ጥበበኛው ሰሎሞን
“ተንሥኢ ወንዒ” የነፍሴ ደስታ የኾንሽ ውድ እናቴ ሆይ ተነሥተሽ ወደ እኔ ነዪ (መኃ ፪፥፲) ብሏታል።
ቅዱስ ያሬድም
«ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ ሞታ ለማርያም የዐጽብ ለኲሉ፤ ሞት ለማናቸውም ሰው ሁሉ የተገባ ነው የማርያም ሞት ግን ሁሉን ያስደንቃል» በማለት ገልጾታል።
አስተርእዮ ማለት መታየት፣ መገለጥ ማለት ነው። ቃሉ አስተርአየ ታየ፣ ተገለጠ ከሚለው የግዕዝ ግሥ የተገኘ ነው። ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በገባው ቃል ኪዳን መሠረት በሥጋ የተገለጠበት(የታየበት) ፣ አንድነት ሦስትነቱም የተገለጠበት ወቅት በመሆኑ ከልደት በዓል እስከ ጥር መጨረሻ በሙሉ ዘመነ አስተርእዮ በመባል ይታወቃል።
የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ሞትና ትንሣኤ በነገረ ማርያም አበው እንደሚያስረዱት ዕረፍቷ በጥር ፳፩ እሑድ ነው ። አባቶቻችን በጾመ ፍልሰታ ውዳሴ ማርያም ቅዳሴ ማርያም ሲተረጉሙ የእረፍቷን ነገር እንዲህ ብለው ይተርካሉ።
የእረፍቷስ ነገር እንደምን ነው ቢሉ ስድሳ አራት ዓመት በዚህ ዓለም ኖራ ጥር ፳፩ በእሑድ ቀን ጌታ እልፍ አዕላፋት መላእክቱን አስከትሎ መጥቶ እናቴ ሆይ ከዚህ ዓለም ድካም ላሳርፍሽ መጣሁ አላት። ልጄ ሰማይና ምድር የማይወስኑህ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በማህጸኔ ተሸክሜ በድንግልና ወልጄህ እሞታለሁን? አለችው። በሲዖል የሚሰቃዩ ነፍሳትን አሳይቶ እናቴ ሆይ ሞትሽ ለእነዚህ ቤዛ ይሆንላቸዋል አላት። እሊህን ከማርክልኝስ ይሁን አለችው። ቅድስት ሥጋዋን ከቅዱስ ነፍሷ ለይቶ በቃለ አቅርንት በዝማሬ መላእክት አሳረጋት። ደቀመዛሙርቱንም ከያሉበት በደመና ጠቅሶ ካለችበት አድርሶ እመቤታችሁን ስጋዋን በክብር አሳርፉ አላቸው። ሐዋርያት በአጎበር አድርገው ወደ ጌቴሰማኒ ይዘው ሲሄዱ አይሁድ ቀድሞ ልጇን ተነሳ ዐረገ እያሉ ሲያውኩን ይኖራሉ አሁን ደግሞ እሷን ተነሳች ዐረገች እያሉ ሊያውኩን አይደለምን በእሳት እናቃጥላታለን ብለው ተነሱ። ታውፋንያ የሚባል አይሁዳዊ ተራምዶ አጎበሩን ጨበጠው። መልአክ መጥቶ በሰይፍ ሁለት እጁን ቀጣው ከአጎበሩ ተንጠልጥሎ ቀረ። በድያለሁ ማሪኝ ብሎ ቢማጸናት እጁ ተመልሶለታል። ከዚህ በኋላ ዮሐንስን ጨምሮ በደመና ነጥቆ ከገነት አግብቶ ከዕፀ ሕይወት ሥር አኖራት።
ቅዱስ ዮሐንስን እንደምን ሆነች አሉት ከገነት ከዕፀ ሕይወት ሥር አለች አላቸው ቅዱስ ዮሐንስ አይቶ እኛ ሳናይ ብለው በነሐሴ መባቻ ጾም ጀመሩ ሁለት ሱባዔ ሲፈጸምም እሑድ አምጥቶ ሰጥቷቸው ቀብረዋታል በሶስተኛው ቀን ማክሰኞ “ከመ ትንሳኤ ወልዳ” እንደ ልጇ ተነሥታለች።
የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን❣️