Abduljelil Sheikh Ali Kassa @abduljelilshekhalikassa Channel on Telegram

Abduljelil Sheikh Ali Kassa

@abduljelilshekhalikassa


Articles, audio visual posts

Abduljelil Sheikh Ali Kassa (English)

Are you interested in thought-provoking articles and engaging audio visual posts? Look no further than the Abduljelil Sheikh Ali Kassa Telegram channel! This channel, run by the knowledgeable and insightful Abduljelil Sheikh Ali Kassa, offers a variety of content that will stimulate your mind and spark interesting discussions. Whether you're looking for informative articles on current events, in-depth analysis of trending topics, or captivating audio visual posts that will entertain and educate, this channel has it all. Abduljelil Sheikh Ali Kassa is a trusted source for quality content that is both engaging and informative. Join the Abduljelil Sheikh Ali Kassa Telegram channel today and elevate your knowledge and awareness with every post!

Abduljelil Sheikh Ali Kassa

12 Nov, 03:29


እዚህ አገር ልጅ መውለድ በደል አይደለምን?

በደረቀ ሌሊት ይህን ቪዲዮ ተመልክቸ ይሄው እንደፈጠጥኩ አለሁ።

ይህን ነውር፣ ይህን ወንጀል፣ ይህን ጉድ፣ ይህን ፅያፍ፣ ይህን በጭካኔና በነውር የመሰልጠን ውድድር፣ ይህን መሳይ እጅግ ከሰውነት የወጣ ወንጀል በምን ትገልፀዋለህ?

ወንጀለኞች ዛሬ ጊዜው ተመችቷቸዋል። ወንጀሎችን ተደብቆ ሰው አየኝ አላየኝ፣ ታወቀብኝ አልታወቀብኝ ብሎ ከሰው ተሸሽጎ ወንጀል መስራት ድሮ ቀረ። የክፋት ውድድር ላይ ናቸው። በወንጀላቸው በክፋቱ፣ በጭካኔው፣ በነውርነቱ ክረት እየተፎካከሩ በቪዲዮ ቀርፀው ለሰፊው ህዝብና መንግስት ይለቁለታል።

ወንጀለኞች ወንጀላቸውና ፈፃሚዎቹ በህግና በሥርዓት እንዳይዳኙ ወቃሾች ወንጀለኞቹንና ወንጀላቸውን ትተው የተገኙበትን ብሄር ታርጌት ያደረገ ውግዘትና ዘመቻ ያደርጋሉ። ወንጀለኞቹ የተገኙበት ብሄር ብሄርተኞች በአልክና በታቀደ መልኩ ለወንጀለኞቹ ከለላ ይሰጣሉ። ያቅፋሉ። በዚህ አዙሪት እንሆ አመታት አሳለፍን።

ሁለት ወጣቶችን (እህትና ወንድሞች ናቸው ይላሉ። ግን ቋንቋ ስለማልችል አላረጋገጥኩም) ወደ ጫካ ወስዶ በዝንጣፊ ዱላ ቶርች እያደረጉ ወሲብ እንዲፈፅሙ ማስገደድ፣ እጅግ ጨካኝ በሆነ መልኩ መደብደብ፣ ወሲብ አስገድዶ በማስፈፀም ያንን መቅረፅ፣ እየሳቁ እየፈነደቁ ቆሞ በግድ ማስፈለፀምና መቅረፅ አንድ ሰውነትን ተጎናፅፎ ሰው ከተባለ ፍጡር የሚገመት አይደለም። መድፈር ያለ እና የተለመደ ወንጀል ነው። እህትና ወንድምን (ከሆኑ) ወይም ሁለት ወጣቶችን ጫካ ወስዶ እያስገደዱ ወሲብ እርስ በእርሳቸው እንዲፈፅሙ አስገድዶ ያንን ቀርፆ ለህዝብና ለመንግስት መላክ ግን ኢትዮጵያ የምንላትንን አገር የደረሰችበትን የባርባሪዝም ተጨባጭ የሚያሳይ ነው።

ብሄርተኞች፣ ወንጀለኞች፣ ነውረኞች ባርባሪያን፣ እንዳሻቸው ወንጀል እየፈፀሙ ይኖሩ ዘንድ ሆነ ተብሎ የተተወ የህግ የባላይነት፣ የተቀለበሰ law and orders ያስገኙልን ትሩፋቶች መካከል አንዱ ይህ ነው።

Mob justice and collective punishment
Cruel genocide and ethinic cleansing
Insecurity and uncertainty
Social decay and gangsters

Abduljelil Sheikh Ali Kassa

12 Sep, 02:40


ሸኽ ዐሊ ጂሩ! ተከፍሎበታል ወዳጄ!!
******

ወሎስ መች አፈራ …እንደ ጂሩ ያለ
በቂረአት ከርሞ… ከጂሀድ የዋለ

እስልምና ወሎ ላይ ታሪክ ሰርቷል፡፡ ወሎ ላይ ስልጣኔን ገንብቶ መንግሥታዊ ሥርዓትን ዘርግቶ፣ ዩኒቨርሲቲዎችን አንብሮ ለመላ ኢትዮጵያ የእስልምና መዐከል ሆኖ የሀይማኖቱ የትምህርት ስርጭት ኒዩክለስ የመሆኑን ያክል ለመዐከላዊው መንግሥት ተወዳዳሪ ኢማማዊ ስርዎ መንግሥትን አቅርቦ ለመአከላዊው መንግሥትነት ከሚፋለሙት ሰለሞናዊው ሥርዎ መንግሥት ጋር ሲፋለም ኖሯል። ከእነ አሊ ጎዳናው ፡የማመዶች ሥርዎ መንግሥትን ብቻ አይደለም ወሎ በተፎካካሪነት ያቀረበው። የየጁው ወረ ሸኽ ሥርዎ መንግሥት ጎንደር ድረስ ዘልቆ ልዕልናውን አሳይቷል። ዋጎቹ ዋግሹሞች አይረሴ ናቸው፡፡ ወሎ ላይ መሰረቱን ጥሎ በመንግሥትነትም በሃይማኖቱ መስፋፋትና ትምህርት ኒኩዩለስነቱ ምክንያት ከቴዎድሮስ እስከ ኃ/ሥላሴ ወሎ እጅጉን መከራ አይቷል፡፡ ከፓለቲካው ባሻገር ሃይማኖታዊ ጥቃትን ለመከላከል አያሌ የወሎ መሻኢኾችና ዑለማዖች ጎራዴ ታጥቀው፣ ሰይፍ አንግበው ደረሳ አስከትለው ከመአከላዊው መንግሥት ጋር ሲፋለሙ ኖረዋል፡፡ አስገዳጅ አጥምቆትን ለመከላከል ሰይፍ አንግበው ከታገሉ ሙጃሂዶች መካከል የቢለኑ ጌጥ ሸኽ ዐሊ አደም ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ሸኽ ዐሊ አደም በገናና ስማቸው ሸኽ ዐሊ ጂሩ ተብለው ይታወቃሉ፡፡

ሸህ አሊ ገራዶ …የቢለኑ ኑር
ሸህ አሊ ጃሩላህ …የቢለኑ ኑር

በጂሀድ የሞተው… ዲኑን ሲያነስር
ቀን ሲያቀራ ውሎ… በሶላት የሚያድር

ሸኽ ዐሊ ጂሩ የጃማው ንጉሥ የሸኽ ሙሀመድ ሻፊ ደረሳ ናቸው፡፡ በአላህ መንገድ ላይ ወንድ ሆነው ጥቃትን ለመከላከል ይጋደሉ ዘንድ ፈቃድ የሰጧቸውም እሳቸው ናቸው፡፡ ደሴ ደርሶ ቢለንን ማን ይረሳል! ቢልን የሸኸ አሊ ጂሩ የትውልድም የፍጻሜም ምድር! የሸኽ አሊ ጅሩ የጀግንነት ሽታ ቢለን ላይ አለ፡፡ ቢለን የወሎየዎቹ ኩራት! ቢለን የወሎየዎቹ የዚያራ መከተቻ! ሸኽ ዐሊ ጂሩ ለዲን መዋደቅን ከአባታቸው ከሸኽ አደም የወረሱት ነው ይላሉ ፕሮፌሰር ሁሴን አህመድ፡፡ በኦሮሚያ ልዩ ዞን ሥር የምትገኘው ርቄ የሸኽ ዐሊ ጅሩ አባት ሸኸ አደም በአይበገሬነት በጅሃድ የገነኑባት ቀዮ ናት ይላሉ ፕሮፌሰሩ፡፡

