ኦርቶዶክስ ሃይማኖታችን @haymanotachn Channel on Telegram

ኦርቶዶክስ ሃይማኖታችን

@haymanotachn


✞የኦርቶዶክስ ቻናል✞
> የየዕለቱ ስንክሳር
>ኦርቶዶክሳዊ ጥያቄዎች ከነመልሱ
> በቅርብ የጀመረው አስተማሪ ታሪኮች
> መንፈሳዊ ዝማሬዎች
> የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ
> መንፈሳዊ ፊልሞች
> መንፈሳዊ ትምህርቶችና
የተለያዩ ፁፎች
#ሁሉም_በየእለቱ

ኦርቶዶክስ ሃይማኖታችን (Amharic)

ከላቀ መሥዋዕት እስከ ምሳሌ ሁለቱ ቅንጅት እና መጽናናዎችን የሚፈጠር ኦርቶዶክስ ሃይማኖታችን የተለያዩ ቀላል ቻናላ ነው። የየዕለቱ ስንክሳር፣ ኦርቶዶክሳዊ ጥያቄዎች ከነመልሱ እና በቅርብ የጀመረው አስተማሪ ታሪኮች፣ መንፈሳዊ ዝማሬዎች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ፣ ፊልሞች እና ትምህርቶችን ለመቃወም ይህ ቻናል ይቀርባል። ሁሉም በየእለቱ በተከሰቱ ፁፎች ይታወቃሉ።

ኦርቶዶክስ ሃይማኖታችን

21 Nov, 13:36


🕊

[    ርኅሩኁና የይቅርታ መልአክ    ]

የርኅራኄ መዝገብ፣ ትሑት፣ ታዛዥና ለዘለዓለም ፈጣሪውን አመስጋኝ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ጌታ በሚያደርገው ቸርነት ላይ ለሰው አንድ ወገን የሚሆን መልአክ ነው፡፡ [ ሄኖ.፮፥፭ ፣ ፲፪፥፭ ፣ ፲፥፲፪ ]

⇨ Michael, one of the Holy Angels, namely the one put in charge of the best part of humankind, in charge of the nation. [ሔኖ ፮፥፭]

⇨ This first is Michael, the merciful and long-suffering without an urge to harm. [ሔኖ ፲፥፲፪]

አምላካችን እግዚአብሔርን የሚፈሩትን እንደ አጥር ሆኖ የሚጠብቃቸው ፣ የመልእክት አለቃቸው ፣ ምሕረት ማድረግን የተሰጠው ፣ የክብር አክሊልን የተቀዳጀ ፣ በግርማው የተፈራ ፣ የቅዱሳን ወዳጅ ፣ የኃጥአን የምሕረት አማላጅ ፣ በብርሃን መጎናጸፍያ የሚጎናጽፍ ፣ ከክብሩ ብርሃን የተነሣ ምድርን በብርሃን የሚሞላት ፣ የቅዱሳንን ጸሎት ከዕጣኑ ጢስ ጋር ወደ እግዚአብሔር የሚያሳርግ ፣ በትንሣኤ ዘጉባኤ የመለከት ድምጽ የሚያሰማ ፣ በሰማይ ካሉ ሁሉ በላይ በማዕረግ የከበረ ፣ ድንቅ ተአምራትን የሚያደርግ ቅዱስ ሚካኤል !


† ሊቀ መላእክት በክንፈ ረድኤቱ ከክፉ ሁሉ ይጠብቀን::

†                       †                        †
💖                    🕊                     💖

ኦርቶዶክስ ሃይማኖታችን

20 Nov, 21:54


† በተለይ ለቅኔ ትምሕርት ማበብ ልዩ የሆነ አስተዋጽኦ እንዳደረጉ ይነገራል:: ልክ በነገሡ በ፲ ዓመታቸው ግን መንግስተ ምድር በቃኝ ብለው በምናኔ በርሃ ገብተዋል:: በዙፋናቸውም አፄ እስክንድር ተተክተዋል:: ጻድቁ ንጉሥ ግን ቅዱስ ሚካኤልን ይወዱት ነበርና በዚህች ቀን ዐርፈዋል::

አምላከ ቅዱሳን በክንፈ ሚካኤል ከክፉው ሁሉ ይሰውረን:: ከበረከታቸውም አይለየን::

🕊

[  †  ኅዳር ፲፪ [ 12 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት   ]

