አንድ መለስተኛ ከተማ ላይ የአእምሮ ህክምና ይጀመርና ለታካሚዎች መድሀኒት ይሰጣቸዋል። በተጨማሪ የንግግር የስነ ልቦና ህክምና ለመጀመር የህብረተሰቡን ፍላጎት ለማጥናት አንድ ባለሞያ የአካባቢውን አንድ ግለሰብ እያወያየ ነው...
"...ከመድሀኒት በተጨማሪ የንግግር የስነ ልቦና ህክምና ቢሰጣችሁ ምን ይመስሎታል?"
"የንግግር ህክምና አልከኝ? እሱ ደግሞ እንዴት ነው?"
"ከባለሞያ ጋር ጊዜ ወስዳችሁ ስላሳለፉት እና አሁን ስላሉበት ሁኔታ በመወያየት የሚደረግ ህክምና ነው።"
ሰውየው አሽሟጠጡና "ወሬ ቢበዛ በአህያ አይጫን" ብለው መለሱ።
ብዙ ሰዎች የንግግር የስነ ልቦና ህክምና አይዋጥላቸውም። ህመምና ህክምና ሲባል ብዙ ሰው የሚመጣለት የሚታዩ ነገሮች ናቸው። የሚታይ የህመም ምልክት (ማነከስ፣ እብጠት፣ ሙቀት መጨመር)፣ ህመሙን
ለማረጋገጥ የሚደረግ የሽንት፣ የፓቶሎጂ (እንዲሁም የታይፈስና የታይፎይድ) ምርመራ፣ ከዛ በመጨረሻ በቀዶ ጥገና የሚወጣ እጢ
ወይም የሚወሰድ ኪኒን- እነዚህ ሁሉ የሚታዩ ነገሮች ናቸው።
በአንፃሩ የንግግር የስነ ልቦና ህክምና ላይ ታካሚው ያለፈባቸውንና አሁን ያለበትን ሁኔታ 'ማውራት' ነው። ህክምናውን የሚሰጠው ባለሞያ ድርሻ በፅንሰ ሀሳብ ላይ ተመስርቶ ታካሚው የታፈኑ ስሜቶቹን እንዲያወጣ፣ ችላ ሲላቸው የነበሩ ነገሮች ላይ ትኩረት እንዲያደርግ፣ ያለፈባቸውን ሁኔታዎች እንዲመረምር እና መለመጥ የሚፈልጋቸው
ፀባዮችና አስተሳሰቦች ሲኖሩ እንዲሞክራቸው ማገዝ ነው። ጥቂት የማይባሉ ሰዎች 'ወሬ' ምንም ለውጥ አያመጣም ይላሉ። ነገር
ግን 'ወሬ' ሰውን ሊያፅናናም ተስፋ ሊያስቆርጥም እንደሚችል ይዘነጋሉ። አስተማሪ ለተማሪዎቹ እውቀቱን የሚያስተላልፈው በ'ወሬ' እንደሆነ ይረሳሉ። የፓለቲካ ሰዎች ብዙ ሰው የሚያነሳሱት በ'ወሬ'
እንደሆነ ትዝ አይላቸውም። ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው ይባል የለ እንዴ የንግግር የስነ ልቦና ህክምና በጣም ውጤታማ የህክምና አይነት ነው። በተለይ በተለይ ከፍተኛ ደረጃ ላልደረሰ ድብርት እና የጭንቀት ህመሞች ተመራጭ ነው።
@UoG_Psych