘረዘሩት እና ሌሎች ያልተጠቀሱ ከእርግዝና ጋር ተያይዘው የሚመጡ ለውጦች ታድያ ለአፍ ውስጥ እና ለጥርስ ኢንፌክሽኖች መነሻነት :እድገት እና ወደ ከፍተኛ ደረጃነት መሸጋገር የራሳቸው ድርሻ አላቸው።

እናም መነሻቸው ቀለል ያሉ የሚመስሉ ወይም የሆኑ የጥርስ እና ተያያዥ አካላት ኢንፌክሽኖች ከእርግዝናው ጋር ተያይዘው ከሚመጡ የሰውነት ውስጥ ለውጦች እና ሌሎች ተጨማሪ ነገሮች እንዲሁም ከነፍሰጡሯ ወይም ከአንዳንድ የጤና ባለሞያዎች ቸልተኝነት ጋር ተዳምሮ ነፍሰጡር ሴቶችን ከፍተኛ ለሆነ እና የራሳቸውንም ሆነ የፅንሱን ህይወት አደጋ ላይ ለሚጥል የጥርስ ኢንፌክሽን ሊያጋልጣቸው ይችላል።

ከእነዚህ አደገኛ ከሆኑ የጥርስ ኢንፌክሽኖች ውስጥ አንዱ ታድያ ሉድ-ዊግስ አንጂና (Ludwig's angina) ተብሎ ይታወቃል።

ይህ ከቀላል የጥርስ መቦርቦር ወይም ተያያዥ የአፍ ውስጥ አካላት ኢንፌክሽን ተነስቶ ወደ ተለያዩ የፊታችንክፍሎች:በአንገታችን እና በምላሳችን ስር ባሉ ስጋዎች ውስጥ በፍጥነት በመሰራጨት (እብጠት በመፍጠር) አልፎም ወደታች እስከ ደረታችን ሊወርድ በመቻል የላይኛውን የመተንፈሻ አካላቶቻችንን በመዝጋት(አየር ወደ ሳንባ መተላለፍ በመከልከል) ለከፍተኛ ህመም ስቃይ እና አልፎም ለሞት ሊዳርግ የሚችል የጥርስ ኢንፌክሽን ሲሆን :በእርግዝና ወቅት ላይ ከሆነ የተከሰተው ደግሞ የሚያስከትለው የጤና ቀውስ እጅግ የከፋ እና የእናቲቱንም ሆነ የተሸከመችውን ፅንስ ሂይወት እስከመንጠቅ የደረሰ ነው።

በአብዛኛው የሀገራችን ህብረተሰ ዘንድ የጥርስ ህመም ሲከሰት ወደ ተገቢው ህክምና ባለሞያ ቀጥታ ከመሄድ ይልቅ ካለማወቅም ይሁን ከቸልተኝነት እና የጥርስ ህመምን' ቀላል 'አርጎ ከማየትም የተነሳ በተለምዶ የሚወሰዱ የባህል መድሃኒቶችን /መፍትሄዎችን መሞከር ወይም የተለመዱ ጊዜያዊ ማስታገሻዎችን/ መድሃኒቶችን ሀኪም ሳያማክሩ በራስ በመውሰድ ለጊዜው ህመሙን ለማርገብ መሞከር እና ህመሙ በጣም ሲብስ ወይም ለእነዚ ጊዜያዊ መፍትሔዎች አልመለስ ሲል ብቻ ወደ ሀኪም ዘንድ መሄድ የተለመደ ነው።

እናም ይህ ባለማወቅም ይሁን በቸልተኝነት የሚደረግ መዘናጋት ታድያ በተለይ በእርግዝና ወቅት ላይ ሲሆን ለዚህ አደገኛ የሆነ የጥርስ ኢንፌክሽን ሲያጋልጥ እና ብዙ ዋጋ ሲያስከፍል ይታያል።

የጥርስ ኢንፌክሽኑ ወደ አደገኛ ደረጃ አየሄደ ነው የምንለው መቼ ነው?

1.ትኩሳት ሲኖረው
2.ከፍተኛ እብጠቶች ፊት ላይ:አንገት ላይ:ከምላሳችን ስር:በሁለቱም የፊት ጎኖች ላይ ሲከሰት /በፍጥነት እያደገ ሲሄድ
3.ምግብ ለመዋጥ መቸገር እና ማቅለሽለሽ ሲኖር
4.ለመተንፈስ መቸገር ሲኖር
5.አፍችን በከፊል ወይም በሙሉ ለመክፈት ስንቸገር / ሳንችል ስንቀር
6.ድካም እንዲሁም የምራቅ ከአፋችን ውጪ መዝረክረክ ሲኖር...

መፍትሔዎቹ

*በእርግዝና ወቅት 'ቀላል'የሚባሉ የጥርስ ህመሞች እንኳን ቢሆኑ በጊዜ/በቶሎ እና በተገቢው ባለሞያ መታከም ይኖርባቸዋል

**በእርግዝና ወቅት ላይ ከጥርስ ህመም እና ህክምና ጋር ተያይዘው ያሉ የተሳሳቱ አመለካከቶች/አረዳዶችን ማስተካከል
"በእርግዝና ወቅት ጥርስ ፈፅሞ አይነቀልም"
"በእርግዝና ወቅት ለጥርስ ህከምና የሚሰጡ መድሃኒቶች ሁሉ ፅንሱ ላይ ጉዳት ያደርሳሉ"
"የጥርስ ህመም ቀላል ነው እርግዝናውን ከተገላገልኩ ቡሀላ እታከመዋለሁ"
"በእርግዝና ወቅት የጥርስ ራጆች እና ህክምናዎች ፅንሱን ይጎዳሉ"...

እነዚህ እና ሌሎችም የተሳሳቱ ወይም በከፊል የአረዳድ ችግር ያለባቸው በህብረተሰቡ ዘንድ በስፋት የተሰራጩ አመለካከቶች ታድያ ብዙዎችን እርጉዝ ሴቶች የጥርስ ህመም ሲያጋጥማቸው ወደ ተገቢው ባለሞያ እንዳይሄዱ የሚያዘናጓቸው ምክንያቶች ሲሆኑ ይህም ለከፍ የጥርስ ኢንፌክሽን ሲዳርጋቸው ይታያል።

ህክምናዎቹ

*ህክምናው ሁኔታው በሚፈቅደው ልክ የእናቲቱን ጥቅም (ጤና ያስበለጠ) ያስቀደመ እንዲሁም በፅንሱ ላይ ሊደርስ የሚችልን ማነኛውም ጉዳት መቀነስን አለማው ያደረገ ነው።

*በእርግዝና ወቀት ላይም እንኳን ቢሆን የተለያዩ የአፍ ውስጥ እና የጥርስ ኢንፌክሽኖች በተለያዩ የጥርስ ህክምናዎች:ጥርስን ከመንቀል ጀምሮ የተመረጡ መድሃኒቶች እስከመስጠት እንዲሁም መለስተኛ እና ብሎም ከፍተኛ የቀዶ ህክምናዎችን በተገቢው ባለሞያ:ሁኔታው ባገናዘበ መልኩ ተገቢውን ወቅት/ጊዜ በማመቻቸት በእናቲቱም ሆነ ፅንሱ ላይ ጉዳት በማየስከትል/በቀነሰ መልኩ ሊሰጥ ይችላል።

*ማንኛውም የጤና ባለሞያ ቢሆን የእዚህ አይነት አደገኛ የሆነ የጥርስ ኢንፌክሽኖችን ምልክት ምታሳይ ነፍሰጡር ሴት ስታጋጥመው ያለምንም ማመንታት ታካሚዋን በአስቸኳይ ተገቢውን ህክምና ወደምታገኝበት ሆስፒታል በተለይ : የማግዚሎፋሻል ሰርጅን :የማህፀን እና ፅንስ እንዲሁም የአንስቲዢኦሎጂስት ስፔሻሊስቶች እና የፅኑ ህሙማን ከፍል ወደያዘ ተቋም መላክ ይኖርበታል።

ቸር ያሰማን!!

Dr. Fuad M, Assi.Prof. of Oral & Maxillofacial surgery



https://t.me/ethiodoc

ዶክተር ኢትዮጵያ | Doctor Ethiopia

14 Nov, 12:47


ከምጥ በፊት ሚከሰት የእንሽርት ውሀ መፍሰስ (Pre Labour Rupture of Membrane) ምንድነው?

