*******
የጎንደር የኒቨርሰቲ “የአካል ጉዳተኞችን የአማራርነት ሚና በማጉላት አካታችና ዘላቂ ልማትን ማረጋገጥ” (Amplifying the Leadership of Persons with Disabilities for an Inclusive and Sustainable Future)” በሚል መሪ ቃል፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ 33ኛ ጊዜ - በሀገራችን ደረጃ ደግሞ ለ 32ኛ ጊዜ የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን ዛሬ ህዳር 28/2017 ዓ.ም በተለያዩ ዝግጅቶት አክብሯል፡፡
በእግር ጉዞ የተጀመረው ይህ መርሀ ግብር፣ በዩኒቨርሰቲው የአካል ጉዳት ጥናትና አገልግሎት ዳይሬክትር፣ በዩኒቨርሲቲው ማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ስኮላርስ ፕሮግራም እንዲሁም በዩኒቨርሰቲው የአካል ጉዳተኞች ማህብር በጋራ በትብብር የተዘጋጀ ሲሆን፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስራት አጸደወይን፣ የዕለቱ ልዩ የክብር እንግዳ አቶ መርሀፅድቅ መኮንን፣ የአማራ ክልል ሴቶች፣ ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ም/ኃላፊ ወ/ሮ ንጹህ ሽፈራው፣ የአማራ ክልል የአካል ጉዳተኛ ማህበራት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ፍሬሰላም ዘገየ፣ የዩቨርሲቲው ማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ስኮላርስ ፕሮግራም ዳይሬክተር ዶ/ር ሞላልኝ በላይ (ስለ በዓሉ መልዕክት ያስተላለፉ)፣ የዩኒቨርሲቲው የአካል ጉዳት ጥናትና አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ታረቀኝ አስናቀ (እንግዶችን በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር የተቀበሉ)፣ የዩኒቨርሰቲው የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው የአካል ጉዳተኛ ሰራተኞችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በበዓሉ አከባበር ስነ-ስርዓት ላይ ተሳትፈዋል፡፡
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ያለው አሰራርና ሌሎች ምቹ ሁኔታዎች ለአካል ጉዳተኛ ተማሪዎችም ተስማሚ በመሆናቸው ተቋሙ በቀዳሚ ደራጃ እንዲመረጥ እንዳስቻለውና በአሁኑ ሰዓት በሌሎች የትምህርት ተቋማት ባልተለመደ ሁኔታ ከ 500 በላይ የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎችን፣ ከ 86 በላይ የአካል ጉዳተኛ ሰራተኞችን እንዲሁም 22 የአካል ጉዳተኛ መምህራንን በልዩ ትኩረት ለማካተት እንደተቻለ ዶ/ር አስራት በመክፈቻ ንግግራቸው ተናግረዋል፡፡ ዩኒቨርሰቲው ከመማር ማስተማሩ በተጨማሪ ልዩ ድጋፎችን በማድረግና የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን በማሟላት አካል ጉዳተኞች በትምህርት፣ በማህበራዊ ጉዳይና በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ በላቀ ሁኔታ እየሰራ እንደሚገኝም በፕሬዚዳንቱ ተገልጿል፡፡
ይህ በዓል ሲከበር አካል ጉዳተኞች ያሉባቸው ውስንነቶች የሚታወሱበት ሳይሆን፣ ለሀገራችን ብሎም ለዓለማችን ያላቸውን ጉልህ ድርሻ የምንዘክርበት እንዲሁም ጥንካሬአቸውን፣ አይበገሬነታቸውንና ቁርጠኝነታቸውን የምንዘክርብት ዕለት ጭምር እንደሆነ ዶ/ር አስራት በማጠቃለያ ሀሳባቸው ተናግረዋል፡፡
እንደ ሌሎች ሰዎች ሁሉ ሰብዓዊ ከበሬታ (Human Dignity) ሲገባቸው የአካል ጉዳተኞች በሀገራችን ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚገባቸው ልክ የሰብዓዊ መብቶች ባለቤት ሆነዋል ለማለት እንደሚያስቸግር ባደረጉት የቁልፍ ንግግር የገለጹት ደግሞ የዕለቱ የክብር እንግዳ አቶ መርሀ-ጽድቅ መኮነን ናቸው፡፡ ስለሆነም ከዚህ ስሁት አመለካከት በመላቀቅ እርስ በእርስ ተደጋግፎና ተሳስቦ የመስራት ባህል ማሳደግ እንደሚገባ በአቶ መርሀጽድቅ ንግግር አጽንኦት ተሰጥቶታል፡፡
የአማራ ክልል ሴቶች፣ ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ም/ኃላፊ ወ/ሮ ንጹህ በተመሳሳይ መልኩ በዕለቱ መርሀ ግብር አብይ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ በሁሉም የህይዎት መስኮች ከአካል ጉዳተኞች ጋር ተያያዥነት ያላቸው ሚዛናዊ ያልሆኑ አመለካከቶችን፣ የተዛቡ አቋሞችንና ጎጂ ልማዶችን በጋራ መዋጋት እንደሚገባና፣ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በአካል ጎዳተኞች እምቅ ችሎታና አስተዋጽኦ ረገድ ሊኖረው የሚገባውን ግንዛቤ ከፍ ለማድረገ ሰፊ ስራ መሰራት እንዳለበት በም/ል ኃላፊዋ መልዕክት ትኩረት ተደርጎበታል፡፡
በዕለቱ መሰናዶ አካል ጉዳተኝነትና አመራርነትን የተመለከተ ለውይይት የሚሆን መነሻ ጹሁፍ በዩኒቨርሲቲው የህግ መ/ር በሆኑት በ ዶ/ር በቀለ አዳነ ቀርቦ ከተሳታፊዎች ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡ በዩኒቨርሰቲው የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች የተለያዩ ኪነ-ጥበባዊ ስራዎች ቀርበዋል፣ ስፖርታዊና የጎዳና ላይ ትይንቶችም ተከናውነዋል፡፡ በመጫረሻም በዩኒቨርሲቲው የአካል ጉዳተኛ ሰራተኞች ማህበር ፕሬዚዳንት በሆኑት በአቶ ስዩም ጥላሁን የማጠቃለያና የመዝጊያ ንግግር ተደርጎ ፕሮግራሙ ተጠናቋል፡፡
*******
ለልህቀት እንተጋለን!
የህዝብና ዓለምአቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት
ህዳር 28/2017