የአትሌቲክሱ አውራ ለመሆን 6 ዕጩዎች ተፋጠዋል…..
*…. የክልልሎችን ውክልናና ድጋፍ ይጠበቃል….
*…. ከበርካታ አመታት በኋላ የተደረገ ምርጫ
ይሆናል….ብቸኛ ዕጩ የለም…..
*….. ከዕጩዎቹ ጀርባ ድጋፍ ሰጪ ሃይል ይጠበቃል..
*….. ለፍልሚያው ስካይ ላይት ተመርጧል…..
በመጪው ታህሳስ ወር የሚካሄደው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባኤና ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ገና ከአሁኑ ትኩረት ስቧል።
ከታማኝ ምንጮች በተገኘ መረጃ በእግርኳሱ ምርጫ ላይ ይታይ የነበረውን የምረጡኝ ዘመቻን ለመጀመሪያ ጊዜ በአትሌቲክሱ ላይ ለመከሰት አትሌት ስለሺ ስህን ፣ አትሌት ገ/እግዚአብሄር ገ/ማሪያም ፣ አትሌት መሰረት ደፋር ፣ አትሌት አሰፋ መዝገቡ፣ አቶ ጌታ ዘሩና አቶ ቢኒያም ምሩጽ የረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ የስልጣን በትርን ለመረከብና የኢትዮጵያ ኩራት የሆነውን አትሌቲክስን ለመምራት ትልቅ ፍጥጫ ላይ መሆናቸው ተሰምቷል።
ባለፉት አራት አመታት ፌዴሬሽኑን የመራችው ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ያሸነፈችውን ምርጫ ጨምሮ ወደ ኋላ የተካሄዱት ምርጫዎች ውድድር ያልነበረባቸውና ከጀርባ ባሉ አካሄዶች የሚጠናቀቁ ምርጫዎች እንደነበሩ ይታወቃል። የዘንድሮ ግን የምረጡኝ ግብግቦች የሚታዩበት ከመጋረጃ ጀርባ ምክክሮች የሚኖሩባቸው ፖለቲካዊ አመራሮች፣ ባለሀብቶች ፣ ታዋቂ ሰዎች ተጽዕኖ ፈጠሪዎች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ እጃቸውን የሚያስገቡበት እንደሚሆን ይጠበቃል።
የቶኪዮው የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሊካሄድ ወራቶች በቀሩበት በአሁኑ ወቅት የሚመረጠው ፕሬዝዳንት ስፖርቱን የማረጋጋት የአትሌቶችን ስነልቦና የሚደግፍ ስራ መስራት ፣ ብሄራዊ ቡድኑን ዳግም መመስረትና የማናጀሮችን እጅ መመለስ ከምንም በላይ በየትኛውም አቅጣጫ የማይጎተት ለአንድ አላማ የቆየ የስራ አስወጻሚ ኮሚቴ ውህደት መፍጠር አትሌቲክሱን ከዘርና ከሃይማኖት ልዩነት ማጽዳት የሚጠበቅበት ሆኗል።
በፓሪስ ኦሎምፒክ የተገኘውን ደካማ ውጤት ተከትሎ እንደ ዋና ችግር ከታዩት ምክንያቶች መሃል ዋናው የብሄራዊ ቡድን መፍረስ ሲሆን ይህን የማስተካከልና ቡድኑን ዳግም የመመለስ የማናጀሮች አሰልጣኞችና የአትሌቶች ባሎች ከፍተኛ ጫና የሚወገድበት ሁኔታን የመፍጠርና አትሌቲክሱን የማዳን ትልቅ ሃይል የሚይዝ ፕሬዝዳንትና ስራ አስፈጻሚ የሚመረጥበት እንዲሆን የመምረጫ ካርዱን የያዙ ተወካዮች ትልቅ ሀገራዊ ሃላፊነት እንደሚሆን የብዙዎችም እምነት ሆኗል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባኤ በመጪው ታህሳስ ወር በስካይላይት ሆቴል ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።