ጀግና ሆኖ ኖሮ በጅሃድ ታሪክ መስራትን ከአባታቸው የወረሱት፣ ከጃማው ንጉስ ሸኽ ደግሞ በአደራ የተቀበሉት ሸኸ አሊ ጂሩ በሥራቸው አምስት መቶ ፈረሰኞችን አስከትለው በጦር በጎራዴ ታሪክ ሊሰሩ የወሎ ሃይቋ ዋሄሎ ላይ “ለዲኔ ካልሞትኩ አሉ!” የዐጼው ወኪልም በዘመናዊ መሳሪያ የጠገበ በመንግሥትነት ክንድ የበረታ ነበርና የሸኽ ዐሊ ጅሩ ጦር ተፈታ ሸኹም በዚያው ሸሂድ ሆኑ። ይህ የሆነው በፈረንጆቹ አቆጣጠር ጁላይ 1881 ወይም ሸዕባን 1298 ዓ.ሂ ገደማ ነበር።የሸይኹ አስከሬንም ወደ ደሴ ተመልሶ በድብቅ ተቀበረ። ደሴ ጀርባ ቢለን ላይም ሥርዐተ ቀብራቸው ተፈጸመ፡፡ እንሆ ወሎም በስማቸው “ሸኽ ዐሊ ጅሩ” ብላ አንድ መንደሯን ሰየመችላቸው፡፡ ማነህ በስም እርማት ላይ የምትላላጠው የትምክህት ኃይል ስያሜው ዋጋ ተከፍሎበታል፡፡ የሸኽ ዐሊ ጅሩ ጦር ቢፈታም አጼ ዩሐንሳውያኑን ፅንፈኛ ኃይል በተደራጀ መልኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈተነው የሸኽ ዐሊ ጅሩ ጦር ነው ስትል ታሪክ ከገጿ አስፍራለች፡፡


ከታች የምታየው ልጅ ደግሞ የኔ ልጅ ነው! ወረ ወርቂት! ወረ መስታዎት! ሸኽ ዐሊ ጂሩ ስምንተኛ አያቱ ናቸው!

ማጣቀሻዎቼ
Hussein Ahmed (2001). Islam in Nineteenth-Century Wollo, Ethiopia: Revival, Reform, and Reaction, Leid, Boston, Cologne: Brill.

Ali Yassin Ali (2015), The Development of Islamic Education System in Ethiopia: Its features, Relevance and Influence on Muslim culture with reference to South Wallo.

Abduljelil Sheikh Ali Kassa

11 Sep, 14:54


ትርክርክ ማዲሆች
★★★//💔//★★★
(በዐብዱልጀሊል ሸኽ ዐሊ)

የተወለድነው ወሎ ነው! በሃድራ ቤት ውስጥ ተወልደን አድገናል። በመንዙማ፣ በአውራድና በአጀም እስልምናን ተሰብከን፣ ተምረን አድገናል። አንድ የተወዳጁን ማዲህ የሸኽ ሙሀመድ አወልን መንዙማ ለናሙና አንስቼ የማዲኾችን ተዋዱዕ ላስቃኛችሁ!
__ __. ____


በዚህ መንዙማ ማዲሁ የነብዩ ፍቅርን በኪነጥበብ ተጠቦ ይገልፀው ዘንድ ነፍስያው ትጎተጉተዋለች ደግሞ ይፈራል! … ደግሞ የራሱ ማንነት ያሳፍረዋል… ነፍስያውን " ተይ አርፈሽ ተቀመጪ!" ይላታል… ግን ነፍስያው እምቢ ትለዋለች! ፈራ ተባ እያለ ሄዶ ለሸኽየው ስሞታ እያሰማ ነው። እያዘነ እምባው ተንቆርዝዞ «እስኪ እዩልኝ ነፍሴኮ ልጓም በጥሳ ጋጠ ወጥ ሆነች!!» ይላል።

ነፍሴን ተይ በሉልኝ ጌቶቼ
ሰበረች ልጓሟን

ከሱ በዒልምና ወራእ፣ በተቅዋና አኽላቅ የመጠቁ የአላህን ወዳጆች፣ እነዚያን የወንድ አውራ መሻኢኾች " ነፍስያየ ልጓሟን በጥሳ፣ ያለ አቅሟና ቅዋዋ ረሱሉን ያክል የከውን ሞገስ፣ ባልደረቦቻቸውን ያክል የምድር ድንገቴ ትዕይንቶች ካላወሳሁ ብላ አስቸግራኛለችና እባካችሁ አስቁሙልኝ! እባካችሁ «ተይ!» ብላችሁ ገስፁልኝ! እያለ ይማፀናል።

ነፍስያው ግን በአቋሟ ፀንታለች! ውዷን ማውሳት እንጅ ስለ ቀድሯ ግድ የሰጣት አትመስልም!። በከውን የሞላ ነውር፣ በወንጀል ያደፈ ኑረቷን፣ እንደ ሙጀሌ ከምድጃ ያለፈ የተቅዋ ግዝፈት ያነሳች እንዳልሆነች፣ ባልሰከነ ማነነነት፣ በሀጢያት በወየበ ማንነት፣ በኢባዳ ውሃ ያልታጠበች ትርክርክ መሆኗን ረስታ ውዷን አበል ቃሲምን ማውሳት ላይ ቀልቧ እንደተንቃቃ ነው።

በከውኑ የሞላ…… ተሸክማ ነውሯን
ተምድጃ ሳትወጣ ……አሳንሳ ቀድሯን
ማን በነገረልኝ ……ትርክርክ መሆኗን
አባሮ ማን ይዞ…… ባሰረልኝ እግሯን

የምድጃን ጥቀርሻ የመሰለ ማንነቷ፣ አልባሌ ግብረ ፉንጋነቷ ሳይበግራት ምላሷ የኒዟሙን ጌጥ ካልጠራሁ ስትለው ከግሳፄ አልፎ «አርፈሽ ተቀመጭ!» ከሚላት አልፎ የሩህያውን እጅና እግር በእግረ ሙቅ እግር ከወርች አስሮ ፣ ሰንክሎ የሚያሰቀምጥለት የበላይ ፍለጋ ይለማመጣል!

ከሩህያው አልፎ ራሱንም ይወቅሳል! በአደፈ ማንነት፣ ላይ ሳለ ነብዩን መጥራቱን ነውር አድርጎት ለሸኾቹ ስሞታ ይናገራል።

ይሄን ልጅ ተው በሉት… ተቆጭ የለውም ወይ
ሸኾቼ እጄን ያዙኝ ……ይላችሁ የለም ወይ?

ተቆጭ አልባ ስድ አደግ ነው ወይ? እባካችሁ ይህን ድፍረት ሲዳፈር ዝም አትበሉት። እጁን ይዛችሁ ከድፈረቱ አቅቡት! እያለ ይማፀናል። ሸኾቹን ይታዘባል! እንዴት ይህን ድፍረት እያያችሁ ዝም ትላላችሁ? ይላቸዋል።

እዋኛለሁ አለ ……ልኩን ያውቀዋል ወይ
አዟሪት ያለበት… ባህር አያውቅም ወይ?
ኪታብ ዘረጋሳ …ሀርፉን ያውቀዋል ወይ?
ልጅ ኪታብ ሲያበላሽ—አባት ዝም ይላል ወይ?

እያለ ራሱን ይሄይሳል! የአላህን ውድ የነብያቱን አለቃ ልክ፣ የላይ ገንዳውን ዘማች ዲካ! ዛቱ ጀነት ፊቱ ራህመት የሆነውን ሰው ልቅና፣ ወልዳው ስታበቃ እናቱ የተደነቀችበትን ፍጡር የማንነቱን ባህር ያውቀው ይመስል ነብዩን በትርክርክ ማንነቱ ውስጥ ሆኖ ሊያነሳቸው መዳዳቱ እጅግም አስገርሞታል። አ ድፍረቱ አበሳጭቶታል።

የባህርን አዙሪት አደገኛነት ሳያውቁ አዙሪት ያለበት ባህር ውስጥ እንደመግባት… ደግሞ እንደተዓለመ፣ ሀርፉን እንደለየ የቀለም ቀንድ ኪታብ መዘርጋቱ ይበልጥ አስገርሞታል…ወግ የሌለው ድፍረት ሆኖበት ጉድ ጉድ አሰኝቶታል፣ ቢጨንቀው ለሸኹ ተናግሮ ልጅ ኪታብ ሲያበላሽ አባት እንዴት ዝም ይላል ወዲያ አሳርፉት እያለ "ሸክዋ" ያሰማል።

የሚበሳጭባትን በድፍረቷ የተፀየፋት ትርክርክ ሞገደኛ ሩህ የዚያ ልጅ ናት… የዚያ ሀርፍ ገዳፊ ኪታብ ገላጭ! የዚያ ልኩን የማያውቅ ነውረኛ ሰው። ያ ነውረኛ ሰው ደግሞ እሱ እራሱ ነው።

ራሱንና ሩሁን የሃያበት አውድ ነው። የምድራችንን ክስተት፣ የሲድረተል ሙንተሃን እንግዳ፣ የአሏህን ባለሟል ለመጥራት እና ለማውሳት እርሱ ብቁ ያልሆነ፣ ነፍስያውም በወንጀል ያደፈች፣ የኢማንና ንፅህናዋ የተበላሸ፣ የዛች ተራ የምድጃ አመድና ጣላ የተኳለች ነፍስ ባለቤት ነውና እነሱን ለመጥራት ብቁ ስላለመሆኑ ይናዘዛል።

ደግሞ ዋሪዳው ነፍስያው ላይ ተሳፍሮ ነፍስያው አበል ፋጢመትንና ወዳጆቻቸውን ካልጠራህ ብላ አስጨንቃ ይዛዋለች!

