ምስለ ፍቁር ወልዳ @mesle_fikur_welda Channel on Telegram

ምስለ ፍቁር ወልዳ

@mesle_fikur_welda


[ ጽዮን እናቴ ሆይ ከጎኔ አትሽሺ ]

[ማነው የሚያፈቅረው እስከሞት ድረስ?]

" እርስ በርሳችሁ ከመዋደድ በቀር ለማንም ዕዳ አይኑርባችሁ፥ ሌላውን የሚወድ ሕግን ፈጽሞታልና።" (ወደ ሮሜ ሰዎች 13:8)

[የእግዚአብሔርን ቃል በማጋራት ግዴታዎን ይወጡ።]

ሀሳብ አስተያየቶን ይላኩ
@Mesle_Fikur_Welda_Bot

ምስለ ፍቁር ወልዳ (Amharic)

ምስለ ፍቁር ወልዳ ድረስ በጀርመን እና ሥነ ስለሺዎች ድረ ጽሁፋ ተመረቅ። ይህ እንዴት ታስነንና ከራሱ በተመረተ ዕዳ መዳር፣ የወይር ቅርጽና በእያንዳንዱ የሚዳገበው ህግ ይገለጹ ይሆናል። የእግዚአብሔርን ቃል በማጋራት ግዴታዎን እንዴት ይወጣል ስለሚባል። ምስለ ፍቁር ወልዳ ዘንድ ለሥራ አገልግሎት አሁን መያዝ አይችልም። ውጤታ አስተዳዳሪና ባህል በቀላሉ የሔዋን እና መንፈሳዊ የጽሁፍ ድረ ጽሁፍን ያገኛሉ።

ምስለ ፍቁር ወልዳ

24 Nov, 18:44


=>አምላከ ቅዱሳን ጸጋውን ክብሩን: አእምሮውን: ለብዎውን ያሳድርብን:: ከወዳጆቹ በረከትም ያሳትፈን::=>ኅዳር 16ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ አኖሬዎስ ጻድቅ (ንጉሠ ሮም)
2.አባ ዳንኤል ገዳማዊ
3.ቅዱስ አውሎጊስ መነኮስ
4.ቅድስት ጣጡስ ሰማዕት
5.አባ አቡናፍር ገዳማዊ
6.ቅዱስ ኪስጦስ ሰማዕት
7.ቅዱስ ፊቅጦር ምዑዝ
8.አባ ዮሐንስ መሐሪ

=>ወርኀዊ በዓላት
1.ኪዳነ ምሕረት (የሰባቱ ኪዳናት ማሕተም)
2.ቅድስት ኤልሳቤጥ (የመጥምቁ ዮሐንስ እናት)
3.ቅዱስ ገብረ ማርያም ጻድቅ ንጉሠ ኢትዮዽያ
4.ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌሉ ዘወርቅ

=>+"+ ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ:: በዓለም ያለው ሁሉ: እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት: ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም ስለ ሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ: ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም:: ዓለሙም: ምኞቱም ያልፋሉ:: የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘለዓለም ይኖራል:: +"+ (1ዮሐ 2:15)

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ምስለ ፍቁር ወልዳ

24 Nov, 18:43


✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

✞✞✞ እንኩዋን ለቅዱሳን "አኖሬዎስ ንጉሥ" : "አባ ዳንኤል" : "ቅድስት ጣጡስ" : "ወአባ አቡናፍር" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞

+"+ ቅዱስ አኖሬዎስ ወአባ ዳንኤል +"+

=>አኖሬዎስ የሚለው ስም በቤተ ክርስቲያን እጅግ ተወዳጅ ነው:: በሃገራችንና በሌሎች አብያተ ክርስቲያናትም ብዙ ቅዱሳን በዚህ ስም ተጠርተዋል:: ቅድሚያውን ግን ቅዱሱ ንጉሥ አኖሬዎስ ይወስዳል::

+ቅዱስ አኖሬዎስ ተወልዶ ያደገው በሮም ከተማ ሲሆን የደጉ ንጉሥ ዐቢይ ቴዎዶስዮስና የመርኬዛ ልጅ ነው:: ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ ሙሽራው እና ደጉ አርቃዴዎስ ወንድሞቹ: ጻድቁ አቡነ ኪሮስ ደግሞ አጐቱ ናቸው:: በልጅነቱ ክርስትናን የተማረው ከታላቁ ቅዱስ አርሳኒ ነው::

