በጋ ነዉ ብለህ ከሰማይ ጠብ የሚል የዉሃ ጠብታ በምትናፍቅበት አናትን በስቶ የመግባት ያህል አያል እና የከረረ ፀሃይ በሚወጣበት በዚህ የበጋ ወቅት ድንጋቴ የሚወርድ ያልታሰበ እና የሚያግሮመርም ዶፍ ዝናብ መጣል ሲጀምር ኩልል ባለዉ እና ጨረቃዋ በጃሌዎቿን እና ወዳጆቿ እልፍ ኣህላፍ ኮከቦች ዙሪያዋን ተከባ ለሊቱን ልትነግስበት ገና ከምሽቱ ጅማሮ በጠራዉ ሰማይ ስር ማደማመቅ ስትጀምር፣
ያለ አንዳች የመብረቅ ብልጭታ፣
ያለ አንዳች ጉርምርምታ፣
ለአፍታ ድባቡን ሳያሳይ፣
የጨረቃዋን ደማቅ እና የረጋ ዉበት ያጠለሸዉ ድንጋቴ ዝናብ በአያል ንፋስ እየተመራ መጣል ጀመረ።
ይገርማል።
ሚገርመዉ ደግሞ የዝናብ ቅፅባቴ መጣልም አይደለም፣
ክዉ ባለዉ የበጋ ወቅት ለምን ይዘንባል ማለትም አይደለም፣
ሚገርመዉ ነገር እኔ እና እሁድ ኮከባችን ሲገጥም የነገሩ ሁሉ አፍራሽ መሆኑ ነዉ እንጂ።
ይገርማል፣ ምኑ ነዉ ሚገርመዉ አትለኝም?
የዝናብ ባልተለመደ ጊዜ የደስታዬ አፍራሽ መሆን መደጋገሙ ነዉ።
ምን መሠለህ ወዳጄ፣
ጊዜ ካለህ፣
ልትሰማኝ ከወደድክ፣
ስማኝማ አንዲት ትንሽዬ ታሪክ ላጫዉትህ፣
ምን መሠለህ ኣባ......
የእኔ እና ክረምት የባላንጣነታችን ጅማሮ ከልጅነት ዘመኔ የጀመረ የደረጀ ታሪክ አለን።
ዝናብ ጠል ከሚባሉ ሰዎች ባልመደብም ግን እርስ በርስ ያለን ቁርሾ የከረረ ነዉ።
ያኔ ድሮ ድሮ...
የልጅነት መልኬ ሳይደበዝዝ፣
ፍልቅልቅ ፈገግታዬ እንዳለ በነበር ሳለ ጊዜ፣
እኔ ከትምህርት እና ከቤተሰብ አገልጋይናት የተረፈኝ ተሰልቶ በቤተሰቡ የበላይ አለቃ ተሰልቶ የእረፍት ጊዜ በአዋጅ ፀድቆልኝ በደስታ ብዛት ምሆነዉን አጥቼ የሰሃት እላፊ ገደብ የተበጀለትን "ሂድ ተጫወት" የሚለዉን የመጨረሻ የድምፅ ዉሳኔ በጉጉት በመጠባበቅ ሳለዉ፣ ባልታሰበች በዛች ቅፅበታዊ ሰዓት ድንገት እያጉረመረመ መደንፋት ጀመረ።
ደንፍቶም በቃረ እያልኩኝ ስፀልህ ስንት ዘመን መስኩ ላይ ከእኩዮቼ ጋር እየተሯሯጥኩ የምጫወትበትን የልጅነት ዘመን ዉድ ጊዜዬን እየነጠቀኝ ስንት ጊዜ እንዳባባኝ ያ ዘመን ይቁጠረዉ።
እንግዲህ የኔ እና የክረምት ባላንጣነት የጀመረዉ እንዲህ ነዉ።
ይሄ ቁርሾ ይሄ የዝናብ የኔን ደስታ ጠል ባህሪያት በጊዜ ሂደት እና ርዝማኔ የኔን ደስታ ከመንጠቅ ገሸሽ ሳይል ጊዜ ጊዜን እየተካ ከአመታት ንግስና በዋላ የወጣትነትን ካባ ስቀዳጅም፣
ይሄዉ...
እንዳለፈዉ ዘመን፣
ልክ እንደ ያኔዉ፣
እንደ ልጅነቴ፣
ዛሬም እየደጋገመ እኔን ማስቀየም እና ማሳቀቁን ተያይዞታል።
ሁፍፍፍ!!!!!