እናንተን ለመጥራት …አህል ሆኜም አይደል
ብታዘኝ ነው ነፍሴ
ከእብቅ ላይ ሳትወጣ …ይህን መተንፈሴ
ሸዳ ነስባ ሳለ… ይህ ሁሉ መድረሴ

ይላል። ከእብቅና ንፋሽ ያልወጣች ነፍስያየ፣ ከነስባና ሸዳ (ውጥጡ፣ ማፋገጥ) ያልዘለለ እውቀት ላይ የሆነው ጃሁሉ እኔ ወግ አይቀርም ብሎ አሊፍና ነስባን እንደማውጣጣት መስሎት ከዟሂሩ ልቆ በዓይነል የቂን እጅጉን ድካ አልባ የሆነውን "መሀበተ ረሱል ወአስሃቢሂ" ባብ ላይ ገብቶ ሲንደፋደፍ ማግኘቱ ገርሞታል። ያለ አቅሙ መፈራገጡ አስደንግጦታል።

ውድ ማስደፈሩን ……አየሁት በራሴ
ፈቃድ አድርጉልኝ…… ትናገር ምላሴ

መውደድ፣ ነብዩን መናፈቅ፣ የነብዩን አሻራ ሁሉ ማፍቀር ፍቅር እውር ነው እንዲሉ ያለአቻ ፍቅር ይዞት፣ እውር ድንብሩን አውጥቶት ጥራዝ ነጠቅ ደፋር፣ እጅግም ግብተኛ እንደሚያደርግ በራሱ ጀርቦ የወደደ እብድ ነውና አትድረዱበት! ይልቅ ፍቅሯን ትገልፅ ዘንድ ፍቀዱላት ብሎ "እዝን" ሲጠይቅ ይታያል።

ራሱን ዝቅ አድርጎ፣ ፍቅሩን ለመግለፅ መሞከሩ ራሱን አስታዝቦት ከሩህ ከጀሰዱ ጋር ሲታገል ይታያል።

በዚህ መንዙማ ውስጥ አንድ ሰው ነብዩን በጥበብ ለማወደስ ከሩህያው፣ ከጀሰደዱ ጋር የሚያደርገው ግብግብ አለ! ይህ ነው ረገቢወ ተዋዱዕ

ኤድያ……

ተው ዝምበለኝ ደህኔ

Abduljelil Sheikh Ali Kassa

02 Sep, 04:02


ኸይረ- ዑመቲን!
★★★////★★★

የነጂ ሃይል (Driving force) እና አቃቢ ሃይል (restraining force) የተሰኙ ሃይላት የሰው ልጆችን ይወስኗቸዋል።

ነጂ ሃይል አንድን እምነት ወይም ድርጊት ለመፈጸም የሚጎተጉት፣ የሚቀሰቅስ እና የሚያነሳሳ ገፊ ሃይል ሲሆን አቃቢ ሃይል ደግሞ ድርጊቱን ወይም እምነቱን ሰዎች እንዳይፈጽሙ የሚያቅብና የሚከለክል ሃይል ነው፡፡

ትዕግስት (ሶብር) የተሰኘችው ቅመም በሁለቱም ላይ ገቢራዊ መሆን ስትጀምር ሰዎች የስኬትን መንገድ ላይ ስለመሆናቸው እርግጠኛ መሆን ይቻላል፡፡

አንዳንድ ሰዎች መልካም ነገርን ለመፈጸም፣ ጠቃሚና አልሚ ድርጊትን ለመከወን፣ ለራስም ሆነ ለፕላኔታችን ነዋሪዎች መልካምን ለማድረግ በቂ ተነሳሽነት እና ይህንንም በጎ (መዕሩፍ) ተግባር በመፈጸም ረገድ በቂ ጉልበትና ትዕግስት ሲኖራቸው ይስተዋላል፤ በጎ በመሆኑ ሂደት ላይ ለሚያጋጥማቸው መሰናክልም ትዕግስታቸው በዝቶ ይስተዋላል፡፡ ግና ራሳቸውን ከእኩይና ከመጥፎ ድርጊት በማቀቡ ረገድ ላይ እጅጉን ድኩማን ሆነው ይገኛሉ፤ በሚሊዮን ብር ለየቲሞች ሲለግስ የማይጨንቀው ሀብታም የድሃ ጎረቤቱን መሬት ሲጋፋ እንደማየት ያክል ማለት ነው፡፡ የነዚህ ሰዎች በእኩይ ሁነቶች (ሙነከር) ላይ ትእግስት ማጣት ሊያስገርም ይችል ይሆናል፤ ግና ብዙው እንዲህ ነው፤ “አይይ ይህን የሚያክል ትልቅ ሰው እንዲሃል ቅሌታም ነው፤” የሚባለው አይነት ማለት ነው፡፡

ሌሎች አንዳንድ ሰዎች በአቃቢ ሃይላቸው (restraining force) ላይ ነግሰው እናስተውላቸዋለን፤ የነዚህ ሰዎች መለያ በከንቱ፣ ዓላማ ቢስ፣ የተጠላ አና ጎጂ ሁኔታዎችና ተግባሮች ጋር የተጣሉ መሆናቸው ነው፤ በማንኛውም ቦታና ጊዜ ራሳቸውን ከተጠሉ (ሙንከራት) ድርጊቶች ሲያቅቡ ይስተዋላሉ፤ "እኔን አይመጥነኝም!" የሚል የራስ መተማመን አላቸው፤ መለኮታዊም ሆነ ሰዋዊ ህግና ደንብን ያከብራሉ፤ በድርጊቶቻቸው መዋረድን ይጸየፋሉ፤ በዚህ ማንነታቸው ላይ ጽናት ይስተዋልባቸዋል፤ ከእኩይ በመራቅ ላይ ትእግስተኞች ናቸው፡፡ ይሁን የነጂ ሃይል (Driving force) ድሆች ናቸው፤ በጎ ተግባራትን ለመፈጸም ያላቸው ተነሳሽነት የተራቆተ ነው፤ አስር ሳንቲም ለየኔ ቢጤ መወርወር እንደ አጥቢያ ኮከብ ይርቅባቸዋል፤ አንዲት ስግደት የቋጥኝ ያክል ትከብዳቸዋለች፡፡ መልካም ድርጊቶችን (መዕሩፍ) ላይ ትዕግስት የላቸውም፤ ዝሁርን ቢሰግዱ አሱርን ይዘሏታል፡፡

ሌሎች ደግሞ የሁለቱም ድሃዎች ናቸው፤ መልካም ነገርን የመፈጸም ተነሳሽነቱም፣ ዝግጁነቱም ሆነ ጽናቱ የላቸውም፣ በመጥፎ ድርጊቶች ላይ ግን ፊት አውራሪዎችና ዘውታሪዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ጠንቆች ናቸውና ብዕር አናባክን-ተዋቸው፡፡

በጣም ጥቂቶች እና አራተኞቹ መደቦች ግን የሁለቱ ሃይላት ሃብታሞች ናቸው፡፡ እነዚህ የምድራችን ቅመሞች ናቸው፤ የትውልድ ደህንነት ዋስትናዎች ናቸው፤ የሰማያዊ አዋጆች ግብ የነዚህን ምድቦች ቁጥር ማብዛት ነው፡፡ ኸይረኛ ዑማ! ይሉሃል ይህ ቡድን ነው፡፡ የዚህ ቡድን አባል ያድርገን!!

