አዲስ አበባ፣ የካቲት 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ንብረታችሁ ሊወረስ ነው በማለት ባለሃብቱን አስፈራርተው በቼክ ገንዘብ ሲቀበሉ በፀጥታ አካላት ተይዘዋል የተባሉ ተጠርጣሪዎች ፍርድ ቤት ቀርበዋል።
በብሔራዊ መረጃ ደህንነትና በፌደራል ፖሊስ በቁጥጥር ስር የዋሉት ተጠርጣሪዎቹ አዲሱ የንብረት ውርስ አዋጅ ወደ ስራ ባልገባበትና በፖሊስ ምርመራ ባልተጀመረበት ሁኔታ ላይ ተጠርጣሪዎቹ ''የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት እና የፋይናንስ ደህንነት ሰራተኞች ነን'' በማለት አንድን ባለሃብት አስፈራርተው 5 ሚሊየን ብር ጉቦ ተደራድረው የ1 ሚሊየን ብር ቼክ ሲቀበሉ እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል የተባሉ 4 ተጠርጣሪዎች በተለያዩ መዝገቦች ፍ/ቤት ቀርበው ጉዳያቸው ታይቷል።
በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት የቀረቡት ተጠርጣሪዎች 1ኛ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በሞጆ ደረቅ ወደብ የጥበቃ ኃላፊ ኢኒስፔክተር ሰለሞን ካሳ፤ 2ኛ በግል ስራ የሚተዳደሩት ተስፋ ሀታኡ ገምቴሳ፣3ኛ ጁዋር አወል ጀማል እና 4ኛ በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የአይቲ ባለሙያ ረ/ኢ/ር ኩሉሌ ጉዮ ቦሩ የተባሉ ተጠርጣሪዎች ናቸው።
አዲሱ የንብረት ውርስ አዋጅ ወደ ስራ ባልገባበት፣ በፖሊስ ምርመራ ባልተጀመረበትና በጋዜጣ ባልታወጀበት ሁኔታ ላይ ተጠርጣሪዎቹ ደዘርት ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማህበር ከተባለው ድርጅት ባለቤት አቶ ቢኒያም ሀደር እና ወኪላቸው ስራ አስኪያጅ መሐመድ እስማኤል አሊ ለተባሉት ግለሰቦች ስልካቸው ላይ በመደወል እና ጥር 05 ቀን 2017 ጀምሮ በተለያዩ ቀናት ባለሃብቶቹን በአካል በማግኘት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት እና የመረጃ ደህንነት ሠራተኞች ነን በማለት በመተዋወቅ "በአዲሱ ንብረት ማስመለስ አዋጅ መሰረት በንብረታችሁ ላይ እና የባንክ የሂሳብ እንቅስቃሴዎች ላይ ምርመራ ተደርጎ ንብረታችሁ ይወረሳል፤የባንክ ሂሳብ እንቅስቃሴ እናግዳለን "በማለት ሲያስፈራሩ እንደነበረ ለጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ አብራርቶ ነበር።
በተለይም መንግስት ሃብታቸውን እንዳይወርስባቸው እንደሚያደርጉ በመግለጽ÷ለዚህ ማስፈጸሚያነት የሚውል 5 ሚሊየን ብር በመደራደር በቅድሚያ 20 ሺህ ብር በባንክ ሂሳብ እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቦሌ ክፍለ ከተማ ልዩ ቦታው ቦሌ ሚካኤል አኑዋር ምግብ ቤት ውስጥ አንድ ሚሊየን ብር የተዘጋጀ ቼክ ከደርጅቱ ወኪል ከሆነው ከአቶ ማሐመድ እስማኤል አሊ እጅ ሲቀበሉ በክትትል ላይ በነበሩ ጸጥታ ኃይሎች የተያዙ መሆኑን ጠቅሶ÷ የፌደራል ፖሊስ መርማሪ ለጊዜ ቀጠሮ ችሎት አቅርቧል።
መርማሪ ፖሊስ በዚህ መልኩ ተጠርጣሪዎቹ የሙስና ወንጀል የምርመራ ማጣሪያ ስራ እያከናወነ የሚገኝ ሲሆን ፥ ከእነዚህ ተጠርጣሪዎች መካከል ኢኒስፔክተር ሰለሞን ካሳ በሚመለከት የምርመራ መዝገቡን ለዐቃቤ ህግ ማስረከቡን ለጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ፖሊስ አስታውቋል።
በፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሪክቶሬት ዐቃቤ ህግ በጊዜ ቀጠሮ ችሎት ቀርቦ የምርመራ መዝገቡን ከፖሊስ መረከቡን ጠቅሷል።
ዐቃቤ ህግ የምርመራ መዘገቡን ተመልክቶ በተገቢው ሁኔታ ክስ ለመመስረት እንዲያስችለው በወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ 109(1) መሰረት የ15 ቀን የክስ መመስረቻ ጊዜ እንዲሰጠው ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱን ጠይቋል።
በተጨማሪም ዐቃቤ ህግ በወንጀል ድርጊት ሊገኝ ከታሰበው የገንዘብ መጠን ወይም የደረሰው ጉዳት አንጻር ሲታይ በአዋጅ ቁጥር 434/97 አንቀጽ 4 እና በማሻሻያው አዋጅ ቁጥር 882/2007 አንቀጽ 3 ንዑስ ቁጥር 1 በተደነገገው ድንጋጌ መሰረት ከ10 ዓመት በላይ የሚያስቀጣና ዋስትና የሚያስከለክል መሆኑን ጠቅሶ ፤ የተጠርጣሪው ዋስትናው ታልፎ ክስ እስኪመሰረት ባሉበት በእስር እንዲቆዩ እንዲፈቀድለት ጠይቋል።
ተጠርጣሪው የዐቃቤ ህግ ክስ መመስረቻ ጥያቄን በመቃወም ዋስትና እንዲፈቀድለት ጠይቋል።
የግራ ቀኝ ክርክሩን የመረመረው ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ የተጠርጣሪውን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ለዐቃቤ ህግ የዘጠኝ ቀናት ክስ መመስረቻ ጊዜ ፈቅዷል።
Maddi:FBC