ከምጥ በፊት ሚከሰት የእንሽርት ውሀ መፍሰስ ማለት ፅንሱ ከ28 ሳምንት በላይ ነገር ግን ከ37 ሳምንት በፊት ፅንሱን ሸፍኖ ከያዘው ሽፋን አምልጦ ሚወጣ ፈሳሽ ሲሆን ይህ ሁኔታ ከ28 ሳምንታት በፊት ከተከሰተ ውርጃ (Inevitable Abortion) የመሆን ዕድሉ በጣም ከፍተኛ ነው። በተጠኑ ጥናቶች መሰረት ከ አጠቃላይ እርግዝናዎች ከ 7-10% እናቶች በዚህ ችግር ተጠቂ ሊሆኑ ይችላሉ።

ከምጥ በፊት ሚከሰት የእንሽርት ውሀ መፍሰስ በምን ምክንያት ሊከሰት ይችላል?

1) ከእናት ጋር ተያይዞ በሚመጡ ችግሮች እነዚህም

፦ ከማህፀን በር ጫፍ በሚነሱ ኢንፌክሽኖች (STI) አማካኝነት የሚመጣ የእነንሽርት ውሀ ኢንፌክሽን (chorioamnionitis)

፦ቀደም ብሎ በነበረ እርግዝና ተመሳሳይ ያለጊዜው የእንሽርት ውሀ መፍሰስ ከነበረ (Previous history of PROM)

፦ የማኅጸን ጫፍ ወይም በር አለመጠንከር ይህም ሰውነታችን ላይ ያሉ ጥንካሬን ሚሰጡ (Collagens) በተለያዩ በሽታዎች እንደ(Congenital DES Syndrome) ሲጠቁ ሊከሰት የሚችል ነው።

2) ከፅንሱ ጋር ተያይዞ በሚመጡ ችግሮች ከነዚህም መካከል
፦ማህፀን ውስጥ የሚገኘው የእንሽርት ውሀ መብዛት (Polyhdroaminos)

፦ ትክክለኛ ያልሆነ የፅንስ አቀማመጥ ይህም በይበልጥ የፅንሱ አንድ እግር የቀደመ ከሆነ (Footling) እና የፅንሱ አቀማመጥ ወደ ጎን መሆን (Tranverse Lie)

፦በማህፀን ውስጥ የሚከሰት ከአንድ በላይ እርግዝና (Multiple pregnancy ) ለእንሽርት ውሀ ያለጊዜው መፍሰስ አጋላጭ ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ።

3) በእርግዝና ወቅት በሚሰሩ አንዳንድ ምርመራዎች
፦ ከእንሽርት ውሀ በሚወሰድ ምርመራ (Aminocentsis)

፦ የፅንሱን አቀማመጥ ለማስተካከል በሚደረግ ጥረት (External cephalic version) 

፦ከፅንሱ እምብርት የደም ናሙና በሚወሰድበት ወቅት (Percutaneous Umblical sampling)

እንዲሁም ሆድ ላይ በሚያጋጥም ድንገተኞ የመመታት አደጋ እንዲሁም ምክንያታቸው ባልታወቀ (Idiopathic) የእንሽርት ውሀ ምጥ ሳይመጣ ያለጊዜው ሊፈስ ይችላል።

ከምጥ በፊት ሚከሰት የእንሽርት ውሀ መፍሰስ ምልክቶቹ ምንድናቸው?

፦ ድንገተኛ የሆነ የበዛ ውሃማ ወይም ፈዛዛ ቢጫ ከማህፀን የሚወጣ ፈሳሽ በውስጥ ልብስ ላይ መገኘት። አንዳንድ ጊዜም ያለማቋረጥ አነስተኛ መጠን ያለው ከማህፀን የሚወጣ ፈሳሽ ብቻ ሊስተዋል ይችላል፣

፦ የማህፀን መጠን ፅንሱ ካለበት ዕድሜ ጋር አለመመጣጠን

፦ ከነዚህ ባለፈ ግን ባለሙያ አማካኝነት በትክክል የእንሽርት ውሀው ከማህፀን መሆኑነን በ Sterile speculum Examination ቀጥታ ሲፈስ በማየት እርግጠኛ መሆን ይቻላል።

ከላይ ከተጠቀሱት ባሻገር የእንሽርት ውሀ መሆኑን በባለሙያ አማካኝነት ለማረጋገጥ ከሚሰሩ የተለያዩ ምርመራዎች መካከል ከፈሳሹ ከሚወሰድ ናሙና
Microscopic Ferning test, Nitrazine paper test, እንዲሁም አልትራሳውንድ የእንሽርት ውሀው ያለበትን መጠን እና አጠቃላይ ፅንሱ ያለበትን ሀኔታ ለማየት እንጠቀመዋለን።

የእንሽርት ውሀ ያለጊዜው ከፈሰሰ ምን ማረግ ይኖርብኛል?

የእንሽርት ውሀ ያለጊዜው ከፈሰሰ በአፋጣኝ ወደ ጤና ተቋም መሄድ የመጀመሪያው ተግባር ሲሆን ይህም የፅንሱንም እንዲሁም የእናቷን ሁኔታ በቅርበት ለመከታተል ይረዳል ለዚህም በጤና ተቋም ከሚሰጡ ህክምናዎች መካከል

1) በጤና ተቋም ውስጥ አልጋ በማስያዝ የፅንሱን የልብ ምት ፣ የእናትየውን ሙቀት ፡ የማህፀን ህመም ፡ ነጣ ያለ እንዲሁም ሽታ ያለው ከማህፀን የሚወጣ ፈሳሽ ፣ እንዲሁም የደም ናሙና በመውሰድ ኢንፌክሽን ጠቋሚ ተህዎሶች መኖራቸውን በቅርበት ለመከታተል ይረዳል

2) የእንሽርት ውሀ ያለጊዜው መፍሰስ ፅንሱን በቀጥታ ከመራቢያ አካላት ለሚነሱ በሽታ አምጪ ተህዋሲያን ተጋላጭ በማድረግ ለኢንፌክሽን (chorioaminonitis) ስለሚዳርጉ ፀረ ባክቴርያ መከላከያ እንደ አግባበብነቱ መውሰድ ይኖርባታል።

3) ለሳንባ ማጠንከሪያ ሚሆኑ መድሀኒቶች (Corticosteroids) ያለጊዜው የፈሰሰ የእንሽርት ውሀ ከጥቂት ቀናት ወይም ሰዓታት በዃላ ያለጊዜው ምጥ እንዲመጣ በማድረግ ፅንሱ ያለጊዜው እንዲወለድ በማድረግ የሳንባን እድገት ወይም ጥንካሬን በመገደብ ፅንሱ ሲወለድ ለአተነፋፈስ ችግር እንዲሁም ለድንገተኛ የጨቅላ ህፃን ሞት እንዳይዳረጉ ይረዳል።

4) ለተወሰኑ ጊዜያት ምጥ እንዳይመጣና ለሳንባ ማጠንከሪያ ሚሆኑ መድሀኒቶች ለመስጠት Tocolytics እንዲሁም የእንሽርት ውሀው የፈሰሰው ከ 32 ሳምንት በፊት ከሆነ የፅንሱን የብሬን እድገት ላይ ችግር እንዳይፈጠር (Neuroprotection) Magnesium sulfate ልንጠቀም እንችላለን።

የእንሽርት ውሀው ከፈሰሰ በኋላ እርግዝናው ሚቋረጠው (ምወልደው) መቼ ነው?

፦ የፅንሱ የልብ ምት ከሚጠበቀው በላይ የጨመረ ወይም የቀነሰ ከሆነ (NRFHR)
፦የእንሽርት ውሀ ኢንፌክሽን (Chorioaminonitis) ካጋጠመ ይህም በእናትየውን ሙቀት መጨመር ፡ የማህፀን ህመም ፡ ነጣ ያለ እንዲሁም ሽታ ያለው ከማህፀን የሚወጣ ፈሳሽ ፣ እንዲሁም የደም ናሙና በመውሰድ ኢንፌክሽን ጠቋሚ ተህዎሶች አማካኝነት ሊገለፅ ይችላል

፦የእንግዴዉ ልጅ ከማህፀን ግድግዳ ጋር መላቀቅ
እነዚህ ችግሮች ከታዩ እርግዝናው ተቋርጦ ወድያውኑ መውለድ ይኖርባታል።

ነገር ግን ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች ካልተስተዋሉ በቅርብ ክትትልና ህክምና እርግዝናውን እስከ 37 ሳምንት ከደረሰ በኅላ መውለድ ምትችል ቢሆንም እንደአግባብነቱም ከ34 ሳምንት ጀምሮ ሊወለድ ይችላል ይህም ምጥ በራሱ ጊዜ ያልመጣ ከሆነ የምጥ መርፌን በመጠቀም እንዲሁም ከላይ ከተጠቀሱት አደገኛ ምልክቶች ከታዩ በቀዶ ጥገና (cesarean section ) በአፋጣኝ ልትወልድ ትችላለች።