፩. ቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላእክት
፪. ቅዱስ ኢያሱ ነቢይ
፫. ቅዱሳን ዱራታኦስና ቴዎብስታ
፬. አፄ በዕደ ማርያም ጻድቅ
፭. ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ
፮. ቅዱስ ባሕራን ቀሲስ
፯. አባ ፊላታዎስ ሊቀ ዻዻሳት

[   † ወርሐዊ በዓላት   ]

፩. ቅዱስ ላሊበላ ጻድቅ [ንጉሠ ኢትዮዽያ]
፪. ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ
፫. ቅዱስ ቴዎድሮስ ምሥራቃዊ [ሰማዕት]
፬. ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ
፭. አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ
፮. ቅዱስ ማቴዎስ ሐዋርያ
፯. ቅዱስ ድሜጥሮስ ሊቅ

" በሰማይም ሰልፍ ሆነ:: ሚካኤልና መላእክቱ ዘንዶውን ተዋጉ:: ዘንዶውም ከመላእክቱ ጋር ተዋጋ:: አልቻላቸውምም:: ከዚያም ወዲያ በሰማይ ሥፍራ አልተገኘላቸውም:: ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ወደ ምድር ተጣለ:: " [ራዕይ.፲፪፥፯]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖

ኦርቶዶክስ ሃይማኖታችን

20 Nov, 21:54


🕊

[  †  እንኩዋን ለሊቀ መላእክት "ቅዱስ ሚካኤል" እና "ለቅዱሳኑ" ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ  †  ]


🕊  †  ቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላእክት †   🕊

† ቅዱስ ሚካኤል በጥንተ ተፈጥሮ በኢዮር: ኃይላት በተባሉት ነገደ መላእክት ተሹሞ ነበር:: ሳጥናኤል በካደ ጊዜ እግዚአብሔር ባወቀ: አንድም በትሕትናውና ደግነቱ በ፺፱ኙ ነገደ መላእክት ላይ ሁሉ ተሹሟል::

† ከፍጥረት ወገን ከእመቤታችን ቀጥሎ የቅዱስ ሚካኤልን ያሕል ክብርና ርሕሩሕ የለም:: በምልጃውም: በረዳትነቱም የታወቀ መልአክ ነው:: መጽሐፍ "መልአከ ምክሩ ለእግዚአብሔር" ይለዋል:: "ወስሙ መስተሣሕልም" ይለዋል:: ቂም የሌለው: ለምሕረት የሚፋጠን: ደግ መልአክ ነውና::

† በብሉይ ኪዳን በመከራ ለነበሩ ቅዱሳን ሁሉ ሞገስ: ረዳትና አዳኝ ቢሆናቸው "መጋቤ ብሉይ" ተሰኝቷል:: እሥራኤልን ፵ ዘመን በበርሃ መርቷል:: መግቧልም:: ቅዱስ መጽሐፍ ስለ እርሱ ብዙ ይላል:: (ዘፍ.፵፰፥፲፮, ኢያ.፭፥፲፫, መሳ.፲፫፥፲፯, ዳን.፲፥፳፩, ፲፪፥፩, መዝ.፴፫፥፯, ራዕይ.፲፪፥፯]

† ደስ የሚለው ደግሞ ርሕሩሑ መልአክ ከእመቤታችን ጋር ልዩ ፍቅር አለው:: ከእናቷ ማሕጸን ጀምሮ እስከ ዛሬ እነሆ አብሯት አለ:: ደስ ብሎት ይታዘዛታል:: ማማለድ ሲፈልግም "እመቤቴ ሆይ! ቅደሚ" ይላታል:: ወደ እሳት መጋረጃ አብረው ገብተው ለዓለም ምሕረትን: በረከትን ያወርዳሉ::


🕊   †  ቅዱስ ኢያሱ ነቢይ  †    🕊

ዳግመኛ በዚህች ዕለት ቅዱስ ሚካኤል ኢያሱን እንደ ረዳው ታስተምራለች:: ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ :-

† በመጽሐፈ ኢያሱ ምዕራፍ ፭ ላይ እንደ ተጻፈው ቅዱሱ መልአክ ለኢያሱ ተገልጦለታል:: እሥራኤልን በምድረ በዳ የመራ ሊቀ ነቢያት ቅዱስ ሙሴ ሲያርፍ ታላቅ ሐዘንና ድንጋጤ ተፈጥሮ ነበር::

