………///………
ከአዲስ አበባ በ1 ሺህ 70 ኪሎ ሜትር ርቀት በደቡብ ኦሞ ዞን ኛንጋቶም ወረዳ ላይ እየተገነባ የሚገኘውን የቲርጋ ባለ 132/33 ኪሎ ቮልት ማከፋፈያ ጣቢያ የግንባታ ሥራን ለማፋጠን እየተሰራ መሆኑን የብሔሪዊ የኤሌክትሪክ ግሪድ ደቡባዊ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ገለፀ።
የጣቢያው ሳይት ኢንጂነር አቶ ደረጀ ክፍሌ እንደገለፁት የግንባታ ግብዓቶች በቅርበት ባለመገኘታቸውና በአካባቢው ባለው የአየር ፀባይ ምክንያት ሥራዎችን በመርሃ ግብሩ መሰረት ማከናወን አልተቻለም።
ሥራ ተቋራጩ ለግንባታ ሥራ የሚያስፈልጉትን ጠጠር ከ150 ኪሎ ሜትር ፣ አሸዋ ከ250 ኪሎ ሜትር እንዲሁም ውሃ ከ80 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እያጓጓዘ እንደሚጠቀም የሳይት ኢንጂነሩ አስረድተዋል።
እንደ አቶ ደረጀ ገለፃ በፕሮጀክቱ ቦታ ርቀት ምክንያት የተስተዋለው የግንባታ አቅርቦት ችግር እና በሙቀቱ ምክንያት በማሽነሪዎች ላይ የሚያጋጥሙ ብልሽቶች በሥራው ላይ መስተጓጎል ፈጥረዋል።
በአካባቢው ያለው ሙቀት በኮንክሪት መሠረት ሥራዎች እና በማሽነሪዎች ብልሽት ላይ እያሳደረ ያለውን ችግር ለመቅረፍ የምሽት ሥራ መጀመሩን የተናገሩት አቶ ደረጀ ለሥራው የሚያስፈልገውን በቂ የሠው ኃይልም ከሌላ ቦታ በማምጣት የማሟላት ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
የፕሮጀክቱ ሥራ ተቋራጭ ሀዮሰንግ ሄቪይ ኢንደስትሪስ ኮርፖሬሽን የጥራት ቁጥጥርና ማረጋገጥ ሥራ አስኪያጅ አቶ አዲስዓለም ማሩ በበኩላቸው የፕሮጀክቱ የግንባታ ሥራ ቢጓተትም በአሁኑ ወቅት የሠራተኞች መኖሪያ ቤት፣ የመቆጣጠሪያ ክፍሉ እና የኤሌክትሮ ሜካኒካል ዕቃዎች መትከያ የመሰረት ቁፋሮና የኮንክሪት ሙሊት ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሆነ አብራርተዋል።
የጣቢያው አጠቃላይ አፈፃፀም 8 ነጥብ 7 እንዲሁም የሲቪል ግንባታ ሥራው 3 በመቶ እንደተከናወ የጠቆሙት አቶ አዲስዓለም ሥራውን ለማፋጠን ተጨማሪ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሙያዎችን የማሳተፍና ተጨማሪ ማሽነሪዎችን ወደ ሳይቱ የማስገባት ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።
በፕሮጀክቱ የሳይት 2 ሥራ አስኪያጅ አቶ አርጋው ታዲ እንደገለፁት የማከፋፈያ ጣቢያው ግንባታ ሲጠናቀቅ በአካባቢው የመስኖ ልማትን ለማስፋፋት፣ በዙሪያው ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችና በግንባታ ላይ ለሚገኘው የስኳር ፋብሪካ ኃይል ለማቅረብ እንዲሁም ከፋብሪካው ተረፈ ምርት የሚመነጨውን ብሔራዊ ግሪድ ለማስገባት ያስችላል።
ጣቢያው አንድ ባለ 132 ኪሎ ቮልት ጥምር ገቢ መስመር፣ አንድ ባለ 50 ሜጋ ቮልት አምፔር ትራንስፎርመር እና አምስት ባለ 33 ኪሎ ኪሎ ወጪ መስመሮች እንደሚኖሩት ተናግረዋል።
በግንባታ ግብዓቶች እጥረት ምክንያት በወቅቱ ያልተከናወኑ ሥራዎችን ለማፋጠን ሥራ ተቋራጩ ትኩረት ሠጥቶ እየሰራ እንደሆነም አቶ አርጋው ጠቅሰዋል።
የማከፋፈያ ጣቢያው የግንባታ ሥራ ከ8 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ የሆነ በጀት ተይዞለት እየተከናወነ ይገኛል።
💡 "ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ይፋዊ የማኅበራዊ ትስስር ገጾችን በመቀላቀል ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ያግኙ
ፌስቡክ↠ https://www.facebook.com/Ethioelectric
ቴሌግራም↠ https://t.me/EEPCommuication
ትዊተር ↠ https://twitter.com/EEPethiopia
ዩትዩብ ቻናል↠ https://www.youtube.com/@ethiopowermedia
ቲክቶክ አካውንት↠https://tiktok.com/@ethio_power
ድረ - ገፃችንንም ይጎብኙ www.eep.com.et
ጥር 30 ቀን 2017 ዓ.ም