"ጥጋብ'ኮ ነው....ምን ታረግ እንደላባ የለሰለሰ እንጀራ እየበላህ ባትወጣጠር ነበር የሚገርመኝ...ስማ አንተ እኔ ስማርኮ...."እያለ ረጅም ሀተታ ያለው የወጣትነት ገድሉን ሲነዛብኝ አመሸ።
እናቴ በበኩሏ "ወይኔ አሳድጌ አሳድጌ ዶክተር ትሆናለህ ብየ ስጠብቅ የተጨማደደ ኮሌታና የተዛነፈ ኮት አርገህ የምትዞር ፈላስፋ ልትሆን(ቆይ ማነው ላገሬ ሰው ደራሲዎችና ፈላስፋዎች ሸሚዝ መተኮስ አይችሉም ብሎ የሰበከው)...አሄሄ ክንዴን ሳልንተራስ አታረገውም" ብላኝ እርፍ።
መንደርተኛውም አለ "ሲያልቅ አያምር"(ቆይ መቼ አለቀ?)።
ሮዛ ራሷ(የጓደኛዬ እህት) " በቃ አመረርክ?"አለች።አባቷ እኮ በቴሌቭዥን ማስታወቂያ ነው የሚዘበዝበው። እስኪ ይታያችሁ" አድራሻችን 22 ማዞሪያ፣ ለለስላሳ ቆዳ፣..." ምናምን ብሎ መለፈፍ ስራ ነው? ለኔ ጮክ ብሎ ከማንበብ አይበልጥም። አለ አይደል የ3ተኛ ክፍል አማርኛ አስተማሪዎች 'ማነው ተነስቶ የሚያነብ' ሲሉን ተነስተን እንደምናነበው።
ነፍስ አባታችንም አሉ:- " ቱ ቱ ቱ ምን ስትል አሰብከው....ፍልስምና ደግማ'ዶል እምነት ያስክዳል( በዚች ሰዓት ጎረምሣ ልጃቸው ኢሳያስ የጫት ቀንበጥ እየበጠሰ እንደሆነ ማን በነገራቸው)...ብቻ ብዙ ብዙ ተባለ።
ተማሪ እያለሁ አጎቴን አንድ ቀን ልጠይቀው ተቀጣጥረን እንዲህ ሆነ። ስራ ከምፈታ ብዬ(የፈተናም ሰሞን ስለነበረ) አንድ The history of philosophy የሚል መፅሀፍ ይዤ ወደ ቀጠሮው ቦታ ሄድኩ። ካጎቴ ጋር የባጥ የቆጡን ስናወራ ቆይተን አጎቴ ወደያዝኩት ጥራዝ እየጠቆመ
"ባይዘዌይ(አቤት ይቺን ባይዘዌይ ሲወዳት ፤ሰው ብትሆን በስቅታ ሞታ ነበር)...እሱ ነገር ከትምህርትህ ጋር አይጋጭም" ብሎኝ እርፍ። ፍልስፍና እንደምማር ስነግረው ከት ብሎ ሳቀና" አይ የዛሬ ልጆች...እብዶችኮ ናችሁ"አለ። ለስሙ መሀንዲስ ነው። ለስሙ የምርቃት ፎቶውን የዘመመች የጭቃ ቤታችን ግድግዳ ላይ ሲሰቅል ከቤቱ የመጀመሪያው ነው።ሊያውም ኒሻን በኒሻን የሆነውን ያያቴን ያርበኝነት ፎቶ አውርዶ። ያን ቀን 'አይ አለማወቅ' አላልኩም። ይልቅስ ምን አልኩ? "አይ ማወቅ"።
ባጠቃላይ ህብረተሰቡ ነጠል ስትል አይወድም። ህዝቡ አንድ ላይ ተማግዶ ከሚነድበት ምድጃ ተለይቼ እፈናጠራለሁ ስትል" ሄይ ወዴት ነው...እዚችው አብረን እንነዳታለን" የሚል ቀጭን ትዕዛዝ ይሰጥሀል።
ግን አስቆመኝ? በጭራሽ። እንዲያውም ከፍ ያለ ነጥብ አምጥቼ ተመርቄ ስራ እስካገኝ ከቤተሰብ ጋር ልከርም ወዳገሬ ተመለስኩ። ስራ ፍለጋ የምትለውን ሀሳብ ሲሰማ መንደርተኛው ከወር በፊት የበላው የጎመን ቅሪት ጥርሱ ውስጥ እስኪታይ ሳቀ። "ስራ ማግኘቴ አይቀርም" ባልኩ ቁጥር ሰፈርተኛው በነቂስ የፀሀዬ ዮሀንስን 'ተባለ እንዴ' የተሰኘ ሙዚቃ ጋበዘኝ።
"እስከ12 ብቻ ተምሮ ስራ ይፈለጋል እንዴ?" ተብሎም ሌላ ቀልድ ታከለ።
ግን እዚህጋ ሟርታቸው ሰመረ።ስራ ጠፋ። ስራ የጠፋው አንድ ሰሞን ነጋዴ ሱቁ ውስጥ ደብቆት እንደሚጠፋው ዘይትና ስኳር አልነበረም። ስራ የጠፋው በልጅነቴ ለውትድርና ሄዶ በዛው ደብዛው እንደጠፋው ታላቅ ወንድሜ ነው። አለ አይደል ትንሽ ጭላንጭል ተስፋ ይዘን ይመጣ ይሆናል የምንለው አይነት።ስራ ፍለጋም እንደዛ ነው። በተለይ በኔ ፊልድ። ድሮውንም ያለ ነገር 'የስራ ዕድል' አላሉትም። እጣ ቢሆን አይደል?
እናም እላለሁ
የሰው ልጅ የሚፈልገውን ተምሮ ስራ የሚያገኝበት ሀገር መች ነው የሚኖረን? ሁኔታውኮ ጤፍ መዝራት ፈልገህ ማሽላ አዘርቶ ይባስ ብሎ ምርትህን እንዳትሰበስብ አግዶ አልቦ ጎተራ የሚያስታቅፍ ስርዓት ሆነብን።
@Mejnun_Leyla_poem