References
- ACOG (The American College of
Obstetricians and Gynecologists)
- DC Duta 10th edition

ሰናይ ቀን ይሁንላችሁ
Dr. Ephream Adane


https://t.me/ethiodoc

ዶክተር ኢትዮጵያ | Doctor Ethiopia

12 Nov, 05:09


የኮለስቴሮል መዛባት (Dyslipidemia) ጥቂት ነጥቦች

1.የሰውነት ቅባት መጠን ጠቃሚ እና ጎጂ አይነቶች ተብለው ለ 2 ይከፈላል።

2.የሚፈለገው ጠቃሚው እንዲጨምር መጥፎው እንዲቀንስ ነው። ይህም ምን ያህል እንደሆነ በላቦራቶሪ ገደብ አለው።

3.ብዙ ጊዜ እንደምታሰበው የወፍራም እና በ እድሜ የገፉ ሰዎች በሽታ ብቻ አይደለም።

4.በዘር (በቤተሰብ) የሚተላለፍ አይነትም አለ።

5.ከሚታወቁ መንስኤዎቹ መካከል ከመጠን ያለፈ አልኮል መጠጦችን መውሰድ ÷ስኳር ወይም ግፊት ካለ ÷ የእንቅርት ችግር ካለ ÷''Nephrotic syndrome'' የሚባለው የኩላሊት ችግር ካለ÷በቂ ያልሆነ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ

6. ከምግቦች ብዙ የኮሌስቴሮል መጠን ያላቸው ቀይ ስጋ ÷ የአሳማ ስጋ ÷ጉበት ÷ኩላሊት ÷እንቁላል በተለይም አስኳሉ ÷ ቅቤ ÷ የዶሮ ቆዳ

7. በሌላ በኩል አቮካዶ ÷ ተልባ÷ እና ኦቾሎኒ ''phytosterols'' የሚባሉ ንጥረ ነገሮችን ስላሏቸው ኮሌስቴሮል ከ አንጀት ወደ ደም እንዳይገባ ይከላከሉልናል።

8. የኮሌስተሮል መጠን ከተዛባ የደም ዝውውር ስለሚዛባ ለልብ ችግር ÷ ጭንቅላት ውስጥ የደም መፍሰስ ወይም ደምስር መጥበብ ÷የእግር ደምስሮች ስጎዱ እስከ ''gangrene'' ልያደርስም ይችላል። ለአሞት ከረጢት ጠጠርም ያጋልጣል። ለቆሽት መቆጣትም (PANCREATITIS) መንስኤ ነው።

9.ምንም የኮሌስቴሮል መጠን መዛባት ሳይኖር ሐኪም እንደሁኔታዉ ወስኖ የኮሌስቴሮል መድሀኒት እንዲወስዱ ልያዝ ይችላል። ለምሳሌ ግፊት ÷ ስኳር ÷ ልብ ÷ 'STROKE' ችግር ካለ (ስለዚህ ደሜን አሰርቼኮ ኮሌስቴሮሌ NORMAL ነው አልወስድም ማለት አይቻልም)

ዶ/ር ጋሻሁን መኮንን (የዉስጥ ደዌ ሀኪም, ጅማ ዩኒቨርሲቲ)



https://t.me/ethiodoc

ዶክተር ኢትዮጵያ | Doctor Ethiopia

11 Nov, 17:48


https://www.tiktok.com/@dr_yonas/video/7436078179640560952?_r=1&u_code=dm4a4ge08lalll&preview_pb=0&sharer_language=en&_d=e24l7mbh7k0hl2&share_item_id=7436078179640560952&source=h5_m&timestamp=1731347214&user_id=7038828452133782533&sec_user_id=MS4wLjABAAAAxaDRMuRyFWNO5vyQHt48Pu0VA4t79Bfpaxx8cHel0N35d6XAQ7csq9ihMipmcX7a&social_share_type=0&utm_source=telegram&utm_campaign=client_share&utm_medium=android&share_iid=7418247052183734021&share_link_id=8d71b233-814c-4dda-b0ad-3d4e8dc5faa2&share_app_id=1233&ugbiz_name=MAIN&ug_btm=b8727%2Cb2878&link_reflow_popup_iteration_sharer=%7B%22click_empty_to_play%22%3A1%2C%22dynamic_cover%22%3A1%2C%22follow_to_play_duration%22%3A-1.0%2C%22profile_clickable%22%3A1%7D&enable_checksum=1

ዶክተር ኢትዮጵያ | Doctor Ethiopia

10 Nov, 10:13


የወንዶች የወሲብ ያለማድረግ ችግሮች

የግብረ ስጋ ግንኙነት በሰዉነታችን ዉስጥ አራት ዋና የስርአት ቅንብር ዉጤት ነዉ። የደም ስር ፣ የነርቭ ስርአት፣ የሆርሞኖችና የአእምሮ ዉህድ ዉጤት ነዉ።

ከነዚህ የአንዱ ወይም ከአንድ በላይ ችግሮች የተለያዬ የወሲብ ችግሮችን ያመጣሉ።

የብልት መቆምና እንደቆመ ለግንኙነት ለሚያስፈልግበት ጌዜ መቆየት በዋናነት ወደብልት በሚሄድ የደም ስር በደም መወጠር የሚከሰት ሲሆን የነርቭ መልእክቶችና የሆርሞኖች መልእክቶች በየአእምሮ መልእክቱን የመተንተን ዉጤት ይወሰናል። ስለሆነም የግብረስጋ ግኑኙነት በዋናነት የሚደረገዉና የሚቆጣጠረዉ በእምሮችን ክፍል ነዉ ።

በወንዶች ላይ ሊከሰቱ የሚችሉ የወሲብ ችግሮች ሶስት አይነት ናቸዉ።

1-የብልት የግብረስጋ ግንኙነት በሚፈለገዉ ግዜ ያለመቆም (erectile dysfunction)
በወነዶች ላይ ከሚከሰቱ ችግሮች ዋንኛዉ ሲሆን እድሚያቸው ከ20-75 አመት በሆኑት ላይ ከ6ሰዎች በአንዱ ላይ ይከሰታል(16%)

ችግሮቹ የሚከሰቱበት ምክንያቶ፦
ዉፍረት ፣ ሲጋራ ማጨስ፣ የልብ የደም ስር ችግሮች ፣ የተወሰኑ መድሀኒቶች (ለድባቴ የሚወሰዱ: ለደም ግፊት የፈንገስ መድሀኒቶች)

የስነአእምሮ ሁኔታ ፦የድባቴ ፣ የዉጥረት፣ የፍራቻ ችግሮች

የነርቩ ችግሮች፦ ስትሮክ ፣የጀርባ ጉዳቶች ፣ የህብለሰረሰር ችግሮች

የሆርሞን መዛባት ፦የስኳር በሽታ ፣ የወንድ ሆርሞን (ቴስቴስትሮን) እጥረት

2- የፍላጎት መቀነስ ወይ አለመኖር (diminished libido) በተለይ እድሜ እየጨመረ በሚመጣበት ወቅት የመከሰት ሁኔታ ይጨምራል።

3-የመርጨት ችግሮች (በፍጥነት መርጨት: በመዘግየት ወይ ያለመርጨት ችግሮች ሊሆኑ ይችላሉ) - abnormal ejaculation
በፍጥነት መርጨት (premature ejaculation ) ከሶስት ወንዶች በአንዱ ላይ ሊከሰት ይችላል። በሴቷ ብልት ዉስጥ በተለይ ከ60ሰከንድ በታች ከተረጨ ችግር እንዳለ ያመለክታል።

ይህ ችግር በወንዶች ላይ ከፍተኛ ዉጥረትና የተስፋ መቁረጥ ችግሮች በማምጣት ወንዶችን ከግብረስጋ ግንኙነት መራቅን ብሎም ከትዳር መፋታትን ያስከትላል።

የችግሮችን መንስኤ በማወቅ በህክምና ባለሙያዎች ሊረዱ ስለሚችሉ ያማክሩ ።

ዶ/ር ዘለቀ ከበደ ፤ የማህፀንና ፅንስ ስፔሻሊስት ና የህብረተሠብ ጤና አጠባበቅ ባለሙያ (MD, MPH, gyn-obs specialist)



https://t.me/ethiodoc

ዶክተር ኢትዮጵያ | Doctor Ethiopia

10 Nov, 05:17


የሐሞት ጠጠር የቀዶ ህክምና የሚያስፈልገው ለምንድነው?