መልካም ውሎ፡፡

Abduljelil Sheikh Ali Kassa

19 Jun, 22:56


ኸሊፋው ዑመር (ረዐ) አንድ ቀን ሰዎችን ሰበሰበ። ወደ ሚንበሩም ወጣና እንዲህ አለ፦

«እኔ በጃሂሊያ ዘመን ለአዳዴዎቼ ፍየል አግድላቸው ነበር።እፍኝ ተምርን ወይም ዘቢብን ይከፍሉኝ ነበር። ለቀናት እርሷን አየተመገብኩ የምቆይ ሰው ነበርኩ።»

ብሎ ንግግሩን ጨርሶ ከሚንበሩ ከወረደ በኋላ ዐብዱረሕማን ኢብኑ ዐውፍ (ረዐ) ፦ «ያ አሚረል ሙእሚኒን! ራስህን ከማቃለል ውጭ ምንም አልጨመርክም!»አለው።

ዑመርም አለው ፦ « የዐውፍ ልጅ ሆይ! ወየውልህ! ለብቻዬ ስሆን ነፍሴ የሙእሚኖች መሪና የረሱል ኸሊፋ መሆኔን ነገረችኝ ፤ ስርአት ላሲዛት ፈልጌ ነው!» (አጥጦበቃቱል ኩብራ 3/293)

አላህ ዑመርን ስራውን ይውደድለት፤በጀነትም ከርሱ ጋር ያጎራብተን!

ነፍስያ እንዲህ ነች፤ መቀጣት ያስፈልጋታል።

ቤትህ ስትገባ «አንተኮ የኡማው መከታ ነህ!» «ኡስታዝ ነህ!» «ለኡማው ተሰቃይተህ»፣ «ሀይላንድ ተንጠልጥሎብህ»፣ «አንተ የጀነት ሙሽራ»፣ «በቁስልህ ኡማው ተፈወሰ!» ፣ «የሙስሊሙ ተቆርቋሪ»፣ «ባለ ራእይ አክቲቪስት» ትልሀለች። በዚህ ሰአት የዑመርን መድሀኒት መጠቀም ፍቱን ነው።

ወጣ ብለህ ለሰዎች «እኔኮ ሊስትሮ እየሰራሁ ያደግኩና የቀን ስራ እየሰራሁ ጉርሴን ስለቅም የነበርኩ ሰው ነኝ» ማለት ግድ ይላል።

እኔም በፃፍኩት እናንተም ባነበባችሁት ተጠቃሚዎች ያድርገን!

Abduljelil Sheikh Ali Kassa

15 Jun, 03:32


The dead ideas of the past [አል አፍካር አል መይታህ]

ቆሞ ቀርነት ነው። አንድም ከፍርሃት ሁለትም ከስንፈት ሶስትም ከቆሞ ቀርነት የሚመጣ

የዛሬ ችግሮችን ለይቶ መፍትሄ ከመፈለግ ይልቅ በድሮ ችግሮች ላይ መማረር ይበዛዋል። አሁነኛ ጠላትህ ሳይሆን የድሮ ጠላትህ (old enemy) ሞቶ እንኳን በሱ መማረር፣ መብሰክሰክ፣ እሱን ለማስታገስና ከሱ ለመዳን መፈራገጥን እንደ ስኬት የመቁጠር አባዜ ነው። በተቃራኒው ግን አሁናዊ ጠላትህን፣ ተግዳሮትህን ለይቶ መፍትሄ ለመፈለግ ያልብሃል! በጠላትነት ወይም በስጋትነት ልትበይነው የፍርሃት ቆፈን ያጠምቅሃል!!

ለዘንድሮው በሽታህ የአምና መድሃኒት መፈለጉ ያስደስትሃል። ጤና ጣቢያ ሄደህ የዛሬውን በሽታህን ከማወቅ ይልቅ የድሮው በሽታ መድሃኒትህን መጠቀምን ትመርጣለህ! ይህ የከርሞ ጥጃነት አመል ነው ወዳጄ!

ህያው ዛሬህን በሞተ ችግር አውድ መቃኘት፣ በሞተ መላና መፍትሄ ለማከም መዳከር፣ በሞተ ሜቶዶሎጂ፣ በተቀበረ መፍትሄ ለማሳመር የምታደርገው ሩጫ ነው።

ይህ የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ብቻ ችግር አይደለም። አማራው ኦርቶዶክሱ፣ ኦሮሞው፣ ስልጤው፣ አፋሩ ኦልድ ኢነሚው ላይ እንደተቸነከረ ነው።

ኦልድ ኢነሚህ ስትራቴጂካሊ አጋርህ ሊሆን ቢችልስ?

Your attachment with dead ideas of the past is not derived from appreciation rather it is due to rigidity and uncreativity.

ወዳጄ
የዛሬ ህመማችን፣ የዛሬ ችግራችን፣ የዛሬ ጠላታችን፣ የዛሬ ወዳጃችን፣ የዛሬ ድክመትና ጥንካሬያችን፣ የዛሬ ስጋትና እድላችን፣ የዛሬ የመፍትሄ መንገዳችን ምንድን ነው? የሚለውን ከፊሉ ማወቅም ማሳወቅም እንዲታወቅም የማይፈልግበት ሁነኛ ግብ አለው! በአያ ጅቦ እያስፈራራ አያ ጂቦን የመተካት ህልምም ይኖረዋልና

አብዘሃኛው ግን ዛሬን የመጋፈጥ ወኔና የማሰብ ድፍረቱን ስለሚያጣ ነው

ነጋቲ

Abduljelil Sheikh Ali Kassa

13 Jun, 18:18


እነሸኽ ገታ

እነሸኽ ገታ አዝማሪ አይወዱም። አዝማሪ ነው/ናት ከተባሉ እያስመጡ ይገርፋሉ!

አንድ ቀን አንዲት ሴት አዝማሪ አገሩን አበላሸችውን ሰሙ። አምጧት አሉ። ተይዛ መጣች

መግሪፈያው ተዘጋጅቷል። አዝማሪዋ እንደማይቀርላት ስታውቅ እንዲህ ተቀኘች

እነ ሸኽ ገታ የገታው
ሲነጋገር ያድራል ከጌታው

ሸኽ ገታ ሰሙ።« በይ አጉል አጉሉን ተወት አርገሽ እንዲህ ያለውን ግጠሚ»😜 ብለው ተዋት።

Abduljelil Sheikh Ali Kassa

13 Jun, 07:10


و لقد کرمنا بنی آدم
ይህ ተመጀመሪያው መርህ ነው
የሰው ልጅ ይቀድማል!

ሰው ከሃሳቡ ጋር ተገናኝቶ የሚያመርተው ምርት፣ የሚፈጥረው፣ እድገት፣ ልማትና ብልፅግና እንዲሁም የሚገነባው አገር፣ ሥርዓትና ሥልጣኔ ፋይዳቸው የሰውን ልጅ ለማገልገል ነው።

Pure capitalism

የሠው ልጆችን በገበያ ልክ የሚበይን ነው። በmarket demographic ደረጃ የሚተነትን ነው። ምርትና ትርፍ የተሳሰሩ ናቸው። ለምርቶች የሰው ልጆችን የሚፈልግ ነው።

ለምርትህ የሚሆንህን ሰው ፈልገህ የማያስፈልግህን፣ እንቅፋት የሚሆንህን አሊያም purchasing power አልቦ ሰዎችን የምታስወግድበት፣ የምትቀንስበት፣ የምታፈናቅልበት ሂደት ነው።

………………

ስለዚህም ስልጣኔ ለሰው ወይስ ሰው ለስልጣኔ? አገር ለሰው ልጅ ወይስ የሰው ልጅ ለአገር? ከተማ ለሰው ልጆች ወይስ የሰው ልጅ ለከተማ?

Abduljelil Sheikh Ali Kassa

13 Jun, 03:35


ለአቅመ ኸሊፋ የበቃ ሰው የፊጥራ (nature) እና የስልጣኔ (nurture) ውጤት ነው።

አንድ ሰው በፊጥራው አባታችን አደም "በምድር ላይ ምትክን አድራጊ ነኝ" ብሎ አላህ በገለፀበት ጊዜ ያለውን አደም አሊያም ገና የተወለደን ህፃን ይመስላል። ኸሊፋ ለመሆን አንድም ተገቢው የስልጣኔ ሂደት ማለትም በእውቀት (ወዓለመ አደመ አስማኣ)ን ደረጃ እና think globally act locally እንዲሉ አንድም የመሬት ሁለትም የሰማይ (ቁሳዊና መንፈሳዊ) ሆኖ አውዳዊና ገቢራዊ (contextual and practical) ሆኖ ሽግግሩን ማለፍ አለበት ። ካልሆነ ጭንግፍነት ይሰፍናል።

ብልሹ ስልጣኔ ፊጥራን ያፀልማል።

ነገሮችና እውቀት ብቻቸውን ህልው መሆን አይችሉም። ሰው መኖር አለበት። ሰው ግን ያለ ሃሳብ መኖር ይችላል—አንድም ጃሂል ሁለትም ሸክምና ሀጢያት ሆኖ

አሽኻስ (realm of figures) እና አፍካር (realm of ideas)ሲገናኙ አሽያእን (realm of things) ይወልዳሉ። ሰው ከሃሳብ ጋር ሲገናኝ ያፈራል። ምርቱ አንድም ዱኒያ አኼራን ያሳምራል። ስልጣኔ ይሆናል።

ሰው ሃሳብን ዘሎ ምርት ጋር ሲገናኝ ሸማችነት ( consumerism) ይገናል። የአንድን ስልጣኔ ምርቶች በመሸመት ስልጣኔን መፍጠርም ማስቀጠልም አይቻልም።

ሰው ከሃሳብ ጋር ሳይሆን ቀድሞ ከምርት ጋር ሲገናኝ ስንፍና ይነግሳል። የጥረት ዋጋ፣ የድካም ትርጉም፣ የፅናት ፋይዳ ይጠፋል። ያለ ጥረትና ፅናት የተገኘ ምርትም ለብክነት ይዳረጋል።

ሰው ከምርት ጋር ከተገናኘ ወዲያው ተመልሶ ከሃሳብ ጋር መገናኘት አለበት። ይህም ቢያንስ ሰው በነገሮች (realm of things) ላይ ተብሰልስሎ (realm of ideas) ምርቶችን/ነገሮችን በተሻለ መልኩ ለማምረት እና ለመጠቀም የ dissemination, adaptation and implementation እንዲሁም አሻሽሎ የማምረትና የመጠቀም እድልን ይፈጥራል።

ነጋቲ

Abduljelil Sheikh Ali Kassa

12 Jun, 10:47


ታሪክ

የስነ–ስብእናዎች እውቀትን (ዒልመል አሽኻስ)
የሥነ–ሃሳብ ዕውቀትን (ዒልመል አፍካር)
የሥነ– ነገሮች ዕውቀትን (ዒልመል አሽያእ)

ውቅር ነው። (የማሊክ ቢን ነቢ ግሩም ምልከታ ነው)

የተለምዶው ትርክት በመጀመሪያው ማለትም በግለሰቦች፣ ቡድኖች ላይ የቆመ ነው።

ታሪክ የሃሳብ እና የተግባሮቹ ዝርዝር ነው። ሃሳብ ተግባርን ይወልዳል። ተግባር ምላሽን ያስከትላል። ይህ ሂደት አንድም ስልጣኔን አሊያም ባክዋርድነትን ይፋጥራል።

ስርዓት የሃሳብ ሚስት ናት።

[ ] የህግ የበላይነት (Rule of Law)
[ ] ዴሞክራሲ
[ ] ልማትና ብልፅግና
[ ] ፍትህ
[ ] ነፃነትና እኩልነት

አሊያም

[ ] ስርአት አልበኝነት
[ ] እልቂት
[ ] ጦርነት
[ ] ድህነት
[ ] ሁከት

ሁሉም የቤተሰቦቻቸው ልጆች ናቸው አባት ሃሳብ እናት ሥርዓት (regime)

የጨዋ ልጅ ጨዋ ነው! የጥፍ–ራም ልጅ ጥፍ–ራም ነው! ስለዚህ ዒልመል አፍካር ( realm of ideas ) እጅግ ወሳኝ ነው።

ስርኣትም ከተፈጥሮ ዑደት ተገዥ ነው ዝንተዓለማዊነት ለሱብሀነሁ ወተአላ ብቻ ነው።

ልደት (ሚላድ) አለው።
ከፍታ (ዐውጅ) አለው።
ውድቀት (ዑፉል) አለው።

ሁሉም ዑደቶች ለባለቤቶቹ የፊትና ጊዜ ናቸው። መፈጥፈጥ መውደቅህ፣ ጊዜ መቀየር መገልበጡ ላይቀር በተራህ፣ በነበረህ የregime እድል ሰው ተኮር የሆነ ሥራ ሰርተህ አልፈህበታል? ወይስ Paulo Freire እንደጠቀሳቸው ተጨቋኞች (oppressed) የትናንት ጨቋኞቻቸውን ለመሆን እንደሚፍገመገሙ ዞንቢዎች ነህ?

Abduljelil Sheikh Ali Kassa

11 Jun, 14:21


Godaannisa hin fayyamne

የባኮ ልጅ ነች

መንገድ ላይ ቆማ አገኘኋት ታክሲ እየጠበቀች! ፅሀይ አወይቧታል… ከፀሃይዋ ጨረር ለመከለል እጇን ቅንድቧ ላይ አድርጋለች… በቁሟ ዝላለች

የባኮ ልጅ ነች ኢንተሎ ወለጋ

መኪናየን ፊት ለፊቷ አቁሜ ግቢ አልኳት። ገባች… በትልቁ ተነፈሰች… ረጅም ትንፋሽ!

(እኔ) ምን ሆነሽ ነው?

(እሷ) ቤት ፈርሶብኝ ነው? ንገረኝ የት ልሂድ!

(እኔ) ወደ ቤተሰቦቺሽ።

(እሷ) ቤተሰቦቼ ከወሎ ወደ ወለጋ በደርግ የተፈናቀሉ ነበሩ። ከባኮ ተፈናቅለው እኔ ጋር ነበር ያሉት። አሁን የት ልሂድላቸው።

(እኔ) አገርሽ!

(እሷ) እንደሌላው አገር ቢኖረኝ እንዲህ አይከፋኝም ነበር

(እኔ) ማለት?

(እሷ) ተወልጀ ያደግኩት ወለጋ ባኮ፣ ከዚያ ተባርሬያለሁ። የት ልሂድ?

(እኔ) ወሎ ሂጂ (ያፅናናሁ መስሎኝ)

(እሷ) ወሎንማ እንኳን እኔ ቤተሰቦቼም ከተፈናቀሉበት ስንት መንግሥት አለፈ

……………

ጥርሷን ነክሳ! … በቁጭት እንዲህ ያጉተመተመች መሰለኝ!

osoon biyya qabaachuu danda'ee akkasitti hin yaadda'u ture!

እንደሌላው አገር ቢኖረኝ እንዲህ አይከፋኝም ነበር

Abduljelil Sheikh Ali Kassa

10 Jun, 12:18


Mark my word

(አብዱልጀሊል እንዲህ እያለ ነው ብላችሁ ላኩላቸው!!)

በአንድ አገር ቁልፍ ማእከላዊ ከተማ ላይ የዴሞግራፊ ሚዛን ወሳኝ ነው።

በማእከላዊውና የፌደራል ቁልፍ በሚባለው ከተማ ላይ ያለህ የዴሞግራፊ ፣ የካልቸር፣ የውክልና እና የሱታፌ ፕረዘንስ እጅጉን ወሳኝ ነው።

እስካሁን በኢትዮጵያ ማህበረ ፖለቲካ በዋናዋ የፌደራል መቀመጫ፣ የአገሪቱና የአህጉሯ መዲና አዲስ አበባ ላይ የሱማሌዎችና የአፋሮች ሁለንተናዊ ፕረዘንስ እጅግ ዜሮ በመሆኑ እስካሁን የዳርቻ አገር ነዋሪነት ላይ ናቸው። they are peripherals yet!

አንድ ሃይፖተስስ ላስቀምጥ :—

የኦሮሚያ ሪፐብሊክ ተሳክቶ ተመሰረተ እንበል!

(Fact)

የኦሮሚያ ሙስሊሞች በታሪክና በተጫባጩ ባላቸው የፊንፊኔ እና የሸገር ዴሞግራፊ ውስጥ የዴሞግራፊ ፣ የካልቸር፣ የውክልና እና የሱታፌ ፕረዘንስ እጅጉን መንማና እና የሳሳ ነው።

ስለዚህ ምንድን ነው የሚሆነው?

የዛሬዎቹ የኢትዮጵያ አፋሮችንና ሶማሌዎችን ቦታ የኦሮሚያዋ ሪፐብሊክ ኦሮሞ ሙስሊሞች ይተካሉ! They will be the Peripherals!

ሚና አልቦ የዳር አገር ልጆች!!!

You are hatching your next Atsee!!