+ምንም በቤተ መንግስት ውስጥ ቢያድግም ቅዱስ አርሳኒ እንደ ተራ ሰው እየገረፈና እየቀጣ አሳድጐታል:: ቴዎዶስዮስ ቄሣር (አባቱ) ባረፈ ጊዜ የሮም ግዛትን በስምምነት ከወንድሙ አርቃዴዎስ ጋር ተካፈሉ:: በ390ዎቹ አካባቢም አኖሬዎስ በሮም: አርቃዴዎስ በቁስጥንጥንያ ነገሡ::

+ቅዱስ አኖሬዎስ ይሕንን ዓለም አልፈለገውምና ወደ ገዳም ልኮ አንድ ባሕታዊ (አባ አውሎጊስ ይባላል) አስመጥቶ ሥርዓተ ምንኩስናን ፈጸመ:: አክሊለ ሦኩንም በወርቅ ዘውዱ ውስጥ አደረገው::

+ልብሰ ምንኩስናውን በሰንሰለት በውስጥ አሥሮ በላዩ ላይ የመንግስቱን ካባ ደረበ:: ቀን ቀን እንደ ንጉሠ ነገሥት ሲፈርድ: ሲተች: የተበደለ ሲያስክስ: የተቀማ ሲያስመልስ ይውል ነበር::

+ሌሊት ደግሞ ባጭር ታጥቆ ሲወድቅ ሲነሳ: ሲጸልይ ሲሰግድ: ያለ ዕረፍት ያድራል:: መቼም ቢሆን ከደረቅ ቂጣ: ከጨውና ከጥሬ ጐመን በቀር ሌላ ምግብን አይቀምስም:: ይኸውንም ጾሞ ውሎ ማታ ብቻ ይመገብ ነበር::

+ይሕንንም ሲያደርግ ሰሌን ሰፍቶ: ያንን አሽጦ እንጂ በሌሎች ገንዘብ አልነበረም:: ሰዎች እንዳይጠረጥሩትም "በእልፍኙ ውስጥ ሚስት አለችው" እያለ ያስወራ ነበር:: በዚያ ላይ መልኩ ያማረ ስለ ነበር በዚህ የጠረጠረው የለም:: በዚህ መንገድ ከአባ አውሎጊስና ከደቀ መዝሙሩ ጋር ሆኖ ለ40 ዓመታት ተጋደለ::

+"+ አባ ዳንኤል ገዳማዊ +"+

=>በ4ኛው ክ/ዘመን መጨረሻና በ5ኛው መጀመሪያ በግብጽ ውስጥ ከነበሩ ከዋክብት አንዱ ሲሆን መንኖ ገዳም ከገባባት ቀን ጀምሮ በፍጹም ተጸምዶ: ከእህል ተከልክሎ: ቅጠል እየበላ ለ40 ዓመታት ተጋደለ:: አንድ ቀን ግን ተፈተነ:: በትዕቢት "ከእኔ የሚበልጥ ማን አለ?" ሲል በማሰቡ ፈጣሪ መልአኩን ልኮ ገሰጸው::

+ቀጥሎም "ሒድና ንጉሡን አኖሬዎስን እየው:: እሱ ንጉሥ ቢሆንም በቅድስና ይተካከልሃል" አለው:: አባ ዳንኤልም በደመና ወደ ሮም ሒዶ ቅዱሱን ንጉሥ ተገናኘው:: ቅድስናውን ዐይቶም ለቅዱስ አኖሬዎስ ሰገደለት:: እያለቀሰም ወደ በዓቱ ተመለሰ::

+ቅዱስ አኖሬዎስ ግን ከመምሕሩ ቅዱስ አውሎጊስና ከደቀ መዝሙሩ ጋር መንግስቱን ትቶ: ጠፍቶ: በርሃ ገብቶ ከአባ ዳንኤል ጋር ተቀመጠ:: ከተጋድሎ በሁዋላም 4ቱም ቅዱሳን በዚህች ቀን ዐርፈዋል::

