########
የሪልስቴት ህግ እና ረቂቅ አዋጁ(ቀደም ብሎ የተዘጋጀ) ጉባኤ አሰፋ
----------- --------------
#ሪልስቴት ምን አይነት ትርጓሜ ይሰጠዋል?
ሪል ስቴት ማለት ለሽያጭ፣ለኪራይ ወይም ለሊዝ አገልግሎት እንዲውል የተገነባ ህንፃ ማለት ነው በሚል በህንጻ መመሪያ ቁጥር 5/2003 አንቀጽ 2.34 ላይ ትርጉም ተሰጥቶታል::ከህንጻ መመሪያው ትርጓሜ መረዳት እንደሚቻለው ሪልስቴት የሚባለው የተገነባ ህንጻ ብቻ ነው፡፡ስለዚህ ያልተገነባን ህንጻ ሪልስቴት ማለት ከዚህ የህግ ድንጋጌ አንጻር ተገቢነት አይኖረውም ማለት ነው፡፡
በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በመመሪያ ቁጥር SSB/65/2017 አንቀጽ 2.10 ላይ ስለሪልስቴት የሰጠው ትርጓሜ ከህንጻ መመሪያው ጋር አብሮ የሚሄድ ነው::
#ያልተገነባን ህንጻ ለመሸጥ የሚደረግ ውል የሪልስቴት ሽያጭ ውል ሊባል ይችላልን?
በፍትሀብሄር ህግ አንቀጽ 1678(ለ) ላይ እንደተቀመጠው አንድ ውል የሚጸና ውል ነው ለማለት ሶስት ሁኔታዎች ያስፈልጉታል፡፡ከነዚህ የውል አቋሞች ውስጥ ውል የተደረገበት ጉዳይ(object of the contract) ህጋዊ መሆን አለበት በሚል ተቀምጧል፡፡
በፍትሀብሄር ህግ አንቀጽ 2876 ላይ አንድ ወገን ተዋዋይ ለሌላኛው ወገን ተዋዋይ ገና የሌለ ህንጻ ለመስጠት ግዴታ የሚገባበት ውል የህንጻ ስራ ውል ይባላል እንጅ የሽያጭ ውል ሊባል አይችልም በሚል ይደነግጋል፡፡
ይህ ድንጋጌ እና ለሪልስቴት የተሰጠው ትርጓሜ ተገናዝቦ ሲታይ ገና ያልተገነባን ህንጻ በሚመለከት የሚደረግ የሽያጭ ውል የሪልስቴት ሽያጭ ውል ሊባል የሚችል አይሆንም፡፡በነባሩ ህግ ላይ ችግሩ የሚፈጠረው እዚህ ነጥብ ላይ ነው፡፡
ምክንያቱም የማይንቀሳቀስ ንብረት ሽያጭ ውል ራሱን የቻለ ልዩ ባህሪ ያለው ነው፡፡ሻጭ እና ገዥ ተዋዋይ የሚሆኑበት ነው፡፡ዝርዝሩ በውሉ እና በማይንቀሳቀስ ንብረት ሽያጭ ህግ የሚገዛ ይሆናል፡፡ገና ያልተገነባ ህንጻ ደግሞ በሽያጭ ህግ የሚታቀፍ እንዳልሆነ በፍትሀብሄር ህግ አንቀጽ 2876 ላይ ተደንግጓል፡፡
ስለዚህ ያልተገነባን ህንጻ በሚመለከት የሚደረገው ውል በፍትሀብሄር ህግ አንቀጽ 2610 እና ተከታዮቹ እንዲሁም 3019 ጀምሮ በተመለከተው አግባብ የግንባታ ውል ተደርጐ የሚቆጠር ከሆነ ሪልስቴት አልሚው እንደ ተቋራጭ እና ደንበኛው እንደ አሰሪ ሊቆጠሩ ነው ማለት ነው፡፡
በመሆኑም ይህ ሁኔታ ራሱን የቻለ የሪልስቴት ህግ በሌለበት ወቅት ውዝግብ ሲፈጥር የነበረ የህግ ነጥብ ነው፡፡ሆኖም አሁን ላይ ረቂቅ የሪልስቴት ህግ ተዘጋጅቷል፡፡
#በረቂቅ አዋጁ ላይ ገና ያልተገነባን ህንጻ መሸጥ ተፈቅዷል ወይ?
በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 2(1) ላይ ለሪልስቴት የተሰጠው ትርጓሜ የተገነባን ህንጻ የሚመለከት እንደሆነ የሚጠቅስ ነው፡፡
ሆኖም በረቂቁ አንቀጽ 6 ላይ የሀገር ውስጥ አልሚ ቤቱን ሳይገነባ ለቤት ፈላጊዎች በቅድሚያ በሚሸጥበት ወቅት በዝርዝር የተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎችን ማሟላት እንደሚጠበቅበት የሚደነግገው ሲታይ ያልተገነባ ህንጻ መሸጥ በረቂቅ ህጉ የተፈቀደ መሆኑን ያስገነዝባል፡፡ይሄውም አከራካሪውን ጉዳይ እልባት የሚሰጥ ይሆናል፡፡
#በረቂቅ አዋጁ የተካተቱ አንዳንድ ነጥቦች
ረቂቅ አዋጁ ገና በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀ ባለመሆኑ የተወሰኑ ለውጦች ሊኖሩት እንደሚችሉ ይገመታል፡፡ሆኖም ስለሪልስቴት የተካተቱ መሰረታዊ የሚባሉ ነጥቦች እንደሚከተለው ተዳሰዋል፡፡
አዋጁ ከመውጣቱ በፊት የተጀመሩ የሪልስቴት ልማት ስራዎች በአዋጁ መሰረት ተፈጻሚ እንደሚደረጉ በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 33 ላይ ተቀምጧል፡፡
ማንኛውም ሪልስቴት ልማት ለመስራት የሚፈልግ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ባለሀብት በአዋጁ መሰረት አግባብ ካለው አካል የሪልስቴት አልሚ የብቃት ማረጋገጫ ማውጣት እንዳለበት በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 5 ላይ ተቀምጧል፡፡
ለየቤቱ የተናጠል የይዞታ ባለቤትነት ማረጋገጫ ለመውሰድ ቤቱ 80 በመቶ መጠናቀቅ የሚኖርበት ሲሆን ያለደንበኛው ፍላጐትና ፈቃድ አጠቃላይ ግንባታው ቢያንስ 80 በመቶ ያልተጠናቀቀ ቤት ለደንበኛው ማስተላለፍ እንደማይቻልም በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 6 እና 7 ላይ ተቀምጧል፡፡
ሌላው ሪልስቴት አልሚው የይዞታ ማረጋገጫ፣የቤት ግንባታ እቃዎች አይነት፣ዲዛይኑን፣የግንባታ ፈቃድ እና የሪልስቴት ልማት ፈቃዱን ቅጅ ከሽያጭ ውል ሰነዱ ጋር አያይዞ ለደንበኛው መስጠት ግዴታ ተጥሎበታል፡፡
እንዲሁም የመሬት ይዞታ ማረጋገጫና የግንባታ ፈቃድ የሌለው የሪልስቴት አልሚ ደንበኞችን መመዝገብ ሆነ ቅድሚያ ክፍያ መሰብሰብ አይችልም፡፡
#የቅሬታ አፈታትን በተመለከተ ረቂቅ አዋጁ ምን ይላል?
