ተጨማሪ ይመልከቱ 👉 https://getutemesgen.et/8815/
#Ethiopia | በመጽሔቱ የአፍሪካ ተፅዕኖ ፈጣሪ ተብለው የተመረጡት ረድኤት አበበ (ዶ/ር)፣ አበባ ብርሃኔ (ዶ/ር) እና ናርዶስ በቀለ ናቸው።
ረድኤት አበበ (ዶ/ር) በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ፣ በርክሌይ የኮምፒዩተር ሳይንስ ረዳት ፕሮፌሰር ስትሆን፣ በሰው ሠራሽ አስተውሎት የመረጃ አጠቃቀም እና አልጎሪዝም ምርምር ላይ የምትሠራ ሳይንቲስት ናት።
ረድኤት በኤሌክትሪካል ምህንድስና እና የኮምፒውተር ሳይንስ ክፍል የመጀመሪያዋ ጥቁር ሴት ፕሮፌሰር እንዲሁም በዩኒቨርሲቲው ምህንድስና ኮሌጅ ታሪክ ደግሞ ሁለተኛዋ አፍሪካዊት ናት።
ሒሳብ እና አልጎሪዝምን ከኢ-ፍትሃዊነት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን ለመመለስ እንዴት መጠቀም እንደሚቻል ተግባራዊ ምርምሮችን ሠርታ ተሸልማባቸዋለች።
በኢትዮጵያ በነበረችበት ወቅት ያስተዋለችውን ዕድል ማጣትን መነሻ በማድረግም ብዙ ወጣቶች የተለያዩ ዕድሎችን እንዲያገኙ የኑሮ ልዩነት ጥናቶችን ከኮምፒዩተር ሳይንስ ጋር ለማጣመር ከፍተኛ ጥረት እያደረገች ያለች ተመራማሪም ናት ረድኤት።
የትምህርት ዕድል አግኝታ ወደ አሜሪካ ከማቅናቷ በፊት በናዝሬት ስኩል ስትማር የነበረችው ረድኤት፤ እ.አ.አ በ2016 ኪራ ጎልድነር ከተባለች ሌላ ተመራማሪ ጋር በመተባበር የኮምፒውተር ሳይንስን ለበጎ ማኅበራዊ ዓላማ ለማዋል የሚያስችል ባለብዙ ዲሲፕሊን የምርምር ማኅበር መስርታለች።
በዚያው ዓመት ከትምኒት ገብሩ እና ከ1 ሺህ 500 ተመራማሪዎች ጋር በመተባበር በሰው ሠራሽ አስተውሎት ላይ የሚሠሩ ሰዎች ያሉበት እና በማኅበራዊ ኢ-ፍትሃዊነት ላይ የሚሠራ የጥቁሮች ማኅበር (Blacek AI) መስርታለች።
ረድኤት አበበ (ዶ/ር) በዚሁ በተሰማራችበት ዘርፍ እያደረገችው ባለው ጥረት እና እያመጣችው ባለው ለውጥ ምክንያት ከዚህ ዓመት መቶ ተፅዕኖ ፈጣሪ አፍሪካውያን መካከል አንዷ ሆና ተመርጣለች።
ሌላዋ በዚህ መጽሔት ተፅዕኖ ፈጣሪ ሆና የተመረጠችው ኢትዮጵያዊት “አልጎሪዝም በኮድ ውስጥ የታቀፈ አመለካከት” እንደሆነ የምትናገረው አበባ ብርሃኔ (ዶ/ር) ናት።
ኮዱ የሚፈጠረው በነጭ ወንዶች እንደሆነ የምትገልፀው አበባ፣ ብዙውን ጊዜ ነጭ ላልሆኑ ሰዎችና ለሴቶች የማይታይ ጥላቻ እንዳለው አመላክታ፤ በቀሪው ዓለም ላይ የሚያስከትለው አሉታዊ ውጤት በጣም ሰፊ በመሆኑ ይህን ለማጋለጥ መወሰኗን ትናገራለች።
በባህርዳር ተወልዳ ያደገችው እና ከባህርዳር ዩኒቨርሲቲ በኮምፒውተር ሳይንስ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ዲግሪዎቿን ያገኘችው አበባ፤ ወደ አየርላንድ በማቅናት በሥነ-ልቦና እና ፍልስፍና ሁለተኛ ዲግሪ እንዲሁም ከደብሊን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በኮግኒቲቭ ሳይንስ የዶክትሬት ዲግሪዋን አግኝታለች።
ትውልደ ህንዳዊ ከሆነው ፕሮፌሰር ቪኔ ፕራህቡ ጋር በመተባበርም ሰው ሠራሽ አስተውሎት ሲስተም ውስጥ ያሉ እና ዘረኝነትን የሚያንፀባርቁ መጠነ ሰፊ የምስል መረጃዎችን በምርምር ለይተዋል።
የሰው ሠራሽ አልጎሪስቶች ባላቸው የተዛባ አመለካከት ምክንያትም በዕድሜ የገፉ ሠራተኞችን፣ ለአደጋ ተጋላጭ የሆነ ማኅበረሰብን፣ ስደተኞችን እና ልጆችን በአሉታዊ መልኩ እንደሳሉአቸው በምርምሮቿ ለይታለች።