+"+ ቅድስት ጣጡስ ሰማዕት +"+

=>በቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደዚህች ቅድስት ወጣት መልከ መልካም አልነበረም ይባላል:: ቅድስት ጣጡስ በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን (በዘመነ ሰማዕታት) የነበረች ሮማዊት ክርስቲያን ስትሆን መልኩዋን ያየ ሁሉ ይደነቅ: ይደነግጥም ነበር::

+እርሷ ግን ለወንድሞቿ እንቅፋት እንዳትሆን በፊቷ ላይ ዐይነ ርግብ ጣል አድርጋና እንደ ነገሩ ለብሳ ትኖር ነበር:: (እንዲህ ነበሩ እናቶቻችን!!!) ታዲያ በዘመኑ እስክንድሮስ የሚባል አረማዊ "ለጣዖት ስገዱ" እያለ ክርስቲያኖችን ሲገድል የእርሷ ተራ ደረሰ::

+በዐውደ ስምዕ (በምስክርነት አደባባይ) ላይ አቁሟት "ፊቷን ግለጡልኝ" አለ:: ቢገልጧት ከመልኩዋ ማማር የተነሳ ፈዘዘ:: እጅግ በመፍጠንም "ላግባሽ?" አላት:: "ሙሽርነቴ ሰማያዊ ነውና አይሆንም!" አለችው:: ለመናት: አልሰማችውም:: አስፈራራት: አልደነገጠችም::

+ከዚያ ግን ገላዋን አስገረፈ:: ከአካሏም ስለ ደም ፈንታ ወተት ፈሰሰ:: ተበሳጭቶ ለአራዊት ጣላት:: እነሱ ግን ሰገዱላት:: በእሳትም ፈተናት:: እርሷ ሁሉንም ታግሣ ጸናች:: በመጨረሻው ግን በዚህች ቀን አስገደላት:: ፈጣሪዋ ክርስቶስም በሰማያዊ አክሊል ከለላት::

+"+ ቅዱስ አቡናፍር ገዳማዊ +"+

=>ጻድቁ ተወልዶ ያደገው በ5ኛው መቶ ክ/ዘመን በምድረ ግብፅ ነው:: ወቅቱ ሥርዓተ መነኮሳት የሚጠበቅበት: አበው ባሕታውያን እንደ ሰማይ ከዋክብት በዝተው የደመቁበት ነበር::

+ታላቁ አቡናፍርም ከክርስቲያን ወላጆቹ ተወልዶ: በሥርዓት አድጎ: መጻሕፍትንም ተምሮ ገና በወጣትነቱ መንኗል:: ሥርዓተ መነኮሳትን ከአባ ኤስድሮስ ታላቁ አጥንቶ ገዳሙንና መምሕሩን እየረዳ ለብዙ ዓመታት በጾምና በጸሎት ኑሯል::

+መነኮሳቱ ስለ ትሕትናውና ስለ ታዛዥነቱ ፈጽመው ያከብሩት ነበር:: ከዕለታት በአንዱ ቀን አረጋውያን መነኮሳት ጭው ባለ በርሃ ስለሚኖሩ ባሕታውያን ሲጨዋወቱ: ሲያደንቁዋቸውም ሰማ::

+እርሱ በዛ ወቅት ባሕታውያን በበርሃ መኖራቸውን አያውቅም ነበርና ሒዶ መምሕሩን አባ ኤስድሮስን ጠየቃቸው:: እርሳቸውም "አዎ ልጄ! ከዚሕ በጣም ርቅው: ንጽሕናቸውን ጠብቀው: ከሰውና ከኃጢአት ተይለው የሚኖሩ ገዳማውያን አሉ" አሉት::

+ቅዱስ አቡናፍር "በዚሕ ካሉት መነኮሳትና በበርሃ ካሉት ማን ይበልጣል?" ቢላቸው "እነርሱ በጣም ይበልጣሉ:: ዓለም እንኩዋ ከነ ክብሯ የእግራቸውን ሰኮና አታህልም" አሉት:: ይሕንን የሰማው ቅዱስ አባ አቡናፍር ጊዜ አላጠፋም: ከመምሕሩ ቡራኬ ተቀብሎ ወደ በርሃ ሔደ:: ለብዙ ቀናት ከተጉዋዘ በሁዋላ አንድ ባሕታዊ አግኝቶ አብሯቸው ተቀመጠ:: ከእርሳቸው ዘንድም ሥርዓተ ባሕታውያንን ተምሮ እንደገና ወደ ዋናው በርሃ ጉዞውን ቀጠለ::

