መፀፀቷን አራከሱት
ገልጠው ሰው ፊት አነበቡ
የተዘጋው ምዕራፏን
ተንቀልቅላ ቤቱ ሄደች
እያነባች ይዛ አፏን
ሰውነቷን ተጠየፈች
የፀፀቷ ጅራፍ በዛ
ከጌታ ጋር አልተዋትም
እዛው ልቧን እንድትገዛ
የወገብ ላይ ውጋት ሆኑ
እንዳትቆም አሳቀቋት
በመጠየፍ አይን እያዩ
ቅን እምነቷን መነጠቋት
ውለው አድረውም
እንዲያው ናቸው
ሁሌ ግራ የሚሄዱት
ጥፋቷን ሰርክ እያነሱ
ንስሀዋን አከበዱት
አዎን ብዙ በድላለች
ሀጥዕ ሆና ጋለሞታ
ማንም ጣቱን እንዳይጠቁም
ከመጣች ግን ወደጌታ
ወርቅ ምንጣፍ ይዘርጋላት
ወደ ቤቱ እስክትገባ
ከግብዞች ፀሎት በላይ
ጌታ ይሰማል ንፁህ እምባ
ታሪክ ገጿ ምንም ይሁን
የትላንቷ ምንም ያክል
ማነው ሸክሟ በዝቷል ብሎ
እንዳትገባ ሚከለክል ?
.
አወሩባት ብዙ ነገር
.
አይን አውጣ ነች የማታፍር
አይተናታል ከዚህ ቦታ
ከጀርባዋ ይዘልፏታል
ታለቅሳለች በዝምታ
እንዲህ ሴት ነች
እንዲያ ሴት ነች
ክፉ ግብሯን ዘረዘሩት
ምንም ጥፋት እንዳልሰሩ
አሽሟጠጡ የተቀሩት
ምናለበት ሰው አይደለች?
ምናለበት ሰው አይደለች?
የልብሳቸው ጨርቃ ቢወልቅ
ቀሽም ቀሊል የሚሆኑ
ሱባኤዋን እስክትጨርስ
ገመናዋን ቢሸፍኑ
ባይፈርዱባት ምናለበት
በአደባባይ ለህዝበ አገር
የሀዲስ ኪዳን ሀጥያተኛ
በቃላት ነው የሚወገር?
ይበቃታል ህሊናዋ
ሰርክ አስታውሶ የሚቀጣት
ይበቃታል ህሊናዋ
በሀሳብ ማዕበል የሚንጣት
ይበቃታል ሰውነቷ
የሚቀፋት እንደ ሩቅ ሰው
ይበቃታል ይህ ጭንቀቷ
ውስጧን በልቶ የጨረሰው
አታድክሟት ደካማዋን
አትጨምሩት መከራዋን
አንድም የለም ከኛ መሃል
ችሎ ችሎ የማይደክም
እስቲ ተዋት ከአምላኳ ጋር
የሷን ህመም እሷው ታክም!
@mikiyas_feyisa