በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን አርባምንጭ ከተማ አስተዳደር ጉርባ በሚባል ቀበሌ የገዛ እጮኛዉን ጭካኔ በተሞላበት መልኩ በአሰቃቂ ሁኔታ በስለት አንገቷን በመቁረጥ ሕይወቷ እንዲያልፍ ያደረገዉ ወጣት በፅኑ እስራት መቀጣቱን የአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ም/ኢንስፔክተር ጋፋሮ ቶማስ ተናግረዋል።
የወንጀል ድርጊቱ የተፈፀመዉ ነሐሴ 16/2016 ዓ/ም በአርባምንጭ ከተማ ጉርባ ቀበሌ ነው።
ተከሳሽ ዮናስ ጫፊቄ የተባለው ግለሰብ የጂንካ ዩኒቨርሲቲ 1ኛ ዓመት ተማሪ የሆነችዉን ሟች ሊዲያ ዮሐንስ እሱን ለማስመረቅ ወደ አርባ ምንጭ ከተማ በመጣችበት ተከራይቶ በሚኖርበት ቤት አሰቃቂ ድርጊቱን መፈፀሙን የምርመራ መዝገቡ ያስረዳል።
ወጣቷ " እጮኛዬ ይመረቅልኛል " በሚል ደስታ ከቤተሰቦቿ ተደብቃ ተከሳሽ ተከራይቶ ወደ ሚማርበት ቤት መጥታ በዋዜማዉ ለምረቃዉ የሚሆኑ የዲኮር፣ የዳቦና ለስላሳ መጠጦችና በቡና ዝግጅት ቤቱን አሰማምራ በምሽቱም ግቢ ዉስጥ ያሉ ተከራዮችን ጠርተዉ ከሸኙ በኋላ ሟች ሀገር ሰላም ብላ በተኛችበት ከሌሊቱ 7 ሰዓት ገደማ እራሷን መከላከል በማትችልበት ሁኔታ በቢላዋ አንገቷን አርዶ መግደሉን የምርመራ መዝገቡን ዋቢ አድርገው ፖሊስ አዛዡ ገልፀዋል።
ፖሊስ አዛዡ አክለው እንደገለጹት ፥ በወቅቱ በተደረገዉ ማጣራትም ሆነ በክስ መዝገቡ ላይ እንደሰፈረዉ ወንጀለኛው " ወደ ዩኒቨርሲቲ በሄድሽበት ሌላ የወንድ ጓደኛ ይዘሻል " በሚል ነው በር ዘግቶ አሰቃቂ የወንጀል ድርጊቱን የፈጸመው።
ፖሊስ በዚህ ዘግናኝ ወንጀል ዙሪያ ተገቢዉን ማጣራትና ምርመራ አድርጎ ለዐቃቤ ሕግ ማቅረቡን አስታውቀዋል።
ዐቃቤ ሕግም ክስ በመመስረት ለፍርድ ቤቱ ተከሳሽ የወንጀል ድርጊቱን መፈፀሙን የሰዉ፣ የሰነድና የህክምና ማስረጃዎችን በማቅረብ አስረድቷል።
በቀረቡ ማስረጃዎች እና ምስክሮች ግራ ቀኙን ሲያጣራ የቆየዉ የጋሞ ዞን ከፍተኛዉ ፍርድ ቤት በቀን 29/5/2017 ዓም በዋለዉ ችሎት ተከሳሽ ዮናስ ጨፊቄ በተከሰሰበት በአሰቃቂ ሁኔታ ነብስ የማጥፋት ወንጀል ጥፋተኛ መሆኑን በማረጋገጥ በ20 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ መወሰኑንም ኢንስፔክተር ጋፋሮ ቶማስ ተናግረዋል።