+ከብዙ ቀናት መንገድ በሁዋላም አንድ ሠፊ ሜዳ ላይ ደረሰ:: አካባቢው የውሃ ጠብታ የማይገኝበት: ይቅርና መጠለያ ዛፍ የሣር ዘር እንኩዋ የሌለበት ወይም በልሳነ አበው "ዋዕየ ፀሐይ የጸናበት: ልምላሜ ሣዕር የሌለበት: ነቅዐ ማይ የማይገኝበት" ቦታ ነበር:: በዚህ ቦታ ይቅርና የሰው ልጅ አራዊትም አይኖሩበትም::

+ለአባ አቡናፍር ግን ተመራጭ ቦታ ነበር:: ቅዱሳኑን ይሕ አያሳስባቸውም:: ምክንያቱም ለእነርሱ ምግባቸውም: ልብሳቸውም ፍቅረ ክርስቶስ ነውና::

+አባ አቡናፍር ወደ ፈጣሪ ጸለዩ:: በእግዚአብሔር ቸርነት ከጎናቸው አንዲት ዘንባባ (በቀልት) በቀለች:: ከእግራቸው ሥርም ጽሩይ ማይ (ንጹሕ ምንጭ) ፈለቀች::

+ጻድቁ ተጋድሏቸውን ቀጠሉ:: ዓመታት አለፉ:: ልብሳቸውን ፀሐይና ብርድ ጨርሶት ቅጠል ለበሱ:: በዚያ ቦታም የሰው ዘርን ሳያዩ ለ60 ዓመታት በተጋድሎ ኖሩ:: የሚያርፉበት ጊዜ ሲደርስ እግዚአብሔር አባ በፍኑትዮስን (የባሕታውያንን ዜና የጻፈ አባት ነው) ላከላቸው::

+ቃለ እግዚአብሔርን እየተጨዋወቱ ሳለ የአባ አቡናፍር አካሉ ተለወጠ:: እንደ እሳትም ነደደ:: አባ በፍኑትዮስም ደነገጠ:: ታላቁ ገዳማዊ ግን እጆቻቸውን ዘርግተው ጸለዩ: ሰገዱና አማተቡ:: ነፍሳቸውም ከሥጋቸው በፍቅር ተለየች:: ቅዱሳን መላዕክትም በዝማሬና በማኅሌት አሳረጉዋት:: የሚገርመው ደግሞ አባ በፍኑትዮስ ይሕን ሲያይ ቆይቶ ዘወር ቢል ዛፏ ወድቃለች: ምንጯም ደርቃለች::

ምስለ ፍቁር ወልዳ

23 Nov, 12:55


​​​​ጾመ ነቢያት (የገና ጾም)
ኅዳር ፲፭ ቀን

ጾመ ነቢያት በየዓመቱ ከኅዳር ፲፭ ቀን ጀምሮ እስከ በዓለ ልደት ዋዜማ ድረስ የሚጾም፤ ከሰባቱ አጽዋማት መካከል አንደኛው ጾም ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ዓለምን ለማዳን ሲል የሰውን ሥጋ ስለ መልበሱ፤ ወደ ግብጽ ስለ መሰደዱ፤ በባሕረ ዮርዳኖስ ስለ መጠመቁ፤ በትምህርቱ ብርሃንነት ጨለማውን ዓለም ስለ ማብራቱ፤ ለሰው ልጆች ድኅነት ልዩ ልዩ መከራን ስለ መቀበሉ፤ ስለ መሰቀሉ፣ ስለ ሞቱ፣ ትንሣኤው፣ ዕርገቱና ዳግም ምጽአቱ በየዘመናቱ የተነሡ ቅዱሳን ነቢያት በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝተው ትንቢት ተናግረዋል፤ ትንቢቱ ደርሶ፣ ተፈጽሞ ለመመልከትም ‹‹አንሥእ ኃይለከ ፈኑ እዴከ፤ ኃይልህን አንሣ፤ እጅህን ላክ›› እያሉ በጾም በጸሎት ተወስነው አምላክ ሰው የሚኾንበትን ጊዜ በቀናት፣ በሳምንታት፣ በወራትና በዓመታት እያሰሉ ሲጠባበቁ ቆይተዋል፡፡

