“ሰው ከምግብ ውጪ አርባ ቀን መኖር ይችላል፤ ከውኃ ውጪ ሶስት ቀን ሊኖር ይችላል፤ ከአየር ውጪ ስምንት ደቂቃዎች መኖር ይችላል፤ ከተስፋ ውጪ ግን ከአንዲት ደቂቃ በላይ መኖር አይችልም” – Hal Lindsey
በአሁን ሰአት ያለህበትን ወዳጅነት፣ የፍቅር ግንኙነትት፣ ስራ፣ ንግድም ሆነ ማንኛውንም በየእለቱ ጠዋት መንጋቱን የምትጠብቅበትን ነገር ተመልከተው፣ በዚያ ነገር ውስጥ ያለህ ተስፋ ነው እንደዚያ የሚደርግህ፡፡ በአንድ ነገር ላይ ተስፋ እንደሌለህ እንዳሰብክ ወዲያውኑ አቅም የማጣት ስሜት፣ እንቅልፍ መጣትና አንዳንዴም መኖር ያለመፈለግ ስሜት ይጫጫንሃል፡፡ ተስፋ ማለት የነገ መሄጃ ነውና ተስፋ ከሌለ ወደየት ይኬዳል?
ተስፋ የጉልበት ምንጭ ነው፡፡ ተስፋ ዛሬ ካለህበት ሁኔታ ወጥተህ ነገ እንዲሆን ከምታስበው ነገር ጋር አጣብቆ የሚያቆይህ ወሳኝ ሂደት ነው፡፡ ሆኖም ተስፋ ለአንዳንድ ሰዎች የሕመም ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ የሚሆንበት ምክንያት የማይሞላን ተስፋ ከሰዎች በመጠበቅ ከአመት እስከ አመት ሲኖሩ ነው፡፡
ሰዎች በተለያየ ጊዜ በተስፋ እንድንጠብቃቸው ቃል በመግባት ያስጠብቁናል፡፡ የምንወዳቸውንና የምናምናቸው ሰዎች በተስፋ መጠበቅ የጨዋዎች ምልክት ነው፡፡ ነገር ግን የተገባው ተስፋ ከመጠን ያለፈ ፈተና ውስጥ በሚጨምረን ጊዜና ዝም ብለን የምንጠብቅ ከሆነ፣ የተስፋ እስር ቤት ውስጥ እንዳለን ማወቅ አለብን፡፡
ወይ በተስፋው ምክንያት በጉጉት አንኖር፣ ወይም ደግሞ አንደኛችንን የራሳችንን መንገድ አንከተል፣ እንዲሁ ተስፋውን በመጠበቅ እንደ እስረኛ እንከርማለን፡፡ ሰዎች በማይሞላ ተስፋ ውስጥ አንጠልጥለውን እየኖርን እንደሆነ ከተሰማን ሰዎቹን እውነተኛነት ለመመዘን የሚከተሉት ጥያቄዎች መጠየቅ እንችላለን፡-
1. ተስፋ የሰጡን ሰዎች ጉዳዩን የሚያስታውሱት እኛ ስናነሳላቸው ብቻ ሲሆን
2. ተስፋውን የመጠበቃችን ሁኔታ አመታቶቻችንንና እድሜያችንን የሚበላ ሲሆንና ስጋት ውስጥ ስንገባ
3. ሰዎቹ የሚያደርጉት ነገር ከምንጠብቀው ተስፋ አንጻር ተቃራኒ ሲሆን
4. ስለተሰጠን ተስፋ ለመወያየት ስንፈልግ (ልክ እንደተጠራጠርናቸው በማሳየት) በእኛ ላይ የቁጣና የንዴት ስሜት የሚያሳዩ ከሆነ
ከላይ የተጠቀሱትንና መሰል ሁኔታዎች ከተመለከትን መስጠት ከምንችላቸው ምላሾች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል . . .
1. ግልጽ ውይይት የማድረግ ጉዳይ አጽንቶ በመጠየቅ የሚቻለውን ያህል መታገስ
2. ሁኔታዎች ግልጽ ባለመሆን ከቀጠሉ የጊዜ ገደብ በማስቀመጥ አቋምን ግልጽ ማድረግ
3. ልብን ከስብራት ለመጠበቅ መዘጋጀትና ከተገባልን ተስፋ ውጪ መኖር እንደምንችል ራስን ማሳመን
4. የተገባውን ተስፋ በማይጣረስ መልኩ የግል ሕይወትን እቅድ በማውጣት ራስን የመቻል ሂደት መጀመር
በማይሞላ ተስፋ ድባብ ውስጥ ለአመታት መኖር አደገኛ የሆነ “የተስፋ እስር ቤት” ነውና ዛሬውኑ ተነሱና ከዚህ እስር ቤት ውጡ!