Abduljelil Sheikh Ali Kassa

03 Jun, 02:50


የብልፅግና ሮንግ ተርኖች (wrong turn)
★★★//💢//★★★

ሳብ ሳብ አረጉ በኛ ላይ ሊነዱ
እስኪ እናየዋለን ካስኬደ መንገዱ
(ሸኽ አደም ደርቃ)
………………………

ብልፅግና መንግሥት ከሆነ በኋላ በበርካታው ኢትዮጵያውያን ሙስሊም ልሂቃን ዘንድ በአንድ ወሳኝ ጉዳይ ላይ መግባባት አለ።

የመግባቢያ ነጥቡ የሚከተለው ነው:—

"ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ለዘመናት ከመጣው መንግሥት ጋር ሁሉ እየተጋጩ፣ እያኮረፉ ከኢኮኖሚ ተጠቃሚነት፣ ከሁለንተናዊ ሱታፌ እየተገለሉ፣ ለስልጣን ለሚቋምጥ ሃይል ሁሉ መጠቀሚያ የሚሆን ትግል እያደረጉ፣ ለስደት፣ ለእስር፣ለእመቃ፣ ለሞት እየተዳረጉ መኖር ትክክል ስለማይሆን ረፍት ያስፈልጋቸዋልና …ከመጣው ሁሉ መንግስት ጋር መጋጨት ብልህነት አይደለምና… በማናቸውም ሁኔታ ከመንግስት ጋር ሆድና ጀርባ የሚያደርግ እንቅስቃሴ መደረግ የለበትም!

ህዝበ ሙስሊሙን መንግስት ጋር የሚያቃቅሩ፣ የሚያጋጩ፣ የሚያጠራጥሩ፣ የሚያራርቁ እንቅስቃሴዎች በፍፁም መደረግ የለባቸውም!

የፖለቲካ ፍላጎት ኖሮን ስለማያውቅ በመንግስት ፖለቲካ ውስጥ በመግባት ከመንግስት ጋር መጋጨት እና ህዝቡን ድጋሚ ረፍት አጥቶ፣ እየተሰደደ፣ በፍርሃት ድባብ ውስጥ መኖር የለበትምና በተለየ መልኩ ሃይማኖታችንን የሚጋፋ፣ ሰላማዊ ማምለካችንን የሚያቅብ፣ ያለንን የሚያሰጣ፣ ቀጥተኛ የሆነ ጥቃት እስካልፈፀመ ድረስ ሆደ ሰፊ ሆነን የሠላምን መንገድ ሙጥኝ ማለት አለብን፣ እረፍት ማግኘት አለብን።» የሚል የፀና አቋም ነበረን።

በዚህ ጉዳይ ላይ በተለያዩ አጋጣሚዎች ውይይት ተደርጎ በዚህ ስምምነት ላይ መደረሱንም አስታውሳለሁ። ለባለፉት አምስት አመታት በርካታ የሚፈታተኑን ክስተቶች ተፈጥረው በዚሁ መርህ መሰረት፣ በሆደ ሰፊነትና ሠላምን ተቀዳሚ በማድረግ ሙስሊሙ ህብረተሰብ ለመንግስት አንድም ጊዜ እንቅፋት፣ ፈተና፣ ተገዳዳሪ ሳይሆን፣ የረባ ያልረባ ጥያቄና ፍላጎት በማሳደር መንግስትን ማስቸገርን በመፀየፍ የብልፅግና አመራሮች ጭምር "ሙስሊሙ ብቻ ነው" የማይረብሸን እስኪሉ ድረስ እጅግ የሰከነና ሰላም ወዳድ እንቅስቃሴ ተደርጓል

መንግስት በአገሪቱ ውስጥ በሁሉም ህዝቦች፣ በተለያዩ ብሄሮችና በክርስቲያኑ ህዝብ ጋር ለሚፈጥራቸው ግብግቦችና ለሚፈፅማቸው በደሎች የህዝበ ሙስሊሙ ልሂቃን ህዝበ ሙስሊሙ በገለልተኛነት እንዲንቀሳቀስ ሰፊ ጥረትና አመራር እየሰጠ ዘልቋል። ይህ ሁሉ ዙልምን እያዩ እስከማለፍ የደረሰ አቋም ያራመደው "ህዝበ ሙስሊሙ ረፍት ያስፈልገዋል ከመጣው ሁሉ መንግስት ጋር መጋጨት ብልህነት አይደለም!" በሚል መርህ ነበር።
______

ግና ሠላምን አጥብቆ መፈለግ፣ ረፍትን መሻት በአንድ ወገን ጥረት ብቻ የሚገኝ አይደለምና፣ የህዝበ ሙስሊሙ ፀብንና ግጭትን መሸሽ ዘላቂ መፍትሄ ሆኖ አልተገኘም። መንግስት የማይደረገውን አድርጎ ከህዝበ ሙስሊሙ ጋር የማይፋቅ ችግር ውስጥ ራሱ ገብቷል።
_____

የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችን የትግል ሂደት ላጠና ሰው የብልፅግና "ጠብ ያለሽ በዳቦ" ጉዞ በተለይ የትናንት የግንቦት 25ቱ የአንዋር መስጅድ ጭፍጨፋ በህዝበ ሙስሊሙና በመንግስት መካከል ያለው ጉዳይ ላይቃና መታጠፉንና አዲስ ምእራፍ ከፍቶ ማለፉን መረዳት ቀላል ነው።

Abduljelil Sheikh Ali Kassa

31 May, 03:21


ኦሮሞ ጠል እንደተባልነው ሁሉ አማራ ጠልም ተብለንም ነበር
★★★////★★★

በኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ጉዳይ ፈርተን የምንተወው ብሔርም ሆነ ኃይማኖት አይኖርም

ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ኢትዮጵያዊነታቸውን አጽንተው የኢትዮጵያ አገረ መንግሥት መሥራቾች ፣ ግንበኞች እና ኩሩ ዜጋዎች እንጅ መጤዎች፣ አገር አልባዎች ኦብጀክቶች አለመሆናቸውን በትግላቸው ለማጽናት የዘመናት ትግል ጠይቋል። የየካቲት 1966ቱ ታላቁ ሰልፍ “ኢትዮጵያዊ ሙስሊሞች እንጅ በኢትዮጵያ የሚኖሩ እስላሞች ልንባል አይገባም!” የሚለው ሃሳብ የሰልፉ አምድ ነበር።

ድህረ 1966 እስከዛሬ ድረስ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችን ከዜግነት ከአገር ባለቤትነት፣ ከአገር ካስማነት የሚፍቅን፣ በአገራቸው ማህበረ ፖለቲካ እንዲሁም በሀገራቸው ሁለንተናዊ ሱታፌ ድርሻና ሚና እንዳይናራቸው የሚያደርግ ሥርዓትን፣ አመለካከትንና አሰራርን፣ በአገራቸው እኩል ተጠቃሚነትንና ምክንያታዊ ድርሻቸውን የሚጋፋና የሚነጥቅ አመለካከትን፣ ሥርዓትንና አሰራርን እንዲሁም የዚህ አመለካከት እና ሥርዓት አንባሪና ጠባቂ ኃይላትን ተጋፍጦና ታግሎ ዛሬ ለደረሰበት ደረጃ ደርሷል።

ዛሬ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች እዚህ የደረሱት በሆነ ብሄር ወይም በሆነ ሥርዓት ሥጦታ አይደለም!! እዚህ የተደረሰው በመራር ትግልና ሰማእትነት ነው!! ዜግነትን፣ የሀገር ባላቤትነትን፣ የሀገር ግንባታ ሂደት ወሳኝ ባለድርሻነትን፣ በሀገር ሁለንተናዊ ግዴታዎች፣ ማህበረ ፖለቲካ ሃላፊነቶች መታመንን፣ መሳተፍን፣ ሚና መውሰድና ሀላፊነት መሸከመን፣ ሁለንተናዊ ሱታፌን ማረጋገጥንና ምክንያታዊ ድርሻን ማስከበርን ተቀዳሚና የማንደራደርባቸው አብይ አጀንዳዎቻችንና የትግል ምዕራፎቻችን አድርገን እዚህ ደርሰናል።

ትግሉ መራር ነበር። ከወንድም ከእህት፣ ከዘመድ ከብሔር መነጠልን ይጠይቅ ነበር! ሞትና እስራትን ይጠይቅ ነበር፣ መሰደድ መገረፍን ይጠይቅ ነበር!!

የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችን ዜግነት፣ የሀገር ባለቤትነት፣ ሁለንተናዊ ተሳታፊነትና ድርሻን በአመለካከትና በእውቀት ታግዞ፣ ሥርዓት አንብሮ፣ መንግሥት ሆኖ ለዘመናት የነፈገን፣ ያገለለለን፣ የገፋን፣ ያባረረን በሃይማኖት የኦርቶዶክስ ሃይማኖትን በብሔር የአቢሲኒያ (አምሃራና ትግራይ በዝ) ሃይል ስለነበር ለዘመናት ከዚህ ሃይል ጋር ተጋፍጠናል!! ይህ ማለት ኦርቶዶክሱንና አማራውን ትግሬውን እንጠላለን ማለት አይደለም!

በአማራ ትግራይ ኦርቶዶክሱ ውስጥ መሽጎ የኢትዮጵያን ሙስሊሞች ዜግነት እስከመግፈፍ የደረሰውን አመለካከት፣ እውቀት፣ ስርኣትና ሃይል ግን መራር የትግል ምአራፍ ከፍተን ታግለነዋል። በዚያ የትግል ሂደት ከበርካታ የኦርቶዶክስ አማራና ትግራይ ወገኖቻችን ጋር ተቋስለናል፣ ተገፋፍተናል፣ ተነጣጥለናል፣ ተቆራርጠናናል።

ጥቂቶቹ ተረድተውናል። በመጨረሻም ፍላጎታችን የእኩልነትና የፍትሕ ጥያቄ መሆኑን ሲረዱ ተረድተውናል። በብሔርተኝነቱ ሳቢያ የአማራው ሃይል በደረሰበት መገፋት ስሜታቸው የተጎዳ በርካታ የአማራ ክልል ሙስሊም ወገኖቻችን ሳይቀር ጠልተውናል! ግን ትግላችን የኢትዮጵያውያንን ሙስሊሞች አገራዊ ተክለ ቁመና የማስተካከል መም ነውና አኩራፊውን፣ ተናካሺውን ብሄርተኛውን እየተራመድን እዚህ ደርሰናል።

ዛሬ ዛሬ የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችን ዜግነትን የሚቀሙ፣ የሀገር ባላቤትነትን የሚክዱ፣ የሀገር ግንባታ ሂደት ወሳኝ ባለድርሻነትን የሚነፍጉ፣ በሀገር ሁለንተናዊ ግዴታዎች፣ ማህበረ ፖለቲካ ሃላፊነቶች መታመንን፣ መሳተፍን፣ ሚና መውሰድና ሀላፊነት መሸከመን፣ ሁለንተናዊ ሱታፌን የሚነፍጉ “የእስላም አገሩ መካ የወፍ አገሩ ዋርካ፣ የእሰላም አገር የለው የሰማይ ምሰሶ የለው!” የአስተሳሰብና የእውቀት ተጋሪዎች ከኦሮሚያ ምድር እያቀጠቀጡ መሆናቸውን ታዝበናል።

ይህ አመለካከት የኦሮሞው ሙስሊም አመለካከት ሊሆን እንደማይችል ማውራት የኦሮሞውን ሙስሊም መናቅ ይሆናል። ይሁን እንጅ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ለዘማነት ከአቢሲኒያው የኦርቶዶክስ ሰለሞናዊ ኃይላትና አመለካከቱን ተጋሪዎች ጋር ሲታገልባቸው የነበሩ የዜግነትና፣ የባለቤትነት፣ የተሳትፎና የድርሻ አጀንዳዎች የሚጋፋ ሃይል በትቂቱም ቢሆን በኦሮሚያ ቀጠናና በኦሮሙማው ሂደት ውስጥ እሰከታየና ይህም ሃይል የኢዶሎጂ፣ የእውቀት፣ የስልጣን ባካብ አፕ እስካለው ድረስ የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ተቀዳሚና የማንደራደርባቸው አብይ አጀንዳዎቻችንና የትግል ምዕራፋችን አካል መሆኑ ይታወቅ!!

በዚህ የትግል ሂደት እንደ በርካታ የአማራ፣ ትግራይ፣ ኦርቶዶክስ ወገኖቻችን ሁሉ በጠላትነት ፈርጆ የሚታገለን በርካታ የኦሮሙማው ሃይል እንደሚኖር ከወዲሁ እንገነዘበዋለን። ስለዚህ መነጠል፣ መገፋፋት፣ መፈራረጅ፣ መጠላላትን ፈርተን የምናጠበጥበው የትግል አጀንዳ የለንም!!

እንደ ኦርቶማራው ከፊል ጽንፈኛ ኃይል ሁሉ፣ የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችን ነባር የትግል አጀንዳዎች ተጻርሮ የመጣ ኃይል የኦሮሙማም ሆነ የሌላ አካል የማንለሳለስለት፣ የማንበገርለት ጠላቶቹ መሆናችንን እንዲያውቅ ማስረገጡ ተገቢ ነውና!! ወይ ፍንክች የጦልሃ ጃዕፈር ልጅ! ነው መልሳችን!!

Abduljelil Sheikh Ali Kassa

27 May, 10:34


ዛሬ ግንቦት 19/2015 የኢ/እ/ጉ/ጠ/ቤት በጠራው አስቸኳይ ስብሰባ ላይ የኦሮሚያ መጅሊስ አመራር
በሸገር ከተማ መስጂዶቻችንና ተቋሞቻችን ላይ የደረሱ እና አሁንም እየደረሱ ያሉ ፈታናዎች ሶስት ስልቶችን በመከተል እንደሆነ አብራርተዋል ።

ስልት 1 🔘
ነባሩን መስጅድ ከማስተር ፕላን መሰረዝ እና ለሌላ ነገር አድርገው መስራት
ምሳሌ (ሰዕድ አንፎ መስጅድ) 30 ዐመት በላይ የቆየ መስጅድ ፤
(ዳሩ ሳላም መስጅድ) ከ50 ዐመት በላይ የቆየ..

ስልት 2 🔘
መስጅዱ ባለበት ለእንቨስትመንት ወይም ለግለሰብ ካርታ ፕላን በማሳራት ወይም የገበሬ ነው በማለት በፍርድ ቤት ክስ መመስረትና ማስወሰን
ምሳሌ: መስጅድ ሙሀጅር አሸዋ ሜዳና ሱመያ መስጅድ..

ስልት 3 🔘
ህገ ወጥ ናቸው በማለት ሙሉ በሙሉ ማፍረስ

#የመስጂድፈረሳይቁም
#19Mosques
#19መስጂዶች
#ሸገርሲቲ
#ሙስሊምጠልነት

Abduljelil Sheikh Ali Kassa

20 May, 03:25


«الفتنة نائمة لعن الله من أيقظها»
ብዙ ተስፈኞች…አያሌ ህልመኞች…እልፍ "በሬ ሆይ ሳሩን አየኽና ገደሉን ሳታይ" የተባለውን በሬ መሳዮች…እነ እንትናን መሳይ አልጠግብ ባይ ሲተፉ አዳሪዎች… እንደገና የኋሊት ጉዞ እንደምሚጣ ያልገመትን ችኩሎች…

……መናቅ፣ መጨቆን፣ መገፋትን የሚያውቁ ሁሉ ለሰው ልጆች እኩልነት፣ ለዴሞክራሲ፣ ለብሔሮች አርነት የተሻሉ ነፃ አውጪዎች ይሆናሉ የሚል የተቻኮለ ድምዳሜ ላይ የደረስን ሚሊዮኖች… garbage in, garbage outን ህግ የረሳን ወገኖች ቁርሾ ተግቶ በቀል ተጠምቶ ከመጣ ፍቅር ይሰራ ዘንድ የጠበቅን የዋሆች "አተርፍ ባይ አጉዳይ" ሆነን ፈተናን/መከራን ካሸለበችበት የቀሰቀስን ትውልዶች…

……እኔን መሳይ ሌላ ዘመነ—ዙልም በኛ ትውልድ ይፈጠር የማይመስለን ከንቱዎች የተኛች ፈተናን ቀስቅሰን…ለፍቅር ተኝተን ፈርዖን ወልደን…የዴሞክራሲ እንቁላል ያቀፍን መስሎን አምባገነንትን የፈለፈልን…ነውር ጌጡ፣ ግፍ ውበቱ የሆነን ኃይል ያነበርን…የተረገምን ትውልዶች ነን

……………

መፍትሔው ምንድን ነው?

«አላህ ያብጀው… በተሻለው ተካን» የሚለው ይመስለኛል።

በጠቅላላ ህዝቡ በነቂስ የተውበትና የንሰሃ መንገድን መከተል አለበት የሚለው ይመስለኛል።

Abduljelil Sheikh Ali Kassa

30 Mar, 02:36


የኢትዮጵያ ህዝብ እንዴት ይድናል?

