ብሌን ?
ወዬ
ችስታ መሆኔ አልታየሽ ይሆን ? በኋላ አስቤዛ እንዴት በዚህ ፍጥነት አለቀ? አንበጣ ግሪሳ አሰማርተሽ ነው ወይ ?ማለቴ አይቀርም ....
ዋ ...መምረጥ አይደለም የሚከብደው ምርጫን መኖር እንጂ
አልኳት ፌዝ ባዘለ አኳኋን
ሳቀች ሳቅ ከፊቷ አይጠፋም ። አይኔን እያየች ትህትና ባለው ፈገግታ
"እየውልክ እኔ ድህነትን አልፈራም ። አባቴ ግንበኛ ነበር እናቴ እንጀራ ትሸጥ ነበር ። አባቴ አባወራ ነው እቤት ውስጥ ንጉሱ እሱ ነው ። ትሁት ንጉስ ።
እናቴ አባቴን ታንቀባርረዋለች ። ሲሚንቶ ሲያቦካ አሸዋ እና ድንጋይ ሲታገለው ውሎ ነው የሚመጣው ብላ ጥሙን የሚቆርጥለት ጠላ ትጠምቅለታለች ። ሲመጣ እንደእንግዳ ነው ሽርጉድ የምትለው ።
እንደ እንግዳ እየተገለገለ ይመገባል ። እየተገለገለች ትጎርሳለች ያጎርሳታል ።
አባቴ እናቴን አልማዜ የኔ አልማዝ ይላታል ። ስትቆጣው ይሰማታል እኛን ስትቆጣ ጣልቃ አይገባም ስሞታ ስትነግረው
ይሰማታል ።
እናቴ ሃይለኛ ናት ከጎረቤት ስትጣላ አልማዝ አልማዜ ግቢ ሲላት አባቴን ትሰመዋለች ትገባለች ከገባች በኃላ ተይ ተያቸው እያለ ያረጋጋታል ታብራራለች እያብራራች በዝምታ እየሰማት ትረጋጋለች ።
እወድሃለሁ እወድሻለሁ ሲባባሉ ሰምቼ አላውቅም መዋደድን ይኖራሉ ።
እናቴ አመም ካደረጋት ቶሎ ቶሎ እቤት ይመጣል።
እናታቹ እንዴት ዋለች አመማት እያለ በር ላይ ያገኘውን ይጠይቃል ።
አልማዜ እንዴት ነሽ ይላል እንደገባ አጠራሩ እና አጠያየቁ ስጋት እና ስስት አለው ። ምን ልግዛልሽ? ምን ላምጣልሽ ? ይላል
የፊቱ ሁኔታ ያለችውን ሁሉ እንደሚያመጣ አይነት ነው ።
ሽቦ አልጋችን ላይ ጫፍ ላይ ተቀምጦ እጁን ግንባሯ ላይ እያስቀመጠ ሙቀቷን ይለካል አይበሉባዋን ይስማል ።
ስታየው የምትበረታ ይመስለኛል ።
ጠንካራ ሰራተኛ ስለሆነ ወይ ደሞ በየቀኑ እየተለማመጠች ስለምትመግበው ይሆን ? ምችት ጥብስቅ ድልድል ያለ ሰውነት ነው ያለው ።
እኔን ጨምሮ ሶስት ልጆች ነበራቸው ። ደስተኛ ነበሩ ደስተኛ ነበርን ።
ማታ ማታ ካርታ እንጫወታለን ። አሹቅ ወይ በቆልት አልያ ሽንብራ አይጠፋም ሻይ ይፈላል ። አባቴ ጨዋታ ይችላል አናቴ ጨዋታ ይገባታል ስትስቅ በሳቅ እያጀብናት ነው ያደግነው ።
እንዴት ደሃ ሆነን ድህነታችን ሳይታወቀኝ አደኩኝ ?!
በዛ ድህነት ውስጥ እንዴት ጨዋ ጌጣጌጥ የማይባርቅብኝ የማልታለል ሆኜ አደኩኝ ? እንዴት ቁጥብ ጨዋ ህልም ያላቸው ወንድሞች ኖሩኝ ?
ድህነት አይደለም የሚያስፈራኝ ። ፍቅር አልባ ህይወት መተማመን የሌለበት ኑሮ እንጂ ። ሃብት ኖሯቸው የቀዘቀዘ ጎጆ ያላቸው ብዙ ሰዎች አውቃለሁ ።
ከወደድኩህ ፣አምላክህን ከፈራህ ፣ህልም ካለህ ፣ጠንካራ ከሆንክ ትበቃኛለህ I think ሁሉም አለህ ሊያውም ትበዛብኛለህ ።
እወድሃለሁ ❤
© Adhanom Mitiku
@fikrhn
@fikrhn
@fikrhn