✔️ የሐሞት ጠጠር ማለት በተለያዩ ምክንያቶች የሐሞት ፊኛ ውስጥ የሚፈጠር ጠጠር ነው።

ታዲያ ይህ ጠጠር ያለበት ሰው ቅባትነት ያላቸውን ምግቦች በሚመገብበት ጊዜ ጠጠሮቹ ከተጠራቀመው የሐሞት ፈሳሽ ጋር አብረው ወደ ትንሹ አንጀት ክፍል ለመውጣት ሲሞክሩ የሀሞት ፊኛ አንገት ቱቦ ውስጥ በመቀርቀር መስመሩን ለጊዜው ይዘጋሉ በዛ ጊዜ የሆድ ህመሙ ይከሰታል ማለት ነው።

የሐሞት ጠጠር ሆድ ህመም በባህሪው

👉 የላይኛው የቀኝ ሆድ ወይም የላይኛው የመሀል ሆድ አካባቢ የሚሰማ ህመም ሲሆን ከጨጓር ህመም ጋር ተመሳሳይነት አለው

👉 ህመሙ ፋታ የሌለው ከ1-5 ሰአት ድረስ ሊቆይ የሚችል እና ከዛም የሚለቅ በቀኝ በኩል ወደ ጀርባ የሚሄድ ወይም ከጀርባ ህመም ጋር ሊያያዝ ይችላል

👉 ከህመሙ ጋር በተያያዘ ማቅለሽለሽ እና ማስመለስም ሊከሰት ይችላል አብዛኛውን ጊዜ የማቅለሽለሽ ስሜት ስለነሚኖር በራስ ፍላግት ጉሮሮን በጣት በመንካት ማስመለስ ሊኖር ይችላል

👉 በአብዛኛው ጊዜ ይህ ህመም የሚከሰተው ማታ ማታ እና በተለይ ቅባትነት ያላቸውን ምግቦች ወይም በአንድ ጊዜ ብዙ ምግብ ሲበላ ነው

✔️ ታዲያ ይህ ህመም ጨጓራ እና አንጀት የተመገብነውን ምግቦች ፈጭተውና አዋህዶ እስኪጨርሱ ድረስ የሐሞት ፊኛ ጠጠሩ እንደተቀረቀረ ይቀጥልና ይህ የምግብ መፈጨት ስርአቱ ሲያልቅ የሐሞት ፊኛ እንቅስቃሴ ስለሚቀንስ የተቀረቀረችው ጠጠር ወደ ቦታዋ ትመለሳለች በዚህ ጊዜ ህመሙ ይጠፋል ማለት ነው።

✔️ በተገቢ ምርመራ ካልታወቀ የዚሁ አይነት ተመሳሳይ ሁኔታዎች እና ህመም በተደጋጋሚ ይከሰታል ማለት ነው።

⚠️ ነገርግን ይህ ሁኔታ የሚደጋገም ከሆነ እና በጊዜ ካልታከመ በህክምናው በዋነኝነት በጣም የሚያሰፈሩ እና ሂወትን አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ ሶስት የጤና እክሎችን ያስከትላል።

1. የሐሞት ፊኛ መብገን እና ኢንፌክሽን መከሰት

በዋነኝነት የሚታየው ምልክት የሐሞት ጠጠር ምልክቶቹ እንዳሉ ሆነው የሚለየው ህመሙ
👉 ከ24 በላይ የሚቆይ ካልታከመ ፋታ የሌለው የላይኛው የቀኝ ሆድ ክፍል እና ወደ ጀርባ የሰውነት ክፍል የሚሄድ ህመም እንዲሁም
👉 ትኩሳት መኖር ናቸው።

2. የሐሞት ፈሳሽ ወደ ትንሹ አንጀት ማስተላለፊያ ቱቦ መዘጋት እና መብገን
የሐሞት ጠጠር አይነት ህመም እንዳሉ ሆነው በዋነኝነት የሚታዩት ምልክቶች
👉 ትኩሳት
👉 የአይን ቢጫ መሆን
👉 የሰውነት ማሳከክ
👉 የሽንት ቀለም መጥቆር እና የሰገራ ቀለም መንጣት ናቸው።

3. የቆሽት ብግነት እና ኢንፌክሽን
በዋነኝነት የሚታዩት ምልክቶች
👉 ጠንከር ያለ የላይኛው መሀል ሆድ ክፍል ህመም
👉 ተያይዞ ህመሙ በመሀል ሆድ ክፍል አልፎ ወደ ጀርባ የሚሄድ እና
👉 ከወገብ ወደፊት ዘንበል ወይም ጎንበስ ሲባል የሚቀንስ ህመም ነው።

✔️ ስለዚህ በአጠቃላይ የሚመከረው ነገር አንዴም ይሁን በተደጋጋሚ የሐሞት ጠጠር ምልክቶች ከተከሰቱባቹ እና በአልትራሳውንድ ምርመራ የሐሞት ጠጠር የተገኘባቹ ሰዎች ካላቹ ከተደጋጋሚ የሆድ ህመም ስቃይን ለመዳን እንዲሁም የጠቀስኳቸው ሶስቱ አደገኛ የጤና እክሎችን ቀድሞ ለመከላከል በቀዶ ህክምና መታከም የግድ ያስፈልጋቹሀል።

👉 በተጨማሪ የጠጠሩ መጠን 2.5 ሳ.ሜ እና ከዛ በላይ ከሆነ ለሐሞት ፊኛ ካንሰር የማጋለጥ እድል ስላለው ምልክት ባይኖራችሁም የቀዶ ህክምና መታከም ያስፈገዋል።

✔️ ታዲያ የቀዶ ህከምና ስናደርግ ጠጠሩን ብቻ ሳይሆን ድጋሚ እንዳይከሰት እና ለጠጠር መፈጠር ምክኒያት የሆነውን የሐሞት ፊኛም አብሮ እንዲወገድ እናደርጋለን።

የሐሞት ጠጠር የቀዶ ህክምናው ሁለት አይነት ሲሆን
1. ክፍት የሐሞት ፊኛ ማስወገድ
ይሄ የቀዶ ህክምና በቀኝ የላይኛው የሆድ ግድግዳ ክፍል ሆድ ተከፍቶ የሚሰራ የቀዶ ህክምና ነው።

2. በካሜራ የታገዘ የሐሞት ፊኛ ማስወገድ
ይሄ ደግሞ የሆድ ግድግዳ ሳይከፈት አራት ቦታ ላይ ትናንሽ ቀዳዳ በመፍጠር በካሜራ እይታ እየታገዘ የሚሰራ የቀዶ ህክምና ነው።

👉 ከቀዶ ህክምናው በኋላ ቶሎ ማገገም ስለሚያስችል እና ተያያዥ ችግሮች የመፈጠር እድላቸው አነስተኛ ስለሆነ ከክፍቱ የቀዶ ህክምና ይበልጥ በካሜራ የታገዘው የቀዶ ህክምና ተመራጭ ነው።

✔️ ነገርግን እነዚህ የጠቀስኳቸው የህመም ምልክት ሳይኖራቹ በአጋጣሚ በአልትራሳውንድ ምርመራ የሐሞት ጠጠር ከተገኘባቹ ሰዎች ካላቹ አስፈላጊ ሆኖ ካልተገኘ በቀር የቀዶ ህክምና ማድረግ አያስፈልጋችሁም ማለት ነው።

👨‍⚕️ ዶ/ር ዮናታን ከተማ: በቅዱስ ጳውሎስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የህፃናት ቀዶ ህክምና ሬዚደንት ሐኪም



https://t.me/ethiodoc

ዶክተር ኢትዮጵያ | Doctor Ethiopia

08 Nov, 17:35


"ልጄን ፀሀይ ለማሞቅ ሳወጣው በቅቤ ወይም በቫዝሊን አሸዋለሁ"

እስኪ ስለ ፀሐይ ብርሃን ለህፃናት ያለው ፋይዳ እና በማህረሰባችን ወስጥ የሚፈፀሙ የተለመዱ የተሳሳቱ ልማዶችን ጀባ ልበላችሁ

አስራ ሁለት ወራት ፀሐይ እስከ ቤታችን ደጃፍ በምትወጣበት ሀገር : በፀሐይ እጥረት አጥንታቸው ተጣሞ የሚመጡ ልጆች ቀላል አይባሉም። ይህን ከማየት በላይ ምን ልብ የሚሰብር ነገር አለ?

እድሜ ልክ የሚከተል አካል ጉዳት ከሚያስከትሉት የህፃናት ህመሞች መካከል አንዱ ሪኬትስ መሆኑን በቅጡ ያውቃሉን?