ዛሬ ደሞ እሁድ ነዉ።
የሳምንቱ የመጨረሻ ቀን፣
የላብ አደሮች የእፎይታ እለት፣
ሳምንቱን ሙሉ...
ተጠበን፣
ተጨንቀን፣
ያሰለፍናቸዉን የሳምንቱን ቀሪ ቀናቶች ምታስመልጠን፣
በድካም የዛለዉን ሰዉነት የምናፍታታበት፣
በድግግሞሽ የተሰላቸዉን አይምሮ የምናድስበት፣
ከልብ ወዳጅ ጋር ቁምነገር የምናወጋበት፣
ናፍቀን የምናገኛት፣
ልዩ ቀናችን ናት።
እንግዲህ ዛሬም እኔ እና እሁድ ተነፋፍቀን ተገናኘን።
እሁድ ስትደርስ በርሷ ጎጆ ስር ያለዉን የእረፍት ጥላ ለአፍታ ተጠልለሁበት የሚነግዱት ሰዓታት እና ሽርፍራፊ ደቂቃዎች ሁሉ ዉድ ናቸዉ።
ሆኖም ግን ከቀኑ የፀሃይዋ ሙሉ ብርሀን ይልቅ የምሽቷ ጨረቃ በዙሪያዋ እልፍ አህላፍ ኮከቦችን አስከትላ፣ እና በተራ መንገድ ዳር ተሰልፈዉ እኔ ይበልጥ፣ እኔ ይበልጥ የሚል የፉክክር መንፈስ የተጋባባቸዉ ከሚመስሉ የመንገድ ማብራት የብርሀን ባህር ጋር ዉህደት ፈጥራ ምሽቱን ጉራማይሌ ዉበት ስታላብሰዉ ከቀኑ በላይ፣
ለልብ ትቀርባለች፣
ነፍስን በሀሴት ትሞላለች፣
እዩኝ እዩኝ በሚል
የዉበት አክሊል ደፍታ ስትታይ፣
ያያት ሁሉ የቤቱን ጉዳይ ትቶ፣
አማላይ ዉበቷን ለማድነቅ እና ለመድመቅ ደጅ ያመሻል።
እንግዲህ እኔም የምሽቷ የዉበት እስረኛ ነኝ።
ዛሬም እንደወትሮዉ እንደለመደብኝ በሷ ታዛ ስር ልደምቅ እነሆ ተሰናድቼ፣ ከምወደዉ ቦታ መገኛቴ በራሱ ልቤን በሀሴት ሞልቶታል።
ለወትሮዉም ከጫጫታዉ መሀል ዝምታን መፈለግ ደስታዬ ነበር።
ዛሬ ግን ለአፍታ እንደ ፏፏቴ ጅረት ተያይዞ እንደ ሚወርደዉ የተፈጥሮ በረከት፣ የትዝታ ሙዚቃ ከድምፁ ጋር ተስተካክሎ በተቀኘ ዜማ፣ አሳብን ሰርቆ ካለፈ ትዝታ ጋር ሊያቆራኛት ከነፍስ ጋር ትግል ይገጥማል።
እንዲሁም እንዲህ ነኝ
ወሳጅ እና መላሽ ሲገኝ ችዬ እምቢ የምልበትም ሆነ ለመንገራገር አቅምም ቢሆን አይል የለኝም።
በትናንሽ ጭላንጭል ኩነቶች እና ድምፀቶች የዋሊት ተስቤ ትላንት በዛሬ ተክቼ ዳግማዊ መልሼ ልኖራት የምመኝ ነኝ።
በሙዚቃዉ ቃና ስመሰጥ፣
ምሽቷን በfree style ልቀዉጥ፣
"ሀ" ብዬ ሪቫኑን ቆርጬ ወደ ዉስጧ ዘልቄ በመግባት ላይ ሳለዉ ነበር ይህ አይበገሬ ያለ ወቅቱ የተገኘዉ እንግዳ ዝናብ ደስታዬን ከአፈር ቀላቅሎት ያረፈዉ።😭
እንግዲህ እንዲህ ነዉ እኔና እሁዴ
እየተነፋፈቅን፣
እየተፈላለግን፣
እየተያየን የተለያየነዉ።
ምን አደርጋለሁ እንግዲህ
እየደበረኝ፣
እየከፋኝ፣
እየመረረኝ፣
ወደ ቤት እየተመለስኩ ነዉ።
እኔን የገጠመኝ አይግጠማቹ
አሚን በሉ።
"
ፀሃፊ✍️NUREDIN BURKA [ H O L L Y ]
ታህሳስ 28/2016