ይህንን ደብዳቤ ለመጻፍ የፈለኩት ያለብሽን እዳ ላስታውስሽና እንድትከፍለኝ ለመጠየቅ ነው፡፡
• ግቢ ውስጥ ያደገውን ሳር የቆረጥኩበት = 5 ብር
• ክፍሌን ያጸዳሁበት = 2 ብር
• ወደ ሱቅ የተላላኩበት = 3 ብር
• ሱቅ ስትሄጂ ወንድምህን ጠብቅ ብልሽኝ የጠበቅኩበት = 4 ብር
• ቆሻሻ የደፋሁበት = 5 ብር
• ትምህርት ቤት ጥሩ ውጤት ያመጣሁበት = 5 ብር
ያለብሽ እዳ ጠቅላላ ድምር = 24 ብር
ብዙ ውለታ ያደረገችለትና በጣም የምትወደው ልጇ ሁኔታውን በዚህ መልኩ ማየቱና ያደረገውን ሁሉ እንደ እዳ መቁጠሩ በጣም አስገረማት፡፡ ሁኔታውን በምን መልክ እንደምትይዘው ካሰበች በኋላ ወረቀቱን ገለበጠችና እንዲህ የሚል የምላሽ ደብዳቤ ጻፈችለት፡-
እዳዬን ስላስታወስከኝ አመሰግናለሁ፡፡ በመጀመሪያ አንተ ያለብህን እዳ ላስታውስህና አሁንም እዳ አለብሽ ካልከኝ እከፍልሃለሁ፡፡
• ዘጠኝ ወር ሙሉ ማህጸኔ ውስጥ የተሸከምኩበት = ከክፍያ ነጻ
• በታመምክ ጊዜ ሁሉ ወደ ሃኪም ቤት ያመላለስኩበትና ገንዘብ ከፍዬ ያሳከምኩበት = ከክፍያ ነጻ
• ሌሊት ስታለቅስ ቁጭ ብዬ በመንከባከብ ያደርኩበት = ከክፍያ ነጻ
• ከልጅነትህ ጀምሮ ጡት ያጠባሁበትና በየቀኑ ምግብ ሰርቼ ያበላሁበት = ከክፍያ ነጻ
• መጫወቻ፣ ልብስና ጫማ የገዛሁበት = ከክፍያ ነጻ
• አንድ ነገር እንዳይደርስብህ ወደ ፈጣሪ ጸሎት በማድረግ ያሳለፍኳቸው ቀናትና ሰዓታት = ከክፍያ ነጻ
ያለብህ እዳ ጠቅላላ ድምር = 0
ይህንን የእናቱን ደብዳቤ ያነበበው ይህ የአስራ ሶስት አመት ልጅ ሳያስበው አይኖቹ በእንባ ተሞሉ፡፡ እስከዛሬ የታየው እሱ አደረኩኝ የሚለው እንጂ የተደረገለት ነገር አልነበረም፡፡ የእናቱ ምላሽ እድሜ ልኩን የማይረሳ ትዝታን ተወለት፡፡
አንዳንድ ሰዎች እነሱ የከፈሉትን መስዋእትነት ብቻ የመቁጠር ዝንባሌ አላቸው፡፡ ካለፈው ሁኔታቸው አልፈው እዚህ ለመድረሳቸው ምክንያት የሆናቸው ሰውና ሁኔታ እንዳለ ለማሰብ ጊዜም የላቸው፡፡
የታሪኩን ተግባራዊነት ለእናንተው ትቼዋለሁ፡፡
(“ትኩረት” ከተሰነው የዶ/ር ኢዮብ መጽሐፍ የተቀነጨበ)