ብሔረ ሕያዋን ያሉ እነ ሄኖክና ኤልያስም ‹‹ሰው ከሚሞትበት ሀገር ሞት ወደሌለበት አገር ማን አመጣው?›› አሉ፡፡ መልአኩም በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር ባዘዘኝ ጊዜ እኔ ገብርኤል ነኝ ያመጣሁት›› አላቸው፡፡ ቀጥሎም መልአኩ ‹‹አንተ ሄኖክ ምንም ንጹሕ ብትሆን በሥርዓተ ሥጋ ተወልደህ በሥርዓተ ሥጋ አድገህ ሚስት አግብተህ ወልደሃል፣ እግዚአብሔርም እዚህ ያደረሰህ በንፅህናህ ነው፤ አንተም ኤልያስ ምንም ድንግል ብትሆን በሥርዓተ ሥጋ ተወልደህ በሥርዓተ ሥጋ አድገህ ከዚህ ደርሰሃል፤ ይህ አባ ዮሐኒ ግን ከተወለደ ጀምሮ የእናቱን ጡት አልቀመሰም፣ ቀን ቀን ሰሳ እያጠባችው ሌሊት ሌሊት ንስር አሞራ በክንፎቹ እያለበሰው አድጓል እንጂ›› ብሎ ነገራቸው፡፡ ቀጥሎም መልአኩ የአባ ዮሐኒን ገድል ዘርዝሮ ከነገራቸው በኋላ ሊሞት ያለበትንም የአሟሟቱን ነገር ከነገራቸው በኋላ ‹‹ታዲያስ እንዲህ ያለውን አምጥቼ ከብሔር ሕያዋን ባስገባው ፍርዴ እውነት አይደለምን/›› አላቸው፡፡ ሄኖክና ኤልያስም ይህን ጊዜ ‹‹ይገባዋል›› ብለው አባ ዮሐኒን በምስጋና ተቀበሉት፡፡
ከዚህም በኋላ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ወደ ደብረ ዓሣ ተመልሶ መጥቶ ለአባ አበይዶ ተገለጠላቸውና አባ ዮሐኒን ብሔረ ሕያዋን እንዳስገባው ነገራቸው፡፡ በመጀመሪያ ሄኖክና ኤልያስ አላስገባ ብለው እንደነበርና በኋላም መልአኩ ራሱ የአባ ዮሐኒን ገድላቸውን ከነገራቸው በኋላ በምስጋና እንደተቀበሉት ለአባ አበይዶ ነገራቸው፡፡ ቀጥሎም መልአኩ የአባ ዮሐኒን ገድላቸውን እንዲጽፉትና እንዲያስተምሩበት ለአባ አበይዶ አዘዛቸውና ዐረገ፡፡ አባ አበይዶም አባ ዮሐኒ ከገደሉ ተወርውረው ሲወደቁ አንድ ደስ የሚል ወንድ ሲቀበለው አይተው ነበርና አሁን መልአኩ ሲነግራቸው እጅግ ደስ አላቸው፡፡ አባ አበይዶም በታዘዙት መሠረት የአባ ዮሐኒን ገድል ጻፉት፡፡ እርሳቸውም ትናንት ኅዳር 4 ቀን በሰላም ዐረፉ፡፡
ረድኤት በረከታቸው ይደርብን በጸሎታቸው ይማረን!
+ + +
ዳግመኛም በዚኽች ዕለት በአስቄጥስ ገዳም በሰማዕትነት ያረፉት የ49 መነኮሳትም በዚሁ ዕለት መታሰቢያቸው ሆነ፡፡ (የዕረፍታቸውን ዕለት ጥር ሃያ ስድስትን ይመልከቷል፡፡) ረድኤት በረከታቸው ይደርብን በጸሎታቸው ይማረን!