ይህ ጾም የእግዚአብሔርን ሰው መኾን ሲጠባበቁ የኖሩት የነቢያት ትንቢትና ጸሎት በጌታችን መወለድ ፍጻሜ ያገኘበት ወቅት በመኾኑ ‹‹ጾመ ነቢያት (የነቢያት ጾም)›› እየተባለ ይጠራል፡፡ ለአዳም የተነገረው የድኅት ተስፋ ስለ ተፈጸመበትም ‹‹ጾመ አዳም (የአዳም ጾም)›› ይባላል፡፡

ስለ እግዚአብሔር ሰው መኾን በስፋት ትምህርተ ወንጌል የሚሰጥበት ወቅት በመኾኑም ‹‹ጾመ ስብከት (የስብከት ጾም)››፤ የጾሙ መጨረሻ (መፍቻ) በዓለ ልደት በመኾኑ ደግሞ ‹‹ጾመ ልደት (የልደት ጾም)›› በመባል ይታወቃል፡፡

እንደዚሁም ‹‹ጾመ ሐዋርያት›› ይባላል። ቅዱሳን ሐዋርያት ‹‹በዓለ ትንሣኤን ዐቢይ ጾምን ጾመን እናከብረዋለን፤ በዓለ ልደትንስ ምን አድርገን እናከብረዋለን?›› በማለት ነቢያት የጾሙትን ከልደተ ክርሰቶስ በፊት ያለውን ጾም ጾመዋልና፡፡

በተመሳሳይ መልኩ ይህ ጾም ‹‹ጾመ ፊልጶስ (የፊልጶስ ጾም)›› ተብሎ ይጠራል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ፊልጶስ በአፍራቅያና አውራጃዋ ዅሉ እየተዘዋወረ በጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ወንጌልን በማስተማር፣ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን በማድረግ ብዙዎችን ወደ አሚነ እግዚአብሔር ሲመልስ ቆይቶ ትምህርቱን በማይቀበሉ የአፍራቅያ ሰዎች አማካይነት በሰማዕትነት ዐርፏል፡፡

ደቀ መዛሙርቱ ሥጋውን ሊቀብሩ ሲሉም ስለ ተሰወረባቸው የሐዋርያውን ሥጋ ይመልስላቸው ዘንድ ሱባዔ ይዘው፣ በጾም በጸሎት ተወስነው በለመኑት ጊዜ እግዚአብሔር ልመናቸውን ተቀብሎ በ፫ኛው ቀን መልሶላቸው ሥጋውን (አስከሬኑን) በክብር አሳርፈውታል፡፡ ደቀ መዛሙርቱ የሐዋርያውን ሥጋ ካገኙ በኋላ እስከ ጌታችን ልደት ድረስ ጾመዋል፡፡ ስለዚህም ጾመ ነቢያት ‹‹ጾመ ፊልጶስ›› እየተባለ ይጠራል፡፡

ከዚሁ ዅሉ ጋርም ወልደ አምላክ ክርስቶስን በግብረ መንፈስ ቅዱስ እንደምትፀንሰው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ካበሠራት በኋላ እመቤታችን ‹‹ሰማይና ምድር የማይወስኑትን አምላክ ፀንሼ ምን ሠርቼ እወልደዋለሁ?›› በማለት ጌታችንን ከመውለዷ አስቀድማ ጾማዋለችና ይህ ጾም ‹‹ጾመ ማርያም›› በመባልም ይታወቃል፡፡

በአጠቃላይ በዚህ በገና ጾም ነቢያትም ሐዋርያትም ጾመው በረከት አግኝተውበታል፡፡ እኛ ምእመናንም እንደ እነርሱ በረከትን እናገኝ ዘንድ ይህንን ጾም መጾም እንደሚገባን የቤተ ክርስቲያን አባቶች ሥርዐት ሠርተውልናል፡፡