ሪኬትስ በቫይታሚን D እጥረት የሚከሰት ሲሆን አጥንቶቻችን እንዲሰሩ የሚያደርጉት ካልሲየም እና ፎስፈረስ ሰውነታችን ከምግብ መጦ መጠቀም እንዳይችል ያደርገዋል። የዚህ ቫይታሚን እጥረት ከብዙ ምክኒያቶች ሊመጣ ቢችልም ባብዛኛው የሚታየውና ዋንኛው ከፀሀይ ብርሃን እጥረት የሚከሰተው ነው! የፀሀይ ብርሃን በቆዳችን አልፎ የማይሰራውን ቫይታሚን D አይነት ወደሚሰራው አይነት ስለሚቀይረው ዋንኛ የቫይታሚኑ ምንጭ ነው።

በማህረሰባችን ወስጥ በፀሀይ ማሞቅ ዙሪያ የሚፈፀሙ የተለመዱ የተሳሳቱ ልማዶችን ጀባ ልበላችሁ

1. ሳወጣው በቅቤ ወይም በቫዝሊን አሻዋለሁ
2. አውጥቼው አላውቅም ለረዥም ጊዜ ምከንያት የሰው አይን ይበላዋል ብዬ / መች እንደሚወጣ ስለማላውቅ
3. የቤት መስኮት አጠገብ በመስታወት አሞቀዋለሁ
4. ግቢው ወይም ሰፈሩ ስለሚቀዘቅዝ እቤት ዉስጥ በእሳት አሞቀዋለሁ ወዘተ ዋና ዋናዎቹ ናቸው ።

የፀሐይ ብርሃን ፋይዳው ለህፃናት ምንድነው ?ህፃናት ከመች ጀምረው ነውና ፀሐይ መወጣት ያለባቸው? የትኛው የፀሐይ ብርሃን ነው ተመራጩ የጥዋት ወይም የከሰኃት? ህፃናት ፀሃይ በሚሞቁበት ጊዜ ቅባት ወይም ቅቤ በቂዳቸው መቀባት ጠቃሚ ወይስ ጎጂ ልምድ ነው? ይኸው

የፀሐይ ብርሀን ከቆዳችን ሲያርፍ ቫይታሚን ዲ የተባለውን ንጥረ ነገር እንዲመረት ያደርጋል::

ህፃናት ከተወለዱ ከ14ኛው ቀን ጀምረው በቀን ከ10 እስከ 15 ደቂቃ የጠዋት ፀሀይ ብርሃንን ማሞቆ ይህን በሽታ ይከላከላል።

ታዲያ ልብ ይበሉ ቫዝሊን ወይም ሌላ ቅባት ከመሞቁ በፊት ወይም እየሞቀ አይቀባም! የፀሀይ ብርሃኗን ስለሚሸፍንባቸው ከሞቁ በኋላ ብቻ ነው ሚመከረው! በሚወጡበት ጊዜ በተቻለ መጠን ያለ ልብስ ቢሞቁ ይመከራል።

የፀሐይ ብርሃን ፋይዳው ለህፃናት ?

ከአንጀት ውስጥ ካልሲየም የተባለውን ንጥረ ነገር ወደ ሰውነት እንዲገባ ያደርጋል ። ይሄ ንጥረ ነገር ለአጥንት እና ለጥርስ እድገት በጣም አስፈላጊ ነዉ። የዚህ ንጥረ ነገር እጥረት ያላቸው ልጆች የአጥንት ጥማት ፣ የጥርስ እድገት መዘግየት ወይም በሚጠበቀው ወቅት አለማብቀል።

ሌላው የቫይታሚን ዲ ጠቀሜታ የሰውነታችንን የበሽታ የመከላከያ አቅም እንዲጨምር ያደርጋል። ሪኬትስ ያለው ልጅ ለተደጋጋሚ የሳንባ ኢንፌክሽን ለቲቢ ወዘተ ኢንፌክሽን የተጋለጠ ይሆናል ማለት ነው።

ህፃናት እስከ መቼ ነው ፀሃይ መውጣት ያለባቸው ?

ፀኃይ ሁሌም ስለሚያስፈልጋቸዉ ህፃናቱ በራሳቸዉ ወደ ፀኃይ መዉጣት እስኪ ጀምሩ ድረስ በቤተሰብ እርዳታ ፀኃይ ማግኘት አለባቸዉ ።

የፀሐይ ብርሀን በማይኖርበት ወቅት ለምሳሌ በክረምት ወረት የተዘጋጁ ቫይታሚን ዲ መድሃኒቶች በመጠናቸው ልክ በባለመያ ትዛዝ መውሰድ ይኖርባቸዋል።

ዶ/ር መሐመድ በሽር የህፃናት ሐኪም
መልካም ጤንነት ተመኘሁ
ለብዙሃን እንዲደርስ ሼር በማድረግ ይተባበሩን 🙏

https://t.me/ethiodoc

ዶክተር ኢትዮጵያ | Doctor Ethiopia

08 Nov, 03:58


ሞት የራሱ መገለጫ መልክ አለው! - Death has a face and I can diagnose it! Will you?

ጤና ይስጥልኝ የዶክተር ኢትዮጵያ ገፅ ተከታታዮች! እንዴት ከረማችሁ?

ከቅርብ ግዜያት ወዲህ ስለማውጠነጥነው አንድ ሀሳብ ላጫውታችሁ ወደድኩ! በካንሰር ህክምና ውስጥ ከስድስት ዓመታት በላይ ያሳለፍኩ ሲሆን ብዙ ለየትም ግርምም የሚሉ ሳይንሳዊ ገጠመኞችን/ግኝቶችን ሳስተውል ቆይቻለው።

አሁን ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ታካሚዎችን ከማከም በተጨማሪ የህክምናችንንም ውጤቶች ለመገምገም የተለያዩ ምርምሮችን እና ጥናቶችን ለማድረግም በቅተናል! ታድያ አንድ ግርም የሚለኝን ፅንሰ ሀሳብ ልወርውር - The will to live (በግርድፉ - የመኖር ጉጉት)። በአንድ አይነት የካንሰር በሽታ ተጠቅተው፤ በአንድ አይነት የበሽታ ደረጃ ላይ ሆነው፤ አንድ አይነት ህክምና እየወሰዱ፤ የኢኮኖሚውም ሆነ የማህበራዊ ኑሯቸው ተመሳስሎ የህክምና ውጤቱ ግን የመለያየቱ አባዜ?! አለ አይደል እንደ ሐኪም ብዙ የተለያዩ ምክንያቶች ለመደርደር ቢያስችለንም ከምክንያቶቹ ባለፈ ግን ልንረዳው የምንችለው ለመኖር የመጓጓት መንፈስ አለ ብዬ አስባለው።

አያንዳንዳችን በተለያየ የስነልቦና እና የስነአዕምሮ ውቅር የተገነባን ሲሆን ሁላችንም ለመጥፎ ዜና ወይም ለብዙ አመታት ለሚሰጥ ህክምና ያለን ቅቡልነት የሰሜን እና የደቡብ ያክል የተራራቀ ነው። ህክምናን ምሉዕ ከሚያደርጉት ጥቂት ፈርጥ ክፍሎች መካከል የስነ አእምሮ ብስለት እና ጥንካሬም ነው።

ይህን ንድፈ ሀሳብ ያጠነክር ዘንዳ ከሁለት ሺህ ዘመናት በፊት በፕላቶ እና ጋለን የተከተበችውን መደምደሚያ ላክል "The Cure of many diseases is unknown to physicians, because they are ignorant of the whole. For the part can never be well unless the whole is well." ይላል ፕላቶ በዚያን ዘመን የነበረን ህክምና ሲያብጠለጥል። ከላይ ህክምናን በራሱ ነቆር ያደረገ ቢመስልም ቅሉ ግና ታካሚዎች በራሳቸው የተገነቡበትን ውስጣዊ የስነ ልቦና መዋቅር ለመተንተን ነው።

አንዴ አሁን ላይ በማላስታውሰው የቴሌቪዥን ጣቢያ የቀረበ ታዋቂ ኮሜዲያን ልጅ እያለ ከማይረሳቸው ትዝታዎቹ መኃል አንዱ ነቅሶ እንዲህ ሲል ለዝግጅቱ አጋፋሪ ደሰኮረለት "ይገርምኃል ልጅ እያለው ጨዋታ እወድ ነበር፤ የሆነ ቀን ታድያ አባቴ በጠና ታሞ ነበር እና በቅርብ ወደሚገኝ ቤተስኪያን ሄጄ ፀበል እንዳመጣለት አዘዘኝ። እኔ ታድያ የጠበል ኮዳውን ይዤ ስሮጥ መኃል ላይ ኳስ የሚጫወቱ ልጆች ተመለከትኩ። ጠበሉ ቀርቶ ኳሴን ስጫወት ረፈደ፤ ፋዘር ከሚቆጡ ብዬ በዛው ኮዳ ከሰፈር ተራ ውኃ ቀድቼ ወሰድኩላቸው ብሎ ለፈፈ። ልጀነት አሸንፎት አባቱን ላታለለው ህፃን ያን ምሽት ከባድ ቢመስልም ፋዘር ድነው አደሩ፡ 'በፀበሉ'!😊" ታድያ አዕምሯችን ይሄን ያክል ሰውነታችን ላይ ማዘዝ መቻሉን ብዙ የተጠኑ ጥናቶች ያመለክታሉ።

