ዩኒቨርሲቲው የካንሠር የጨረር ህክምና፣ የስነ አእምሮ ተኝቶ ህክምና፣ የፎሮንሲክ እና የስነ መመረዝ ህክምና እንዲሁም የማህበረሰብ ሞዴል መድሀኒት ቤት አስመርቆ ለአገልግሎት ክፍት አድርጓል። ከዚህ በተጨማሪ የጨቅላ ህጻናት የጽኑ ህክምና የልህቀት ማእከል፣ የአጥንትና መገጣጠሚያ ህክምና በአዲስ መልክ አደራጅቶ ወደ ስራ ያስገባ ሲሆን የሴንትራል ኦፕሬሽን ክፍል የማስፋፋያ ስራዎች እየሰራም ይገኛል።
በማስመሪቂያ መርሀ ግብሩ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ድጉማ ለብዙ ጊዜ ሲጠበቅ የቆየው የካንሰር ማእከል የጨረር ህክምና ለአገልግሎት በመብቃቱ እንኳን ደስ አላችሁ ካሉ በኋላ በሲዳማ ክልል የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ በጤና ሳይንስ ኮሌጅ እየተሰሩ ያሉ የጤና ፕሮጀክቶች በቅርቡ ይፋ የሆነውን አራተኛው የጤና ፓሊሲ ላይ የተቀመጡ ጉዳዮች ጋር በእጅጉ የተሳሰሩ መሆናቸው ገልጸዋል። እነዚህ አገልግሎቶችን ወደ ስራ ማስገባቱ የጤና ፖሊሲውን ለመተግበር ብሎም ዜጎች በጤናው ዘርፍ ላይ ያላቸውን ፍላጎት ማርካት እንደሚያስችል ተናግረዋል።
የአዋሳ ዩኒቨርስቲ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ውስጥ የተገነባው የጨረር ህክምና በአገራችን አራተኛው የጨረር ህክምና መሆኑን የገለጹት ዶክተር ደረጀ የህክምና ዘርፉን አንድ እርምጃ ወደፊት የሚወስድ በመሆኑ ስራው ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት እንደሆነም ነው የተናገሩት።
በከፍተኛ ወጪ ተገዝተው በጤና ሚኒስቴር በኩል የቀረቡት ማሽኖችን በአግባቡ ወደ ስራ በማስገባት፣ ተገቢው ጥገና እየተደረገላቸው ረጅም ጊዜ አገልግሎት እንዲሠጡ ጥንቃቄ እና እንክብካቤ እንዲደረግላቸው ዶክተር ደረጀ ያሳሰቡ ሲሆን ማሽኖችን ወደ አገር ውስጥ በማስገባት ለተባበሩት፣ ለማሽኖቹ አቅራቢ ኩባንያ፣ ማእከሉን ላስገነባው እና ስራው ስኬታማ እንዲሆን ጥረት ያደረጉ አካላትን ሁሉ አመስግነዋል።
መንግስት አቅዶ እየሰራቸው ካሉ ስራዎች መካከል አንዱ የጤናው ዘርፍ መሆኑን አንስተው የህዝቡን ጤና ሊያሻሽሉ የሚችሉ ፕሮግራሞችን ቀርጾ በመተግበር ላይ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የሲዳማ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር አቶ በየነ በራሶ ሲሆኑ እንደ ክልል የጤና አገልግሎቱን በማሻሻል ህዝቡ ከዘርፉ ተጠቃሚ ለማድረግ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ መሆኑን ገልጸዋል። ይኼውም በእለቱ ተመርቀው ወደ ስራ የገቡት አገልግሎቶች ለዚህ ማሳያ መሆናቸው ጠቅሰው ከዚህ በፊት ብርቅ የነበሩ የህክምና አገልገሎቶች መንግስት ባሳየው ቁርጠኝነት በክልሉ ማቅረብ መቻሉን ገልጸዋል። እነዚህ አገልግሎቶች በህመሙ ለተጋለጡ ሠዎችን ችግር መቅረፍ የሚችል መሆኑን አክለዋል። አሁንም ሌሎች መሠል አገልግሎቶች በሆስፒታሉ እንዲሠፋፉ የጤና ሚኒስቴር የበኩሉን እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
