>>>
አንዳንድ ግቢዎች በቆርቆሮ ይታጠራሉ። ወደ ገጠር ከሄድክ በአጋምና በኮሽም ይታጠራሉ። በግንቡ ላይ ደግሞ «አደገኛ አጥር» የሚል እሾሀማ ሽቦ ይደረግበታል። ኃይለኛ ተናካሽ ውሻ ግቢው ውስጥ ይኖራል።
እንደየአስፈላጊነቱ ደግሞ የጦር መሳሪያ የሚሰጠው የሰለጠነ ጥበቃ ሠራተኛ ሊኖርም ይችላል። ግቢውና ቤት ውስጥ የሚገጣጠም የደህንነት ካሜራ አለ። ይህ ሁሉ አጥር ግቢው ውስጥ ያሉትን ሰዎች ከሌሎች አደጋ መከላከያ ነው። ቤት ውስጥ ገብተንም በሩ በጥሩ ቁልፍ ይቆለፋል።
ሁላችንም እንዲህ የሚታይና የማይታይ ራሳችንን ከአደጋ የምንከላከልበት አጥር አለን። እንደየአስተዳደጋችን ችግር አጥሩ እየረዘመና እየጠነከረ ይሄዳል።
ራሳችንን ከጥቃት የምንከላከልባቸው የተለያዩ ዓይነት አጥሮች ይኖሩናል። በልጅነታችን ባሳለፍነው ክፉ ትውስታ ልክ የማንፈልገውን ኮተት አልጋ ስር አድርገን ከእይታ እንደምንከላከለው ራሳችንን የምንከልልበት የራሳችን አጥርም አለን።
ችግሩ ሲመጣ አጥሩ ሳያስፈልግ እንጋፈጠው ብንል የልጅነት ትውስታችን እየመጣ ስለሚረብሸን አራቱን ዓይነት አጥሮች እንጠቀምባቸዋለን። «አንተ ተወዳጅ አይደለህም። ብቁ አይደለህም። ከሌሎች ታንሳለህ» የሚል ረብሻ ውስጥ እንዳትገባ ከቻልክ ትጋፈጠዋለህ። አሊያም ንዴትህን ዋጥ አድርገህ ጤነኛ መስለህ ለመታየት ትሞክራለህ።
ጭምብል አጥልቀህ የሆንከውና የመሰልከውን አለያይተህ ታሳያለህ። ወይም በትንሽ በትልቁ እየጮኽክ ሰዎች በጩኸትህ ስር እንዲገቡ ትሞክራለህ ካልገቡልህ ትሸሻለህ። እነዚህ ሁሉ ራስህን ከሌሎች አደጋና ጥቃት የምትከላከልባቸው አጥሮች ናቸው። እነዚህ አጥሮች የተሰሩት በልጅነታችን ነው።
ከላይ የተዘረዘሩት ሀሳቦች በልጅነታችን በህይወት እንድንቆይ ያደረጉን ናቸው። በጣምም ጠቃሚ ነበሩ። እነርሱ ባይኖሩ ምናልባት የዛሬዋን ቀን ላናይ እንችላለን፤ አስፈላጊም ነበሩ።
አዋቂነት እድሜ ላይ የሚያስፈልገን ከችግሮቻችን መሸሽ፤ ጭምብል ማጥለቅ ወይም መደንዘዝ ሳይሆን ነገሮችን በተቻለ መጠን በተረጋጋ መንፈስ ማየት እና አቅም በፈቀደው መጠን ለችግሮች መፍትሄ መፈለግ ነው።
━━━━━━━━
✍ ትዕግስት ዋልተንጉሥ
ቴዎድሮስ ተ/አረጋይ
📄 198 - 199
🗓 ሐምሌ 2016 ዓ.ም.
📖 📖 📖 📖 📖
https://t.me/Ethiobooks