መች ይሄ ብቻ አእምሯችን በእያንዳንዷ ቅንጣት የሰውነት ህዋስ ላይ የማዘዝ ብቃትም እንዳለው የዘርፉ ጠቢባን ምክረ ሀሳባቸውን ያቀርባሉ። ይህንንም ምክረ ሀሳብ Psychoneuroimmunology ይሉታል። የአዕምሮን ብርታት በቀጥታ መለኪያ መጠን ባይኖርም በህክምና ሂደት ውስጥ ግን የዚህን መጠን ልኬት በህክምናው ግብረ መልስ ላይ ፍንትው ብሎ እንድትመለከቱት ያስችላል።

ይህን እንድል ካስደፈሩኝ ነገሮች መካከል የሀገራችንን የትምህርት ዕውቀት ደረጃ በማስረጃነት ላቀርብ እወዳለው። በትልቅ የጥናት ልኬት ያልተዳኘ ቢሆንም ስለበሽታው ያለው አመለካከት እና የትምህርት ደረጃው አናሳ የሚባለው የህብረተሰባችን ክፍል ለDiagnosis እና ለStaging/Prognosis ያለው ግብረ መልስ ምንም ነው። ያም ብቻ አይደለም በእምነት እና የፈጣሪን መኖር/Supernatural power ዕውቅና የሚሰጡት ታካሚዎች ያላቸው ቅቡልነት መልካም የሚባል ነው።

የትምትርት ደረጃው ምንም ከሆነው ገበሬ አስከ ዩኒቨርስቲ መምህሮች እና ፕሮፌሰሮች የማከም ዕድሉ የነበረኝ ሲሆን፤ በተለይ ለህክምና ቅርበት ያላቸው ባለሞያዎች ደግሞ የተሻለ የስነ ልቦና ዕገዛ እንደሚያስፈልጋቸው እሙን ነው። ለመኖር ያለህ/ሽ ፍላጎት መገለጫ መንገዶቹ ብዙ ሲሆኑ፡ የምርመራው ውጤት ከታወቀበት ግዜ አንስቶ የሚደረጉ የአመጋገብ ስርአቶች፣ ለህክምናው ያለው ፍላጎት፣ የሐኪምን ትዕዛዝ ለማክበር የሚደረጉ ጥረቶች እንዲሁም የበሽታውን እና የህክምናውን የጎንዮሽ ጉዳቶች የመቋቋም ጥንካሬ ማሳያ ሊሆኑ ይችላሉ።

ህክምናው ለረጅም ወራቶች ከመደረጉ አንፃር የታካሚውን እልህ እና ወኔ ሊገነቡ የሚያስችሉ ብዙ አነቃቂ ነገሮች የግድ ይለዋል። በብዛት ሲስተዋል የምናየው ካንሰርን እንደ ሞት ደብዳቤ የመፈረጅ አባዜ(Bone-pointing) ከተለያዩ ፊልሞች እና ትርክቶች የተንፀባረቀ ለመሆኑ ታካሚዎቻችን ማሳያ ናቸው። ለዚህም ነው ትምህርት ቀመሱ የማህበረሰብ ክፍል ለዚህ አይነት የተሳሳቱ ትርክቶች በሰፊው ገፈት ቀማሽ መሆኑ።

መማር፣ ማንበብ፣ ማወቅም የተሻለ ጥቅም ቢያስገኙም እራሱን የቻለም የአዕምሮ ግብግብ ይፈጥራሉ ብዬ አምናለው። ማመን/አለማመን?!፣ መጋፈጥ/አለመጋፈጥ?!፣ ቀቢፀ ተስፋንም ቢሆን መሻቱን/አለመሻቱን?!፣ ለምን እኔ የማለቱንም?!. እና የመሳሰሉትን?!

በአንድ ወቅት ስመ ገናና + ቁጥር አንድ የሜዳ ቴኒስ ተጫዋች የነበረው ጥቁር አሜሪካዊው አርተር አሽ በAIDS በሽታ ተይዞ በነበረበት ወቅት ለጋዜጠኞች ያጣቀሳትን አባባል ጀባ ልበላቹ፦ "If I were to say, 'God, why me?' about the bad things, then I should have said, 'God, why me? about the good things that happened in my life. የሰውየውን አመለካከት እና እምነት ፍንትው ያደረገ አባባል ሲሆን በወቅቱ HIV/AIDS ያደርሰው ከነበረው ዕልቂት አንፃር አርተር ህይወትን የሚያይበት መነፅር ባለ ህቡዕ ስነ ልቦና መዋቅር ባለቤት መሆኑን ያሳያል።

ታድያ እኔም ልሁን የሞያ ጓደኞቼ በህክምና ሂደት ውስጥ ያስተዋልነው ታካሚዎች ለመኖር ያላቸውን ጉጉት መግለጫ በየቀኑም ቢሆን ስናስተውለው እንውላለን። ደረጃ አራት ተብላ በሽታው በሰውነቷ ተሰራጭቶ የመኖር ጉጉቷ በልጆቿ እና በጠንካራ ባለቤቷ ሲፈካ የምንደሰተውን ያክል በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ኖሮ በቂ ህክምናን ማግኘት ሲችል፤ ተስፋውን ለሚከሰክሰው ደግሞ በዛኑ ያክል እናዝናለን። ማንኛውም የስነ ልቦና ወይም የስነ አእምሮ ዕገዛዎች ለታካሚዎቻችን የህክምናውን ያክል ፋይዳቸው እትየለሌ ነው።

ለዛም ነው እንደ ሐኪም ያ የመኖር ፍላጎት፤ ረጅሙን መንገድ የመጓዝ ብርታት ሲቀነጭር ግብረ መልሱን በማየት ብቻ ሞት መቅረቡን የምናውቀው። እውነትም ሞት መልክ አለው፤ በእያንዳንዱ ህዋስህ ሊገለፅ የሚችል ፈዘዛ!

አእምሮህ በተስፋ ሲጎለብት + በወኔ ሲበረታ እንኳን ሰውነትህን ቀርቶ ምሉዕ ጤንነትህን የመቆጣጠር ልዕለ ሀሳብ ላይ ትደርሳለህ ብዬ አምናለው። Yet we fail even knowing that, that's the beauty of life I guess.

References:
The will to Live, by Ernest H.Rosenbaum on Stanford Center for Integrative Medicine

ዶ/ር ሚካኤል ሻውል ለማ: በካንሰር ህክምና ረዳት ፕሮፌሰር
ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ


https://t.me/ethiodoc

ዶክተር ኢትዮጵያ | Doctor Ethiopia

07 Nov, 03:35


የማንኮራፋት ችግር | Snoring disorder
    
የማንኮራፍት ችግር ማህበራዊ ጫና ከመፍጠሩ ባሻገር ጤና ላይ የሚያመጣዉ መዘዝ የጎላ ነው።

የማንኮራፋት ችግር የሚከሠተዉ አየር ከሳንባ ወይም ወደ ሳንባ በሚወጣበት እና በሚገባበት ጊዜ በሚያልፍባቸው የአየር ቱቦ በቂ የሆነ ክፍተት ካላገኘ ወይም የሚያልፍበትን የተመቻቸ መስመር የሚያስቀይር ችግር ካጋጠመው የሚፈጥረው የተዛባ ድምጽ (turbulent air flow) ነው።
   
ይህን የማንኮራፋት ችግር የሚያስከትሉ ምክነያቶች በህጻናት እና አዋቂዎች ላይ የተለያዩ ቢሆንም የሚከሠቱበትን ቦታ በ 4 ከፍሎ ማየት ይቻላል።

1. ከአፍንጫ እስከ ላንቃ ያለው የአየር መተላለፊያ ሲሆን ህጻናት ላይ በአብዛኛው አዴኖይድ የምንለው የቶንሲል ክፍል መጠን መጨመርና በአፍንጫ የሚያልፈውን አየር ሲዘጋ የሚከሠት ነው። አዋቂወች ላይ ከዚህ ቦታ በሚነሳ ችግር ማንኮራፋት ከተከሠተ ካንሠርን ጨምሮ ሌሎች እብጠቶችን ማሠብ እና ምርመራ ማድረግ ግድ ይላል።

