ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ እንኳን ለጌታችንና ለመድሃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ለማለት እወዳለሁ።
ጌታችንና መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ
በዲያብሎስ እስራት ተይዞ የነበረውን አዳምን ወደ ሚደነቅ ብርሃን ለማሸጋገር፣ በአዳም በደል ምክንያት አጥተነው የነበረውን የክርስቶስ ልጅነትን ዳግመኛ በልደቱ ሊመልስልን፣
እርሱ የሰው ልጆችን ሀጢያት ሳይቆጥር በደለኛ የነበርንበትን የፍዳ ዘመንን በአመተ ምህረት ለውጦ አዳምና ልጆቹን ነፃ ሊያወጣ ፍቅርንም ይመሰርት ዘንድ ክርስቶስ በቤተልሔም በከብቶች በረት ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወለደ።
ቸሩ እግዚአብሔር ለእርሱ ዘመን የማይቆጠርለትና ቦታ የማይወሰንለት ጌታ አምላክ ሆኖ ሳለ እኛን ለማዳን በፍፁም ፍቅር፣ በፍፁም ትህትናና የሰው ሰጋን ለብሶ ዝቅ በማለት ታላቅ ነገርን አድርጎልናል።
ክርስቶስ የሰው ልጆችን በደል ሳይቆጥር ሁሉን ይቅር እንዳለ ሁላችንም ያለፈውን ትተን በአዲስ አስተሳሰብና በተሰጠን ነፃነት ተጠቅመን ቅንና ታማኝ አገልጋዮች በመሆን ሀላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል።
ጌታችንና መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲወለድ ሰብአ ሰገል ልዩ ልዩ ገጸ በረከቶችን ይዘው በቤተልሔም እንደተገኙ፥ እኛም የተቋሙ ሰራተኞች በአንድ ልብ መክረን በጋራ በመሆን፣ በተሰጠን ፀጋና ልዩ ልዩ ችሎታ፣ ፞በህዝብ አገልጋይነት መንፈስ፣ የተጣለብንን አደራና ሀላፊነት እንድንወጣ የዩኒቨርስቲውንም የመማር ማስተማር፣ የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎትና አጋርነት ተልዕኮ በሚገባ እንድናከናውን አሳስባለሁ።
እጅግ ባለጠጋ የሆነው አምላክ ስለእኛ ደሃ የሆነበት ምክንያት በእግዚአብሔርና በሰው ዘንድ የነበረው የጥል ግድግዳ አፍርሶ በልደቱ አዲስ ኪዳን ለመመስረት ነው።
ውድ የተቋሙ ሠራተኞች ተቋሙን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር የአንድነት እርብርብ እና እጅ ለእጅ ተያይዞ በቁርጠኝነት መነሳት ይጠይቃል። በመሆኑም ሁላችንም የአገልጋይነት ባህሪን በመላበስ፣ የተገልጋይ እርካታን በመጨመር፣ በትህትናና በህብረት ዝቅ ብለን በመስራት የተቋሙን ተልዕኮ ልናስፈፅም ይገባል።
በመጨረሻም በዓሉ የሰላም፣ የጤና የፍቅርና የመተሳሰብ እንዲሆንላችሁ ልባዊ ምኞቴን ለመግለጽ እወዳለሁ።
መልካም በዓል ይሁንላችሁ!
ዶ/ር ዳዊት ሃዬሶ
የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት
28/04/2017 ዓ.ም