👉🏼እየተከሰተ ያለዉ የመሬት መንቀጥቀጥ በተለይ በአካባቢው ህንጻዎችን ሊያፈርስ ይችላል
በፈንታሌ እና በዶፈን ተራራዎች መካከል እየተከሰተ የሰነበተው ርዕደ መሬት በተለያዩ ከተሞች እያስከተለው ያለው ንዝረት መጠኑ ቢለያየም አሁንም ቀጥሏል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂዮ ፊዝክስ፣ ስፔስ ሳይንስና አስትሮኖሚ ተቋም ዋና ዳይሬክተር ኤሊያስ ሌዊ (ዶ/ር) በተለይ ለኢቢሲ ዶት ስትሪም እንዳሉት፥ በተራራዎቹ መካከል መሬት ውስጥ ያለው ቅልጥ አለት ወደ ሰሜን ምስራቅ 50 ኪሎ ሜትር አዳርሷል።
የርዕደ መሬቱ መነሻ በሁለቱ ተራራዎች መካከል ያለ መሆኑን የተናገሩት ዶ/ር ሌዊ፤ የንዝረቱ መጠን ቢለያየም አዲስ አበባ፣ አዳማ፣ አዋሽ፣ መተሀራ እና ደብረ ብርሃን ድረስ መሰማቱን ዳጉ ጆርናል ከኢቢሲ ዘገባ ተመልክቷል።
በአዋሻ አርባ፣ በሳቡሬ፣ በመተሀራ ከተሞችና አካባቢዎቻቸው የንዝረት መጠኑ ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል።
ከፈንታሌ ወደ ዶፈን ባለው አቅጣጫ የውስጥ ለውስጥ ቅልጥ አለቱ ባለፈው መስከረም ሲጀመር እስከ 10 ኪሎ ሜትር ነበር፤ በመሀል ቆም ብሎ ነበር፤ አሁን ግን እስከ 50 ኪሎ ሜትር አዳርሷል ብለዋል ዶ/ር ኤሊያስ።
አዲስ አበባን ጨምሮ እየተከሰተ ያለው የንዝረት መጠን መነሻው በተራራዎቹ አካባቢ መሆኑን አንስተው፤ በተለይም እዛው አካባቢ ቤቶችን እና ህንፃዎችን ሊያፈርስ ይችላል ብለዋል።
ቅልጥ አለቱ መሬት ውስጥ ሊቀር ይችላል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በተቃራኒው እሳተ ገሞራ በማንኛውም ሰዓት ወደ ገፀ መሬት ሊወጣ የሚችልበት ዕድልም ስላለ፣ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በአካባቢው የፈላ ውሃ ፈንድቶ ፍል ውሃው ስብርባሪ ድንጋይ ይዞ ወደ ላይ እየወጣ መሆኑን ያነሱት ዶ/ር ኤሊያስ፤ ወደ ላይ የሚፈነዳው ውሃ ከፍተኛ ሙቀት ያለው፣ ሰልፈር ዳይኦክሳይድና ሌሎች መርዛማ ጋዞችን የያዘ በመሆኑ ለሰው ልጆች ጤና አደገኛ መሆኑን ጠቁመዋል።
የሰመራ ዩኒቨርሲቲ የስነ ምድር ክፍል ቡድን ሰሞኑን እየወጣ ባለው ፍል ውሃ ባደረገው የናሙና ምርመራ፤ ውሃው ለእንስሳትም፣ ለሰው ልጅም አገልግሎት የማይሆን በመሆኑ ህብረተሰቡ እንዳይጠቀም አሳስበዋል።
የሰዎች ወደ ፍንዳታው ሥፍራ መጠጋት ችግር ሊያስከትል ስለሚችል ማህበረሰቡ በተቻለ መጠን ከአካባቢው ራቅ ማለት እንዳለበትም አሳስበዋል።
ከባለፈው መስከረም ጀምሮ እየተከሰተ ያለው ርዕደ መሬት በሕይወትም ሆነ በንብረት ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ እንደ ሀገር ኮማንድ ፖስት ተቋቁሞ ሰዎችን ከስፍራው የማስወጣት ሥራ እየተሰራ ይገኛል።
Via ኢቢሲ
#ዳጉ_ጆርናል