self-love / ራስን መውደድ
ሰው ራሱን አለመውደድ አይችልም። ራሱን አይወድም የሚያሰኙ ድርጊቶችን ቢፈጽም እንኳ ራሱን ስለሚወድ ነው። ይህን በአንድ ምሳሌ እንየው ፦ አንድ ሰው በጣም ከመጨነቁ የተነሳ ራሱን ቢያጠፋ ራሱን ያጠፋው ራሱን ስለሚጠላው ይመስላችኋል? አይደለም።ይልቁንም ከነበረበት ጭንቀት እና መረበሽ ለመላቀቅ ለራሱ ሰላምን፣ የተሻለ እረፍትን ለመስጠት ነው ይህን ያደረገው። ማንም ሰው በራሱ ላይ ክፉ ቢያደርግ እንኳ በኋላ (ክፉ ካደረገ በኋላ) የሚያገኘውን ጥቅም በማሰብ ነው። ምን አልባት አንድ ሰው ራሱን ሊያጠፋ ሲያስብ ከዚህ ኑሮ ሲኦል ይሻለኛል በሚል ስሜት ሊሆን ይችላል ነገር ግን ይህም ራሱን እንደሚወድ ያሳያል ምክንያቱም ሲኦል ይሻለኛል ያለው በራሱ ግምት ይቀላል ብሎ በማሰቡ ነው (ትክክል ባይሆንም)።ስለዚህ ሰው ራሱ ላይ ክፉ ቢያደርግ እንኳ ጭንቀቱን release ለማድረግ እና በኋላ የሚገኘውን የተሻለ እረፍት በማሰብ ነው እንጂ ራሱን በመጥላት አይደለም።
--> የቤተክርስቲያን አስተምህሮ
ቤተክርስቲያን ራስ ወዳድነትን(selfishness'ን) እንጂ ራስን መውድድን (self love'ን) አትቃወምም። ራስ ወዳድነት ፦ በሌሎች መጎዳት ላይ ፣ ከራስ ውጪ ሌላውን ባለመውደድ ላይ ፣ ሁሌም እኔ ብቻ በሚል ስሜት ላይ የተመሰረተ ራስን መውደድ ሲሆን ይህም ለጊዜው ራስን መውደድ ቢመስልም ነገር ግን አርቀው ቢያስቡት በኋላ ብዙ ችግሮችን የሚያስከትል ነው።
ቤተክርስቲያን ሰው ራሱን አለመውደድ እንደማይችል አስቀድማ የተረዳች በመሆኗ ትእዛዛቶቿ ራስን ከመውደድ የተነሳ እንዲፈጸሙ ሆነው ተሰርተዋል። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ አንስተን በምሳሌ እንመልከት ፦ “በእናንተስ እንዲህ አይደለም፤ ነገር ግን ማንም ከእናንተ ታላቅ ሊሆን የሚወድ የእናንተ አገልጋይ ይሁን፥” ማርቆስ 10፥43 ። ይህን ኃይለ ቃል አስተውለን ብንመለከተው አንድ ሰው የሌሎች አገልጋይ የሚሆነው በኋላ ታላቅ የሆነችውን መንግሥተ ሰማያት ለመውረስ ሲል ነው። ራሱንም ዝቅ የሚያደርገው በኋላ ከፍ ያለ(ከኃጢአት የተለየ) ህይወት መኖር ስለሚፈልግ ነው። ከዚህ ሀሳብ ጋር የሚመሳሰሉ ጥቅሶች ፦ 1ኛ ቆሮንቶስ 3፥18 ፣ ሉቃስ 22፥26 ፣ ማርቆስ 9፥35 ፣ ማርቆስ 10፥44 .....።
"አፍቅር ቢጸከ ከመ ነፍስከ" " ወንድምህን እንደራስህ ውደድ"
“ነገር ግን ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።”ዘሌዋውያን 19፥18 ፣ ማቴዎስ 22፥39 ፣ ገላትያ 5፥14
የሰው ልጅ ምንም ነገር ለመሞከር ቢፈልግ እና እርግጠኛ የሆነ ውጤት ሊያገኝ ቢወድ ከራሱ የተሻለ ሌላ የለም። የአንድን ምግብ መጣፈጥ እና አለመጣፈጥ ለመለየት ከአንተ የተሻለ ሰው የለም(ምግቡ ለራስህ ከሆነ)። ስለዚህ ይህም እንዲህ ነው ቀምሰህ የጣፈጠህን ምግብ ለወንድምህ ስጠው ነው ሀሳቡ። ምናልባት ይህ ሰው ራሱን የማይወድ ቢሆን የሚመርጠውም ምግብ የማይጣፍጥ ይሆናል ለወንድሙም የሚጣፍጠውን ለመስጠት አይቻለውም ስለዚህ ራስን መውደድ ለኛ ለወጣኒዎቹ የሚጣፍጠውን የምንለይበት መንገዳችን ነው። ምናልባት የፍፁማኑን ነገር ስላልደረስኩበት ራሳቸውን ይወዳሉ ብዬ ከመናገር ይልቅ በክርስቶስ ፍቅር ከመስከራቸው የተነሳ ራሳቸውን ይተዋሉ ማለትን እመርጣለሁ። ወደዚህ ደረጃ ከመድረሳቸው በፊት ግን አስቀድመው ፍቅርን በራሳቸው እንደተለማመዱት ከቀድሞ ህይወታቸው እንረዳለን።
--> self-esteem / ለራስ ያለ አዎንታዊ ግምት
ሰው ለራሱ ያለው ምልከታ/ግምት አዎንታዊ(positive) ካልሆነ ሌሎችን በአዎንታዊ ዕይታ ለመመልከት ይቸገራል አንድ ሰው ቀይ መነጽር ቢያደርግ አከባቢው ሁሉ ቀይ ሆኖ እንደሚታየው ሁሉ ሰው ሌላውን የሚገምተው ለራሱ ካለው ግምት በመነሳት ነው።
ስለራሳችን ጥሩ እና ትክክለኛ አረዳድ ሲኖረን ለራሳችን ጥሩ ነገር መመኘት እንችላለን።ምሳሌ፦ የሰው ልጅ ከቅዱስ ቁርባን ከሚርቅበት ትክክል ያልሆኑ ምክንያቶች አንዱም ለራሱ ያለው አረዳድ ትክክል ባለመሆኑ ቅዱስ ቁርባንንም የተረዳበት መንገድ ትክክል ስለማይሆን ነው። ሰው ኃጢአተኛ ቢሆንም ከኃጢአቱ መንጻትን የሚመኘው ለራሱ ጥሩ ግምት ሲኖረው ነው።
“አጥብቀህ ልብህን ጠብቅ፥ የሕይወት መውጫ ከእርሱ ነውና።” ምሳሌ 4፥23
ዲ/ን ኤፍሬም ሲሳይ
መጋቢት 19/2016ዓ.ም