#Ethiopia | የወንጀል ድርጊቱ የተፈፀመው በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 ክልል ልዩ ቦታው አርሴማ ፀበል እየተባለ ከሚጠራው አካባቢ ነው። ሟች ወ/ሮ አልማዝ እሸቱ ተከሳሽ ፀሀዬ ቦጋለ ከተባለው ግለሰብ ጋር ትዳር መስርተው የሚኖሩ ጥንዶች ነበሩ።
ነሀሴ 27 ቀን 2014 ዓ/ም ከቀኑ 5:00 ሰአት ሲሆን ተከሳሽ ሟች አልማዝ እሸቱን ከሌላ ወንድ ጋር ትገናኛለሽ ስልክ ትደዋወያለሽ በሚል ጥርጣሬ ተነሳስቶ ሟች ለጉዳይዋ ከቤት ለመውጣት ልብስ ለብሳ ጫማ ለማሰር ባጎነበሰችበት ወቅት በሊጥ መዳመጫ እንጨት ማጅራቷን በመምታት ህይወቷ እንዲያልፍ በማድረግ የሟችን አስክሬን በመኖሪያ ቤቱ ውስጥ ባለው መጸዳጃ ቤት ውስጥ በማስገባት የግራ እግሯን ከዳሌዋ እስከ ባቷ ያለውን የሰውነት ክፍሏን በመቁረጥ፣ ስጋዋን በመመልመልና በመክተፍ የመጸዳጃ ሲንክ ውስጥ ውስጥ በመክተት ቀሪውን የሰውነት ክፍሏን ደግሞ መፀዳጃ ቤት ውስጥ ይደብቃል፤ የፖሊስ የምርመራ መዝገብ እንደሚያስረዳው ተከሳሽ ፀጋዬ ቦጋለ የአልማዝ መጥፋት ላሳሰባቸው ለቤተሰቦቿ እና ለስራ ባልደረቦቿ ገዳም እንደሄደች ለማሳመን ሞክሯል።
ሆኖም በመኖሪያ አካባቢው የተለየ ሽታ መከሰቱ ያሳሰባቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ለፖሊስ ያቀረቡትን አቤቱታ መነሻ በማድረግና ወደ አካባቢው በመሄድ የሟችን አስክሬን በማንሳት ወንጀል ፈፃሚውን በቁጥጥር ስር ያውለዋል፡፡
ተከሳሹ ላይ የሚቀሩ የምርመራዎችንና ተጨማሪ ማስረጃዎችን በማሟላት የወንጀል ድርጊቱን መፈፀሙን በሰጠው ቃል ከማረጋገጡም ባሻገር የወንጀል አፈፃፀሙን የሚመለከታቸው የሕግ ባለሙያዎችና ታዛቢዎች በተገኙበት መርቶ አሳይቷል።
ጉዳዩን ሲከታተል የቆየው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ ወንጀል ችሎት ነሃሴ 28 ቀን 2016 ዓ/ም በዋለው ችሎት ተከሳሽ ፀሀዬ ቦጋለ ጥፋተኛ ሆኖ በማግኘቱ በእድሜ ልክ ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ከተወሰነ በኋላ ውሳኔውን በመቃወም ጉዳዩን ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ቀርቦ የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ጥር 12 ቀን 2017 ዓ/ም በዋለው ችሎት ተከሳሽ በሞት እንዲቀጣ ወስኖበታል።
ዘገባ:-ኢንስፔክተር እመቤት ሀብታሙ