.....የቀጠለ
4.esse est percibi -በርክሌይ
በርክሌ esse est percipi የሚል ፍልስፍናዊ ሀረግ አለው ሃረጉ የተፈጠረው ከላቲን ቃላት ሲሆን፣ ትርጓሜውም “መሆን ማለት ማስተዋል" ነው፡፡ ወንበር በውኑ ዓለም ላይ ያለ ነገር ለመሆን የግድ የሚያስተውለው አካል ያስፈልገዋል፡፡ የሚዳስሰው አልያም የሚመለከተው ሰው ከሌለ ወንበሩ በእውኑ አለም አለ ማለት አንችልም፡፡ በጫካ ውስጥ የወደቀው ዛፍ ሰሚ ከሌለው ድምጽ አያሰማም፣ ጓደኛህም አንተ ካላየኸው ወይም ካልነካኸው በውኑ ዓለም አለ ማለት አንችልም።
የእውኑ ዓለምም የሚፈልቀው ከአንተ አእምሮ በመነሳት ነው፡፡ ህንጻዎችን ስትመለከት፣ የአበባ መዓዛን ስትምግ፣ ትኩስ ቡና ምላስህን ሲያቃጥለው እነዚህ ሁሉ በአእምሮህ ያሉ የእውኑ ዓለም መገለጫዎች ናቸው፡፡ የእውኑ ዓለምም የሚያየው (የሚያስተውለው) አካል ሳይኖር ሲቀር መኖሩ ያበቃለታል፡፡
ሆኖም ግን ሰው (ወይም ሌላ አስተዋይ) በማይደርስበት በረሃ ላይም እኮ ዛፎች፣ ተራሮች፣ ድንጋዮች አሉ ይህ ስለምን ሆነ? ለምንስ እነርሱም አልተሰወሩም፡፡
የባርክሌ ምላሽ ቀላል እና አጭር ነው፤
“እግዚአብሔር አለ!” ተመልካች በሌለበት ሁሉ፣ በአጽናፈ አለሙ በሙሉ እግዚአብሔር ተመልካች ነው፡፡ ለዛም ነው የተከልናት አበባ ወደ ቤታችን እስክንመለስ ድረስ ሳትሰወር የምትጠብቀን፤ ለዚህም ነው በጥቅጥቅ ደን መሃል የወደቀ ዛፍ ድምጽ የሚያሰማው፡፡
5.ቅዱሱ አባትችን -ፍሮይድ
እድሜያችን ምንም ያህል ቢሆን እንኳን በውስጣችን ልጅነት አለ፡፡ ሁሌም ቢሆን እንፈራለን፤ ሁሌም ቢሆን ከችግር የሚያወጣን አልያም እጃችንን ይዞ ጨለማውን የሚያሻግረን አባት እንፈልጋለን፡፡ ህግ አልባ በመሰለችን ዓለም ላይ ነጋችን ምን እንደሚሆን አናውቅምና “አይዞህ አትፍራ እኔ አለሁ” የሚለን አባት ከጎናችን እንዲኖር እንፈልጋለን፡፡
በአለማችን ላይ ስሙ የገነነው ኦስትሪያዊው ኒሮሎጂስት ሲግመንድ ፍሮይድ- ይህ ነው ሰዎች የማይታይ፣ የማይጨበጥ አባት እንዲፈጥሩ ያስገደዳቸው ይለናል፡፡ ሁሉን ቻይ፣ ሁሉን አድራጊ፣ ደስ ባለን ጊዜ የምንጨቀጭቀው ልክ እንደ አባታችን የሆነ አምላክ - እግዚአብሔር።
ፍሮይድ ሁላችንም በህጻንነታችን ደካማ እና እርዳታ ፈላጊ ነበርን ይለናል፡፡ እርዳታም ባስፈለገን ቁጥር ወደ ወላጅ አባታችን እንሄዳለን፤ ሆኖም እያደግን ስንመጣ አባታችን እንደኛ ከፍጹምነት የጎደለ ፍጡር እንደሆነ እና ሁሉንም ፍላጎቶቻችንን ሊያሟላልን እንደማይችል
እንረዳለን፡፡ ነገር ግን ሁሌም ቢሆን ከአደጋ የሚጠብቀን አካል እንዲኖር እንፈልጋለን፡፡