† እግዚአብሔር ግን ኢያሱን አስነስቶ አረጋግቷቸዋል:: ቅዱስ ሚካኤል ፵ውን ዘመን እሥራኤልን ደመና ጋርዶ: መና አውርዶ: ክንፉን ዘርግቶ: ጠላትን መክቶ ከሙሴ ጋ እንደ መራቸው ከኢያሱ ጋርም ይሆን ዘንድ ከሰማይ ወረደ::

† በኢያሪኮ አካባቢም የተመዘዘ ሰይፉን ይዞ በግርማ ለኢያሱ ታየው:: ኢያሱም ወደ እርሱ ቀርቦ "አንተ ከእኛ ወገን ነህን? ወይስ ከጠላቶቻችን?" ሲል ጠየቀው:: ቅዱስ ሚካኤልም መልሶ "እረዳህ ዘንድ እነሆ የሠራዊት አለቃ ሆኜ ተሹሜ መጥተቻለሁ" አለው::

† ያን ጊዜ ታላቁ ነቢይ ቅዱስ ኢያሱ በግንባሩ ተደፍቶ ለሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ሰገደለት:: ቅዱሱ መልአክም አክሎ "ፍታሕ ቶታነ አሳዕኒከ እም እገሪከ: እስመ ምድር እንተ ትከይዳ ቅድስት ይዕቲ - የረገጥካት ምድር የተቀደሰች ናትና ጫማህን ከእግርህ አውጣ" አለው::

† ኢያሱም የተባለውን አደረገ:: ለዚህ ነው ቤተ ክርስቲያናችን "ለመላእክት የጸጋ [የአክብሮ] ስግደት ይገባል: በቅዱሳኑ ፊትም ጫማ ተለብሶ አይቆምም" የምትለው:: ያ መሬት ሊቀ መላእክት ቢቆምበት ተቀድሷል:: ዛሬም ቤቱ በታነጸበት: ታቦቱ በተቀረጸበት ቦታ ሁሉ ቅዱሱ መልአክ አለና ጫማን አውልቆ: ባጭሩ ታጥቆ መግባት ይገባል::

† ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ከኢያሱ ጋር ሆኖ አማሌቅን ጨምሮ የእሥራኤልን ጠላት አጥፍቷል:: ጥቅመ ኢያሪኮን [ቅጥሩን] አፍርሷል:: ምድረ ርስትን አውርሷል:: በገባኦን ፀሐይን: በቆላተ ኤሎምም ጨረቃን ሲያቆም ከእርሱ ጋር ሆኖ ረድቶታል::


🕊   † ዱራታኦስና ቴዎብስታ  †   🕊

ቅዱሳኑ ዱራታኦስ [ዶርታኦስ] እና ቴዎብስታ [ቴዎብስትያ] የቅዱስ ሚካኤል ወዳጆች ናቸውና በዚህች ዕለት ይታሰባሉ:: በድርሳነ ሚካኤልና በመጽሐፈ ስንክሳር ተጽፎ እንደምናገኘው 2ቱ ቅዱሳን በተቀደሰ ትዳር ተወስነው: ሕጉን ትዕዛዙን ፈጽመው: ለነዳያን ራርተው: ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ተቀብለው የሚኖሩ ነበሩ::

† ይልቁኑ ግን የጌታችን: የእመቤታችንን እና የቅዱስ ሚካኤልን መታሰቢያ ያለማስታጐል ያደርጉ ነበር:: ከጊዜ በሁዋላ ግን ሐብት ንብረታቸው አልቆ ተቸገሩ:: ግን የጨነቃቸው መቸገራቸው ሳይሆን የቅዱስ ሚካኤልን መታሰቢያ ሊያቆሙ መሆናቸው ነው::

† አማራጭ ሲያጡ ተቀምጠው ተመካከሩ:: የቅዱሱ መልአክ ዝክር ከሚቀር ልብሳቸውን [ያውም የክብር ልብሳቸውን] ሊሸጡ ተስማሙ:: በዚህ መሰረት ቅዱስ ዱራታኦስ ወደ ገበያ ሲሔድ ወዳጁ ቅዱስ ሚካኤል ከሰማይ ወረደለት::

† መንገድ ላይም የጦር መኮንን ሃገረ ገዢ መስሎ ተገናኝቶ አጫወተው:: ችግሩን ጠይቆም መፍትሔውን ነገረው:: "እኔ እዋስሃለሁና ለበዓል የሚያስፈልጉህን ነገሮች ሁሉ ገዝተህ አሰናዳ" አለው::