የአዋሳ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት አቶ አያና በራሶ በበኩላቸው
በደቡብ የአገሪቱ ክፍል የካንሠር ህክምና ማእከል በአዋሳ ለመገንባት ተመርጦ ማእከሉ መሠራቱን የተናገሩ ሲሆን ከሁለት አመት በፊት ግንባታው ተጠናቆ የኬሞቴራፒ አገልግሎት በማስጀመር ከ6 ሺህ በላይ ታካሚዎችን ሲያክም መቆየቱንና ዛሬ ላይ የጨረር ህክምናው የጤና ሚኒስቴር ባደረገው የራድዮ ቴራፒ እና ሲቲ እስካን ማሽን ድጋፋ የጨረር ህክምና መጀመር መቻሉን ገልጸው ለጤና ሚኒስቴር እና ደጋፍ ላደረጉ አካላት ምስጋና ቅርበዋል።
በተጨማሪም የፎረንሲክ እና ሦስት ሌሎች አዳዲስ አገልግሎቶች ተመርቀው ስራ መጀመራቸውን ያስረዱ ሲሆን ጥገና የሚያስፈልጉ የሆስፒታሉ ህንጻዎች እንዳዲስ የመገንባት፣ የኦክስጅን ጋዝ ማምረቻ ፕላንት የተጀመሩ ግንባታዎችን በመገንባት ላይ መሆናቸውን አቶ አያና አስተውቀዋል።
በ800 ተማሪዎች እና 104 መምህራን፣ በሁለት ፋካሊቲ ስር አምስት የስራ ክፍሎች በማቀፍ በ1989 የተቋቋመው የጤና ሳይንስ ኮሌጁ በአሁኑ ጊዜ 12 የመጀመሪያ ዲግሪ፣ 17 ሁለተኛ ዲግሪ፣ 10 ስፔሻላቲ ፣ አንድ ሰብ ስፔሻሊቲ እና አንድ ሶስተኛ ዲግሪ ፕሮግራሞች በመያዝ መማር ማስተማሩን በማሣለጥ ላይ እንደሚገኝ እንዲሁም ሪፈራል ሆስፒታሉ በአራት የአገልግሎት ዘርፎች መጀመሩን የአዋሳ ዩኒቨርስቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስኩቲቭ ዳይሬክተር አቶ አለሙ ጫሜሶ ገልጸዋል። በዚህም ላለፉት 27 አመታት በርካታ የጤና ባለሞያዎች ማበርከቱን የገለጹ ሲሆን
ሆስፒታሉ በአሁኑ ጊዜ በአመት በአማካይ 150 ሺህ ታካሚዎችን በማስተናገድ ላይ እንደሚገኝና የተወሰኑ የትኩረት መስኮችን የልህቀት ማእከል ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝ አቶ አለሙ አክለው ገልጸዋል።
ከዚህ በፊት ያልነበሩ አዳዲስ አምስት አገልግሎቶችን ማስጀመር መቻሉንም የተናገሩት ዳይሬክተሩ እነዚህ አገልግሎቶች መቅረባቸው የህብረሰተቡን ችግር የሚፈቱና ከአላስፈላጊ ወጪ እና እንግልት የሚያድኑ መሆናቸውን ገልጸው በቀጣይ የልብ እና ኩላሊት ህክምና አገልግሎትም ለማቅረብ የባለድርሻ አካላት ድጋፍ ጠይቀዋል።
በመጨረሻም የተጠናቀቁ አምስት ፕሮጀክቶች በእለቱ ክብር እግዶች የተመረቁ ሲሆን የህክምና ክፍሎቹ እና የተጀመሩ ፕሮጀክቶች ተጎብኝተዋል።