ካትሱ
አንዳንድ አገሮች በስንት ዘመን አንድ ጊዜ ብቻ አንድ ትልቅ ሰዉ ሲያገኙ እንደ ትልቅ ብርቅ ነገር ይቆጥርላቸዋል። ለዚሁም በቱርክ አገር ኤል ፓሻ፡ በህንድ አገር ጋንዲ፡ በሺና ሰን ፡ ያን፡ሴን ምሳሌ ሆነዉ ሊጠቀሱ ይችላሉ። ጃፓን ግን ባንድ ዘመን ዉስጥ ወዲያዉ ከሥልጣኔ ጋር እንደተዋወቀች ከአሥር የሚበልጡ ታላላቅ ሰዎች ባንድ ጊዜ አፈለቀች። እግዚአብሔር በዚህ ረገድ ላንዳንዶቹ ቸር፡ ላንዳንዶቹ ግን ንፋግ የሚሆንበት ምክንያት የማይመረመር ምሥጢር ነዉ።
ካትሱ አያቱ ዐይነ ስዉርና ለማኝ ሰዉ ነበር። ጃፓኖች በሃይማኞት ጉዳይ ከፓርቱጌዞች ጋር ተጣልተዉ የክርስቲያንን ሃይማኖት ካገራቸዉ ካጠፋት የዉጪ አገር ሰዎች ወደ አገራቸዉ እንዳይገቡ ያገራቸዉ ሰዎች ወደ ዉጪ አገር እንዳይሄዱ ከከለከሉ በኋላ ሁለት መቶ አምሳ ዓመታትን የሚሆን ዘመን ከዓለም ጋር ተለያይተዉ ሲኖሩ በመጨረሻ ጊዜ አሜሪካኖች፡ፈረንሳዮችና እንግሊዞች በጦር ኋይል ጥሰዉ በጃፓን አገር ዉስጥ ከመግባታቸዉ በፊት ቀደም ብሎ አንዳንድ የጃፓን ወጣቶች አገራቸዉ የተከተለችዉን ከዓለም ጋር ተለያይቶ የመኖር ፓለቲካ የሚጎዳ እንጂ የማይጠቅም መሆኑን ማስተዋል ጀምረዉ ነበር።
ካትሱ በዝና ብቻ ያወቀዉ ይህ ያዉሮፓ ሥልጣኔ ምሥጢሩ ምን እንደሆነ ለመረዳት ስለፈለገ ቋንቋቸዉን ሊማር ቁርጥ አሳብ አድርጎ ተነሣ። በዚያን ጊዜ በጃፓን አገር ያሉ ነጮች ሆላንዶች ብቻ ስለ ሰለሆኑ የሆላንድን ቋንቋ መማር ግዴታ ሆነበት። በጃፓን አገር የነበሩትም የሆላንድ ተወላጆች የሆኑት ነጋዴዎች ሁሉም የነበራቸዉን ትምህርት ቃላት ማግኝት አሰበና ፈልጎ ሳያገኝ ቀረ። ስለዚህ የመምህሩን የዲክሲዮኒር መጽሐፍ ለምኖ በእጁ እየፃፈ በሁለት ቅጅ ገለበጠዉና አንዱን ለራሱ አስቀርቶ ሁለተኛዉን በዉድ ዋጋ ሸጦ ባገኝዉ ገንዘብ ሌላ መጻሕፍት ገዛበት። ዕዉቀትን ለማግኝት ሲል ዕድሜዉን ሙሉ የመጽሐፍ አዳኝ ሆኖ ቀረ።
መጀመሪያ ከገዛዉ መጻሕፍቶች አንዱ ስለ ጦር እቅድ ትምህርት የሚናገር መጽሐፍ ነበር። ይህኑ ጽሑፍ ለመግዛት የሚበቃ ገንዘብ ስላላገኝ ለተወሰነ ጊዜ ማንበብ ብቻ ሲል ያለዉን ገንዘብ ሁሉ ከፍሎ ላንድ ዓመት ተከራየዉና በእጁ እየጻፈ እንደ ልማዱ ገለበጠዉ።
በብዙ ድካም ገልብጦ ከወረሰዉ በኋላ ጥቂት ጊዜ የተጻፈ ዳግም አንድ ሌላ መጽሐፍ ድንገት አገኝ። ነገር ግን ለመግዛት ቢጠይቅ ዋጋዉ ዉድ ስለሆነበት ይህን መጽሐፍ ለመግዛት ሲል ከወዳጅ ከዘመድ ገንዘብ እየለመነ ሲያጠራቅም ቆየና ለመግዛት የሚችልበት ብዙ ገንዘብ ሲያገኝ ወደ መደብር ሔደ። ነገር ግን ከመደብሩ ገብቶ በጠየቀ ጊዜ የሚፈልገዉ መጽሐፍ ከጥቂት ሰዓት በፊት አንድ ሌላ ሰዉ ገዝቶ እንደወሰደዉ ነገሩት።