በተደራጁ አጀንዳዎች ምክንያት ተፈጥሯል ስለአለችው ‘Algorithmic Colonization’ በስፋት የጻፈች ሲሆን፣ የኮምፒውተር ሳይንስን ከቅኝ ግዛት አስተሳሰብ ነፃ ለማድረግ ያደረገችው ጥረት በሥርዓቱ በተጎዱት ወገኖች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነትን አስገኝቶላታል።
እ.አ.አ በ2019 ተዛማጅ ሥነ ምግባርን አስመልክቶ ያከናወነችው ውጤታማ ምርምር በBlack In AI የምርምር ማኅበር ሽልማትን አስገኝቶላታል።
እ.ኤ.አ በ2021 ደግሞ የምርጥ ሴቶች ስብስብ በሆነው AI Ethics Hall of Fame መቶ ምርጥ ሴቶች ዝርዝር ውስጥ ተካትታለች።
በታይም መጽሔት የ2023 መቶ ከፍተኛ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ውስጥ የተካተተችው አበባ፣ እየተጠናቀቀ ባለው የፈረንጆች ዓመት በደብሊን ትሪኒቲ ኮሌጅ የሰው ሠራሽ ሥነ-ምግባራዊ ተጠያቂነትን የሚያሰፍን የምርምር ቡድን አቋቁማለች። አበባ በሞዚላ ፋውንዴሽን ስር ሰውሰራሽ አስተውሎትን ለበጎ ዓላማ ለማዋል በተቋቋመው ክፍል ውስጥ ከፍተኛ ተመራማሪም ነች።
ናርዶስ በቀለ የአፍሪካ ሕብረት አዲስ ትብብር ለልማት (AUDA-NEPAD) ዋና ዳይሬክተር ናቸው። በዚህ ኃላፊነታቸውም ሕብረቱ እ.አ.አ በ1963 የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ተብሎ ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ የያዛቸውን ታላላቅ ራዕዮች እውን እንዲያደርግ ብዙ ይጠበቅባቸዋል።
የሕብረቱ የቴክኒክ አካል የሆነው ኔፓድ ድርሻው የፕሮጀክችን እቅድ ማዘጋጀት፣ ቴክኒካዊ እርዳታ ማድረግ እና ለአባል ሀገራት የአቅም ግንባታ ድጋፍ ማድረግ ሲሆን፤ ዋና ዳይሬክቷራ ናርዶስ ይህን ኃላፊነታቸውን በብቃት እየተወጡ እንደሆነ ከመጽሔቱ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
እ.አ.አ በ2022 የኔፓድ ዋና ዳይሬክተር ሆነው ከመሾማቸው በፊት በደቡብ አፍሪካ የተመድ ማስተባበሪያ ቢሮን ጨምሮ በዓለም አቀፍ የልማት ድርጅቶች ውስጥ ከአራት አሥርት ዓመታት በላይ በኃላፊነት ሠርተዋል። በኬንያ እና በቤኒን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም (UNDP) ተወካይ እንዲሁም በተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ ቢሮ ከፍተኛ ዳይሬክተር ሆነው አገልግለዋል።
ኔፓድን ለመምራት የመጀመሪያዋ ሴት እንደመሆናችም፤ በአፍሪካ ሕብረት ውስጥ የሴቶች እና የወጣቶች ተሳትፎ እንዲያድግ እና ፍትሃዊነት እንዲሰፍን እየሠሩ እንደሆነ ተጠቅሷል።
በአፍሪካ ሀገራት መካከል ቀጣናዊ ግንኙነት እንዲጠናከር፣ የግብርና ትራንስፎርሜሽን እንዲስፋፋ እና የወጣቶች ሥራ አጥነት እንዲቀንስ የክህሎት ሥልጠናዎች ላይ ትኩረት አድርገው መሥራታቸው ተፅዕኖ ፈጣሪነታቸውን እንደሚያጎላው በመጽሔቱ ላይ የወጣው መረጃ ያመላክታል።
በለሚ ታደሰ
የጌጡ ተመስገንን ትክክለኛ የቴሌግራም ቻናል ይቀላቀሉ 👉
@getutemesgenet
@getutemesgenet
@getutemesgenet
@getutemesgenet