2. ከምላስ የኋለኛው ክፍል እና በጎኑ ከሚገኙ ቶንሲሎች (posterior tounge and palataine tonsilar hypertrophy) ጋር ተያይዞ የሚከሠት ማንኮራፍት ነው። የዚህ ከምላስ ጎን የሚገኘው ቶንሲል የማንኮራፍት ችግር ከመፍጠሩ በላይ በ ተደጋጋሚ የቫይረስ እና የባክቴሪያ ኢንፌክሽን በመፍጠር ተጨማር የጤና እክል ያስከትላል።

3. በአፍና መንገጭላ አካባቢ የሚከሠቱ የአፈጣጠር ችግሮች እንዲሁም ከነዚህ ቦታወች ተነስተው የኅለኛውን የአየር መተላላፊያ ሊዘጉ የሚችሉ እብጠቶች እንደ ምከንያት ይጠቀሳሉ።

4. የኋለኛው የአየርና የምግብ የጋራ መተላለፊያ ግድግዳን የሚሠሩ ጡንቻወች መዛል ፣ በስብ መሞላት ፣ በእብጠት መጠቃት ወይም መግል መቋጠር ከተፈጠረ የሚከሠት ይሆናል።

ማንኮራፍት የሚከሠትባቸውን ምክነያቶች በወፍ ዘረር ካየን የዚህ ችግር መጠን ከሠው ሠው እንደተፈጠረው የአየር መተላለፊያ መስመር መጥበብ መጠን ይለያያል። ይሔም ከልማዳዊ ማንኮራፍት (habitual snorer) እስከ ሳንባ ከረጢቶች መጠን መቀነስ (pulmonary alveolar hypoplasia) ብሎም የሳንባ ደም ስሮች ግፊት እና የልብ ችግር ሊፈጥር ይችላል።

በተጨማሪም አካላዊና አእምሯዊ የእድገት ችግር ፣ የጸባይ ችግር (በተለይም ህጻናት ላይ) ፣ ቀን አብዝቶ የመተኛት ችግር ፣ በስራ  የመዛልና ውጤታማ ያለመሆን እና የመሳሠሉ ተጽኖወችን ይፈጥራል።

በትዳር አጋር ላይ የሚፈጥረው ጫና እና ማህበራዊ ቀውሡም ሌላው ጉዳቱ ነው። ማንኮራፍት የፈጠረውን የጤና ችግር ደረጃ ለማወቅ አይነተኛ የሚባለው መሣሪያ (polysomnography ) ሲሆን በሀገራችን የለም ማለት ይቀላል። ነገር ግን ይሔንን ለመተካት የሚፈጠሩ ስሜቶችን እና ምልክቶችን በማየት እና የልብ ፣ የአተነፋፈስ ምርመራወችን በማድረግ ደረጃውን ማወቅ ይቻላል። የዚህን ጀረጃ ማወቁ ጥቅሙ ለእያንዳንዱ ደረጃ የሚሠጠው ህክምና የተለያየ መሆኑ ነዉ።

ወደ መፍትሔው ስንመጣ ፤ መፍትሔው የሚወሠነው ማንኮራፍቱን በፈጠረው ችግር እና የችግሩ መጠን ሲሆን

1. በአብዛኞች ህጻናት ላይ ከአፍንጫ ጀርባ እና ከምላስ ጎን ያለውን ቶንሲል በሠርጀሪ በማስወገድ የሚስተካከል ይሆናል።

2. በአዋቂወች ደግሞ እባጮች (እጢወች) እንደሌሉ ከተረጋገጠ በኋላ ክብደት መቀነስ ፣ የኦክስጅን ህክምና (CPAP) ብሎም የአየር መተላለፊያን ቱቦ ለማሥፍት የ ሚደረጉ ሠርጀሪወች (uvuloplalatopharyngoplasty
,uppp እና ሌሎች ዘርፈ ብዙ ሠርጀሪወች) የህክምና አማራጮች ናቸው።

ስለዚህ፦ ማንኮራፋትን እንደ ቀላል ችግር በማየት አንዘናጋ፤ቢያንስ ያለንበት የማንኮራፍት ጀረጃ በምን መሥተካከል እንደሚችል ሀኪሞችን እናማክር።
    
ዶ/ር አለማየሁ እሸት (ከአንገት በላይ ስፔሻሊስት ፣ መምህር እና ረዳት ኘሮፌሰር )
አቢሲኒያ ሆስፒታል ደሴ



https://t.me/ethiodoc

ዶክተር ኢትዮጵያ | Doctor Ethiopia

03 Nov, 16:40


"ልጄ ምንም ክብደት አትጨምርም/አይጨምርም... ጡቴ ስላልበቃው ፎርሙላ ጀመርኩኝ"

ከላይ የተጠቀሱትን እንዲሁም ሌሎች የቤተሰብ ጥያቄዎችን ይረዳ ዘንዳ እስኪ ስለ ልጆች አካላዊ እድገት ከተወለዱ አንስቶ እስከ አመት ያለውን ጀባ ልበላችሁ።

ልክ እንደ ብዙ ወላጆች ፣ ልጅዎ በመደበኛነት እያደገ መሆኑን እያሰቡ ይሆናል። ነገር ግን ፈተና ቢኖረውም የልጅዎን ዕድገት ከሌሎች ልጆች ጋር ማነጻጸር አይመከርም። እያንዳንዱ ልጅ ግለሰብ ነው እናም በእሱ ወይም በእሱ ፍጥነት ያድጋል።

አንዳንድ ልጆች ትልቅ ናቸው ፣ አንዳንድ ልጆች ትንሽ ናቸው። በእርግጠኝነት ጤናማ የእድገት ደረጃዎች አሉ። እድገቱ በብዙ ሁኔታዎች ላይ የተመሰረተ ስለሆነ ሁሉም ሰው ተመሳሳይ ንድፍ አይደለም።

በመጀመሪያው አመት ክብደትን እና ቁመትን ደረጃዎች እነሆ። ነገር ግን ያስታውሱ ልጅዎ ከነዚህ አማካኝ ልኬቶች ትንሽ ወይም ትልቁ ቢሆን ይህ የተለመደ አይደለም ማለት አይደለም።

የልጅዎን አካላዊ እድገት እንዴት ነው የምንከታተለው?

የዓለም ጤና ድርጅት እና ሲዲሲ የዕድገት ሰንጠረዥ
እነዚ የእድገት ሰንጠረዥ በጊዜ ሂደት የህጻናትን እድገት ለመከታተል የሚረዱ መሳሪያዎች ናቸው። የልጅዎን ቁመት እና ክብደት ጨምሮ ብዙ ነገሮች የጂን, የአመጋገብና የእንቅስቃሴ ደረጃን ይጨምራሉ። ጤናማ ህፃናት በ 5 ኛ መቶኛ እና በ95ኛ መቶኛ መቶኛ ውስጥ ይገኛሉ።

የዓለም ጤና ድርጅት እና ሲዲሲ የዕድገት ሰንጠረዥ
ሁሉም የእድገት ሰንጠረዦች ተመሳሳይ አይደሉም። የCDC የእድገት ሰንጠረዦች ማጣቀሻዎች እና ልጆች በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በተወሰነ ጊዜ ውስጥ እንዴት እንደሚያድጉ ያሳያሉ። አብዛኛዎቹ ጤናማ ሕፃናት ሲወለዱ ከ2.5 እስከ 4 ኪሎ ግራም ይመዝናሉ።

የልጆችን የውልደት ክብደት ከሚወስኑ ነገሮች ጥቂቶቹ :
- ያለጊዜው የተወለዱ ህፃናት በተለምዶ አነስ ያሉ ናቸው,
- ማጨስ ያጠቡ እናቶች አነስ አነስ ያሉ ህጻናት ይኖሩታል.
- በእርግዝና ወቅት የስኳር በሽታ
- በእርግዝና ጊዜ የአመጋገብ ሁኔታ
- የቤተሰብ ታሪክ- አንዳንድ ህጻናት የተወለዱት ትናንሽ ወይም ትላልቅ ናቸው እናም በቤተሰቡ ውስጥ ብቻ ሊሄድ ይችላል
- ጾታ በአማካይ አዲስ የተወለዱ ሕጻናት ሴቶች ከወንዶች ከወንዶች ያነሱ ናቸው

በመጀመሪያዎቹ ጥቂት የህይወት ቀናት 14 ቀናት ጨቅላ ሕፃናትከ 10 እስከ 14 % ክብደት መቀነስ የተለመደ ነው ፤ ነገር ግን ከሁለት ሳምንትበኃላ በየቀኑ ክብደታቸው ይጨምራል።

ጤነኛ ልጅ የሆነ እና በበቂ የእናት ወተት ያገኘ ልጅ በየቀኑ ምን ያክል መጨመር አለባቸው?

