በሐረሪ ክልል የመኸር እርሻ ወቅት እስካሁን 11 ሺህ 774 ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን የክልሉ ግብርና ልማት ቢሮ አስታወቀ።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ልማት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሮዛ ኡመር እንደገለፁት በክልሉ በተለይም በአሁኑ ወቅት ፆም ሲያድር የቆየ መሬት ጥቅም ላይ እንዲውል በማድረግ ጭምር ምርታማነትን በማሳደግ ከተረጂነት ለመላቀቅ በቁርጠኝነት እየተሰራ ይገኛል።
ለዚህም የማዳበሪያ፣ የዘርና ሌሎች የግብርና ግብዓት አቅርቦት በማሟላት የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት የማሳደግ ስራ በተጠናከረ መልኩ መቀጠሉን ተናግረዋል።
በየደረጃው ያሉ የግብርና ባለሙያዎችም ለአርሶ አደሩ አስፈላጊውን ሙያዊ እገዛና ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ገልፀዋል።
በዚህም አርሶ አደሩን ከዝናብ ጠባቂነት ከማላቀቅና ተጠቃሚነትን ከማሳደግ አንፃር አበረታች ስራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።
በክልሉ በተለይም ለስንዴ፣ ለማሽላ ፣ ለአትክልትና ፍራፍሬ ልዩ ትኩረት በመስጠት በክላስተር እየለማ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
አርሶ አደሩ እያከናወናቸው ባሉ የተቀናጀ የግብርና ልማት ስራዎች ምርታማነትን በማሳደግ የከተማውን ህዝብ የኑሮ ውድነት ጫና ለመቀነስ ፋይዳው የላቀ ስለመሆኑ ጠቁመዋል።
በክልሉ መኸር እርሻ እስካሁን 11 ሺህ 774 ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን ጠቅሰው በማሳያነትም 450 ሄክታር መሬት በስንዴ እንዲሁም 800 ሄክታር መሬት በአጭር ግዜ ምርት በሚሰጥ የማሽላ ኢንሼቲቭ መሸፈኑን ገልፀዋል።
በቀጣይም የተገኙ አበረታች ውጤቶችን በማስቀጠል የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማጎልበትና ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የላቀ ትኩረት እንደሚሰጥ አመላክተዋል።