ጥር 02/2017 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከ298 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ባለብዙ መንደር የመጠጥ የውሃ ግንባታ ከሶዳክ ኮንስትራክሽን ኃ/የተ/የግ/ማ እና ከጃርሶ የውሃ ስራዎች ኮንስትራክሽን ጋር የውል ስምምነት ተፈረመ፡፡
ስምምነቱን የፈረሙት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ ውሉን የሚፈርሙት ኮንትራክተሮች በሀገራችን የተለያዩ ቦታዎች የሰሩና ልምድ ያካበቱ በመሆናቸው ጠቅሰው፤ በሶማሌ ክልል ጉራዳሞሌ ወረዳ እንደሚገነባና አካባቢዎቹ ምንም አይነት የውሃ መሰረተ ልማት የተሰራላቸው ባለመኖሩ እንዲሁም ውሃ አጠር አካባቢ በመሆኑ ውሉን የወሰደው ድርጅት በተቀመጠው ጊዜና ጥራት ስራውን አጠናቆ በማስረከብ የህብረተሰቡን የውሃ ጥያቄ በመመለስ በአካባቢው ያለውን የውሃ ችግር የሚፈታ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።
ክቡር አምባሳደር አያይዘውም ፕሮጀክቱ በ One-WaSH ፕሮግራም CR-WaSH ኮምፖኔንት የሚተገበር ሲሆን ስራው በአጭር ጊዜ ተሰርቶ እንዲጠናቀቅ አሳስበው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ተገቢውን ክትትልና ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።
የሶዳክ ኮንስትራክሽን ኃ/የተ/የግ/ማ ስራ አስኪያጅ ኢ/ር ሰለሞን ዳኜ በበኩላቸው ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር አብሮ ለመስራት እድል በማግኘታቸው መደሰታቸውን ገልፀው፤ በተዋዋልነው መሰረት ሥራውን በጥራትና በፍጥነት ከተዋዋልንበት ጊዜ አስቀድመን ሰርተን ለማስረከብ ቃል እንገባለን ብለዋል።
በሶማሌ ክልል ጉራዳሞሌ ወረዳ የሚገነባው የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ወጪው ከ 298,610,241.78 ሚሊዮን ብር እንደሆነ፣ የውሃ ጉድጓድ ግንባታው ሲጠናቀቅ 32,891 የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ እንደሚያደርግና በ21 ወራት እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል።