† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን †
[ † እንኩዋን ለእናታችን "ቅድስት ማርያም እንተ ዕፍረት" እና "ቅዱስ አቡሊዲስ" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ † ]
[ † 🕊 ቅድስት ማርያም 🕊 † ]
ቅድስት ማርያም እንተ ዕፍረት ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚለን በስምዖን ቤት የመድኃኔ ዓለምን እግር በእንባዋ አጥባለች:: በፀጉሯም አብሳ የ300 ብር ሽቱ ቀብታዋለች:: ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም የቀደመ ኀጢአቷን ይቅር ብሎ ከ36ቱ ቅዱሳት አንስት ደምሯታል:: [ሉቃ.፯፥፴፮-፶] (7:36-50)
+ ስለዚህች ቅድስት ሙሉ ታሪክ :-
፩. ትርጉዋሜ ወንጌልን
፪. ተአምረ ኢየሱስን
፫. ስንክሳርን እና
፬. መጽሐፈ ግንዘትን በማንበብ ማግኘት ይቻላል::
እንት ዕፍረት [ባለ ሽቱዋ ማለት ነው] ማርያም መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሚያስተምርበት ዘመን [በዘመነ ስብከቱ] የነበረችና ይህ ቀረሽ የማይሏት ቆንጆ ሴት ነበረች:: ግን መልክ የመልካም ነገሮች ምንጭ ሲሆን አይታይም::
በመልካቸው ማማር የጠፉና ያጠፉ ብዙ ሴቶችን ዓለማችን አስተናግዳለች:: ከክሊዎፓትራ እስከ ዘመናችን "ሞዴል" ነን ባዮች : እግዚአብሔር የሰጣቸውን ጸጋ የሰይጣን መደሰቻ : የገሃነም መንገድ አድርገውት ማየት [መስማት] እጅግ ያሳዝናል::
በአንጻሩ ደግሞ ብዙዎችን ያስደመመ መልካቸውን ንቀው : ሰማያዊ ሙሽርነትን የመረጡትን ቅዱሳቱን:- አርሴማን : ቴክላን : ጤቅላን : መሪናን : ጣጡስን : ሔራኒን : ኢራኒን : አትናስያን : ሶፍያን : ኢላርያን . . . ስናስብ ደስ ይለናል:: ዛሬም ጌታ በሚያውቀው ብዙ እናቶቻችን [እህቶቻችንም] ተመሳሳዩን በጐ ጐዳና መርጠው እየተጉዋዙ መሆኑን እናውቃለን::
ቅድስት ማርያምም ከፈጣሪዋ በተሰጣት ቁንጅና ክፋትን ትሠራ ዘንድ ሰይጣን ሲያገብራት "እሺ" ብላ የእሱ ወጥመድ ልትሆን ተራመደች:: ለዘመናትም ዓይነ-ዘማ : ልበ-ስስ የሆኑ ወንዶችን ወደ ኃጢአት ጐዳና ማረከች::
ለመልኩዋ ከነበራች ስስት የተነሳም ቶሎ ቶሎ ራሷን በመጽሔት [መስታውት ማለት ነው] ትመለከት ነበር:: መቼም አምላካችን ለሁሉም የመዳን ቀን ጥሪ አለውና [የሚያስተውለው ቢገኝ] ለማርያም ጥሪውን ላከላት:: ጥሪው ግን በስብከት : በመዝሙር : በመጽሐፍ . . . አልነበረም::
እንዳስለመደች ውበቷን ለመመልከት መስታውት ፊት ቆማ የራሷን ጸጉር : ግንባር : ዐይን : አፍንጫ : ጥርስ . . . እየተመለከተች ተደመመች:: ወዲያው ግን ይህ አካል አፈር እንደሚበላው የሚያስብ ልቡና መንፈስ ቅዱስ አምጥቶባት በጣም አዘነች:: የመኖር ተስፋዋ እንዳይቆረጥ ደግሞ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ዜና ሰማች::
መወሰን ነበረባትና ከሞት ወደ ሕይወት : ከጨለማ ወደ ብርሃን ልትሔድ ቆረጠች:: በአምላኩዋ ፊት የሚቀርቡም 3 ስጦታዎችን አዘጋጀች:: ሰይጣን ሊያጣት አልፈለገምና ወደ ክርስቶስ እንዳትደርስስ ብዙ መሰናክልን ፈጠረባት:: ግን ውሳኔዋ የእውነት ነበርና እያሳፈረችው ወደ አምላኩዋ ገሰገሰች::