በዚህም መሠረት የነቢያት፣ የሐዋርያት፣ የጻድቃንና የሰማዕታት አምላክ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ከቅዱሳን ነቢያትና ሐዋርያት በረከት እንዲያሳትፈን፤ መንግሥቱንም እንዲያወርሰን ዅላችንም በዚህ በጾመ ነቢያት ወቅት በጾም በጸሎት ተወስነን እግዚአብሔርን ልንማጸነው ይገባል፡፡

ምንጭ፡- ፍት.ነገ ንባቡና ትርጓሜው፣ አንቀጽ ፲፭፡
ጾምና ምጽዋት፣ ዲያቆን ቃኘው ወልዴ፤ ገጽ ፵፯ -፶፡

ጾሙን የበረከት እና የምሕረት ያድርግልን!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡
💚💚💛💛❤️❤️

ምስለ ፍቁር ወልዳ

23 Nov, 12:52


✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

❖ኅዳር ፲፭ (15) ❖

+"+ ቅዱስ ሚናስ ምዕመን ሰማዕት +"+

=>ቅዱስ ሚናስ (ማር ሚና) በምድረ ግብጽ ተወዳጅ
ከሆኑ ሰማዕታት ዋነኛው ነው:: ልክ በሃገራችን ቅዱስ
ጊዮርጊስ ልዩ ቦታ እንዳለው ሁሉ ግብፃውያን ማር ሚናስን ጠርተው አይጠግቡትም::

+ምክንያቱም ከታላላቅ ሰማዕታት አንዱ በመሆኑና ዛሬም
ድረስ ለጆሮና ለዐይን ድንቅ የሆኑ ተአምራትን ስለሚሠራ
ነው:: በተለይ ለታመመ: ለደከመና ለተጨነቀ ፈጥኖ
ደራሽ: ባለ በጎ መድኃኒት ፈዋሽና አማላጅ ነው::

+"ግብጽ ውስጥ ቅዱሱን የማያውቅ ሰው ካገኛችሁ
እርሱ ኦርርቶዶክሳዊ አይደለም ማለት ነው" ሲባልም
ሰምተናል:: በነገራችን ላይ ለቅዱሳን ተገቢውን ክብር
በመስጠት: ታሪካቸውን በመጻፍ: በማጥናት: በመጽሔት:
በፊልምና በመሳሰሉት ለሕዝቡ በማስተዋወቅ
ግብጻውያኑ ከእኛ ብዙ ርቀት ሒደዋል:: ዛሬ እንኩዋ
የምንጠቀምበትን ስንክሳር 80 ከመቶ እጁን ያዘጋጁት እነርሱ ናቸው::

+አባቶቻችንና እናቶቻችን ኢትዮጵያውያን ቅዱሳን ግን
አብዛኞቹ ተረስተው ቀርተዋል:: መጽሐፈ ገድላቸውንም
ብል በልቶታል:: ዛሬም የቤት ሥራው የእኛ ብቻ ነው::

+ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና ቅዱስ ሚናስ (ትርጉሙ ታማኝና ቡሩክ ማለት ነው)

*በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን የነበረ የደጋግ ክርስቲያኖች ልጅ::
*በልጅነቱ የቅድስና ሕይወትን ያጣጣመ::
*በዘመኑ ሰው እጅግ ተወዳጅ የነበረ::
*ሃብትን: ክብርን: ሥልጣንን ንቆ በጾምና በጸሎት የተወሰነ::
*በመጨረሻም በክርስቶስ ስላመነ አላውያን የገደሉት ሰማዕት ነው::

+እርሱ ሰማዕት ከሆነ ከበርካታ ዘመናት በሁዋላ
ምዕመናን ክቡር አካሉን ፈልገው ያጡታል::
የሚገለጥበት ጊዜ ሲደርስ ግን እርሱ የተቀበረበት ምድረ
በዳ የበጎችና የእረኞች መዋያ ነበርና ተአምራትን አደረገ::

+አንድ እረኛ በጎቹ ድውያን ሆኑበት:: በዚያ ሰሞን
ከቅዱሱ መቃብር ላይ ጸበል ፈልቆ ነበርና እረኛው ተርታ
ውሃ ነው ብሎ በጎቹን ሲያጠጣቸው አንዱ ድውይ በግ ወደ ጸበሉ በመዘፈቁ ዳነ::