† "እኔ ወደ ቤትህ መጥቼ ስለምስተናገድ አንድ አሣ አምጥተህ አቆየኝ:: እኔ ሳልመጣ ግን አትረደው" አለው:: ቅዱስ ዱራታኦስ የተባለውን ሁሉ ፈጽሞ ወደ ቤቱ ሲሔድ ድንቅ ነገርን ተመለከተ:: ሚስቱ ቅድስት ቴዎብስታ በቤቱ መካከል ሁና ቤቱ በበረከት ሞልቷል::

† ማሩ: ቅቤው: እሕሉ ሁሉ በየሥፍራው ሞልቷል:: ባልና ሚስቱ ደስ ብሏቸው:: ነዳያንን ሲያበሉ: እንግዳ ሲቀበሉ ዋሉ:: በሁዋላ ያ መኮንን [ቅዱስ ሚካኤል] በቤታቸው መጥቶ ተስተናገደ::

† በእርሱ ትዕዛዝ የአሣው ራስ [ሆድ] ሲከፈት በውስጡ ፫ መቶ ዲናር ወርቅ [እንቁ] ተገኘ:: ቅዱሳኑ ይህን ተመልክተው ሲደነግጡ ቅዱስ ሚካኤል ክንፉን ዘርግቶ ራሱን ገለጸላቸው:: ደንግጠው በግንባራቸው ተደፉ::

† እርሱ ግን "በተገኘው ሃብት እዳችሁን ክፈሉ:: ከዚህ በሁዋላ ግን በምድር አትቸገሩም:: በሰማይም ክፍላችሁ ከእኔ ጋር ነው" ብሎ ባርኩዋቸው ወደ ሰማይ ዐረገ:: እነርሱም በሐሴትና በበጐ ምግባር ኖረው ዐርፈዋል:: ለርስቱም በቅተዋል::


🕊   †  ቅዱስ ባሕራን ቀሲስ  †   🕊

የደጋግ ክርስቲያኖች ግን የድሆች ልጅ::

- በሕጻንነቱ በግፍ ወደ ባሕር የተጣለ::
- በእግዚአብሔር ጥበብ አድጎ የግፈኛውን ንብረት የወረሰ::
- በመልካም ትዳር በቅስና ያገለገለ::
- ምጽዋትን ያዘወተረ::
- አብያተ ክርስቲያናትን ያሳነጸ ደግ ክርስቲያን ነው::
¤ አርፎ ቅዱስ ሚካኤል ወዳጁ በዕረፍተ ገነት አኑሮታል::


🕊   †  አፄ በእደ ማርያም  †   🕊

"በዕደ ማርያም" ማለት "በማርያም እጅ" እንደ ማለት ነው:: እኒህ ሰው የኢትዮዽያ ንጉሥ ሲሆኑ የነገሡትም በ፩ ሺህ ፬ መቶ ፷ [1460] ዓ/ም ነው:: ደጉ አባታቸው አፄ ዘርዓ ያዕቆብ ሲያርፉ በመንግስቱ ተተክተው ሃገራችንን አስተዳድረዋል:: ድርሰት ደርሰዋል:: አብያተ መቃድስ አንጸዋል::

ኦርቶዶክስ ሃይማኖታችን

20 Nov, 17:51


                          †                          

🕊     [     እንኳን አደረሰን !    ]     🕊


" እንኳን ለሊቀ መላአክት ለቅዱስ ሚካኤል ዓመታዊ በዓል በሰላምና በጤና አደረሰን !

🕊

❝ የተጨነቀውን የተጨቆነውን ነፃ የምታወጣው ሚካኤል ሆይ ፦ ሰላም ላንተ ይሁን ፡ ሠራተኛው ሠርቶ እንዲበላ ውሎ እንዲገባ የምትጠብቀው ሚካኤል ሆይ ሰላም ላንተ ይሁን፡፡

ችግረኛውን ለመርዳት ከልዑል ዘንድ የምትላክ ሚካኤል ሆይ ሰላም ላንተ ይሁን። አዳኝነትህን በማመን የለመነህን በክንፈ ረድኤትህ የምትሠውረው ሚካኤል ሆይ ሰላም ላንተ ይሁን፡፡