የሰው ልጅ ተፈጥሮ ሲከፋበት፤ ልክ አባቱን እርዳኝ እንደሚለው ሁሉ ፈጣሪውን ይማጸናል፡፡ ልክ በመኪና መንገድ ላይ እጃችንን ይዞ መንገድ እንደሚያሻግረን ወላጅ አባታችን ሁሉ፣ ይህ ፈጣሪ በጨለማ ጊዜያቶቻችን ላይ እጃችንን ይዞ ያሻግረናል፤ ፈጣሪ ለመልካምነታችንም ከረሜላ (ገነትን) ይሸልመናል፤ ስናጠፋም በቀበቶው ይገርፈናል (ወደ ሲኦል ይዶለናል)
ኃይማኖት ከጥንት ጀምሮ የሰዎችን ምኞት ሲያሳካ ቆይቷል። ደካማነታችን ከምንም፣ ከማንም በላይ ሃያል የሆነ አባትን እንድንፈጥር አደረገን፡፡' ኃይማኖት ለሰው ልጆች የሞት ፍርሃትን አስወገደላቸው፤ ነገውን ለማያውቅ ሰውም ሁሉ ነገሩን በአምላኩ ላይ እንዲጥል አስቻለው፤ መልካም በማድረጉም ይሸለማልና መልካምነትን ወደደ፤ ቢያጠፋም በዘላለም እሳት ይቃጠላልና ከእኩይነት ሸሸ፡፡ ለራሱም፤ ሁሉም ነገር ጥሩ ይሆናል... በታላቁ አባትህ እጅ ነህና! "አለው::
6.Abductive reasoning
ፔሊ
በአስራ ስምንተኛው ክፍለ ዘመን የነበረ ዊልያም ፔሊ የሚባል አንድ ቄስ የእግዚአብሔርን መኖር ወይም ሃልወተ እግዚአብሔርን ሊያረጋግጥልን የሚችል ሙግት አነሳ፡፡ ሙግቱም teleological argument ይሰኛል። በእርሱ ሙግትም በጫካ ውስጥ ሲጓዝ ሰዓት ወድቆ ያገኘ ሰው በእርግጠኛነት ሰዓቱ ሰሪ እንዳለው ያውቃል። ሰዓቱም እንዲሁ በዘፈቀደ ንፋስ በሰበሰባቸው ብረቶች አልተሰራም፡፡ እናስ ለዚህ ተራ ሰዓት እንኳ ፈጣሪ ካለው፣ እንዴት ውስብስብ ተደርጎ የተሰራን ሁለንተና (ዩኒቨርስ) ፈጣሪ የለውም እንላለን?
የስው ልጅ ልብ ሳያቋርጥ በደቂቃ ደም እየመጠነ ይረጫል፤ ሳንባው ለሰከንድ እንኳ ሳያቋርጥ አየር ያስገባል አየር ያስወጣል፤ አይኖቹ በዓለም ላይ ካሉ ካሜራዎች ሁሉ በብዙ እጥፍ ምስልን ይቀርጻሉ እናስ ይህ ከእጅ ሰዓት በላይ የተወሳሰበን ፍጡር የአጋጣሚ ሂደት ፈጠረውን?
ከሰው ጀምረን እስከ ሁለንተና ድረስ ተፈጥሮን እየተነተንናት ብንጓዝ ልክ ገዢ እንዳላት ሁሉ፣ በህግ እና በስርዓት ስትመራ እንመለከታታለን፡፡ ተፈጥሮ ከቅንጣት ጀምሮ እስከ ግዙፍ ከዋክብት ድረስ ያሉ ውስብስብ ሰርዓቶችን ይዛለች።
እናም የፔሊ ጥያቄም ይህ ነው - ሰዓትን ለመፍጠር ሰዓት ሰሪ ካስፈለገ፣ ስለምን ተፈጥሮስ ንድፍ አውጪ የላትም?
ይህ የቴሎሎጂካል ሙግት abductive reasoning ወይም ጠላፊ የምክንያት ሂደት ይባላል፡፡ ይህም የነገሩን መጨረሻ በማየት ብቻ መጀመሪያውን ለመገመት ያስችለናል፡፡ ለምሳሌ በግማሽ ነዶ ያለቀ ሲጋራ በመንገድ ላይ ቢያጋጥመን፣ ሲጋራውን ሲያጨሰው የነበረ ሰው እንዳለ መገመት እንችላለን፡፡
በተመሳሳይ ሂደትም የቴሎሎጂካል ሙግትም- የምናየውን የተወሳሰበ ዓለም የፈጠረ እና ዓለም ሁሉ በህገ ተፈጥሮ እንዲመራ ያደረገ አካል አለ፤ እርሱም እግዚአብሔር ነው ይለናል።
@zephilosophy