የቤ/ጉ/ክ/መ/ጤ/ቢሮ ኃላፊ አቶ አለም ደበሎ በኡንዱሉ ወረዳ ወረዳ በተካሄደዉ የጤና መድህን ማስጀመሪያ ፕሮግራም ላይ እንዳሉት ወረዳዉ ከ50 በመቶ በላይ የጤና መድህን ተጠቃሚ ማህበረሰብ መዝግቦ ለጉባኤ መድረስ መቻሉ የወረዳውን ጥንካሬ የሚያሳይ መሆኑን ገልጸው ማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት እስከታች በማውረድ ለማህበረሰቡ አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ የሁሉንም ርብርብ የሚጠይቅ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ቢሮ ኃላፊው አክለው እንዳሉት ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተየይዞ የተነሱ ችግሮችን አስመልክቶ የወረዳው ጤና ጽ/ቤት በጤና ተቋሙ ያለውን ክፍተት ለይቶ እንዲያቀርብና ቢሮው በተቻለው መጠን ችግሮቹን ለመቅረፍ የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት ዝግጁነታቸውን ገልጸው በወረዳው የጤና ጣቢያ ጤና ኬላ ትስስርን በማጠናከር ችግሮችን በጋራ መቅረፍ መቻል እንዳለባቸውም አሳውቀዋል፡፡
የፌደራል ጤና መድህን አገልግሎት ባለሙያ አቶ ጋሻው አሰፋ በበኩላቸው የኡንዱሉ ወረዳ በአገር አቀፍ ደረጃ የጤና መድህን ከጀመሩ ወረዳዎች 1057ኛ እንዲሁም በክልል ደረጃ 9ኛ ወረዳ በመሆናቹ እንኳን የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ከጀመሩት ወረዳዎች መሆናቸውን ገልፀዉ የወረዳው አመራሮች ለሥራዉ ቅድሚያ ሰጥተዉ መሥራት እንዳለባቸዉ ገልፀዉ ለፕሮግራሙ መሳካት በተቋማቸዉ በኩል አስፈላጊውን ሁሉ እገዛ እንደሚያደርግላቸው ቃል ገብተዋል፡፡
የኡንዱሉ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታጁዲን አልጀሊ በበኩላቸው የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ተግባራዊ እንዲሆን በነበረው ሂደት ውስጥ የወረዳው አመራሮች፤ የወረዳው ነጋዴ ማህበረሰብ እና አጠቃላይ ማህበረሰቡ ላደረገው ጥረት ምስጋናቸውን በማቅረብ ለብዙ አመታት ማህበረሰቡ ሲያቀርብ የነበረው ጥያቄ ዛሬ መልስ በማግኘቱ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
አስተዳዳሪው አክለውም ምንም እንኳን ወረዳው የጤና መድህን ተጠቃሚ መሆኑ ትልቅ ድል ቢሆንም ስራውን አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚመለከታቸው አካላት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲያበረክቱ ጠይቀዋል ።
በጉበኤው ላይ የተሳተፉ የወረዳ ነዋሪዎች በማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን በወረዳቸው መጀመሩ እንዳስደሰታቸውና አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል።
በጉባኤው ማስጀመሪያ መርሀ ግብር ላይ የቤ/ጉ/ክ/መ/ክልል መስተዳድር ምክር ቤት የማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ አቶ ጌታቸው ፊሊጶስ ፤ የአሶሳ ዞን/ም/አስተዳዳሪ አቶ አህመድ ሙሳ የቤ/ጉ/ክ/መ/ጤ/ቢሮ ኃላፊ አቶ አለም ደበሎ ፤የቤ/ጉ/ክ/መ/ ጤና የፕሮግራም /ም/ቢሮ ኃላፊ
አቶ አብዱልሙኒየም አልበሽር እንዲሁም የአሶሳ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ አንዋር ያሲን ተገኝተዋል፡፡