" የምሥጢር ሙዳይ ሁን እንጂ የእሳት ማንደጃ ወናፍ አትሁን ። ሰዎች ሊሰሙህ በሚችሉበት ችሎታቸውና ፍላጎታቸው መጠን ብቻ ተናገር ፣ ቁጥብ እንጂ ዝርው አትሁን ። ለዕውቀት ትጋ ። በከፊል በተረዳኸው ነገር ራስክን እንደ አዋቂ አትቁጠር ። በከፊል ከማወቅ አለማወቅ ይሻላል ። ሥራ ስትሠራ ደግሞ ነገ ትቼው ለምሞተው ወይም ብሠራ የሚጠቀመው ሌላ ነው በሚል ተስፋ ቢስ ሆነህ ሳይሆን ዘላለም እንደምትኖር ያክል በመትጋት ነው ። ትጋት ጥሩ ነው ። ችኮላህ ግን ውጤት አያመጣም ፣ በችኮላ መሥራትና በፍጥነት መሥራት የተለያዩ ናቸው ። ርኩሰት የዕውቀትና ስልጣኔ መገለጫ አይደለምና ማንነትንና ሰብዓዊ ክብርን ከሚያጎድፉ ተግባራት መታቀብን ገንዘብ አድርግ ። "
" እናም በየዕለቱ በኑሮህ ጠንቃቃ ሁን ። ያለጸጸት ነገን ለመኖር ዛሬን በቁም ነገር አሳልፍ ፤ ውሳኔዎችህ ትክክለኛ መሆናቸውን መርምር ፤ ልክ እንደገና ሕይወትን የመኖር ዕድል ቢኖርህ ወይም እንደገና ሕይወትን የመኖር ዕድል ቢኖርህ ደግመህ የምትኖረውንና ለማከናዎን የምትመርጠውን ዐይነት ሕይወት ለመኖር ሞክር ። .... "