(አንድ)

አዲስ የፖለቲካ አተያይና አረዳድ በማምጣት። አንድ ህዝብ ወይም አብዛኛው ህዝብ መረን በለቀቀ ሁኔታ ለሌላኛው ህዝብ መረን የለቀቀና ሎጅክ አልቦ ጥላቻ ሲኖረው ፖለቲከኞች ያንን ጥላቻ በማጋጋልና አብዝቶ በመስበክ በተጠላው ህዝብ ላይ ፍፁም አገር አጥፊ የሆነ በዳይነትን በማራመድ በጥላቻ የታወረውን ህዝብ ተከታያቸው፣ የግፋቸው ተባባሪ ያደርጉታል።

በአንድ ወቅት ስለ ህወኃት ክፉነት፣መሰሪነት፣ ሰይጣንነት መተንተን ሁነኛ ፖለቲካ አዋቂነት ሆኖ በመተረኩ፣ በመገለፁ፣ በመለፈፉ፣ በመወሰዱ ህወሃትን ለማጥፋት ኢትዮጵያን ማጣት፣ ኢትዮጵያዊነትን ማጣት ኢቭን ትግራይ ተገንጥላ ኢትዮጵያ የቅርፅና የመልክ ብታመጣ እንኳን ግዴለሽ በመሆን፣ የአገሪቱ ኢኮኖሚ የማይሸከመው እጅግ አውዳሚ ጦርነት ተከስቷል። በሁሉም ወገን ኢትዮጵያውያን ወጣቶች አልቀዋል። በመላ ኢትዮጵያ በተጋሩዎች ላይ አሳዛኝና ታሪካዊ ወከባ፣ እመቃ፣ ማግለል፣ ማሳደድ፣ ማሸማቃቅ ሲፈፀም ህዝቡም ተባባሪ ሆኗል። የዙልም ደጋፊና ይሁንታ ሰጪ ሆኖ አልፏል። በተለየ መልኩ የአማራ ፖለቲከኞች ቀጥሎ ስለሚሆነው ለቅፅበት ሳያስተውሉ ትግራይ ጋር "እንዳይታረቁ ሆነው መጣላትን" የፖቲካ ብቃታቸው ማሳያ አድርገውት ነበር።

በአገር ላይ እጅግ አሳዛኝ ቀውስ ተፈጥሯል። የኢኮኖሚ ቀውሱ ከዘር ጥላቻው ጋር ተዳምሮ ቁጥር አልባ ዜጎችን ከቤት ቀያቸው አፈናቅሎ ጎዳና ላይ አውጥቶ ለልመና ዳርጓል። የዘር ጥላቻው ለማኞችን በአሸባሪነት፣ በመፈንቅለ መንግስት አድመኝነት እንድትፈርጅ የሞራል ስንቅ ይሆንሃል። ዜጎችን በግፍ ማዋከብ፣ ማፈናቀል፣ ማራቆትን ተገቢነት እንድታፀድቅ፣ ይሁንታ እንድትሰጥ የሞራል ስንቅ ይሆንሃል። የዙልም (በደል፣ ግፍ) ደጋፊ፣ አጫፋሪ፣ ይሁንታ ሰጪ፣ አመቻማች ፣ እያዩ አላፊነትን ምክንያት አልቦ ጥላቻህ "ሚዛናዊነት፣ ትክክለኝነት፣ ኖርማልነት" አድርጎ ያረጋጋሃል። ዛሬ ለአማራ ያለ የተፃነፈ ጥላቻ ትናንት ለተጋሩ የነበረ የተፃነፈ ጥላቻ ብጤ ነው።

በዚህ ጥላቻ መር የፖለቲካ ድባብ፣ የስርዓት ኑባሬ፣ የህዝብ ተባባሪነት፣ የዘር ፖለቲካ ሃዋርያት መካከል ስለምትፀይመው ኢትዮጵያ፣ ማዲያት ስለሚለብሰው የአንድ አገር ልጅነት፣ ስለሚሰቃየው ህዝብ፣ ስለሚነግሰው በደል፣ ስለሚንኮታኮተው ኢኮኖሚ፣ ስለሚፈጠረው ሁለንተናዊ ቀውስና ውድቀት፣ እየተፈጠረ ስላለው የህዝብ አለመተማመንና መሰገጋት፣ እየሰፈነ ስላለው አምባገነናዊነት፣ እየሆነ ስላለው የህዝብ መጎሳቆል የሚረዳና ለፍትህ የሚቆም፣ ከጥላቻው ከፍ ብሎ ማስተዋልን የታደለ አዳኝ የፖለቲካ አረዳድ ህዝቡ ማማጣት ግድ ይለዋል።

"እነ እንትናን ለማጥፋት አገር ትጥፋ" ይሉትን የውርደት መሰላል የሚያመፃድቅ ህዝብ ሊድን አይችልምና

Abduljelil Sheikh Ali Kassa

22 Mar, 18:34


አሰላሙ ዐለይኩም ወራሕመቱላሂ ወበረካቱሁ

ውድና የተከበራችሁ ሙስሊም ወንድሞችና እሕቶች!

እንኳን 1,444ኛው የረመዷን ወር ፆም አላህ በሰላም አደረሳችሁ!!

አላህ ወሩን የዚክር፣ የዱዓእ፣ የቂያም፣ የድል ወር ያድርግልን

Abduljelil Sheikh Ali Kassa

17 Mar, 18:42


https://gofund.me/1a247a9e

#ማንአለ?
በሠውሠራሽ እና ተፈጥሯዊ ምክንያቶች ከቀያቸው ተፈናቅለው በተለያዩ ካምፓችና በየቦታው የሚገኙ በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች ያሉበት ሁኔታ በጣም አሳዛኝ ነው።
እነዚህን ወገኖች መርዳት የሁሉም ኢትዮጵያዊ ወገናዊ ግዴታ ነው።

#አግማስ_ኢትዮጵያ የበጎ አድራጎት ድርጅት ላለፉት ጊዚያት ከወለጋና እና አካባቢው ተፈናቅለው በተለያዩ መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ  ወገኖችን የአስቸኳይ የምግብ እርዳታ፣የህክምና አገልግሎት፣ የንፅህና መጠበቂያ እንዲሁም ወላጆቻቸውን ያጡ 320 ህፃናትን በቋሚነት በማሳደግ ማህበራዊ ሀላፊነቱን በመወጣት ላይ ይገኛል።
አሁን ደግሞ መጪውን
የረመዷን ፆም መዳረስ ተከትሎ በተለያዩ የመጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ወገኖቻችን ባስተላለፉት
የእርዳታ ጥሪ መሰረት ለጥሪያቸው ምላሽ ለመስጠት መላዉ ኢትዮጽያዊያንን አስተባብረን ከ15 ሽህ በላይ ወገኖችን (3,000 አባወራዎችን) ለማስፈጠር እንድሁም ከ1000 በላይ ወላጆቻቸውን  ያጡ ህጻናትን በቋሚነት ለማሳደግ አግማስ ኢትዮጵያ ይህንን የድጋፍ ጥሪ ለሁሉም ኢትዮጽያዊያን ያቀርባል፡፡

ደብረ ብርሃን ፥ አርጎባ ፥ ገራዶ ፥ ኩታበር ፥ ሃይቅ መካነየሱስ ፥ ጃራ 1 ፥ ጃራ 2 እንድሁም ድሬ ሮቃ በመጠለያ ጣቢያ ውስጥ የሚገኙ ወገኖች ለከፍተኛ ችግር የተጋለጡ ስለሆነ እነዚህን ወገኖች ለመታደግ እንድሁም በየመጠለያዎቹ የሚገኙ ወላጅ አልባ ህጻናትን በቋሚነት ለማገዝ ዩቲዩብን ጨምሮ በተለያዩ የሶሻል ሚድያ አማራጮችና የቲቪ ቻናሎች  ከአርብ መጋቢት 8 ከቀኑ 11፡00 ጀምሮ ታላቅ የገቢ ማሰባሰቢያ ( fund raising) ፕሮግራም ይካሄዳል፡፡

በፕሮግራሙ ላይ ታላላቅ እንግዶች የሚገኙበት ሲሆን በመላው አለም ያለ ኢትዮጵያዊ በሙሉ ለዚህ የመልካም ስራና የበጎነት አብዮት ቀና ምላሽ እንድሰጥና እንድተባበር ጥሪያችንን እናስተላልፋለን ፡፡

ለተጨማሪ መረጃዎች አድራሻችን ደንበል ሲቲ ሴንተር ፊትለፊት ሞባይል ፕላዛ 3ኛ ፎቅ
ስልክ 0901443322
 
አግማስ ኢትዮጽያ የበጎ አድራጎት ድርጅት
Home of humanity!

https://gofund.me/1a247a9e