የስምዖን ዘለምጽ በረኞችም ሊያስቀሰሯት አልተቻላቸውም:: ወደ ውስጥ ዘልቃ የያዘችውን ሁሉ ለመድኃኒታችን ሰዋች::
፩. ከውስጧ እንባዋን:
፪. ከአካሏ ጸጉሯን:
፫. ከንብረቷ ውድ የሆነውን ሽቱ አቀረበች::
ብዙ ወዳለችና ብዙ ኃጢአቷ ተሠርዮ ቅድስት እናታችን ሆነች:: ብዙ አዝማናትን ከሐዋርያት ጋር አገልግላም በዚህች ቀን ዐርፋለች::
" ቅዱስ አቡሊዲስ መምህረ ኩሉ ዓለም "
+ የዓለም ሁሉ መምህር:
¤ ባለ ብዙ ድርሳንና ተግሣጽ:
¤ የቤተ ክርስቲያን ምሰሶ:
¤ ፴፰ [38] ሕግጋትን የደነገገ:
¤ ስለ ቀናች እምነት የተጋደለ:
¤ መራራ ሞትን በደስታ የተቀበለ:
¤ የቀደመችዋ ሮም ሊቀ ዻዻሳት የነበረና:
¤ ሐዋርያትን የመሰለ አባት ነው::
+በ2ኛው መቶ ክ/ዘመን መጨረሻ አካባቢ ያበራው ይሀን ኮከብ ካቶሊካውያን ክደውታል:: እነርሱ "አቡሊዲስ የሚባል ዻዻስ አልነበረም" ቢሉም ምክንያታቸው ግን ከሰይጣን ነው:: ሃይማኖታቸውን ከመለወጣቸው 250 ዓመታት በፊት ስለተናገረባቸውና አንድ ባሕርይን ስላስተማረ መሆኑን ዓለም ያውቃል::
አባታችን ቅዱስ አቡሊዲስ የተገደለ የካቲት ፭ [5] ሲሆን የካቲት ፮ [6] ሥጋው የተገኘበት ነው::
አምላከ ቅዱሳን ከቅድስት ማርያም ንስሃዋን : ከአባ አቡሊዲስ ምሥጢረ ቅድስናውን ያድለን::
[ † የካቲት ፮ [ 6 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]
፩. ቅድስት ማርያም እንተ ዕፍረት
፪. የዓለም ኁሉ መምሕር ቅዱስ አቡሊዲስ [ብዙ መንፈሳዊ ድርሳናትን የደረሰ ሊቀ ዻዻስና ሰማዕት]
፫. ቅዱሳን አቡቂርና ዮሐንስ [ሰማዕታት]
፬. ቅድስት አትናስያና ፫ [3] ቱ ሰማዕታት ልጆቿ [ቴዎድራ : ቴዎፍናና ቴዎዶክስያ]
[ † ወርኀዊ በዓላት ]
፩. ቅድስት ደብረ ቁስቁዋም
፪. አባታችን አዳምና እናታችን ሔዋን
፫. አባታችን ኖኅና እናታችን ሐይከል
፬. ቅዱስ ኤልያስ ነቢይ
፭. ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ
፮. ቅዱስ ዮሴፍ አረጋዊ
፯. ቅድስት ሰሎሜ
፰. አባ አርከ ሥሉስ
፱. አባ ጽጌ ድንግል
፲. ቅድስት አርሴማ ድንግል
ከበረከተ ቅዱሳን ይክፈለን::
" . . . አንተ ራሴን ዘይት አልቀባኸኝም:: እርሷ ግን እግሬን ሽቱ ቀባች:: ስለዚህ እልሃለሁ : እጅግ ወዳለችና ብዙ ያለው ኃጢአቷ ተሰርዮላታል:: ጥቂት ግን የሚሰረይለት ጥቂት ይወዳል:: እርስዋንም:- 'ኃጢአትሽ ተሰርዮልሻል' አላት:: ከእርሱም ጋር በማዕድ ተቀምጠው የነበሩት በልባቸው:- 'ኃጢአትን እንኩዋ የሚያስተሰርይ ይህ ማነው' ይሉ ጀመር:: ሴቲቱንም:- 'እምነትሽ አድኖሻል: በሰላም ሒጂ' አላት::" [ሉቃ.፯፥፳፮] (7:46)
† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †
[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ ]
† † †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖 🕊 💖