አማካኝ የልጆች ክብደት ርዝመት (ቁመት) የራስ ቅል እድገት ወራዊ እድገት

አማካኝ የቀን ክብደት ጭማሪ በግራም

እድሜ በወር - አማካኝ የቀን ክብደት ጭማሪ በግራም
ከ 0 እስከ 3 .... 30
ከ 3 እስከ 6 .... 20
ከ 6 እስከ 9 .... 15
ከ 9 እስከ 12 ....12

ወራዊ አማካኝ የልጆች ርዝመት (ቁመት) በሴንቲ ሜትር

እድሜ በወር - ወራዊ አማካኝ የልጆች ርዝመት በሴንቲ ሜትር
ከ 0 እስከ 3 ......... 3.5
ከ 3 እስከ 6 ......... 2.0
ከ 6 እስከ 9 ......... 1.5
ከ 9 እስከ 12 ......... 1.2

ወራዊ አማካኝ የልጆች የራስ ቅል እድገት በሴንቲ ሜትር

እድሜ በወር - ወራዊ አማካኝ የልጆች የራስ ቅል እድገት በሴንቲ ሜትር
ከ 0 እስከ 3 ......... 2
ከ 3 እስከ 6 ......... 1
ከ 6 እስከ 9 ......... 0.5
ከ 9 እስከ 12 .........0.5

ይህ ማለት የልጆች ክብደት ሲወለዱ የነበራቸውን እጥፍ የሚሆነዉ ወደ 5 ወይም 6 ወር ሲሆናቸዉ እና አንድ አመት ሲሆናቸዉ 3 እጥፍ ይሆናል። ለምሳሌ ሲወለድ 3 ኪሎ የሆነ ልጅ ወደ 6 ወር ሲሆነው 6 ኪሎ ሲሆነው አንድ አመት ላይ 9 ኪሎ ይሆናል እንደማለት ነው።

ልጆች ግላዊ ናቸው። እነሱ በተለያየ ፍጥነትደረጃ ያድጋሉ. ወንድሞችና እህቶች ቢሆኑም እንኳ አንዱን ልጅ ከሌላው ጋር ማወዳደር አስቸጋሪ ነው።

ልጅዎን ከሌሎች ልጆች ጋር ሲመለከቱ ፣ ልጅዎ ከእሱ ይልቅ ትንሽ ነው ብሎ ካሰቡ ወይም በዕድሜው ላይ ከሚያስችለው በላይ ክብደት ያለው ነው ብለው ካሰቡ ሊፈሩ ይችላሉ። ፍራቻዎትን ለማቃለል እና ልጅዎ እንደተጠበቀው እየጨመረ መሆኑን እርግጠኛ ለማድረግ የሚያስችሎት ቀላል መንገድ አለ። የጤና እንክብካቤ አቅራቢዎ የሚሰጠውን ጤናማ ልጅ ጉብኝት መደበኛውን መርሃ ግብር መከተል ብቻ ነው።

አንብበው ሲጨርሱ ለወዳጅ ዘመድዎ ሼር ያድርጉት
መልካሙን ሁሉ ተመኘው
ዶክተር መሐመድ በሽር የህፃናት ሐኪም



https://t.me/ethiodoc

ዶክተር ኢትዮጵያ | Doctor Ethiopia

02 Nov, 18:27


የጥርስ ሳሙና ፡ አፍ ያሸታል! ወይ?

"በጥርስ ሳሙና ፡ ጥርስ ማፅዳት ጀምረን ፡ ስናቆም ፡ አፋችን መሽተት ጀመረ.."
☝️
ይህን ትርክት ፡ በሙሉ ልብ ፡ ሲናገሩ የምንሰማቸው ፡ ጥርስን ፡ በሳሙና ማፅዳት ጀምረው - ከዛም ያቆሙ ፡ በጣም ጥቂት ሰዋች ፡ ናቸው ። ከነዚህ ጥቂት ሰዋች ፡ ሁሉም ማለት ይቻላል ፡ ወንዶች ናቸው (ሴቶች 'ለንፅህና' ያላቸው ቦታ ፡ ለዚሁ ምክንያት ነው) ።

የእነዚህን ጥቂት ሰዋች ትርክት - ግን ፡ ጥርስ መቦረሽ ባልጀመሩ ሰዋችም ፡ በግማሽ ልብ (ሁኔታው ሳይገጥማቸው) ሲነገር ይሰማል ።

ምክንያቱን ለማስረዳት ፡ ሁለት ምሳሌ እንጠቀም ፡-

ምሳሌ1 (በጥሩ ጠረን) ፡- ሽቶ የተቀባን ሰው ፡ ግና ስናገኝ የሚኖረው ፡ የሽቶ ግነት ፡ አብረነው ስንቆይ ፡ ቀስ በቀስ ፡ ጠረኑ እንደሚቀንሰው (እንደተቀባው እስክንዘነጋ ድረስ ፡ እንደምንለምደው) ሁሉ!

ምሳሌ2 (በክፍ ጠረን) ፡- ጠረን ያለው ሽንት ቤት ስንገባ ፡ መጀመሪያ የሚኖረው ፡ ሽታ ፡ ለአፍንጫ የሚከብድ ይሆንና ፡ ነገር ግን ፡ ረጅም ሰአት ፡ ሽንት ቤት ውስጥ በቆየን ቁጥር ፡ ምንም ሽታ እንደሌለ እስክናስብ ድረስ ፡ ውስጥ ያለውን ጠረን እንደምንለምደው ሁሉ!

የምሳሌው ሀሳብ ምንድነው?

እኚ "መቦረሽ ጀምረን ፡ ስናቆም ፡ አፋችን መሽተት ጀመረ.." የሚሉት ሰዋች ፡ ጥርስ ማፅዳት ከመጀመራቸው በፊት ፡ ለምደውት የነበረውን የአፍአቸውን ጠረን/ ጣዕም (የተጋነነ ላይሆን ይችላል ፤ እንደውም ለሌላ ሰው ማይታወቅ ሊሆን ይችላል) ጥርስ ማፅዳት በጀመሩበት ወቅት ፡ በሚኖረው የአፍ ውስጥ ንፅህና ፡ ይጠፋል ።

ከዛም ፡ መቦረሽ በሚያቆሙበት ጊዜ ፡ ወደ ቀድሞው ፡ የአፍ ውስጥ ሁኔታ ፡ ስለሚመለስ ፡ ጠረኑን/ ጣዕሙን ፡ እንደ አዲስ እስኪለምዱት ድረስ 'ብቻ' ፡ የአፍ ጠረን አለኝ/ አመጣው ብለው ፡ ያስባሉ ።

በተጨማሪም ፡ ለሰው ፡ ጥሩ ቃና ፡ እንዲሰጥ ፡ ተብለው ፡ በአንዳንድ ጥርስ ሳሙና ውስጥ ፡ ተጨምረው የሚገኙ ፡ የተለያዩ ፡ ቃናዊ ንጥርነገሮች/ flavoring chemicals ፡ እኚህ ሰዋች ፡ ማፅዳት በሚያቆሙበት ጊዜ ፡ ስለሚያጡት ፡ ከላይ የተጠቀሰውን ለውጥ (adapting the transition) እንዲገን ያደርጋሉ ።

ነገር ግን ፡ በጤናማ ሁኔታ ፡ የአፍ እና የጥርስን ጤና ፡ በአግባቡ ፡ ባለማቋረጥ ፡ በጥርስ ሳሙና ፡ ማፅዳት ፡ በተቃራኒው ፡ በአፍ ውስጥ በሚገኙ ፡ ጎጂ ህዋሳት እና በጥርስ ዙሪያ በሚከማቹ ፡ የምግብ ቅሪት/ ቆሻሻ ፡ ምክንያት የሚከሰትን ፡ የአፍ ጠረንን ማጥፋት ይቻላል ።

የአፍ ጠረን ፡ የተለያየ/ ብዙ ምክንያቶች ፡ ያሉት የጤና ችግር ሲሆን ፤ በሀኪም በሚደረግ መጠይቅ እና ሙሉ ምርመራ ፡ ምክንያቱን መሰረት በማድረግ ፡ የተለያየ መፍትሄ ሊቀርብ ይችላል ።

ዶ/ር በረከት ማተያስ ፡ Dental Surgeon




https://t.me/ethiodoc

ዶክተር ኢትዮጵያ | Doctor Ethiopia

01 Nov, 16:47


ነፃ የስኳርና የደም ግፊት ምርመራ
በቅዱስ ሉቃስ ክሊኒክ
ጎንደር



https://t.me/ethiodoc

@MedNotev