የበርጤሜዎስ ጸሎት
በርጤሜዎስ ጌታ ኢየሱስ በተአምራዊ ጉብኝቱ የዐይን ብርሃናቸውን ከመለሰላቸው መካከል አንዱ ነበር። በስም የምናውቀው ብቸኛ ዐይነስዉር ሲሆን፣ ወደ ጌታ ካቀረበው ልመናም የሚከተሉትን ትምህርቶች ልንቀስም እንችላለን።
1 ጌታን ስለመፈለግ
“ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ከብዙ ሕዝብ ጋራ ከኢያሪኮ ሲወጡ ዐይነ ስውሩ የጤሜዎስ ልጅ በርጤሜዎስ በመንገድ ዳር ተቀምጦ ይለምን ነበር።
እርሱም የናዝሬቱ ኢየሱስ መሆኑን በሰማ ጊዜ፣ “የዳዊት ልጅ፣ ኢየሱስ ሆይ፤ ማረኝ!” እያለ ይጮኽ ጀመር።”
ማርቆስ 10:46-47
በርጤሜዎስ ጌታ ወደ እርሱ በቀረበበት ጊዜ እድሉን በመጠቀም ልመናውን አቀረበ።
እኛ ጌታን ቀርቦ ሳለ ልንፈልገው ይገባል። ቃሉ እንዲህ ይለናልና:-
“እግዚአብሔር በሚገኝበት ጊዜ ፈልጉት፤ ቀርቦም ሳለ ጥሩት።”
ኢሳይያስ 55:6
2 ጌታን በጽናት መፈለግ
በርጤሜዎስ ወደ ጌታ ጩኸቱን ባሰማ ጊዜ የገጠመው ነገር ተስፋ አስቆራጭ ነበር። እርሱ ግን በልመናው ጸና። እንዲህ ተብሎ እንደተፃፈው:-
“ብዙዎችም ዝም እንዲል ገሠጹት፤ እርሱ ግን፣ “የዳዊት ልጅ ሆይ፤ ማረኝ!” እያለ የባሰ ጮኸ።”
ማርቆስ 10:48
እኛም ምንም አይነት ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ቢገጥመን ከልባችን ጌታን በመፈለግ በፀሎት እንጽና።
3 ጌታን መከተል
“ኢየሱስም፣ “ሂድ፣ እምነትህ አድኖሃል” አለው፤ ወዲያውም ዐይኑ በራለት፤ በመንገድም ኢየሱስን ተከትሎት ሄደ።”
ማርቆስ 10:52
በርጤሜዎስ ከተፈወሱ በኋላ የፈወሳቸውን ጌታ ከተከተሉ መካከል አንዱ ነበር። በጸሎት የተቀበለው ፈውስ ከሰጪው አላራቀውም፥ ይልቁንም ወደ ፈወሰው ጌታ ይበልጥ እንዲጠጋ አደረገው። እኛስ በጸሎት የሙጥኝ ብለን ከጌታ እጅ የተቀበልነው ስጦታ ወደ እግዘአብሔር አቀረበን ወይስ አራቀን?
አባት ሆይ እኛም ቀርበህ ሳለህ በጽናት እንድንፈልግህ፣ በጸሎታችን መልስ ካንተ የምንርቅ ሳይሆን ወደ አንተ የምንቀርብ እንድንሆን በጸጋህ እርዳን። አሜን።