========
የሳምንቱ ሌሊቶች በታላቅ የዒባዳ ዘርፍ [በተሀጁድ ሶላት] መለዮ ሲደረግላቸው ለአላህ ነቢይም [ﷺ] ከዒባዳ ውስጥ ከእርሳቸው ጋር የሚያያዝ ድርሻ ተደረገላቸው። የጁሙዐ ሌሊት ላይ ልዩ የሶለዋት ድግስ ተደነገገ። የእለቱም ሶለዋት የተለየ እንዲሆን ተደረገ።
ይህ የአላህ ልማድ ነው። ምንጊዜም ወደ ዒባዳ እንድንዞር ሲያዝዝ ሁሉንም የዒባዳ ዘርፍ እርሱን ከመዝከር ጋር የሚወዳቸውን ነብይ [ﷺ] ማስታወስም እንዲካተትበት ያደርጋል።
ሸሃዳ የኢስላም መግቢያ፣ የመድኅን ሰርተፍኬት ነው። ሁለት ክፍል አለው። አንዱ የአላህ፤ ሌላኛው የነቢይ [ﷺ]።
አዛን ውስጥ አላህን እንደምናወሳው እርሳቸውንም እንዘክራለን።
ሶላት ውስጥ ከአላህ ጋር እንደምናወራው እርሳቸውንም እንድናወራ ታዘናል።
ሌሎችም የዒባዳ ዘርፎች የአላህን ልእልና በመሰከርንበት ግብር የርሳቸውንም ከፍታ እንድናስብ የሚያደርግ ክፍል አይጠፋቸውም።
አላህ ነቢዩን [ﷺ] በጣም ይወዳቸዋል። ከፈጠረው ፍጥረት ሁሉ የበላይ፣ የኸልቅ ሁሉ ዓይነታ አድርጓቸዋል። ለዚህ ማሳያም ከየዒባዳው አይነት ለርሳቸው ዝክር የሚሆን ክፍል ይመድባል። ወደ አላህ የሚያደርስ ብቸኛው መንገድ መሆናቸውን ለማሳበቅ፣ በኡመታቸው ላይ ያላቸው መብት ግዙፍ መሆኑን ለማሳየት፣ ውለታቸው የማያልቅ መሆኑን ለማስገንዘብ ሁሌም እርሱ በተወሳ ቁጥር እንዲወሱ ያደርጋል።
አላህ እርሳቸውን ይወዳል። የሚወዳቸውንም ይወዳል!…