+በዚህ የተገረመው እረኛ ሁሉንም የታመሙ በጎቹን
አምጥቶ ነከራቸው:: እነርሱም ተፈወሱ:: ይህ ዜና
በምድረ ግብፅ ሲሰማ ድውያን ሁሉ እየመጡ ይፈወሱ
ገቡ:: ግን እነሱም ሆነ እረኛው ምክንያቱን ማወቅ
አልቻሉም:: ነገሩ በሮም ንጉሥ ዘንድ ሲሰማ ሴት ልጁን ከሠራዊቱ ጋር ላካት::

ምክንያቱም እርሷ ከብዙ ዘመን ጀምራ መጻጉዕ ነበረችና ፈውስን አጥታ ነበር::

+መጥታ ተጠመቀች: ፈጥናም ተፈወሰች:: እርሷ ግን
እንደ ሌሎች ያዳናትን ማንነት ሳታውቅ መሔድ
አልፈለገችምና ሱባዔ ገባች:: ቅዱስ ሚናስ በሌሊት
ራዕይ መጥቶ ሥጋው እንዳለ ነገራት:: እርሷም መሬቱን
አስቆፍራ የቅዱሱን አካል በክብር አስወጣች::

+ከዚያም በንጉሡ ትዕዛዝ ምድረ በዳው ከተማ
እንዲሆን ተቀየረ:: ስሙም "መርዩጥ" ተባለ:: ጸበሉ
የነበረበት ቦታም ላይ የማር ሚናስ ቤተ ክርስቲያን
ታንጾበት ቅዳሴ ቤ ተከብሯል::

+"+ ቅዱስ ቂርቆስ ሕጻን +"+

=>ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ካሏት ዐበይት ሰማዕታት አንዱ
ቅዱስ ቂርቆስ ነው:: በተለይ በዘመነ ሰማዕታት ተነስተው
እንደ ከዋክብት ካበሩትም አንዱ ነው:: ቅዱስ ወንጌል
እንዲህ ይላል:- "መልካም ዛፍ መልካም ፍሬን
ያፈራል::" (ማቴ 7:17)

+መልካም ዛፍ ቅድስት ኢየሉጣ መልካም ፍሬ ብጹዕ
ቂርቆስን አፍርታ ተገኝታለችና ክብር ይገባታል:: ቡርክተ
ማሕጸንም እንላታለን:: የተባረከ ማሕጸኗ የተባረከ ልጅን ለ9 ወር ተሸክሟልና::

+በዚያ ክርስቲያን መሆን መከራ በነበረበት ዘመን ይህንን
ደግ ሕጻን እርሷን መስሎ: እርሷንም አህሎ እንዲገኝ
አስችላለችና:: አበው በትውፊት እንዳቆዩልን ከሆነ
በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን በዚህች ቀን እናታችን ቅድስት
ኢየለጡ ብጹዕ ሰማዕት ቅዱስ ቂርቆስን ወልዳለች::

+ፈጣሪ ቢያቆየን የሰማዕትነት ዜናቸውን ጥር 15 ቀን
የምንመለከት ነንና የዚያ ሰው እንዲለን እንማጸነዋለን::

=>አምላከ ሰማዕታት በምሕረቱ ይማረን:: በይቅርታው
ኃጢአታችን ይተውልን:: ከበረከቱ ሰማዕታትም ይክፈለን::

=>ኅዳር 15 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ሚናስ ሰማዕት
2.ልደተ ቅዱስ ቂርቆስ
3.ብጽዕት ኢየሉጣ
4.አባ ሚናስ ዳግማይ

=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ (አፈ በረከት)
2.ቅድስት እንባ መሪና
3.ቅድስት ክርስጢና

=>+ አሁንስ ይላል እግዚአብሔር:: በፍጹም ልባችሁ
በጾምም: በለቅሶና በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ:: ልባችሁን
እንጂ ልብሳችሁን አትቅደዱ:: አምላካችሁም
እግዚአብሔር ቸርና መሐሪ: ቁጣው የዘገየ: ምሕረቱም
የበዛ: ለክፋትም የተጸጸተ ነውና ወደ እርሱ ተመለሱ::(ኢዩ 2:12)

ወስብሐት ለእግዚአብሔር