በኀዘን በትካዜ ላይ ወድቆ የሚፍገመገመውን የሚንፈራገጠውን ፈጥነህ ደርሰህ ደግፈህ የምታጽናናው ሚካኤል ሆይ ፤ አንገትህን ዘንበል ቀለስ አድርገህ በፈጣሪ ፊት ሰግደህ እኛ ባሮቹን በቸርነቱ ይጎበኘን ዘንድ የማናዊት እጁን ዘርግቶ ይባርከን ዘንድ ለምን አማልድ ለዘላለሙ አሜን፡፡ ❞

[   መልክአ ሚካኤል   ]

❝ በቅዱስ ፡ ሚካኤልም ፡ ጸሎትና ፡ ልመና ፡ ሀገር ፡ ከጥፋት ፡ ትድናለች።

ይልቁንም ፡ የቅዱስ ፡ ሚካኤል ፡ በዓሉ ፡ በሚከበርበት ፡ ዕለት ፡ ወይንና ፡ ስንዴ ፡ ጧፍ ፡ ዕጣን ፡ ለቤተ ፡ ክርስቲያኑ ፡ መባ ፡ የሰጠ : እስከ ፡ ግማሽ ፡ እንጀራም ፡ ቢሆን ፡ ለተራበ ፡ ያበላ ፡ እንዲሁም ፡ ቀዝቃዛ ፡ ውሀ : ለተጠማ ፡ ያጠጣ ፡ በክብር ፡ በምስጋና ፡ ዕድል ፡ ፈንታው ፡ ከቅዱሳንና ፡ ከሰማዕታት ፡ ጋር ፡ ይሆናል ፡ እስከ ፡ ዘላለሙ ፡ አሜን። ❞

[    ድርሳነ ሚካኤል     ]

🕊

በዚያም ዘመን ስለ ሕዝብህ ልጆች የሚቆመው ታላቁ አለቃ ሚካኤል ይነሣል ፤ ❞ [ ዳን.፲፪፥፩ ]


🕊                     🍒                      🕊

ኦርቶዶክስ ሃይማኖታችን

20 Nov, 12:50


                          †                          

[    🕊    ገ ድ ለ   ቅ ዱ ሳ ን   🕊     ]

▬▬▬▬▬▬   †    ▬▬▬▬▬▬

[  የአባታችን የቅዱስ መቃርዮስ የተጋድሎ ሕይወቱና ትምህርቱ  ]

[              ክፍል  አርባ ሁለት               ]

💛

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

[  የታላቁ አባት ቅዱስ መቃርዮስና የመቃርዮስ ዘእስክንድርያ ስደት - ፬ -   ]

                         🕊                         

❝ ከዚህም በኋላ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታላቁ አባ መቃራንና የእስክንድርያውን አባ መቃራን ጠራቸው ፤ እንዲህም አላቸው ፦ “በምድር ሳሉ መታሰቢያችሁን የሚያደርጉ ሰዎች የተመሰገኑ ናቸው ፤ የዘለዓለም ሕይወትን ይወርሳሉና፡፡ በራሴ እምላለሁ ፣ ስለ ስሜ የተቀበላችሁትን መከራ በትጋት የሚያስበውና የሚጽፈው የሚሰማው ሁሉ ያመሰግነኝ ዘንድ በቤተ ክርስቲያን የሚያነበውን እኔ በጎ ነገርን ሁሉ እሰጠዋለሁ፡፡ ከበጎ ነገርም ምንም አላሳጣውም ፣ ከመከራውም ሁሉ አድነዋለሁ ፣ ኃጢአቱን ሁሉ አስተሠርይለታለሁ፡፡ ከዚህ ዓለምም በሚለይበት ጊዜ ነፍሱን ወደ ዘለዓለም ተድላ ደስታ ይወስዱ ዘንድ እናንተ ወደ ምታስቡትም መንግሥቴ ያስገቡት ዘንድ የምሕረት መላእክትን እልካለሁ፡፡ በገዳም ወይም በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ወይም በሀገር ውስጥ ይህ ዜናችሁ በሚነበብበት እኔ አድራለሁ ፣ በረከቴንና ሰላሜንም እስከ ዓለም ፍጻሜ በውስጧ አደርጋለሁ፡፡ ለዚህ ደስታችሁ ዜና ተቃራኒ የሚሆን ባልተወለደ ይሻለው ነበር፡፡ በእውነት እነግራችኋለሁ ፣ በሰው ፊት እንዳመናችሁብኝ በሰማያት ባለው አባቴ ፊትና በከበሩ መላእክቶቼ ፊት አምንባችኋለሁ፡፡ አሁን ግን ወደ ሀገራችሁ የምትመለሱበት ጊዜ ደረሰ፡፡” ይህንም ብሎ ሰላምታ ሰጥቷቸው ወደ ሰማይ በክብር ዐረገ፡፡