ካትሉ በዚህ ነገር ተናድዶ ያ እንደ እሱ ዕዉቀት የተጠማውን ሰዉ ማን እንደሆነ ለማወቅ ፈልጎ ስሙን ካልነገርከኝ እገልሃለሁ ብሎ ነጋዴዉን በታጠቀዉ ሰይፍ አስፈራራዉና ስሙን እንዲገልጥለት አስገደደዉ። ነጋዴዉም ደንግጦ የሚፈልገዉን መጽሐፍ የገዛዉ ሀብታም የሆነ አንድ የጃፓን መኮንን ሳሙራዬ መሆኑን ሲነገግረዉ ካትሱ ቤቱን እየጠየቀ ከተማዉን ሙሉ ከዞረ በኋላ ደረሰበት። ከቤቱም ሰተት ብሎ ገብቶ " ይህን መጽሐፍ በጣም እፈልገዋለሁና ለኔ ሽጥልኝ" ብሎ ጠየቀዉ። ያዉ መኮንን " አልሸጥም" ብሎ መለሰለት " እንዲያዉ አከራየኝ አለዉ።" አላከራይም " ሲል መለሰ" ሁለቱንም ልመናዬን እንቢ ካልከኝ እንግዲያዉስ አውሰኝ አለዉ። " መጽሐፉ ሁልጊዜ ስለሚያስፈልገኝ ላዉስህ አልችልም" ሲል ሦስተኛ መለሰለት። ካትሱ አሁንም መለሰና " እንቅልፍ አትተኛም ወይ ? ብሎ መኮንኑን ጠየቀዉ መኮንኑም " ሌሊት እተኛለሁ " ብሎ መለሰለት " እንግዲያዉስ እኔ እንቅልፍ የሚባል ነገር አላዉቅምና ሁልጊዜ ማታ ማታ ከቤትህ እየመጣሁ እንተ ስትተኛ መጽሐፋን ወስጄ ጧት በማለዳ እንድመልስልህ ፍቀድልኝ ለዚሁም መያዣ እንዲሆንልህ ይህን ገንዘብ እንካ። ብሎ መጽሐፉን ለመግዛት የሰበሰበዉን ገንዘብ ሁሉ ሰጠዉ።
የመፅሀፉ ባለቤት ይህን በመሰለ ችክ ባለ ልመና ታክቶት ግልፍ ስላለዉ " መጽሐፌ ከቤቴ እንዲወጣ ጨርሼ አልፈቅድም" ሲል ደረቅ መልስ መለሰለት። አሁንም ደግሞ ካትሱ መለሰና "እንግዲያዉስ አንተ ስትተኛ እዚሁ ቤት ሆኜ ለሊት መጽሐፉን እንዳነበዉ ትፈቅድልኛለህ ወይ?" ሲል ጠየቀዉ የመጽሐፉ ባለቤት ይህ የገጠመዉ ሰዉ የለመነዉን ነገር ሳያገኝ በደኀና እንደማይመለስ አዉቆ ፈቀደለት። ካትሱ ቤቱ ሩቅ ስለሆነ ማታ ማታ እየመጣ መጽሐፉን ሲያነብ እያደረ ጧት ወደ ቤቱ እየተመላለሰ በስድስት ወር በዚህ አኳኋን ሲሠራ ከቆየ በኋላ በስድስት ወር ይፈልግ የነበረዉን መፅሀፍ አንብቦ ከዚያም በእጁ ግልባጭ በሙሉ ሰርቶ ጨረሰ
ሀብታሙ መኮንን ካትሱ ይህን አስደናቂ ሥራ ሠርቶ ባየ ጊዜ በትጋቱ እጅግ ተደንቆ መጽሐፋን ጨምረህ እንድትወስደዉ ፈቅጄልሀሉ፡ የሚገባ ሰዉ ነህና ብሎ መረቀለት።
መንጭ:- ጃፓን እንዴት ሰለጠነች ከሚለዉ ከከበደ ሚካኤል መፅሀፍ
መርሕ የንባብ ቤት
ሕዳር 2017 ዓ.ም
የሚያነብ ትዉልድ ታሪክ ይሰራል!
የማያነብ ትዉልድ ግን ታሪክ ይደግማል!