📖 “እርሱም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን የመንፈስ በኵራት ያለን ራሳችን ደግሞ የሰውነታችን ቤዛ የሆነውን ልጅነት እየተጠባበቅን ራሳችን በውስጣችን እንቃትታለን።” ሮሜ 8፥23
👉 የፍጥረት መቃተትና ምጥ ተብሎ የተገለጸው ፍጥረት ሁሉ በሰው ልጅ የደረሰውን መከራ እንደተሳተፈ ነው። ሰው በኃጢአት ምክንያት በምጥና በመቃተት ይኖራል ከዚሆ ይድን ዘንድም በተስፋ በዳግም ምጽዓት ለሰው ልጅ የሚገለጠው ክብር ይጠባበቃል። አዳም ሲበድል ምድርም ተረግማ ነበር ይህም የበደሉን ውጤት ምድርም እሾህና አሜኬላ በማብቀል ከርግማኑ ተሳትፋ እንደነበር ኃጢአት እስከ ውጤቱ ከሰው በሚወገድበት በዳግም ምጽዓቱ ጊዜም ፍጥረትም ሰው ያገኘውን ክብር ይሳተፋሉ (በርግማኑ እንደተሳተፉ በክብሩም ይሳተፋሉ) አሁን ከነበረበት በተሻለ ሁኔታ ሆኖ ይለወጣል። አሁን በዚህ ዓለም የምናያቸው ጉድለቶች የመሬት መንቀጥቀጥ እሳተ ገሞራ የመሳሰሉት ኃጢአትን ተከትሎ የመጣ የፍጹምነት መጉደል (Imperfection of the creation) ናቸው። እኚህ ሁሉ ጉድለቶች ሁሉ ፍጻሜ ያገኛሉ። ፍጥረትም የእግዚአብሔር ልጆች የሚያገኙትን ክብር በሚመስል ወደ አዲስነት ይታደሳሉ።
ቅዱስ ጳውሎስ ይህ የፍጥረት መቃተት ብቻ ሳይሆን የመንፈስ በኲራት ያለን እኛም እንቃትታለን ይላል። መቃተት ማለት ማዘን መድከም መጨነቅ ማለት ነው።
👉 "የመንፈስ በኩራት ያለን" ሲል የመንፈስ ቅዱስ የመጀመርያው ልጅነት ጸጋ መንፈስ ቅዱስ እኛ የክርስቶስ ቤተሰዎች ፤ ጸጋ መንፈስ ቅዱስን መጀመርያ የተቀበልን ሲል ነው። ይህም ሊመጣ ያለውን ጣዕመ መንግሥተ ሰማያትን በዚህ ምድር ሳለን መቅመስን ያሳያል።
👉 ስለዚህ ፍጥረት ብቻ አይደለም የሚቃትተው ሊመጣ ያለውን ጣዕመ መንግሥተ ሰማያትን የሚመስሉ ጸጋ መንፈስቅዱስን በዚህ ምድር ሳለን የተቀበልን እኛም ጭምር እንቃትታለን ይላል። ተጠምቀን የመንፈስ ቅዱስ ማደርያ ሆነናል። የልጅነት ክብር እስኪፈጸምልን ሥጋችን ከመበስበስ ወደ አለመስበስ ክብር እስኪደርስ ድረስ በውስጣችን እንቃትታለን። የልጅነት ክብራችን የሚፈጸመው ሥጋችን ከሞት ተነስቶ ከመበስበሰሰ ነጻ ሲሆን ነው። የጌታችንን ምጽዓት በኃዘን በመከራ ሆነኖ በተስፋ እንጠባበቃለን ለማለት ነው ይህ የተነገረው።
👉 "የሰውነታችን ቤዛ የሆነውን ልጅነት እየተጠባበቅን" ሲል በጥምቀት የእግዚአብሔር ልጅነትን ጸጋ ስላላገኘን አይደለም። ይልቁኑ በጌታችን ዳግም ምጽዓት በሙታን ትንሳኤ የሚበሰብሰው ሥጋችን በማይበሰብሰው በከበረ ሰውነት ሲለወጥ የልጅነት ክብርን በምልዓት እንጠባበቃለን ሲል ነው። “እርሱም ሁሉን እንኳ ለራሱ ሊያስገዛ እንደሚችልበት አሠራር፥ ክቡር ሥጋውን እንዲመስል የተዋረደውን ሥጋችንን ይለውጣል።” ፊልጵ.3:21 እንዲል። ዳግመኛም ቅዱስ ጳውሎስ "ይህ የሚበሰብሰው የማይበሰብሰውን ሊለብስ ይህም የሚሞተው የማይሞተውን ሊለብስ ይገባዋልና።" 1ኛ ቆሮ.15:53 ይላል። ስለዚህም ይህ ተስፋ የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ የተቀበልን እኛ የልጅነት ክብርን በምልዓት እስክናገኘው ድረስ በትዕግሥት መከራ እንድንቀበል ያደርገናል።