ረቂቅ አዋጁ የቅሬታ መፍቻ ስርአት በአንቀጽ 23 እና ተከታዮቹ ላይ አስቀምጧል፡፡
ለቅሬታ ምክንያት ከሚሆኑ ጉዳዮች ውስጥ ቤት ከሪልስቴት አልሚ ወደ ደንበኛው በሚተላለፍበት ወቅት በስምምነታቸው መሰረት ሳይፈጸም ሲቀር እና የግንባታ ጥራት ጉዳይ እንደሚካተቱ በአዋጁ አንቀጽ 24 ላይ ተቀምጧል፡፡
በሪልስቴት አልሚ በተላለፈለት ቤት በተለይ የግንባታ ጥራት ላይ ቅሬታ ያለው ደንበኛ ቅሬታውን ቤቱን በተረከበ በአንድ አመት ውስጥ ማቅረብ እንደሚችል ተመልክቷል፡፡ከዚህ ድንጋጌ መገንዘብ የሚቻለው የማይታዩ ጉድለቶች የሚባሉትንና ለ10 አመት ተቋራጮች ሀላፊ ሆነው የሚቆዩበትን በፍትሀብሄር ህጉ አንቀጽ 3039 የተደነገገውን የጉድለት አይነት ቢከሰት እንኳ ደንበኛው ከመጠየቅ በይርጋ እንደሚታገድ ነው፡፡ሆኖም ይህ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ቢገባ የተሻለ ይሆናል የሚል ሀሳብ አለኝ፡፡
የፍትሀብሄር ህግ አንቀጽ 3039 ላይ ስራ ተቋራጩ ስራውን ካስረከበበት ቀን ጀምሮ ስለመልካም አሰራሩ እና ስለስራው ስለጠንካራነቱ ለአስር አመት ጊዜ መድን ነው በሚል ተደንግጓል፡፡በዚህ ግዜ ውስጥ በስራ ጉድለት ወይም በተሰራበት መሬት አይነት ምክንያት በተሰራው ስራ ላይ ለሚደርሰው ጉዳት ተቋራጩ ሀላፊነት እንደሚኖርበት ተደንግጓል፡፡ስለዚህ የግንባታ ጥራት ጉዳይ በአጭር ጊዜ ተለይቶ ሊታወቅ የማይችል በመሆኑ በአንድ አመት ግዜ ውስጥ ቅሬታ ካልቀረበበት ሪልስቴት አልሚውን መጠየቅ እንደማይቻል በረቂቅ አዋጁ ላይ የተቀመጠው ድንጋጌ ማሻሻያ ቢደረግበት የተሻለ ይሆናል የሚል ሀሳብ አለኝ፡፡
በሪልስቴት አልሚ እና በደንበኛ መካከል አለመግባባት በተመለከተ የቅሬታ አቤቱታ የሚቀርበው በአዋጁ አግባብ ላለው አካል፣ከዚያም በይግባኝ በ30 ቀናት ውስጥ በጽሁፍ ለአቤቱታ ሰሚ ኮሚቴ፣በኮሚቴ ውሳኔ ቅር የተሰኘ ወገን ደግሞ ውሳኔው በደረሰው በ30 ቀን ውስጥ በህግና በፍሬ ነገር ጉዳይ ላይ ስልጣን ላለው መደበኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ማቅረብ እንደሚችል ተመልክቷል፡፡እዚህ ላይ ስልጣን ላለው መደበኛ ፍርድ ቤት የሚለው አገላለጽ አሻሚ ስለሚሆን የመጀመሪያ ደረጃ የዳኝነት ስልጣን ላለው ወይም ለይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ስለመሆኑ በግልጽና በማያሻማ ሁኔታ ቢቀመጥ ጥሩ ነው የሚል ሀሳብ አለኝ፡፡
#በአጠቃላይ ረቂቅ ህጉ መሰረታዊ የሚባሉ ነጥቦችን ያካተተ በመሆኑ በሪልስቴት ዘርፍ ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ሊቀርፍ የሚችል ነው፡፡በመሆኑም ረቂቅ አዋጁ በተቻለ ፍጥነት እንዲጸድቅ በማድረግ ወደ ስራ ማስገባት የተሻለ ነው፡፡
አመሰግናለሁ