ከዚህ በኋላ ሕዝቡን ሁሉ ንጉሡንም ሰበሰቧቸው፣ ወደ ሀገራቸውም እንደሚመለሱ ነገሯቸው፡፡ የክርስቶስንም ሕጉን ሁሉ እንዲጠብቁ ለሊቀ ጳጳሳቱ ለዮሐንስም እንዲታዘዙ አዘዟቸው:: ከቀናች ሃይማኖት ወደ ቀኝም ቢሆን ወደ ግራ ፈቀቅ እንዳይሉ በብዙ አማፀኗቸው ፣ አስጠነቀቋቸውም፡፡ ሕዝቡም ሰምተው ደነገጡ ፥ መሪር ልቅሶንም አለቀሱ፡፡ ቅዱሳን አባቶቻችንም ከእነርሱ ጋር በአንድነት አለቀሱ፡፡ ከዚያም በኋላ እያንዳንዳቸውን ባረኳቸውና ተሰናበቷቸው፡፡

ያን ጊዜም ከኪሩቤል ወገን የሆነ ወመልአክ መጣ ፣ አውጥቶም በክንፎቹ ተሸከማቸው ፣ ወደ እስክንድርያም አድርሶ በሊቀ ጳጳሳቱ ደጅ እሑድ ጠዋት አወረዳቸው:: ሊቀ ጳጳሳቱ ኣባ ጢሞቴዎስም ሰምቶ እጅግ ደስ አለው:: ሁለተኛም ባያቸው ጊዜ አለቀሰ ፣ ሰገደላቸውም:: እነርሱም ሰገዱለት ፣ እርስ በርሳቸውም እጅ ተነሳስተው ሰላምታ ተለዋወጡ ፣ ጤንነታቸውንም ተነጋገሩ:: ደግሞም ልዩ የነበሩ አሕዛብ ወደ እግዚአብሔር ስለ መመለሳቸውና ስለ ተደረጉት ድንቆች ተአምራት ነገሯቸው:: ሊቀ ጳጳሳቱ አባ ጢሞቴዎስና ይህን የሰሙ ሕዝብ ሁሌም አደነቁ፣ እግዚአብሔርንም አመሰገኑት:: አባቶቻችንም በዚያ ስምንት ቀን ተቀመጡ፡፡ ከዚያም በኋላ ያ መልአክ ተገልጦ በክንፎቹ ደግሞ ተሸከማቸው ፣ ወደ ደብረ አስቄጥስም አደረሳቸው:: አንዱ ኪሩብም ከአየር ሆኖ ፦ “የአባት መቃርስ ልጆች ሆይ ፣ ኣባታችሁ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎችን ተሸክሞ ከስደት ተመልሶ መጥቷልና ወጥታችሁ ተቀበሉ” እያለ ጮኸ፡፡

ይህንም በሰሙ ጊዜ ከታላላቆች እስካ ታናናሾች ወጡ ፣ ቁጥራቸውም አምሳ ሽህ መነኰሳት ሆነ:: ከውስጣቸውም በዚያን ጊዜ አባ ዮሐንስ ሐፂርና አባ ብሶይ ኣሉ፡፡ የደረሰባቸውንም ሥቃይ በነገራቸው ጊዜ እጆቹንና እግሮቹን እየሳሙ መሪር ዕንባ አለቀሱ፡፡ ደግሞ ፊቱን ስላዩ ደስ አላቸው:: እርሱም በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ባረካቸው:: እሊህም ታላቁ አባ መቃርስና ባልንጀራው የእስክንድርያው አባ መቃርስ በመጋቢት ወር በአሥራ ሦስተኛ ቀን ሉቅዮስ ከእስክንድርያ አስቀድመን ወደ አወሳናት ደሴት አጋዛቸው ፤ ደግሞ በዚሁ ቀን ተመልሰው ወደ እስክንድርያ
ደረሱ::

በጸሎታቸው የሚገኝ በረከት በሁላችን የክርስቲያን ወገኖች ላይ ለዘለዓለሙ አድሮብን ይኑር አሜን፡፡ ❞

የአባታችን የቅዱስ መቃርዮስ ምልጃና ጸሎቱ አይለየን፡፡

ይቆየን !


†                       †                         †
💖                    🕊                     💖